Saturday, 19 April 2014 12:32

እህትማማቾቹ

Written by  ደራሲ - ጄምስ ጆይስ ትርጉም - ዮሐንስ ገለታ
Rate this item
(5 votes)

አባ በትለር በልብ ሕመም ሲመቱ የአሁኑ ለሦስተኛ ጊዜ ነበር፤ ምንም ተስፋ አልነበራቸውም፡፡ ዘወትር ምሽት በደጃፋቸው ሳልፍ በብርሃን የተሞላውን መስኮት አጠናለሁ፤ እናም ዘወትር ምሽት በተመሳሳይ ሁኔታ እንደበራ አየዋለሁ፤ ብርሃኑ ደብዘዝ ብሏል፤ ሳይስለመለም፡፡ መቼም ሞተው ቢሆን በመጋረጃው ወደ ውስጥ የሻማ ብርሃን ይታየኝ ነበር… ስል አሰብኩ፡፡ ምክንያቱም ሰው ሲሞት ሁለት ሻማዎችን በአስከሬን ራስጌ የማስቀመጥ ልማድ እንዳለ አውቃለሁኝ፡፡ አዘውትረው እንዲህ ይሉኝ ነበር፤ “በዚህች ዓለም ላይ እምብዛም አልቆይም” እኔ ደግሞ ንግግራቸውን ዋዛ አድርጌ ቆጥሬዋለሁ፡፡ አሁን ግን እውነት መሆኑ ገባኝ፡፡ ዘወትር ምሽት ላይ በመስኮታቸው  ዐይኖቼን ተክዬ “ፓራሊሲስ” የሚለውን ቃል ከአንደበቴ ሳወጣ፣ ቃሉ ጆሮዬ ውስጥ ባይተዋር ይሆንብኝ ነበር፡፡ አሁን ግን ጎጂ እና አነዋሪ ቃል መስሎ ተሰማኝ፡፡ በፍርሃትም ሞላኝ፡፡ ግን ደግሞ የበሽታ አስከፊ ባህሪውን እመለከት ዘንድ ከጎኑ ልጠጋ ሻትሁ፡፡
የራት ሰዓት ደርሶ ከፎቅ ስወርድ ሽማግሌው ኮተር ፒፓውን እያጨሰ እሳት ዳር ተሰይሟል፡፡ አክስቴ ከገንፎው እየጨለፈችልኝ እያለ፣ ቀድሞ ጀምሮት ወደነበረ ንግግሩ እየተመለሰ በሚመስል አኳኋን እንዲህ አለ፤
“አይ፤ በእርግጠኝነት እንደዛ ነበሩ ለማለት ባልችልም… ግን የሆነ ዓይነት እንግዳ ጠባይ ነበራቸው… የሆነ ያልተለመደ ዐይነት ምስጢራዊነት፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ ከሆነ…”
ፒፓውን መማግ ጀመረ፤ አዕምሮው ውስጥ ሀሳቦቹን እያደራጀ ስለመሆኑ አልተጠራጠርኩም፡፡ አሰልቺ ቂላቂል ሽማግሌ! በተዋወቅን ሰሞን ወሬው መሳጭ ነበረ፤ ራስን ስለ መሳት--- ስለ ውሽልሽል ሰዎች እና ጉዳዮች  ብዙ ተረኮችን ነግሮኛል፡፡ ቆይቶ ግን እሱና ማለቂያ የለሽ የመናፍስት ታሪኮቹ አሰለቹኝ፡፡
“የራሴ ምክንያት አለኝ” አለ “ይመስለኛል ለየት ያሉ ከሚባሉ ገጠመኞች እንደ አንዱ ነው… በእርግጠኝነት ለመናገር ቢከብድም…”
ምክንያቱን ሳይነግረኝ ፒፓውን መምጠጡን ቀጠለ። አጎቴ ሰውየው ላይ ማፍጠጤን አይቶ እንዲህ አለኝ፤
“እኒያ የረጅም ጊዜ ባልንጀራህ ሞቱ፤ መቼም ስትሰማ ሀዘን እንደሚገባህ ግልፅ ነው”
“ማን?” አልኩኝ፡፡
“አባ ፍሊን”
“ሞቱ እንዴ?”
“ሚስተር ኮተር ነው’ኮ አሁን የሚነግረን፡፡ ከወደ እነሱ ዘንድ መምጣቱ ነው” ትኩረት ውስጥ እንደገባሁ ስላወቅሁኝ የሰማሁት ዜና እንዳላስገረመኝ ሁሉ መመገቤን ቀጠልኩኝ፡፡ አጎቴ ለሽማግሌው ያብራራ ገባ፡፡
“ከዚህ ጉብል ጋር ጓደኝነት ነበራቸው፤ ሽማግሌው ብዙ ብዙ ነገር አስተምረውታል፤ ልብ በሉ እንግዲህ፤ ትልቅ ቦታ ይደርሳል ብለው ይጠብቁትም ነበር”
“ነፍሳቸውን ይማር እንጂ ሌላማ ምን ይባላል” አለች አክስቴ፤ በመንፈሳዊ ድምጽ፡፡
ሽማግሌው ለአፍታ ያህል አየት አደረገኝ፡፡ ዶቃ መሳይ ትናንሽ ዐይኖቹ ሲመረምሩኝ ይሰማኛል፡፡ ግን ካቀረቀርኩበት ተቃንቼ ደስ አላሰኘውም፡፡ ወደ ፒፓው ተመለሰ፡፡ ቆይቶም ግብረ ገብ በጎደለው አኳኋን ምራቁን ወደ እሳት ማንደጃው ስፍራ ተፋ፡፡
“የእኔ ልጆች ግን” አለ “ከእንደዚያ ዐይነት ሰው ጋር ሰላምታ እንኳን እንዲለዋወጡ አልፈቅድም”
“ምን ማለትህ ነው ሚስተር ኮተር?” አክስቴ ጠየቀች።
“ማለቴ…” አለ ሽማግሌው “ለሕጻናት መጥፎ ነገር ነው፡፡ ሀሳቤ ምን መሰለሽ… አንድ ጉብል ወጣት ከእኩዮቹ  ጋር ይጫወት እንጂ ከእንደዚህ ዓይነቱ… ልክ አይደለሁም ጃክ?”
“የኔም አቋም እንደዛው ነው” አለ አጎቴ፡፡ “ልጅ ራሱን ችሎ መቆም መቻል አለበት፡፡ ለዚህ ደብተራ ሁሌም የምነግረው ይሄንኑ ነው፡፡ የሰውነት እንቅስቃሴ አድርግ። እኔ እንጭጭ ሳለሁ  ክረምት ከበጋ ሳልል ጧት ጧት ሻወር እወስድ ነበር፡፡ እንዲህ ቀጥ አድርጎ ያቆመኝ እሱ ነው’ኮ፡፡ ትምህርት ደግሞ እጅግ በጣም ጠቃሚና ትልቅ… እሱን አጥንት ለሚስተር ኮተር ስጭውማ” ሲል አከለ ለአክስቴ፡፡
“አይ አይ፤ ለእኔማ አይሆንም” አለ ሽማግሌው ኮተር። አክስቴ ድስቱን አምጥታ ጠረጴዛው ላይ አኖረችው። “ግን እንደው ሚስተር ኮተር ለልጆች ጥሩ አይደለም ያልከው ለምን ይሆን?” ስትል ጠየቀች፡፡
“ለልጆች ጥሩ አይደለም ያልኩትማ” አለ ኮተር “ምክንያቱም አዕምሯቸው የሰጡትን ሁሉ ይይዛል፡፡ አየሽ ልጅ ያን የመሰለ ነገር ሲያይ ምን ዓይነት ጉዳት አለው  መሰለሽ…”
ንዴቴ ገንፍሎ እንዳይወጣ በማሰብ አፌን በገንፎ ሞላሁት፡፡ አሰልቺ ሻጉራ ደደብ ሽማግሌ!
እንቅልፍ ሲወስደኝ በጣም መሽቶ ነበር፡፡ ሽማግሌው ኮተር እንደ ህፃን ስለቆጠረኝ ብናደድም ካልተቋጩ ዓረፍተ ነገሮቹ ትርጉም ለማግኘት ጭንቅላቴን አስጨነቅሁት። በጨለማው ክፍሌ ውስጥ የበሽተኛውን ግራጫ ገጽታ ለሁለተኛ ጊዜ ያየሁ መሰለኝ፡፡ በብርድ ልብሱ ተሸፋፍኜ ስለ ገና በዓል ለማሰብ ሞከርኩ፡፡ ሆኖም ግራጫው ፊት ተከተለኝ፡፡ የማይሰማ ነገር አጉተመተመ፤ አንድ ነገር መናገር እንደፈለገ ገባኝ፡፡ ነፍሴ ወደ ሆነ ዓይነት አስደሳች እና አስፈሪ ጥግ ስትሄድ ይሰማኛል፤ እንደገና ግራጫው ፊት እኔን እየጠበቀኝ አገኘሁት፡፡ በማጉረምረም ድምጽ ሊነግረኝ ሲጀምር፣ እኔ ደግሞ ለምን በማያቋርጥ ፈገግታ ታጅቦ እንደሚያናግረኝና ስለምን ከንፈሮቹ በምራቁ እንደረጠቡ ሳስብ ነበር፡፡ ቆይቶ ግን በፓራሊሲስ እንደሞተ አስታወስሁ፡፡
በማግስቱ ከቁርስ በኋላ በግሬት ብሪቴን ጎዳና ላይ የምትገኘውን ትንሽዬ ቤት ለማየት ሄድኩኝ፡፡ “መጋረጃን የመሳሰሉ ጨርቃ ጨርቅ መደብር” በሚል ግርድፍ ስም የተጠራች ደሳሳ መደብር ነች፡፡ በዋናነት ለሽያጭ የሚቀርበው የሕጻናት ቦት ጫማዎችና ጥላዎች ሲሆኑ በአዘቦት ቀናት መስኮቱ ላይ የሚንጠለጠል “ጃንጥላ እንጠግናለን” የሚል ማስታወቂያም አለ፡፡ አሁን ግን መጋረጃው ስለተነሳ ዐይን ውስጥ የሚገባ ማስታወቂያ አልነበረም፡፡ የበሩ እጀታ ላይ የአበባ ጉንጉን በጥብጣብ ታስሮ ተንጠልጥሏል፡፡ ሁለት ድሆች ሴቶችና አንድ የቴሌግራም ሠራተኛ ጉንጉኑ ላይ ባለው ካርድ የሠፈረውን ፅሑፍ እያነበቡ ነበር፡፡ እኔም ተጠግቼ አነበብኩት፡፡
ጁላይ 1፤ 1895
ሬቭረንድ ጄምስ ፍሊን (የቅ/ካትሪን ቤተክርስትያን የቀድሞ አገልጋይ)
በ 65 ዓመታቸው አረፉ፡፡
ነፍሳቸውን በገነት ያኑርላቸው
ካርዱን ማንበቤ በእርግጥም መሞታቸውን አሳመነኝ፡፡ ባይሞቱማ ኖሮ ከመደብሩ ጀርባ ባለችው ትንሿ ጨለምላማ ክፍል ውስጥ እስኪታፈኑ ድረስ በካፖርታቸው ተጀቡነው አገኛቸው ነበር፡፡ ምናልባትም አክስቴ አንድ እሽግ ሱረት ትልክላቸውና ከፍዝዝ አደንግዛቸው አስፈንጥሮ ያስነሳቸው ነበር። እጆቻቸው በጣም ስለሚንቀጠቀጡና ግማሹን ወለሉ ላይ ስለሚደፉባቸው ሱረታቸውን ወደ ሱረት ዕቃው የምገለብጥላቸው እኔ ነበርኩ፡፡ የሚንቀጠቀጥ ግዙፍ እጃቸውን አንስተው ወደ አፋቸው ሲያስጠጉ እንኳን ትናንሽ የጭስ ደመናዎች በጣቶቻቸው መካከል እየሾለኩ ኮታቸው ላይ ይንጠባጠባሉ፡፡ ልብሰ ተክህኖዎቻቸውን ያወየበው ይሄ የሱረት ብናኝ ሳይሆን አይቀርም---- ብናኙን የሚጠርጉበት ቀዩ መሐረባቸው በአገልግሎት ብዛት ጠቁሮ፣ ልብሳቸውን ሊያፀዳላቸው አይችልም ነበር፡፡
ወደ ውስጥ ዘልቄ ላያቸው ብፈልግም ደፍሬ የማንኳኳት አቅሙ አልነበረኝም፡፡ ፀሐይ እየመታኝ በጎዳና ላይ ተንከራተትኩ -  በየመደብሩ መስኮት ላይ ያሉትን የቲያትር ማስታዎቂያዎች እያነበብኩ፡፡ እኔም ሆንኩኝ ቀኑ ምንም ዓይነት የሀዘን ስሜት የማይታይብን መሆኑ ትንሽ አስገረመኝ፡፡ የሆነ ሰዓት ላይማ ጭራሽ ራሴን በሞታቸው አንዳች  ዓይነት የነፃነት ስሜት ሲሰማኝ አገኘሁትና በራሴ ተናደድሁ፡፡ ምክንያቱም አጎቴ ትናንት ማታ እንዳለው እጅግ ብዙ ነገር አስተምረውኛል፡፡ ትምህርታቸውን በሮማ በሚገኘው የአይሪሽ ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን እኔንም የላቲን ቋንቋ አስተምረውኛል፡፡ ስለ ናፖሊዮን ቦናፓርት እና ስለ ግበበ ምድር (ካታኮምብ) ብዙ ታሪኮች ነግረውኛል፤ የተለያዩ የጸሎት ስርዓቶችንም አስረድተውኛል፤ቀሳውስቱ ስለሚጠቀሙባቸው ልዩ ልዩ አልባሳትም አብራርተውልኛል፡፡ አንዳንዴ የሆነ ምሳሌ ይሰጡኝና እኔ ብሆን ኖሮ ምን አደርግ እንደነበር እየጠየቁኝ፣ ራሳቸውን ያዝናናሉ ወይ ደሞ አንድ ሀጢዓት ሞት የሚገባው ይሁን፤ ሞት የማይገባው--- ወይ ደግሞ እንዲሁ የፍፅምና መጓደል ይሁን አይሁን ለይቼ እንድናገር ያደርጉኛል፡፡ ጥያቄዎቹ ከጉዳይ የማልጥፋቸው ትናንሽ ድርጊቶቼ በቤተክርስቲያን ዕይታ እንዴት ውስብስብ እንደሆኑ ያሳዩኝ ነበር፡፡ የፀሎተ ሐሙስና የተቀበሉትን ኑዛዜ በሚስጥር የመያዝ ግዴታዎች እጀግ በጣም ከባድ ናቸው ብዬ ከማሰቤ የተነሳ፣ ቀሳውስቱ እንዲህ ያለውን ከባድ ኃላፊነት ለመውሰድ ያላቸው ፅናት ገረመኝ፡፡ የሃይማኖት አባቶች እነኚህን የመሳሰሉ ውስብስብ ጥያቄዎችን የሚያብራሩ፣ ከፖስታ ቤቱ ግዙፍ ዳይሬክቶሪ የማይተናነሱና እንደ ነጋሪት ጋዜጣ ጥቅጥቅ ብለው የታተሙ መጽሐፍትን መጻፋቸውን ሲነግሩኝ አግራሞቴ ጨመረ፡፡ አንዳንዴ በቃሌ እንድሸመድድ ያደረጉኝን ጸሎት ሙሉውን እንድልላቸው ይጠይቁኝና ስንተባበተብ፤ ዳጎስ ያለ የሱረት እፍኝ በአፍንጫቸው እየማጉ፤ ጭንቅላታቸውን በመነቅነቅ በሀዘኔታ ፈገግ ይሉ ነበር፡፡ የወየበ ጥርሳቸውን ገለጥ አድርገው ምላሳቸውን  አውጥተው ከንፈራቸው ላይ በመጣል፡፡
የሽማግሌው የኮተርን ንግግር እያሰብኩኝና በሕልሜ ያየሁትን ለማስታወስ እየሞከርኩ፣ በፀሐይ ላይ መጓዜን ቀጥያለሁ፡፡ ረጃጅም የሀር መጋረጃዎችና በተንጠለጠለበት ቆየት ያለ ፋኖስ ማየቴን አስታወስኩኝ፡፡ ራቅ ወዳለ አገር እንደሄድኩ ዐይነት ተሰማኝ፤ እንግዳ ዐይነት ባህሎች ያሉበት አገር፡፡ ፋርስ እንደሆነ ትዝ ይለኛል፤ ቀሪው የሕልሜ ክፍል ግን አልታወስ አለኝ፡፡
ማታ ላይ አክስቴ ወደ ለቅሶ ቤቱ ይዛኝ ሄደች፡፡ ፀሐይ ብትጠልቅም ወደ ምዕራብ የዞሩት የመስኮቱ መስታወቶች ወርቃማ ቀለም ያላቸውን የደመናዎች ክምር እያንፀባረቁ ያሳያሉ፡፡ እልፍኙ ውስጥ ናኒ ተቀበሉን፤ መጯጯህ ተገቢ እንዳልሆነ ያወቀችው አክስቴ፤ ስለ ሁሉም ነገር የናኒን እጅ ጨበጠች፡፡
አሮጊቷ ወደ ሰማይ በጥያቄ ዓይነት ሲጠቋቁሙ ቆዩና  በጠባቧ ደረጃ ላይ እያቃሰቱ ሽቅብ ይመሩን ጀመር፤ በሰውነታቸው ጉብጠት ጭንቅላታቸው ከመወጣጫው እጀታ ትይዩ ነው፡፡ ፎቁ ላይ እንደደረስን አሮጊቷ ቆም ብለው በሩ ክፍት ሆኖ ወደሚታየው ክፍል እያሳዩን እንድንገባ ጋበዙን፡፡ አክስቴ ከገባች በኋላ ለመግባት ሳወላውል ያዩት አሮጊቷ፤ እኔም እንድገባ ደጋግመው በእጃቸው ምልክት ሰጡኝ፡፡
በጥፍሮቼ እየተራመድኩ ገባሁ፡፡ በመጋረጃው አንደኛው ጠርዝ የተንሰራፋው ደብዛዛ ወርቃማ ብርሃን የተለኮሱትን ሻማዎች ደቃቃ ነበልባል አስመስሏቸዋል፡፡ አስከሬኑ ሳጥን ውስጥ ነው፡፡ በናኒ መሪነት ሦስታችንም አልጋው አጠገብ ተንበረከክን፡፡ ፀሎት ለማድረግ ብሞክርም የአሮጊቷ ማነብነብ ሀሳቤን በታተነው፡፡ ቀሚሳቸው ወገባቸው ላይ በስርዓት አለመቀመጡንና የቦት ጫማቸው መርገጫ በአንድ በኩል እንደተንሻፈፈ አየሁኝ፡፡ በሳጥኑ ውስጥ የተጋደሙት ሟቹ ሽማግሌ ቄስ ፈገግ ያሉ ይመስሉ ነበር፡፡
ከእንብርክካችን ተነስተን ወደ አልጋው ራስጌ ስንሄድ ፈገግ አለማለታቸውን አረጋገጥኩ፡፡ በፀጥታ ከነግዙፍነታቸው ለባብሰው ጋደም ብለዋል፤ በእጆቻቸው ደግሞ ፅዋ ጨብጠዋል፡፡ ፊታቸው ግዙፍ፣ ግራጫና ቁጡ ነው፤ በፀጉር ተከብበው እንደ ዋሻ የጨለሙ የአፍንጫ ቀዳዳዎች፡፡ ቤቱ ውስጥ ከበድ ያለ የአበባ መዓዛ ነበር፡፡
አማተብንና ከአልጋው ገለል አልን፡፡ ከፎቅ እንደወረድን ትንሿ ክፍል ውስጥ ኤልሳ የቄሱ ወንበር ላይ ቁጭ ብላ አገኘናት፡፡ የአዘቦት ቦታዬን በዐይኖቼ እየፈለግሁ እያለ፣ ናኒ ወደ መደርደሪው ሄደው ደምበጃን ሙሉ የወይን ጠጅ ብርዝ እና የወይን ብርጭቆዎች ይዘው መጡ፡፡ ብርጭቆዎቹን እየሞሉ አደሉንም፡፡ ከኮቾሮውም እንድይዝ ቢጋብዙኝም ስኮረሽም በማሰማው ድምፅ እንዳልረብሽ በመስጋት አልፈልግም አልኩኝ፡፡ በእምቢታዬ እንደመናደድ አሉና--- በፀጥታ ወደ ሶፋው ሄደው እህታቸው ጎን ተቀመጡ፡፡  ማናችንም እያወራን አልነበረም፤ሁላችንም ባዶው የእሳት መሞቂያው ላይ ዐይኖቻችንን ተክለናል፡፡
ኤልሳ በእፎይታ ስትተነፍስ አክስቴ  እንዲህ አለች፤
“ያው መቼስ፤ ወደተሻለ ሥፍራ ነው የሄዱት”
ኤልሳ በመስማማት ራሷን ነቀነቀች፡፡ አክስቴ የወይን ብርጭቆዋን በጣቷ እየነካካች፤
“በሰላም ነበር ነፍሳቸው…?”
“አዎን! በሰላም ነበር፤ የኔ እመቤት” አለች ኤልሳ፡፡
“ትንፋሹ ቁርጥ ስትል ማንም አላወቀም ነበር፡፡ አሟሟቱን አሳመረለት፤ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን”
“መናዘዙም ምኑም…?”
“አባ ኦሩርክ አብረውት ስለነበሩ እሳቸው ናቸው ሁሉንም እንደሚሆን --- እንደሚሆን ያደረጉት”
“ያውቁ ነበር ያኔ?”
“ያው አይቀሬ እንደሆነ አምኖ ተቀብሎ ትነበር”
“እውነት ነው፤ አሁን እንኳ ፊታቸው ሲታይ አምነው እንደተቀበሉ ያስታውቃል”
“አስከሬን አጣቢዋም እንደዚያ ነው ያለችው። እንቅልፍ የያዛቸው ነው የሚመስሉት ስትል ነበር፡፡ አስከሬኑ እንዲህ ያምራል ብሎ ማንም አልገመተም ነበር”
“እውነትሽን ነው” አለች አክስቴ፡፡
አሁንም ከብርጭቆዋ ጎንጨት አደረገችና፤
“መቼም ወይዘሮ ፍሊን፣ እርስዎ የሚችሉትን ሁሉ ያደረጉላቸው ስለሆነ ምንም የሚያስጨንቅዎት ነገር የለም፡፡ እኔ መቼም ሁለታችሁም አቅም በፈቀደ የሚደረገውን አድርጋችኋል ባይ ነኝ”
ኤልሳ ቀሚሷን እያስተካከለች “ምስኪን ጄምስ!” አለች “እኛ እንግዲህ እግዜር በሚያውቀው፤ ምንም ድህነታችን ቢይዘንም የፈለገውን ሁሉ ለማቅረብ ስንሞክር ነበር”
ናኒ የሶፋውን ትራስ ደገፍ ብለው እንቅልፍ ሊጥላቸው ያሉ መሰሉ፡፡
“እስቲ እያት ይህቺን ምስኪን ናኒ” አለች ኤልሳ “በጣም ደከመች፡፡ እሷና እኔ የለፋነው ልፋት’ኮ… ከአስከሬን አጣቢዋ ጋር ሆነን ሬሳውን ወዲያ ወዲህ ስናደርግ፤ ከዚያ ደግሞ ሳጥን ውስጥ ስንከት፣ ከዚያ የጸሎት ስነ ስርዓቱን ስናሰናዳ፡፡ አባ ኦሩርክ ባይኖሩማ የሚሳካም አልነበረ፡፡ አበቦቹንም ሻማዎቹንም ያመጡት እሳቸው ናቸው፤ የቀብር ስርዓቱንም ተጻጽፈው ያሰናዱት ኢንሹራንሱንም ፈር ያስያዙት እሳቸው ናቸው፡፡”
“እንዴት የተባረኩ ሰው ናቸው!” አለች አክስቴ፡፡
“እንደነሱ ያለ ጓደኝነት ታይቶም አይታወቅምኮ”፡፡
 “እውነት ብለሻል” አለች አክስቴ “ደሞ እርግጠኛ ነኝ በሰማይ ቤትም እንናተንም ሆነ ያደረጋችሁትን አይረሱትም”፡፡
“እንደው እሱ ያሳዝናል እንጂ…” አለች ኤልሳ “እኛንማ ምን አስቸግሮን… ከዚህ በኋላእኮ ድምጹን መስማት አንችልም፡፡ መሞቱን አውቄ እንኳ…”
“ሁሉ ነገር ሲፈጻጸም እኮ ነው የሚናፍቁሽ” አለች አክስቴ፡፡
“አውቃለሁ…” አለች ኤልሳ “በቃ ከእንግዲህማ እኔም ሻይ አላፈላለት፤ አንቺም ሱረቱን አትልኪለት… ምስኪን ጄምስ!”
ስላለፈው ጊዜ በተመስጦ ስታስብ ለአፍታ ቆም አለችና እንዲህ ተናገረች፤
“የሚገርምሽ ነገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሆነ ነገር እንደሆነ እየተሰማኝ ነበር፡፡ ሾርባውን ይዤለት በመጣሁ ቁጥር አፉ ተከፍቶ ወለሉ ላይ ከነወንበሩ ወድቆ ተዘርሮ አገኘው ነበር”፡፡
ጣቷን አፍንጫዋ ላይ አድርጋና ፊቷን ከስክሳ መናገር ቀጠለች፤
“እንደዚያም ሆኖ ግን አንድ ቀን በጋው ከማለቁ በፊት አይሪሽ ታውን--- እኛ ሁላችንም የተወለድንበት የድሮው ቤት--- እኔና ናኒን ይዞ ለመሄድ ያስብ ነበር፡፡ አባ ኦሩርክ የነገሩትን እነዚያን ድምጽ አልባ ጋሪዎች ብናገኝ ኖሮ፤ ለአንዲት ቀን ብቻ ይል ነበር፤ ሦስታችን ሆነን በአንዲት እሁድ ምሽት እንሄድ ነበር፡፡ በቃ ይቺኑ ሲያስብ ስንት ጊዜ አለፈ መሰለሽ… ሲያሳዝን!”
“እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ይማር” አለች አክስቴ፡፡
ኤልሳ መሀረቧን አውጥታ እንባዋን ጠራረገች፡፡ ከዚያም መሀረቡን ወደ ኪሷ መለሰችና በፀጥታ ባዶው የእሳት ማንደጃ ላይ ዐይኖችዋን ተከለች፡፡
“ስህትት ላለመሥራት ነበር የሚኖረው” አለች ኤልሳ “የቅስና ግዴታዎቹ እጅግ በዝተውበት ነበር፡፡ ሕይወቱ ደግሞ፤ ምን ልበልሽ፤ የብስጭት ነበር”
“አዎን” አለች አክስቴ “ብስጩ ሰው ነበሩ፤ ይህን ማንም ያውቅ ነበር”
ትንሿን ክፍል ዝምታ ነገሰባት፤ ይሄን ተገን አድርጌም ወደ ጠረጴዛው በመጠጋት የወይን ብርዜን ቀመስ አደረግሁኝ፤ ከዚያ በፀጥታ ጥግ ላይ ወዳለችው መቀመጫዬ ተመለስኩኝ፡፡ ኤልሳ በጥልቅ ትውስታ ውስጥ ተውጣለች፡፡ ፀጥታውን ሰብራ ንግግር እስክታደርግ በአክብሮት ጠበቅናት፤ ከዚያም ከረዥም ቆይታ በኋላ በዝግታ መናገር ጀመረች፡
“ያቺን ፅዋ ሲሰብር ነው ሁሉ ነገር የጀመረው፡፡ በእርግጥ ምንም ማለት እንዳልሆነ ነበር የነገሩን፤ ማለቴ፤ ፅዋው ውስጥ ምንም አልነበረም፡፡ ቢሆንም የእሱ ጥፋት ነበር፡፡ ምፅ! እንዴት እንደደነገጠ’ኮ… እስቲ እግዜር ይማረው!”
“በቃ ይሄው ነበር?” አለች አክስቴ “እኔ’ኮ የሰማሁት…”
ኤልሳ ጭንቅላቷን አወዛወዘች፡፡
“እሱ ነው ጭንቅላቱን የነካው” አለች “ከዚያ በኋላ በቃ በብቸኝነት መተከዝ አበዛ፤ ከሰው ጋር ማውራት ተወ፤ ብቻውን መዞርም ጀመረ፡፡ አንድ ምሽት ተፈልጎ ቢጠራ ከየት ይምጣ… ያልገቡበት የለም ግን እሱን አየሁ የሚል ጠፋ፡፡ ከዚያም የሆነ ሰው ደጀሰላም ሄደው እንዲፈልጉት ነገራቸው፡፡ አባ ኦሩርክና አንድ ሌላ ቄስ ጧፍ እያበሩ በሩን ከፍተው ሲገቡ--- ጨለማ ውስጥ ቁጭ ብሎ አገኙት፤ በኑዛዜ መቀበያ ሳጥኑ ውስጥ ብቻውን ሲስቅ ነበር፡፡”
አንዳች ዓይነት ድምፅ እንደሰማች ሁሉ በድንገት ፀጥ አለች፡፡ እኔም ለማዳመጥ ሞከርኩኝ፤ ግን ቤቱ ውስጥ ምንም ዓይነት ድምፅ አልነበረም፡፡ ሽማግሌው ቄስም ቅድም እንዳየናቸው ሳጥኑ ውስጥ ያለ ምንም እንቅስቃሴ እንዳረፉ አውቃለሁ፤ ኮስተር ቆጣ ብለው፤ ደረታቸው ላይ ደግሞ ጽዋው፡፡
ኤልሳ ቀጠለች፡
 “ንቅት ብሎና ብቻውን እየሳቀ… ያው ከዚያማ… እነሱም ይሄን ሲያዩ የሆነ ነገር እንዳጋጠመው ገባቸው…”


Read 3849 times