Saturday, 26 April 2014 12:39

ናይጄሪያ፡ ትንግርተኛዋ አፍሪካዊት አገር

Written by 
Rate this item
(0 votes)

       ከኢትዮጵያ በእጥፍ የሚበልጥ ሕዝብ የያዘችው ናይጄሪያ በአንድ ምሽት፣ ተዓምረኛ የኢኮኖሚ እድገት አስመዘገበች - 90 በመቶ እድገት። እውነት ነው። ግን፣ “አስመዘገበች” የሚለውን ቃል በቸልታ አትዝለሉት።
ነገሩ ቀላል አይደለም። በፈጣን እድገት እየተንደረደረች መሆኗ የሚነገርላት ኢትዮጵያ፣ አሁን ካለችበት ደረጃ ተነስታ በተዓምረኛ ፍጥነት የ90 በመቶ እድገት እውን ለማድረግ፣ ሰባት አመታት ይፈጅባታል - ከ2500 ቀናት በላይ መሆኑ ነው።
ዎልስትሪት ጆርናል (wsj) እንደዘገበው፤ እስከ መጋቢት 20 ቀን ድረስ፣ በጠቅላላ የኢኮኖሚ ምርት፣ ደቡብ አፍሪካ የአህጉሩ ቀዳሚ ነበረች። የደቡብ አፍሪካ አመታዊ የምርት መጠን 370 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል። ከኢትዮጵያ በአስር እጥፍ የሚበልጥ ማለት ነው። በሁለተኛ ደረጃ ላይ ደግሞ ናይጄሪያ ነበረች - በ270 ቢሊዮን ዶላር አመታዊ ምርት።
ይሄ የደረጃ ሰንጠረዥ ከመጋቢት 21 ቀን በኋላ ተቀይሯል። ናይጄሪያ በጠቅላላ አመታዊ ምርት፣ የአፍሪካ ቁንጮ መሆኗን አውጃለች - ለዚያውም በሰፊ ልዩነት። የአገሪቱ አመታዊ ምርት 510 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ነው የተገለፀው። በሌላ አነጋገር፤ ናይጄሪያ በአንድ ምሽት የ240 ቢሊዮን ዶላር (ወደ ሩብ ትሪሊዮን ዶላር የተጠጋ) እድገት አስመዝግባለች። ኢትዮጵያ በፈጣን እድገት ብትገሰግስ፣ አመታዊ ምርቷ ሩብ ትሪሊዮን ዶላር የሚደርሰው ከ20 ዓመት በኋላ ነው። በናይጄሪያ የአንድ ምሽት ጉዳይ ሆኗል።
ጉደኛውን የናይጄሪያ ዜና የዘገቡ እነ wsj እና ዘ ኢኮኖሚስት የመሳሰሉ የሚዲያ ተቋማት፤ ነገሩ ትንግርት ወይም ምትሃት እንደሚመስል ገልፀዋል። ግን፣ “ሐሰት ነው” ወይም “ስህተት ነው” ብለው አልተቹም። የናይጄሪያ አመታዊ ምርት፣ ከግማሽ ትሪሊዮን በላይ ነው በሚል ተስማምተዋል።
ግን፤ በምንኖርባት ዓለምም ሆነ በሌላ ዓለም፤ “ተዓምር”፣ “ትንግርት”፣ “ምትሃት” የሚባል ነገር የለም። እና ናይጄሪያ በአንድ ምሽት ያስመዘገበችው ወደ ሩብ ትሪሊዮን ዶላር የተጠጋ እድገት፣ “የናይጄሪያ ብሔራዊ ተዓምራት” ውስጥ የማይካተት ከሆነ ምን ተብሎ ሊሰየም ነው? ትክክለኛው ስያሜ፣ “የናይጄሪያ መንግስታዊ ዝርክርክነት” የሚል ነው።
የአንድ አገር አመታዊ ምርት ምን ያህል እንደደረሰ የሚታወቀው፣ ጓዳ ጎድጓዳውን፣ ፋብሪካና ገበያውን፣ የእርሻ ማሳና የከብቶች በረትን ሁሉ እያግበሰበሱ ቆጠራ በማካሄድ አይደለም። በየአመቱ አገር ምድሩን ማሰስ አይቻልም። ታዲያ በመላ አገሪቱ፣ 15 ሚሊዮን የገበሬ ቤተሰቦች ቢኖሩ፤ የሁሉንም አመታዊ ምርት በድምር ለማወቅ ምን መላ አለ? ለምሳሌ፣ ከአንድ ሺ ገበሬዎች መሃል የአንዱ ገበሬ ምርት ላይ በማተኮር ጥናት ማካሄድና በአንድ ሺ ማባዛት ነው መፍትሄው። በዚህ የናሙና ጥናት፣ የ15ሺ ገበሬዎችን የምርት መጠን ላይ መረጃ ይሰባሰባል። ከዚያ፤ ይህ ውጤት በአንድ ሺ ይባዛል - ጠቅላላ የአገሪቱ ገበሬዎች አመታዊ ምርት ለማወቅ። በአንድ ሺ ማባዛት የሚያስፈልገው፤ የአንድ ገበሬ ምርት፣ የአንድ ሺ ገበሬዎችን ምርት ይወክላል ከሚል የጥናት መነሻ ስለተነሳን ነው።
አስር ሺ ትልልቅና ትናንሽ ፋብሪካዎች ቢኖሩ፤ የአንድ ሺ ናሙና ፋብሪካዎችን እንቅስቃሴ በማጥናት በመቶ ማባዛት ይቻላል። የትራንስፖርት፣  የጤና፣ የስልክ፣ የኤሌክትሪክ፣ የባንክ፣ የሸቀጥ አቅርቦት የመሳሰሉ አገልግሎቶችም ላይ ተመሳሳይ የናሙና ጥናት ይካሄድና፤ እንደ ውክልናው ክብደት (weighted mean) በመቶም ይሁን በሺ  እያባዛን ጠቅላላ አመታዊ የአገልግሎት ወይም የምርት መጠን ላይ እንደርሳለን። በሌላ አነጋገር፤ እያንዳንዱ ዘርፍና ንዑስ ዘርፍ፤ እያንዳንዱ አካባቢና መረጃ ... ከላይ እስከ ታች በኢኮኖሚ ውስጥ ምን ያህል ድርሻ እንዳለው በቅጡ ተገንዘበን፣ እንደ የድርሻ ተገቢውን የውክልና ክብደት እስከሰጠነው ድረስ፤ አስተማማኝ ቀመርና ስሌት ይኖረናል ማለት ነው።
በሆነ ምክንያት፣ የውክልናው መጠን ወይም ክብደት ከአመት አመት ቢቀያየርስ? ከጊዜ ወደ ጊዜ ብዙ ነገሮች እንደሚቀየሩ አይካድም። የሕዝብ ብዛትን መጥቀስ ይቻላል። ግን ችግር የለውም። በየአመቱ የሚከሰቱና የተለመዱ ጥቃቅን ለውጦችን ሳንዘነጋ በቀመራችንና በስሌታችን ውስጥ በማስገባት መስመር እናስይዘዋለን። በየአመቱ የገጠር የሕዝብ ብዛት በምን ያህል እንደሚጨምር ይታወቃላ። ግን ባልተለመደ ሁኔታና ፍጥነት፤ ለምሳሌ የአገሪቱ የገበሬዎች ብዛት ወደ አስር ሚሊዮን ቢቀንስ ወይም ወደ ሃያ ሚሊዮን ቢያሻቅብስ? ያኔ ለናሙና ጥናት የምንጠቀምበት ቀመርና ስሌት ላይ ችግር ይፈጠራል። ለምሳሌ፤ ከሃያ አመት በፊት፣ የአበባ እርሻ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ከቁጥር የሚገባ ድርሻ አልነበረውም።
የፊልምና የቪዲዮ ዝግጅትም እንዲሁ። የዛሬውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፤ በቀድሞው ቀመርና ስሌት ለመመዘን ስንሞክር፣ የምናገኘው ውጤት የተሳሳተ ይሆናል። የናይጄሪያ መንግስት ሲጠቀምበት የቆየው ቀመርና ስሌትም እንዲሁ፤ ከሃያ አመታት በፊት የነበረውን የኢኮኖሚ መዋቅር ላይ የተመሰረተ ስለሆነ የዛሬውን ሁኔታ በትክክል የማሳየት አቅም አልነበረውም። በናይጄሪያ ባልተለመደ ፍጥነት የተስፋፉት የቴሌኮምና የባንክ አገልግሎት፤ የቴክኖሎጂና የኮንስትራክሽን ቢዝነስ፣ እንዲሁም የፊልምና የቪዲዮ ሥራዎች፤ በኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸው ድርሻ እየፈረጠመ መጥቷል። ለሃያ አመታት ያልተለወጠው የመንግስት ቀመርና ስሌት ግን፤ በኢኮኖሚ ውስጥ እየጎሉ ለመጡት ለውጦች ተመጣጣኝ የውክልና ክብደት የሚሰጥ አይደለም። እናም የአገሪቱን አመታዊ ጠቅላላ ምርት በትክክል የማወቅ ወይም የመገመት አቅም አልነበረውም። በየአመቱም የግምቱ ስህተት እየተደራረበ ነው የመጣው። ከሳምንት በፊት የመንግስት ቀመርና ስሌት ተለወጠ። ለሃያ አመታት የተጠራቀመው ስህተትም ተስተካከለ። ይሄ ተዐምር አይደለም። ለበርካታ አመታት የዘለቀ ዝርክርክነት እንጂ።

Read 4531 times