Saturday, 26 April 2014 12:35

የአይሁዳውያን ፋሲካ

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(1 Vote)

            ክርስቲያኖች “ጌታችንና መድኃኒታችን” ብለው የሚያመልኩት ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተጻፈው ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበትን የፋሲካ ክብረ በዓል ከፍ ባለ ስነ-ስርአት ካከበሩት እነሆ ዛሬ ስድስተኛ ቀናቸው ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስን “በጭካኔና በድፍረት፣ ሰቀሉት” እየተባሉ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ የሚታሙት አይሁዳውያንም ከአውራ ክብረ በአላቶቻቸው አንዱ የሆነውን “ፔሻ” (የማለፍ ቀን) የተሰኘውን በአላቸውን በታላቅ ሀይማኖታዊ ስርአት አክብረው ከጨረሱ የዛሬው የቅዳሜ ሻባት ልክ ስድስት ቀናቸው ነው፡፡
ክርስቲያኖች እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ አይሁዳውያንም ይህንን የፔሻ ወይም የማለፍ ቀን ክብረ በአላቸውን ፋሲካ በማለትም ይጠሩታል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከአይሁዳውያን ጋር ቅርብ የመንፈስና የአካል ቁርኝት ፈጥረው ለሺ ዓመታት የዘለቀውን የታሪካቸውን አብዛኛውን ዘመን ያህል ኖረዋል፡፡ የሆኖ ሆኖ ዛሬ አይሁዳውያን ቢያንስ ከሀያ ሁለት ዓመት በፊት እንደነበሩት ያህል ለኢትዮጵያዊያን በአካል ቅርብ አይደሉም፡፡
ይሁን እንጂ እንግሊዛዊው ይሁዲ ደራሲ ጀምስ በርንስቴይን ሆዌል እንዳለው፤ “መለያየት የልብን ልብ በመኮርኮር የፍቅርን ሳንዱቅ ማስከፈት ይችላል፡፡ እናም የኛም ልብ ትናንት አብረውን ይኖሩ ስለነበሩት አይሁዳውያን ሲል በትዝታ ቢጎተትና “ከቶ እነኛ አይሁዳውያን ወገኖች ይህን ታላቅ በአለ ፋሲካ እንዴት ባለ አኳኋን አክብረውት ይሆን?” ብለን ብናስብና ብንጠይቅ ሀሳባችን መልካም ጥያቄአችንም ተገቢ ነው፡፡
የአይሁዳውያኑ በአለ ፋሲካ የሚከበርበት ቀን፣ የበአሉ ትርጉም፣ የተለያዩ ስያሜዎቹ ባጠቃላይ በአሉ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ ያሉት የተለያዩ የአከባበር ስነስርአቶች ዋነኛ መሰረታቸው ከአይሁዳውያኑ ቅዱስ መጽሐፍ ከታናክህ የቶራህ ክፍል ውስጥ ነው፡፡
ቶራህ የአይሁዳውያኑ ቅዱስ መጽሀፍ ከሆነው ከታናክህ ሶስት አበይት ክፍሎች አንዱና የሙሴ መጽሀፍት ተብለው የሚታወቁትን ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ኦሪት ዘዳግም ያሉትን አምስት መጽሀፎች ይዟል፡፡
በቶራህ እንደተገለፀውም አይሁዳውያን የእስራኤል ልጆች በግብጽ ፈርኦኖች እጅ ወድቀው ለአራት መቶ ዓመታት ያህል እጅግ አስከፊ የሆነ የባርነት ህይወት ገፍተዋል፡፡ በዚህ እጅግ መራራ የባርነት ቀንበር ስር ሳሉም “እግዚአብሔር እርሱ አምላካችን ነው፡፡ ሀጢያታችንን ሁሉ ይታገሰናል፣ ይቅርም ይለናል፡፡ ከመከራችንም ሁሉ ያድነናል፣ በማይዝለው ክንዱም ይታደገናል፡፡ አምላካችን እርሱ የእኛም ሆነ የልጅ ልጆቻችንን ልመናም ከቶ ችላ አይልም፡፡” ሰእያሉ ዘወትር አፋቸውን ለምህላ ለሚከፍቱለት አምላካቸው ያቀርቡት የነበረው ልመና በዋናነት ሁለት አይነት ነበሩ፡፡ አምላካቸው እንደተለመደው ሀጢያታቸውን በመታገስ ይቅር ብሎ ከግብጽ ባርነት ነፃ እንዲያወጣቸውና ለቀደመው አባታቸው ለአብርሃም ቃል እንደገባለት ለእነርሱ ትሆን ዘንድ መርጦ ያዘጋጀላቸውን ምድር ይወርሷት ዘንድ ከግብጽ ምድር እንዲያወጣቸው፡፡
እስራኤላዊያን ይሁዲዎች እነዚህን ሁለት ልመናዎች በግብጽ ምድር በባርነት ባሳለፉት ጊዜ ውስጥ ለአፍታም ሳይሰለቹ በማቅረብ አምላካቸውን ተማጽነዋል፡፡ ከአራት መቶ ዓመታት የባርነት ኑሮ በኋላ ግን ኒሳን በተሰኘው ወር፣ ከወሩም በአስራ አምስተኛው ቀን ልመናቸውን በመስማት ከመከራቸው ሁሉ የሚታደጋቸውና ልመናቸውን ሁሉ ከቶም ቢሆን ችላ የማይል አምላካቸው እንደሆነ እንደገና አሳያቸው፡፡
እነሆ፣ ወደር በሌለው በባርነት ጭቆና ይገዛቸው የነበረውን የግብጽን ፈርኦን በታላቅ መቅሰፍት በመምታት፣ የባርነቱን ቀንበር ሰብሮ ነፃ አወጣቸው፡፡ በዚያች ቀንም ለአብርሃም ቃል የገባለትን መሬት ለዘልአለም ርስታቸው አድርገው ይወርሷት ዘንድ አምላካቸው እግዚአብሔር ከግብጽ ምድር በሌሊት አወጣቸው፡፡
በእስራኤል ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ተበታትነው የሚኖሩ አይሁዳውያን ይህን በአለ ፋሲካቸውን ከፍ ባለ ስነስርአት የሚያከብሩትና በአሉም ከአይሁዳውያን አውራ ክብረበአሎች ውስጥ እንደ ዋነኛው ሆኖ የሚቆጠረው፣ ከባርነትና ከመከራ ህይወት ነፃ የወጡበት የነፃነት ቀናቸው በመሆኑ ነው፡፡
እነሆ “ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁናችሁ። ለእግዚአብሔር በአል ታደርጉታላችሁ፡፡ ለልጅ ልጃችሁ ስርአት ሆኖ ለዘልአለም ታደርጉታላችሁ።” ተብሎ በቅዱስ ቶራህ እንደተፃፈው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አይሁዳውያን ይህን በአላቸውን ያከብሩታል።
ይህ የአይሁዳውያን በአለ ፋሲካ ከላይ እንደተጠቀሰው፤ ሚያዚያ ስድስት ቀን ተጀምሮ ለአንድ ሳምንት ያህል በተለያዩ ስነ ስርአቶች ሲከበር ቆይቶ፣ ልክ በሰባተኛው ቀን እሁድ ሚያዚያ 12 ቀን በተጀመረበት ድምቀት የበአሉ አከባበር ስነ ስርአት ተጠናቋል፡፡ ከእስራኤል ውጪ እንደ አሜሪካ ባሉ ሀገራት የሚኖሩ አይሁዳውያን ደግሞ አንድ ቀን በመጨመር በአሉን ለስምንት ቀናት ያህል አክብረውታል፡፡
እንግዲህ የበአለ ፋሲካ መነሻው፣ አሰያየሙና ትርጉሙ ከዚህ በላይ የቀረበውን ይመስላል። በመላው ዓለም የሚገኙ አይሁዳውያን ይህንን ታላቅ በአለ ፋሲካቸውን የሚያከብሩት ደግሞ ይህን በመሰለ አኳኋን ነው፡፡
የአይሁዳውያን በአለ ፋሲካ የአከባበር ስነስርአት ዋነኛው እምብርት “ሰደር” በመባል ይታወቃል። ሰደር የሚለው እብራይስጥኛ ቃል ጥሬ ትርጉሙ “ስርአት፣ ቅደም ተከተል” ማለት ሲሆን በበአሉ ወቅት የሚደረገውን የአመጋገብም ሆነ ሌሎች ስነስርአቶች ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ በዚህም መሰረት ሀጋዳህ በተባለው የበአለ ፋሲካ የፀሎት መጽሀፍ እንደተዘረዘረው፤ የበአለ ፋሲካ የአከባበር ሰደር አስራ አምስት አይነት ደረጃዎች ወይም ቅደም ተከተሎች አሉት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ጥቂቶቹ የካዴሽ፣ ኡርሻትዝ፣ ካርፓትዝ፣ ያሼትዝና የማጊድ ስነስርአት ይባላሉ፡፡
ካዴሽ ለበአሉ የቀረበው ወይን ሲጠጣ የሚደረግ የቡራኬ ስነስርአት ሲሆን ኡርሻትዝ ደግሞ ለበአለ ፋሳካ የተዘጋጀውን ምግብ ለመቀደስ የሚደረግ ልዩ የእጅ መታጠብ ስነስርአት ነው፡፡ ካርፓስ በጨው የታሸ ወይም በጨው ውሀ ተነክሮ ከበአሉ ምግብ ጋር የቀረበውን አትክልት የመብላት ስነስርአት ነው። ያሼትዝ ለበአሉ የቀረበውን እርሾ የሌለው ወይም ያልቦካ ቂጣ ሶስቱን መሀል ለመሀል የመቁረስ ስነስርአት ሲሆን ማጊድ ደግሞ አይሁዳውያን የእስራኤል ልጆች፣ ከግብጽ የወጡበትን ታሪክ በቃል የመተረክ ስነስርአት ነው፡
እንግዲህ አይሁዳውያን በአለ ፋሲካቸውን የሚያከብሩት እነዚህንና ሌሎች አስር ስነስርአቶችን በቅደም ተከተል በማከናወን፣ ለበአሉ ተለይቶ የተዘጋጀውን ምግብ በመመገብና ከግብጽ ምድር የወጡበት ድንቅ ታሪክ በመተረክ ነው፡፡
በበአለ ፋሲካ ወቅት ለመላ ቤተሰቡ የሚቀርበው ምግብ የሚዘጋጀው እንደ አዘቦቱ
በበአለ ፋሲካ ወቅት ለመላው ቤተሰብ የሚቀርበው ምግብ በዋናነት ያለ እርሾ ወይም ካልቦካ ሊጥ የተጋገረ ቂጣ፣ ከጠቦት በግ የተዘጋጀ የጎድንና የቅልጥም ጥብስ፣ በጨው የታሸ አትክልትና መራራ ወይም ጎምዛዛ ቅመም ሲሆን ለመጠጥ የሚቀርበው ደግሞ ወይን ነው፡፡
ለበአሉ ተብለው የሚቀርቡት እነዚህ የምግብ አይነቶች የተመረጡት እንዲሁ ሳይሆን የበአሉን ምንነት እንዲያስረዱ ተደርጎ ነው፡፡ ለምሳሌ ካለ እርሾ ወይም ካልቦካ ሊጥ የተጋገረ ቂጣ የሚበላው “እርሾ ያለበትንም ምንም አትብሉ፤ በቤቶቻችሁም ሁሉ ውስጥ ቂጣ እንጀራ ብሉ፡፡” ተብሎ በቅዱስ ቶራህ ስለታዘዘ ነው፡፡ “ሰባት ቀን በቤታችሁ እርሾ አይገኝ፡፡ እርሾ ያለበትንም እንጀራ የሚበላ ነፍስ ከመፃተኛው ጀምሮ እስከ አገር ልጁ ድረስ ከእስራኤል ማህበር ተለይቶ ይጥፋ፡፡” የሚለውን አምላካዊ ትዕዛዝ ለመጠበቅም ማንም አይሁዳዊ ለሰባት ቀን በእርሾ የተጋገረን ቂጣ ወደ አፉ አያዞርም፡፡
የጠቦት በግ ጥብስ የሚቀርበው ጥንታዊውን ለአምላካቸው የሚያቀርቡትን መስዋዕት ለማስታወስ ሲሆን መራራ ወይም ጎምዛዛ ቅመም የሚቀርበው ደግሞ የባርነትን ህይወት አስከፊነት ለማስታወስ ነው፡፡
ለበአሉ የተዘጋጀው ምግብ በዚህ መልክ ተሰናድቶ ከቀረበና የቤተሰቡ አባላት በሙሉ የምግቡን ዙሪያ ክብ ሰርተው ከተቀመጡ በኋላ ስርአቱ በካዴሽ ወይም ለአምላክ ቡራኬ በማቅረብና ለበአሉ የተዘጋጀውን ወይን በመቅመስ ይጀመራል፡፡ የካዴሽ ስነስርአቱ ከተጠናቀቀ በኋላ በቤቱ አባወራ (አንዳንዴ የቤተሰቡ አባላት በመቀባበል ያደርጉታል) የሚቀርብ አይሁዳውያን ከግብፅ ምድር እንዴት እንደወጡ የሚያስረዳ ታሪክ ትረካ ይቀጥላል፡፡
ይህ ትረካ በቤቱ አባወራ የሚቀርበው “እግዚአብሔር እንደተናገረ ወደ ሚሰጣችሁ አገር በገባችሁ ጊዜ ይህን አምልኮ ጠብቁት፡፡ እንዲህም ይሆናል፤ ልጆቻችሁ ይህ አምልኮ ለእናንተ ምንድን ነው? ባሏችሁ ጊዜ እናንተ በግብጽ አገር በእስራኤል ልጆች ቤቶች ላይ አልፎ ግብፃውያንን በመታ ጊዜ ቤቶቻችንን ያዳነ የእግዚአብሔር የማለፍ መስዋዕት ይህች ናት ትሏቸዋላችሁ፡፡” ተብሎ በቅዱስ ቶራህ የተፃፈውን ለመጠበቅ ነው፡፡
በያሻትዝ ስነ ስርአት ጊዜ ካለ እርሾ ከተዘጋጁት ቂጣዎች ውስጥ ወደ ላይ ከፍ በማድረግ፣ መሀል ለመሀል የሚቆረሱት፣ አይሁዳውያን ከግብፅ ምድር በጥድፊያ መውጣታቸውንና ያኔ ምን ያህል ድሆችና ጎስቋሎች እንደነበሩ ለማሳየት ነው፡፡
ለፋሲካ ሰደር የተሰየሙት አይሁዳውያን የቤተሰብ አባላት ለበአሉ ከተሰናዳው ወይን የሚጠጡት አራት ኩባያ ያክል ነው፡፡ ይህም የሆነው እንዲሁ ሳይሆን እያንዳንዱ ኩባያ አምላክ የገባላቸውን ቃል ኪዳን ስለሚወክል ነው። እያንዳንዱ አይሁዳዊ ቤተሰብ ለፋሲካ ሰደር ሲታደም ለመአዱ ከቀረቡት የቤተሰቡ አባላት ቁጥር በተጨማሪ አንድ የወይን መጠጫ ኩባያ ለብቻው ተዘጋጅቶ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡ ይህ የሚሆነው እያንዳንዱ ቤተሰብ ለዚህ የፋሲካ ሰደር ነብዩ ኤልያስን ስለሚጋብዝ መንፈሱ በቤቱ ውስጥ ካረፈ እንዲቀመጥበት በማለት ነው፡፡
የቂጣ ቆረሳው ስነ ስርአት ከተጠናቀቀና የውዳሴ መዝሙር ከተዘመረ በኋላ፣ ቀጣዩ ስነስርአት ዳግመኛ እጅን በመታጠብ ወይም በራሽትዛህ ስነ ስርአት ይጀመራል፡፡ ቀጥሎም የውዳሴና ሌሎች በዚህ በአል ጊዜ የሚቀርቡ የምስጋና ምግብ በመራራ ወይም በጎምዛዛ ቅመም እያጠቀሱ መብላት ወይም የሹልካን ኦርሽ ስነ ስርአት ይቀጥላል፡፡
እንዲህ እንዲህ እያለ የበአለ ፋሲካ አከባበር ስነ ስርአት እስከ ሰባተኛው ቀን ድረስ ይቀጥላል፡፡ ልክ በሰባተኛው ቀን ኒርዛህ በተሰኘውና በመጨረሻው የአከባበር ስነ ስርአት ሞቅ ባለ የምስጋና መዝሙር ታጅቦ የተለመደውን የበአል ማሳረጊያ “ለከርሞ እየሩሻሌይም እንገናኝ!” በመባባል የበአሉ ፍፃሜ ይበሰራል፡፡
ይህን ጽሁፍ ላነበባችሁ ሁሉ ሂይሂየ ላሽዩም ናይም! ቀኑ መልካም ቀን ይሁንላችሁ!!  

Read 6256 times