Saturday, 26 April 2014 12:18

“መልካም ሥራ ሥራና ሰይጣን ይፈር” (Do Good and Shame the Devil)

Written by 
Rate this item
(9 votes)

“መሣሣት የሰው ነው፡፡ ይቅር ማለት ግን የመለኮት!”
(to err is human, to forgive is divine)
ሁለት ሰዎች ከሩቅ አንድ የአውሬ ቅርፅ ያያሉ፡፡
አንደኛው፤
    “ያ የምናየው እኮ ጅብ ነው” አለ፡፡
ሁለተኛው
    “ያ የምናየው እኮ አሞራ ነው” አለ፡፡
አንደኛው፤
    “እንወራረድ?”
ሁለተኛው፤
    “በፈለከው እንወራረድ!”
አንደኛው፤
    “እኔ አንድ በቅሎ አገባ!”
ሁለተኛው
    “እኔም በቅሎ ከነመረሻቷ አገባ!”
መልካም፡፡ ቀረብ ብለን እንየው፡፡ እየተጠጉ መጡ፡፡
አንደኛው፤
    “አሁንም በአቋምህ ፀንተሃል? አሞራ ነው የምትል?”
ሁለተኛው፤
    “ከፈራህ አንተ አቋምህን ቀይር እንጂ እኔ አሞራ ነው ብያለሁ አሞራ ነው!”
አንደኛው፤
    “እኔ ፈሪ ብሆን ጅብ መሆኑን እያየሁ ቀርበን እናረጋግጥ እልሃለሁ?!” አለ በቁጣ፡፡
እየቀረቡ መጡ፡፡
የእንስሳው ቅርፅ አሁንም አልተለየም፡፡
ተያይዘው ቀረቡ፡፡
እጅግ እየተጠጉ ሲመጡ፤ ያ ያዩት እንስሳ አሞራ ኖሮ ተነስቶ በረረ፡፡
ሁለተኛው ሰው፤
    “ይኼው በረረ፡፡ አሞራነቱ ተረጋግጧል፤ ተበልተሃል!”
አንደኛው፤
    “በጭራሽ አልተበላሁም!”
ሁለተኛው፤
    “እንዴት? ለምን? አስረዳኛ?!”
ይሄኔ አንደኛው፤
    “ቢበርም ጅብ ነው! መብረር የሚችል ጅብ መኖር አለመኖሩን በምን ታውቃለህ? አለው፡፡”
                                            *     *      *
በህይወታችን ውስጥ የዋሸነው፣ የካድነውና በዕንቢ-ባይ ግትርነት አንቀበለውም ያልነው፤ በርካታ ነገር አለ፡፡ የሁሉ ቁልፍ፤ ስህተትን አምኖ፣ ተቀብሎ ራስን ለማረም ዝግጁ መሆን ነው!!
ይቅርታ መጠየቅና ይቅር ማለት የዘመኑ ምርጥ አጀንዳ ነው - በተለይ በኢትዮጵያ - በተለይ በዳግማይ ትንሣኤ ሰሞን! ሰሞኑን “በአይዶል” ፕሮግራም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያየናት ልጅ፤ ከፋሲካ እስከ ዳግማይ ትንሣዔ ብሎም እስካገራችን ዕውነተኛ ትንሣዔ ድረስ፣ ከተማርን ከተመካከርንባት፣ ልዩ ተምሣሌት፣ ልዩ አርአያ ናት፡፡ “መሣሣት የሰው ነው፤ ይቅር ማለት ግን የመለኮት” የሚለው አባባል ትርጓሜው” እዚህ ጋ ይመጣል፡፡ የዋሸነውን፣ ለማታለል ያደረግነውን ለማሳመን መንገዱ ይሄ ነው ብለን ሰው ሁሉ/ ህዝብ ሁሉ እንዲያምነን ላደረግነው ነገር፤ ቆይተን፣ ተፀፅተን፣ ለራሳችን ህሊና ተገዝተን፣ ንሥሐ መግባት መልመድን የመሰለ መንፈሣዊ አብዮት የለም፡፡ ያን መሣይ መንፈሣዊ ለውጥ አይገኝም!! እስከዛሬ፤ በቀደሙትም ሆነ አሁን ባሉት ፓርቲዎች ዘንድ፣ በቀደሙት መንግሥታትም፣ አሁን ባለው መንግሥትም ዘንድ የማይታወቀው፤ እጅግ ቁልፍ ነገር፤ “ተሳስቻለሁ… ይቅርታ” ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያየናት የ“አይዶል” ተወዳዳሪ ድምፃዊት ያሳየችንና ያስተማረችን ጉዳይ ይሄው ነው፡፡ በእኛ ግንዛቤ፤ ተወዳዳሪዋ በድምፃዊ አረጋኸኝ ወራሽ ቤት በልጅነቷ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ፣ ቀጣሪውን ማለትም አርቲስቱን ስለራሷ ህይወት ዋሽታዋለች፡፡ አርቲስቱ በሰማው አሳዛኝ የህይወት ታሪክ ልቡ ተነክቷል፡፡ ትምህርት እንድትጀምርም ያደርጋል፡፡ ልጅቱ ድንገት ከቤት ትጠፋለች፡፡
ዛሬ ግን አርቲስቱ በዳኝነት በተገኘበት መድረክ፤ የ“አይዶል” ድምፃዊት ተፈታኝ ሆና ስትቀርብ ድምጿን ካሰማች በኋላ፤ “ከመዳኘቱ በፊት አንድ ነገር ለመናገር እፈልጋለሁ አለች፡፡” ዳኞቹ ፀጥ አሉ፡፡
እዚህ መካከል አንድ የማውቀው ሰው አለ፡፡ እሱም ግር ብሎት ካልሆነ ያውቀኛል፡፡ እሱ ቤት በልጅነቴ ተቀጥሬ ነበር፡፡ ሁኔታዬንና የውሸት ታሪኬን ሰምቶ፤ አምኖኝ፣ ት/ቤት አስገብቶኝ፤ እኔ ግን ከቤቱ ጠፍቼ ሄጃለሁ፡፡ ያ ሰው፤ ድምፃዊ አረጋኸኝ ወራሽ ነው… እሱ ቤተሰቦቼን ሊያፈላልግ ሞክሯል ግን አልተሳካለትም፡፡
“እኔም ተመልሼ ሁኔታውን ለመግለጽ ሁኔታውም ድፍረቱም አልነበረኝም፡፡” የምትለው አርቲስት፤ “ዛሬ ግን ዕውነቱን ለማሳወቅ እፈልጋለሁ፡፡ ስለቤተሰቦቼ አለመኖርና ስራ ስለማጣቴ ሁሉ ያወራሁት ውሸት መሆኑን ዛሬ በግልጽ ማስረዳት እፈልጋለሁ፤ ይቅርታ እንዲያደርግልኝም እጠይቃለሁ” ነው የንሥሐዋ መንፈስ! የዳግማይ ትንሣዔ መሪ መልዕክት (1) “ልናጠፋ እንችላለን ግን ይቅርታ ጠይቀን ቀሪውን ህይወት ማስተካከል እንችላለን” ነው፡፡ ልብ እንበል፤ ልጅቱ ለአረጋኸኝ ወራሽ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ህዝብ ነው ንሥሐዋን የተናገረችው! አቤት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይሄን ቢያውቁ! አቤት ገዢው ፓርቲ ይሄን ቢችልበት አቤት በየደረጃው ይቅርታ መጠየቅ አልባ የሆነ ኃላፊ፣ አለቃ እና የበላይ ይህን ቢረዳ! አቤት አበሻ በጠቅላላ፤ ይሄ ቢገባው!
ሁለተኛው የፋሲካና የዳግማይ ትንሣዔ ግብረገባዊ ትምህርት (The Moral of the Story) የ “ጆሲ ኢን ዘ ሐውስ” ገድል ነው፡፡ የማን ያለብሽ ዲቦን ልጆችና እህት አንድ መጠለያ ለማስገኘት ጆሲ ያረገው ጥረት የወቅቱ መልዕክት ነው፡፡
ትምህርት 1) ከኢትዮጵያ የቤት - ነክ ቢሮክራሲ ጋር፣ ውጣ ውረዱን ችሎ፣ ታግሦ፣ ተቻችሎ ውጤት ማስገኘት
ትምህርት 2) እያንዳንዱን ክስተት በካሜራ ቀርፆ፣ መንግሥትም አምኖበት ለዕይታ መብቃቱ፤
ትምህርት 3) የመንግሥት ፈቃደኝነትና አዎንታዊ እርምጃዎች መረጋገጥ
ትምህርት 4) በየደረጃው ያሉ ስፖንሰሮች ሀ) የደብረዘይት መናፈሻ ቦታው ስፖንሰርሺፕ ለ)የመጓጓዣ መኪናው  ሐ) የአዋሳ ኮሜዲያን መምጣት መ) የጋሽ አበራ ሞላ መምጣት ሠ)የቤት - ዕደሳ ላይ የተሳተፉት ስፖንሰር ድርጅቶች መኖር ረ) የቤት ዕቃዎች ለማሟላት አስተዋጽኦ ያደረጉ ስፖንሰሮች መኖር ሰ) ለልጆቹ ትምህርት መቀጠል የት/ቤቶችና የዩኒቨርሲቲዎች ትብብር፣ ሸ) የኮምፒዩተር እገዛ ለማድረግ የተባበሩ ኮምፒዩተር አስመጪዎች     
ትምህርት 5) የልጆቹ መኖሪያ ጐረቤቶችን ማሰባሰብና ጉዳዩን እንዲረዱ ማድረግ፣ ሰው                   የአካባቢው ውጤት መሆኑን ይነግረናል፡፡
እኒህን ሁሉ ስፖንሰሮችና ነዋሪዎች አስተባብሮ ዓይነተኛና አርአያዊ ተግባር መፈፀሙ ጆሲን ድንቅ የሚያሰኘው ነው፡፡ ማስታወቂያ ሰሪዎች እንማር! አገር አልሚዎች እንማር! የተቀደሰ ተግባር፣ ለተቀደሰ ትንሣኤ እንደሚያበቃን ለማረጋገጥ የጆሲ ዚን ዘ ሐውስን ተምሳሌትነት እንገንዘብ፡፡ አንድ ቤተሰብ መገንባት ሙሉ አገር መገንባት ነው፤ “አምሣ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለአምሣ ሰው ጌጡ ነው” ነው መንፈሱ፡፡ በርካታ ስፖንሰሮች ለመዝናኛ ስፖንሰር እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ይመሰገናሉም፡፡ ሆኖም ዛሬ የተሻለ ስፖንሰራዊ ተግባር አይተናል፡፡ በየማስታወቂያዎች ውስጥ መዝናኛ ብቻ ሳይሆን ቁምነገር፣ ለሀገር የሚጠቅም ጉዳይ፣ መካተት እንደሚችል በአጽንኦት ይጠቁመናል፡፡ ለብዙዎቻችን ትምህርት ነው፡፡ ሁሉን አቀፍ የስፖንሰርሺፕ እንቅስቃሴ አገር ያለማል፡፡ እንደ ጆሲ ያለ ልባዊና ልባም ሥራ ምን መምሰል እንዳለበት ታላቅ ደርዝ፣ ታላቅ ፍሬ - ጉዳይ ያስጨብጠናል፡፡ አገር የሚመራ ይህን ይገንዘብ፣ ማስታወቂያ የሚሠራ ይሄን ይገንዘብ፤ አገርን የሚያስብ ይሄን ይገንዘብ፡፡ “መልካም ሥራ ሥራና ሠይጣን ይፈር” የሚለው የሼክስፒር ጥቅስ ትልቅ ትርጉም የሚኖረው ዛሬና እዚህ ላይ ነው!!

Read 6784 times