Saturday, 19 April 2014 12:43

የአርቲስት ግሩም ኤርሚያስ ጉዳይ መታየት ያለበት በጥበብ ፍርድ ቤት ነው

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

ግሩም ኤርሚያስ በ “ሰይፉ ፋንታሁን ሾው” ላይ ቀርቦ የነበረበትን “አወዛጋቢ” ፕሮግራም እኔ አልተከታተልኩትም። ባልከታተለውም ጉዳዩ ተብራርቶልኛል። አርቲስቱን ወይንም የፕሮግራሙን አዘጋጅ ከተቹት መሀል የቴዎድሮስ ተ/አረጋይን መጣጥፍ አንብቤአለሁ። የሱንም ያነበብኩት፣ ጉዳዩን ከተለመደው የማውገዝ ነሲባዊነት ከፍ ባለ እይታ መንዝሮ ቅድመ መጠይቆችን ያቀርባል ብዬ ገምቼ ስለነበር ነው፡፤ አልሆነም።
ከቴዎድሮስ ተ/አረጋይ በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ አንድ ባለሙያ (አዋቂ) ከህግ አንፃር የተዋናዩ ድርጊት ወንጀል መሆኑንና ሊያስቀጣው እንደሚችል አንቀፆችን እየዘረዘረ መረጃ ሊያስጨብጠን ጥሯል።
የማህበረሰብ ተወካዮች ወይንም ተቆርቋሪዎች የሚሉትን ሰምተናል። አሁን የቀረን የጥበብ ተቆርቋሪዎች ምን እንደሚሉ ብቻ ነው። በማህበረሰብ ፍርድ ቤት አርቲስቱ “7” አመት ሊያስፈርድበት ከቻለ በጥበብ ፍርድ ቤት ምን ይጠብቀው ይሆን? በነፃ ይለቀቃል? ወይንስ ሰባት አመት የጥበብ እድሜ በህይወቱ ላይ “እደግ” ተብሎ ይመረቅለታል? አውቃለሁ ህግ የሚቆመው ለማህበረሰቡ ነው። ግን የማህበረሰቡ ህግ አንዳንዴ በጭፍን ጥበበኞችን ጨፍልቆ እንዳይገድል …ሌላ እይታንም ሚዛን ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ለጥበበኛው እና ለጥበቡ ህልውና ሲባል የማህበረሰብ ተቆርቋሪዎች በጥበበኛው ላይ ፍትህ እንዳያጓድሉ የጥበብ ፍርድ ቤት ጉዳዩን መዳኘት ይገባዋል።
የእስታንስላቭስኪ ሜተድ
ሜተድ “መምሰል ሳይሆን መሆን” በእርግጥም አጠቃልሎ ይገልፀዋል። “መሆን” ማለት ተዋናዩ የሚጫወተው ገፀ ባህርይን በውጫዊ ማንነቶቹ መቅረብ ሳይሆን ውስጡንም በስነ ልቦናው ገብቶ መጨበጥ ማለት ነው። እስታንስላቭስኪ ያስተዋወቀው:- ተዋናዩ ገፀ ባህሪው በአካል ሳይሆን በስነ ልቦና አማካይነት የራስ ማድረግ የሚለውን ዘዴ (Method) ማርታ አብርሃሞቪች የፐርፎርመንስ አርቲስት ነኝ።  ነው። በተመልካቾቿ ፊት ልብሷን አውልቃ በመለመላዋ ቆማ ገላዋን በቢላዋ እየቆረጠች ታደማለች፣ በአለንጋ ገላዋን ትገርፋለች። ባዘጋጀችው ወንበር ላይ ቀና እንዳለች ተቀምጣ ለቀናት ያለ እንቅስቃሴ ትቆያለች። ለእያንዳንዱ ተመልካች በሚሆን የሚያሳዝን ፊት በገጽታዋ ላይ እየሳለች በፊቷ (በአካሏ) አማካኝነት ልባቸውን ትነካለች። በአሁኑ ጊዜ ፐሮፌርመንስ አርት ዘመናዊው የጥበብ መግለጫ አውታር ሆኗል። አርቲስቷ በምታስገባው ተመልካችም ሆነ ገንዘብ መጠን የቀድሞውን የመድረክ አርቲስቶች የት እና የት በልጣቸዋለች።
“እኔ የማፈሰው እውነተኛውን ደም ነው፤ የመድረክ ተዋናይ የሚያሰፈው ደም ግን ቀይ (የውሸት) ቀለም ነው” ትላለች፤ የሷን መሆን ከሌሎቹ መምሰል ጋር ስታነፃፅር።
“ሜተድን” የፈጠረው እስታንስላቭስኪ ቢሆንም ከፊልም ጋር ያዋሀደው ግን (ለኔ) ማርሎን ብራንዶ ነው። እስቴላ አድለር የምትባል የትወና ትምህርት የምትሰጥ ሴት “ከዘዴው” ጋር አስተዋወቀችው፣ ኤሊያ ካዛን የሚባል ዳይሬክተር ደግሞ ዘዴውን በፊልሞቹ ላይ እንዳሻው እንዲጠቀም እድል ሰጠው።
በመጀመሪያዎቹ አራት ፊልሞቹ ሆሊዉድን እንደ አዲስ አፍርሶ መስራት ቻለ። ከአራቱ ፊልሙ አንደኛው ገፀ ባህርይ የጦር ጉዳተኛ ሆኖ የሚተውንበት ነበር። የጦር ጉዳተኛውን ገፀ ባህሪ “ለመምሰል ሳይሆን ለመሆን” የወሰደው የጥናት እርምጃ የጦር ጉዳተኞችን በሚያክም ሆስፒታል ውስጥ ጉዳተኛን መስሎ መግባት ነበር። መግባት ስል… ገብቶ ጐብኝቶ ለመውጣት ወይንም እነሱን ጥያቄ እየጠየቀ ኖት እየያዘ ለማጥናት አይደለም አገባቡ። እንደ በሽተኛ አልጋ ይዞ የቆየውም ወደ ሁለት ወራት ገደማ ለሚገመት ጊዜ ነው። ልክ እንደ እውነተኛ በሽተኛ ሲያነሱት እና ሲያስቀምጡት አካሉ እንደማይታዘዘው ሰው እየተገላበጠ በእግሩ ሳይራመድ ቆየ።
ጥናቱን ጨርሶ ወጥቶ ፊልሙን ከሰራ በኋላ ቆይቶ በሆስፒታሉ ውስጥ አብረውት የከረሙ ታማሚዎች አካለ ስንኩል እንዳልነበረና ተዋናይ እንደሆነ የተገነዘቡት።
እንግዲህ በትንሹ የ “ዘዴ”ው ተከታዮች ዲሲፕሊን ይሄንን ይመስላል። ለመተወን የሚመርጡት ገፀ - ባህሪይ ሁሌ መልካሙን ላይሆን ይችላል። አንዳንዴ እፅ ተጠቃሚ፣ ሌላ ጊዜ ወንጀለኛን ወይንም ጉልበተኛን ይሆናል። …ከራሳቸው ፍላጐት ተነስተው የሚተውኑትን ገፀ ባህርይ ይመርጣሉ።
[N.B የሜተድ አርቲስቱ ሳይሆን የሜተድን ፅንሰ ሃሳብ ነው ማህበረሰቡ መዋጋት  ያለበት። ማህበረሰቡ በህግ ረቂቅ ተዋናይ መከተል የሚችላቸው እና የማይችላቸው እምነቶችን የዘረዘረ አይመስለኝም። ምንም ነገር ካልተከለከለ ሁሉም ነገር ትክክል ነው]  
ማርሎን ብራንዶ በጣም የሚታወቀው “The God father” ፊልም ላይ ዶን ኮርሊዮን የተባለውን ገፀ ባህርይ ወክሎ በተጫወተበት ጊዜ ነበር። ይሄንን ገፀ ባህርይ ሲጫወት እድሜው አርባዎቹ መጀመሪያ ላይ ስለነበረ ገፀ ባህርይውን ለመፍጠር ይሁን አሊያም የጡት አባትነት ባህርይ ለማላበስ በሁለቱ ጉንጮቹ ውስጥ ደረቅ ነገር አስገብቶ የተለጠጠ ፊት ለራሱ ፈጥሮ ተውኔቱን ተጫውቷል።
“Viva Zapata” የተባለውን ፊልምም ሲሰራ የደቡብ አሜሪካውን ጀግና ገጽታ ለመላበስ ሁለት ትልልቅ ቀለበት በአንጫዎቹ ቀዳዳ  ለረጅም ጊዜ ወትፎ የአፍንጫውን ቀዳዳ አስፍቶ ነበር። ይህ ሁሉ ለመምሰል ሳይሆን ለመሆን  የሚደረግ ሙከራ ወይንም መከራ ነው።
“መሆን” ሲባል ገፀ ባህርይውን መሆን ለማለት ነው።
ይህ ከሆነ ሙከራው… ታዲያ በተዋናዩ ግሩም ኤርሚያስ ከገፀ ባህርይው ጋር በሚጋሩት አካል አማካኝነት ገፀ ባህርይው ነፍስ ቢዘራም፣ በሰውየው (ግሩም) እና በገፀ ባህርይው መሀል ምንም ግንኙነት በትወናው ወቅት የለም ማለት ነው። መወገር ካለበት መወገር የሚገባው ገፀ ባህርይው ነው። ግሩም ኤርሚያስ ራሱ በሰይፉ ሾው… ሶፋ ላይ ተቀምጦ የገፀ ባህርይውን ትወና ሲመለከት ተዋናዩ “እኔ ነኝ” ካለ ግራ መጋባት ውስጥ ወድቋል። ሶፋ ላይ ተቀምጦ የሚመለከተው እሱነቱ በፊልሙ ላይ ሲተውን ከሚታየው ጋር አንድ ከሆነማ…ምን መምሰል ወይንስ መሆን የሚል ክርክር ያስፈልጋል?...ሁለቱ ልዩነት ሳይሆን አንድነት ነው ያላቸው ማለት ነው። “ምስሉ ላይ የምታዩት “እንቶኔ” የተባለው ገፀ ባህርይ ነው… እኔ ደግሞ ግሩም ኤርሚያስ ነኝ” እንዲል ነው የሚጠበቅበት። “ዘዴውን” (Method) በማጥናት ላይ ላለ ተዋናይ ግን አልፎ አልፎ በራሱ እና በገፀ ባህሪው መሀል የማንነት መደናበር ሊከሰት ይችላል። አርቲስቱ አርቱን ለመስራት የተጠቀማቸውን መንገዶች… ከመንገዱ ጋር ለማይተዋወቅ ማህበረሰብ መግለጽ ለውዝግብ ምክንያት ይሆናል። “እንቁን እርያ መሀል መጣል” ለባለእንቁው ነው ጉዳቱ፤ እሴቱን እና ልፋቱን ሳይጠቀምበት ይረጋገጥበታል።
ጥበብ እና ማህበረሰብ
ብዙ ፈላስፎች እና አርቲስቶች ከጥንታዊቷ ግሪክ ዘመን አንስቶ (በሚያስደነግጥ ሁኔታ) እስካሁንም ድረስ የጥበብ ፍሬ “መልካምነቱ” የሚረጋገጠው ወይንም የሚበየነው ጥበበኛው በጥበቡ በኩል ለማህበረሰቡ ምን እንዳበረከተ ከተመዘነ በኋላ ነው፤ ብለው ያምናሉ። ጥበበኛው የማህበረሰቡ የጥቅም አገልጋይ ተደርጐ ይወሰዳል።
ጥበበኛው፤ የመምረጥ ነፃነት አለው (ሊኖረው ይገባል)። የፊልሙ ወይንም ተውኔቱ ደራሲ “ካናቢስ ተጠቃሚዎችን” ለድርሰቱ የመረጠበት ምክንያት ከራሱ የሚዛን ምርጫ እና ወቅታዊ/አንገብጋቢ አጀንዳነቱ ተነስቶ ሊሆን ይችላል። እንደ ደራሲው ተዋናዩም የመምረጥ ነፃነት አለው። የፈለገውን ገፀ ባህርይ ወስዶ መስራት ወይንም አለመስራት ይችላል። ያልተሞከረ ገፀ ባህሪን ለመጫወት አርቲስቱ ሲደፍር ፈተናውን ያበዛበታል። የፈተናውን ዳገት መውጣት ከቻለ ሽልማቱም አክብሮቱም ከፍ ያለ ይሆናል። ማህበረሰብ አዲስ ነገርን ለመቀበል ይከብደዋል። አርቲስቱ ግን አዲስ ነገርን ለመፍጠር ይገደዳል። በማህበረሰብ እና በጥበብ መሀል ያለው ግጭት በዚህ ርቀት ውስጥ የሚፈጠር ነው።
ይህ ከላይ ያልኩት የአርቲስቶቹን ምርጫ ሉዓላዊነት በተመለከተ ነው። በበለጠ የሚገርመው ግን ፊልሙን ወይንም ተውኔቱን እንዲሁም ድርሰቱን ተቀባዩ ማህበረሰብም፣ ህዝብም የመምረጥ ነፃነት አለው። የሚፈልገውን የማየት እና የማይፈልገውን የመተው። ይኼንን ምርጫ ማህበረሰቡ ስለራሱ ጥቅም እና አደጋ ሲል መጠንቀቅ የማይችል ከሆነ ህግ እና ህግ አስከባሪ እንዲጠነቀቅለት ይሁንታውን ይሰጠዋል። ይህ ይሁንታ ሳንሱር የሚባለው መሆኑ ነው።
በመንግስት እና ህግ ወይንም ባህላዊ ስነምግባር አማካኝነት የሚጠቅመውን እና የሚጐዳውን የሚመርጥ ከሆነ… በራሱ በግለሰብ መመዘኛ ጥሩ እና መጥፎን መምረጥ የማይችል ነው ማለት ይመስላል።
በአሁኑ ሀገራዊ/ ወቅታዊ ሁኔታ ግን ሁለቱም የሉም። ግለሰቡም በራሱ ምርጫ ሲመራ መንግስትና ህግም በሳንሱር ማህበረሰቡን ከጥፋት ሲከላከሉ (ካልሆነም ሲያፍኑ) አይታይም። ሁሉም መጽሐፍ ይጽፋል፣ ሁሉም ዘፈን ይዘፍናል፣ ፊልም ያመርታል።
“የፈለግኸውን ፍጠር ግን ፈጠራህ ቁጣን እሚያስነሳ ከሆነ እቀጣሀለሁ” ይመስላል… የተደበላለቀው ደንብ።
ለመሆኑ ግን እስካሁን በተበረከቱ “The so called” “ማህበረሰቡን የሚያንፁ አስተማሪ ጥበቦች” ማህበረሰቡ ምን ያህል እንደተማረ ወይንም እንደታነፀ በመረጃ እና ኮስተር ባለ ጥናት የመረመረ ባለሞያ ይኖር ይሆን? ያለ አይመስለኝም። አጠናሁኝ ቢለኝም ጥናቱ ራሱ ፕሮፓጋንዳ መሆኑ ያስፈራኛል።
ማህበረሰቡስ አርቲስቱን ለማነፅ ከሞከረው ሙከራ በዘመናት ውስጥ የተሳካለት ምን ያህል ነው?...ስብሐት ገ/እግዚአብሔር ማህበረሰቡን አንፀ ወይንስ ማህበረሰቡ ስብሐትን? ሁለቱም የተከሰቱ አይመስለኝም።  
አርቲስቱ ግን ሀቀኛ ከሆነ ማህበረሰቡ እየሄደ ያለበትን አቅጣጫ በስሚ ስሚ…በመምሰል ሳይሆን ቀርቦ በመመርመር ይገልፀዋል። አንዳንዱ የመግለጫ ዘርፍ (ሚዲየም) ገለፃውን የሚያቀርበው እንደ ሙዚቀኛ በሙዚቃ መሳሪያ ነው።
ወይንም እንደ ሰአሊ በብሩሽ፤ አሊያም እንደ ፀሐፊ በብዕር። ሌላው ደግሞ በራሱ አካል አማካኝነት የሚጠበብ እንደመሆኑ፣ ገለፃውን “በብዕር ስም” ሊከውነው አይችልም። ልጅ ግሩም ኤርሚያስም ለዚህ ሚዲየም ተሰጥኦ ኖሮት ማህበረሰቡን ገልጦ ለማህበረሰቡ ትችት የተጋለጠ ሰለባ ይመስለኛል።
አስወጋሪዎቸ እና ማህበረሰብ
“ለምን ጫካችንን ገበያ አወጣኸው?!” ይመስለኛል በተዋናዩ ላይ የተሰነዘረው ቅሬታ ሲጠቃለል። ለጥያቄው፤ ጥበበኛው መስጠት ያለበት መልስ (እኔ እንደሚመስለኝ) “የማህበረሰብን ሚስጢር በአደራ ደብቆ ከመንከባከብ ይልቅ መግለጽ እና መፍጠር በአርቲስቱ ማንነት ላይ የበለጠ አስገዳጅ ስለሆነ” የሚል ነው።
በኔ እምነት ግን… በዚህ በሰሞኑ ውዝግብ ላይ የመውገር ፍላጐቱ የመነጨው ከማህበረሰቡ አይደለም። ይሄንን እርግጠኛ ነኝ። ምክንያቱም፤ ማህበረሰቡ የካናቢስ ተጠቃሚነት ችግር አለበት። ችግሩን  የሚገልጽለት እና መፍትሄም ሆነ ማስተዛዘኛ የሚጭርለት ተወካይ እንዲኖርለት የሚመኝ መሆን ነበረበት። ማህበረሰቡ ወደ እስታትስቲክስ እና ቁጥር ከተጨመቀ በአብዛኛው ወጣትን ይመስላል።
ወጣቱ በሱስ ተጠምዷል። ሱሱ በእስታስቲክስ ወደ ቁጥር ከተጨመቀ ካናቢስ ከተጠመደባቸው ሱሶች መሀል አንዱ ነው። ነፃ በተለቀቀ ኢንተርኔት አሰቃቂ እና ገፋፊ ፊልሞችን፣ የጭካኔ ድርጊቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ አውርዶ ይኮመኩማል።
ግሩም ኤርሚያስም ባይተውነው ከተውኔቱ ቀድሞ ወጣቱ በተጠቀሰው ሱስ ደካክሟል። እና አስቀድሞ ለሰፈነው ችግር ተጠያቂው ችግሩን በጥበብ የገለፀው ነው አላችሁ? የጥበብ ፍርድ ቤት የለችም እንጂ ይህንን ውንጀላ አትታገሰውም ነበር!
የፋሲካ ወቅት ነው። አውቃለሁ አዲስ የመስዋዕት በግ ያስፈልጋል። እውነተኛውን በግ ያስታውሰን ዘንድ ከሆን ጥበበኛን መስቀል ያስፈለገው…መስቀሉም የማስታወሻ እንደሆነ አያጠራጥርም።
የምናስታውሰው፤ ማህበረሰብ እና ጥበብ ዝንተ አለም ቅራኔ እንደሚኖራቸው ነው። ጥበብ ማህበረሰብን ለመምራት እንደምትሻው ማህበረሰብ ደግሞ ጥበብን እንደ ባሪያ ቆጥሮ እያገለገለችው እንድትኖር ይሻል። ግን የሚያሳዝነው እያገለገለችውም… ግልጋሎቷ ቀድሞ በለመደው ዘይቤ ባለመገለፁ አመጽ ያስነሳችበት ይመስለውና…መስቀል ሰርቶ ሊሰቅላት ድንጋይ ጠርቦ ሊወግራት ይነሳል።
ይሄ የፋሲካ ወቅት ነው። አንዱ ሌላውን ሳይሰቅል መከባበርን የምናስታውስበት እንዲሆን ምኞቴ ነው።

Read 4022 times