Saturday, 19 April 2014 12:12

በዓለም ገበያ ለመወዳደር የጥራት ፅንሰ ሐሳብ ማጎልበት አለብን

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ጥራት የሚለካው በደንበኛ እርካታ ነው
ዶ/ር ኢ/ር ዳንኤል ቅጣው በ1972 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሜካኒካል ኢንጅነሪንግ በከፍተኛ ማዕረግ ተመረቁ።
በተማሩበት ዩኒቨርሲቲ በረዳት መምህርነትና በመምህርነት ለሁለት ዓመት ከሠሩ በኋላ፣ ለሁለተኛ ዲግሪያቸው ጣሊያን ሄዱ። በጣሊያን ፖሊቴክኒኮ ዲ ቶሪኖ እና ፖሊቲክኒኮ ዲ ሚላኖ የሚባሉ ሁለት ከፍተኛ ዩኑቨርሲቲዎች አሉ። ዶ/ር ኢ/ር ዳንኤል በፖሊቴክኒኮ ዲ ቶሪኖ ትምህርታቸውን ተከታትለው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ተመርቀው በ1977 ዓ.ም ወደ አገራቸው ተመልሰው በአ.አ.ዩ ሜካኒካል ኢንጅነሪንግ ሲያስተምሩ ቆዩ።
በ1988 ዓ.ም ለሦስተኛ ዲግሪያቸው ተመልሰው ወደ ጣሊያን ሄዱ። እዚያም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በተማሩበት በፖሊቴክኒኮ ዲ ቶሪኖ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሩ ትምህርታቸውን ተከታትለው በ1992 ዓ.ም በኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ በዶክትሬት ዲግሪ ተመረቁ፡ ከዚያ እንደተመለሱ እስካሁን ድረስ በአ.አ.ዩ በስኩል ኦር ሜካኒካል አንድ ኢንዱስትሩ የትምህርት ክፍል በተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ በመምህርነት እየሰሩ ነው። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መንግሥቱ አበበ ከዶ/ር ኢ/ር ዳንኤል ቅጣው ጋር በጥራትና በምርታማነት ዙሪያ ያደረገውን ቃለ ምልልስ እነሆ!

ጥራት ወይም ኳሊቲ ምንድነው?
ይህ ጥያቄ በጣም አጭር ነገር ግን በጣም በጣም ሰፊ ምላሽ ያለው ሐሳብ ነው። ጥራት ወይም ኳሊቲ የምንለው ሐሳብ፣ እንደቃል ሳይሆን እንደፍልስፍና የሚታይ ነው። የአዕምሮ መለወጥን የሚጠይቅ፣ ደንበኛን ከደንበኛ የሚያያይዝ፣ ከደንበኛ ፍላጐት ጋር የተገናኘ ነው። የጥራት ትርጉም አሰጣጥ፣ በብዙዎች ዘንድ ስህተት ፈጥሯል። አንዳንድ ጊዜ የሚያብለጨልጭ፣ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ወይም ለየት ያለ ነገር፣ …”ኳሊቲ ነው” ሲባል እንሰማለን። ኳሊቲ ክራቫት አስሯል፤ ኳሊቲ ልብስ ለብሷል፣ ኳሊቲ ጫማ አድርጓል… ይባላል። እነዚህ ነገሮች፣ ኳሊቲ የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ውስጥ ሊኖሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን የኳሊቲ ፅንሰ ሐሳብ ይህ ብቻ አይደለም።
ጥራት ወይም ኳሊቲ በአጭሩ፣ ደንበኛው የሚፈልገውን አገልግሎትም ሆነ ዕቃ ልክ ደንበኛው እንደሚፈልገው ወይም ከሚፈልገው በተሻለ ሁኔታ፣ ደንበኛው በሚፈልገው ጊዜ፣ በሚፈልገው ብዛት፣ ሊገዛ በሚችለው አቅም ማቅረብ ማለት ነው። ለምሳሌ፣ አንድ ሰው “ከአንድ ግመልና ከአንድ ቮልቮ ከባድ መኪና የቱ ነው ጥራት ያለው?” ተብሎ ቢጠየቅ፣ ለጥራት ባለው ግንዛቤ መሠረት “ቮልቮ ነው” ሊል ይችላል። ግን እንደዚያ አይደለም። በረሃ ውስጥ ከሆነ ቮልቮ ሊሄድ አይችልም፤ ስለዚህ እንደተጠቃሚው ወይም እንደደንበኛው ፍላጐት በረሃ ውስጥ ከሆነ ግመል ጥሩና የተሻለ ስለሚሆን ጥራት አለው ማለት ነው። አውራ ጐዳና ላይ ከሆነ ግን ግመል አይደለም የሚያስፈልገው። ጥራት ያለው ቮልቮ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ጥራት፤ የተጠቃሚውን (የደንበኛውን) ፍላጐት፣ ቦታ፣ አቅም፣ አካባቢ… ያገናዘበ ነው ማለት ነው።
ጥራት ማለት ከደንበኛ ጋር የተያያዘ ነው ብለውናል። ስለዚህ ባገራችን የጥራት ትርጉም በኀብረተሰቡ ውስጥ እንዲሰርፅ ልጆቻችንን፣ ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ ደንበኛ ማክበርን ልናስተምራቸው ይገባል። ስለጥራት ከተነሳ፣ የደንበኛ መኖር የግድ ነው። አገልግሎትና ቁስ መቀባበል ብቻ፣ ዕቃ መሸጥና ያለመሸጥ፣ በፋብሪካ ውስጥ ጥሩ ዕቃ ማምረት ወይም ያለማምረት ብቻ አይደለም። እርስ በርስ ስንገናኝ ጀምሮ አንዱ የሌላው ደንበኛ ነው። ሕፃናት ዕቃ ሲነጣጠቁ… ዕቃ የሌለው ልጅ፣ ዕቃ ያለው ልጅ ደንበኛ ነው። “እባክህን፣ ይህን ዕቃህን ልጠቀምበት?” ብሎ እንዲጠይቅ ብናስተምረው ወይም ይህን ፍልስፍና እውስጡ ብናሰርፅ ማክበር እየለመደ ያድጋል። ያደጉ አገሮች ከሚታወቁባቸው ዋና ዋና ነገሮች አንዱ ደንበኛን ማክበር ነው።
በአሜሪካ አንድ ሰው ዕቃ ገዝቶ፣ እቤቱ ከደረሰ በኋላ ዕቃው ባይስማማው፣ ወደገዛበት ሱቅ ተመልሶ “አልፈልገውም፣ መልሼዋለሁ” በማለት ገንዘቡን መቀበል ወይም ሌላ የሚፈልገውን ዕቃ ለውጦ መውሰድ ይችላል። ይኼ አሰራር የመጣው ደንበኛውን ከማክበር ነው። የሠራተኞቹን ደሞዝ የሚከፍለውና ለዚያ ድርጅት መኖር ምክንያቱ ደንበኛው ነው።
ወደ አውሮፓ ስንሄድም ደንበኛ ይከበራል፤ የተሸጠ ዕቃ ይመለሳል። ከአሜሪካኖቹ የተለየ አውሮፓውያኑ ያወጡት ሕግ አለ። “ዕቃውን የገዛህበትን ቲኬት መያዝ አለብህ፤ ዓርማው ወይም ታጉ መኖር አለበት” የሚል ነው። ይሄ ስለኳሊቲ ያላቸው ግንዛቤ ከአሜካውያኑ ያነሰ መሆኑን ያሳያል። ወደ እኛ አገር ስንመጣ ደግሞ፣ ጥሩ ባለሱቅ ከሆነ በትላልቅ ፊደሎች “የተሸጠ ዕቃ አይመለስም” የሚል ጽፎ ፊት ለፊት ይለጥፋል። ይኼ ደንበኛን ካለማክበር የሚመነጭ ነው። ጥራት የተመሠረተበትን ያለማወቅና ያለመረዳት የሚያመጣው ችግር ነው። ስለጥራት፣ ስለደንበኛ አያያዝ ማን አስተማረን? ማንም! ብዙ ጊዜ “ደንበኛ ንጉሥ ነው” እየተባለ ሲነገር እንሰማለን። በየሱቁና በየድርጅቱም ተለጥፎ እናያለን። ግን ደንበኛ አይከበርም። ይህ የሚያሳየው፣ ከቃሉ እንጂ ከጽንሰ ሐሳቡ ጋር እንደማንተዋወቅ ነው። ስለዚህ የአመለካከታችን አወቃቀር መለወጥ አለበት፣ የአስተሳሰብና የአመለካከታችንን ውቅር መለወጥ (የፓራዳይም ሺፍት) ያስፈልገናል።
መንገድ ላይ በመኪና ስሄድ በጣም አዝናለሁ። ብዙ ጊዜ መኪኖች እርስበርስ ተዘጋግተው ይቆማሉ። መዘጋጋቱ የሚፈጠረው መንገዶቹ በመጥበባቸው ወይም ተሽከርካሪዎቹ በመብዛታቸው ብቻ አይደለም። እርስበርስ ስለማንከባበር ነው። የመኪና መንገድ ስንጠቀም፣ አንዳችን የሌላችን ደንበኛ ነን። እኔ ከቀኜ ለሚመጣ መኪና ቅድሚያ የመስጠት ኃላፊነትና ግዴታ አለብኝ። ከጐኔ ያለው አሽከርካሪ ደንበኛዬ ነው፤ እኔ ደግሞ የእሱ ደንበኛ ነኝ። ብንከባበር፣ እሱም ይሄዳል፣ እኔም እሄዳለሁ። ጥቁርና ነጭ በተቀባ የእግረኛ ማቋረጫ (ዜብራ) ላይ የእግረኛ መብት አናከብርም። ባለመኪና አይደለን፣ ጉልበተኞች ነን። እንዲያ መሆን የጥራት ፍልስፍናን ግንዛቤያችን ዝቅተኛ ነው ማለት ነው። ዜብራ ላይ ስደርስ መኪናዬን አቁሜ ለእግረኞች  “እለፉ” የሚል ምልክት ስሰጣቸው በጣም ያመሰግኑኛል። የሚፈልጉትን ነገር ስላደረግሁላቸው ደስ ብሏቸው ነው። አላወቁትም እንጂ መብታቸው እኮ ነው። አብዛኞቻችን ግን ጥራትን ከምርት ጋር ብቻ ነው የምናያይዘው…
ጥራት ስንል፣ በፍፁም ከሸቀጥ (ኮሞዲቲ) ጋር ብቻ የተያያዘ  አይደለም። ለምሳሌ አንድ ሐኪም፣ ታካሚ ደንበኞች አሉት። እነሱ በመኖራቸው ነው ሐኪሙ የሚሰራው። ስለዚህ ደንበኞቹን (ታካሚዎቹን) ተንከባክቦ መያዝ አለበት። እዚህ ላይ አንባቢ እንዲረዳኝ የምፈልገው፣ የሐኪሞችን የሥራ መደራረብና ጫና እንዲሁም የቁጥራቸውን ማነስ፣ ግምት ውስጥ ሳላስገባ አይደለም። ግን መሆን የነበረበትን ነው የምናገረው። ችግሬ ምን እንደሆነ ጠይቆ ሳይረዳና ሳይመረምረኝ፣ ገና በሩን እንደገባሁ፣ አቀርቅሮ ወረቀት እየጻፈ፣ “ምንህን ነው ያመመህ?” በማለት ይጠይቀኛል እንጂ እንደሰውና እንደንበኛው አያየኝም፤ አያስተናግደኝም። ይኼ የጥራት ፍልስፍና ማነስ ስለሆነ ሐኪሞች አዕምሮአቸውን (አመለካከታቸውን) መለወጥ አለባቸው። በሌላውም ዘርፍ እንዲሁ ነው።
እኛ አስተማሪዎች፤ ተማሪዎቻችንን እንዴት ነው የምናየው? ተማሪ ባይኖር እኔ‘ኮ ሥራ የለኝም። ምርምር መሥራት እችላለሁ። ነገር ግን የማስተርስና የዶክትሬት ተማሪዎች ከሌሉ እንዴት ምርምር መሥራት እችላለሁ? አልችልም። ተማሪዎቼ የእኔ ኃላፊዎችና ደንበኞች ስለሆኑ ላከብራቸው ይገባል። ይህ ማለት ግን የማይገባቸውን ውጤት መስጠት፣ በማይሆን ሁኔታ ማባባል፣ ትከሻ ላይ አውጥቶ መሸከም ማለት አይደለም። እንደሰው፣ እንደደንበኛ መታየትና መከበር ይገባቸዋል ማለቴ ነው። ይኼ ነው ጥራት ማለት። ጥራት ከደንበኛ ከተለየ ትርጉም የለምውም ማለት ነው፤ ደንበኛ ሳይኖር ስለ ጥራት ማውራት አንችልም።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እኮ የሚሠራው(የሚኖረው) እኔና ሌሎች ተሳፋሪዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ስንሆንለት ነው። ስለዚህ፣ ተሳፋሪውን በሚገባ መንከባከብና ማስተናገድ አለበት። ሲዘገይ፣ “ይቅርታ ዘግይተናል፤ ለዚህ ጥፋታችንም ማካካሻ እናደርጋለን” በማለት የደንበኞቹን ቅሬታ ማስወገድ አለበት። አስተማሪም ሲያረፍድ፤ “ይቅርታ እንዲህ ዓይነት ችግር አጋጥሞኝ ነው” ብሎ ትክክለኛውን ምክንያት በመንገር፣ ተማሪዎቹን ይቅርታ መጠየቅ አለበት። ምክንያቱም አስተማሪውንና ተማሪውን የሚያገናኘው ኮርሱ ወይም ትምህርቱ ነው። ለምሳሌ ነገ ለተማሪዎቼ የጥራት ኮርስ አስተምራለሁ። ኮርሱ፣ ለእኔ ምርቴ ነው። እሱን ነው የምሸጥላቸው። ኮርሱን ካልገዙኝ ወይም “ዳንኤል የተባለው አስተማሪ ሁለተኛ ክፍላችን እንዳይገባ” ብለው ከከለከሉኝ፣ ሥራዬን አጣለሁ ማለት ነው። ስለዚህ ደስ ብሏቸው ኮርሱን እንዲገዙኝ መትጋት አለብኝ። ነገር ግን ዲግሪውን ስለሚፈልጉት በማስፈራራት ወይም “ምን ታመጣላችሁ!” በሚል ስሜት ኮርሱን መስጠት የለብኝም። እንዲህ ያለው አሠራር ከጥራት ፍልስፍና ውጭ ነው።
ለመሆኑ ጥራት በምን ይለካል?
ጥራት በደንበኛው እርካታ ነው የሚለካው። የመንገድ ጥራት፣ የልብስ ጥራት ወይም የምርትና የአገልግሎት ጥራት ስንል ደንበኛው ባዘዘውና በጠየቀው መመሪያ ነው ወይ የተሠራለት? ብለን መፈተሽ እንችላለን። ለምሳሌ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ መንገድ የሚሠሩለትን ኮንትራክተሮች ጋብዞ ያወዳድራል። ደንበኛው የመንገዶች ባለሥልጣን ነው። እኛ ደግሞ ከእኛ በተሰበሰበ ታክስ መንገዱ ስለሚሠራና ተጠቃሚዎች ስለሆንን ተጨማሪ ደንበኞች ነን። ባለሥልጣን መ/ቤቱ እንዲሠራለት የሚፈልገውን ዓይነት መንገድ ዝርዝር መመሪያ (ስፔሲፊኬሽን) ያቀርባል። የሚሠራው መንገድ ሳይበላሽ ለ10 ዓመት የሚያገለግል፣ ወጣ ገባ የሌለው፤ 8፣ 12፣ 14፣ …ሜትር ስፋት ያለው፣ በሁለቱም ጐን ውሃ ወደ ውጭ የሚያፈስ የመንገድ ትከሻ ያለው፣ መንገዱ ተሠርቶ ሲያልቅ፣ ቁልቁለት ወይም መጠምዘዣ መኖሩን የሚጠቁም ምልክት ያለው፣ የጥገናው ወጪ አነስተኛ የሆነ… ብሎ ፍላጐቱን በመግለጽ አወዳድሮ ኮንትራቱን ለአሸናፊው ድርጅት ይሰጣል።
እንግዲህ ጥራት የምንለው ደንበኛው በፈለገው ዝርዝር መመሪያ መሠረት መሠራቱን ነው። አንዳንድ ጊዜ ደንበኛው ፍላጐቱን በትክክል ያስቀምጣል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ያሰበውንና የፈለገውን ነገር በትክክል ላይገልጽ ይችላል። ስለዚህ ጥራት ማለት የተገለፀውንና ያልተገለፀውን የደንበኛውን ፍላጐት ጭምር ማርካት ማለት ነው። በዚህ ነው ጥራት የሚለካው።
የጥራት መለኪያና መመዘኛ የሚባሉ አውታሮች (ዳይመንሽኖች) አሉ። ለምሳሌ፣ ይኼ ከዚህኛው ይበልጣል ወይም ይሻላል ለማለት ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን ነገሮች ነው የምናወዳድረው። ፈረስን ከፈረስ እንጂ ከበግ ጋር አናወዳድርም። እንዲህ በምናደርግበት ጊዜ ሲስተሙን ኳሊቲ ዳይመንሽን እንለዋለን። አንደኛው የጥራት መለኪያ ፋንኪሽናሊቲ፣ የምንፈልገውን ነገር ይሠራል ወይ የሚለው ነው። ሁለተኛው ፐርፎርማንስ፣ የመሥራት አቅምና ብቃቱ ነው። ለምሳሌ አንድ የልብስ ስፌት መኪና 8 ሰዓት ይሠራል ከተባለ፣ በተከታታይ ለ8 ሰዓት ያለ አንዳች እክል ይሠራል ወይ? ማለት ነው።
ሌላው ሪያሊቢሊቲ (አስተማማኝነት) ነው። ጥገና አስፈላጊ ነገር ቢሆንም፣ በአዲስነቱ ምን ያህል ጊዜ ሳይበላሽ በአስተማማኝነት ይሠራል? ወይም በመጀመሪያውና በሁለተኛው ጥገና መካከል ባለው ጊዜ በአስተማማኝነት ይሠራል? የሚለው ነው። ሌላው የጥራት መመዘኛ ደግሞ ኮንፎርሚቲ የምንለው ነው። ሌላው ደግሞ ዱረቢሊቲ ነው። ዱረቢሊቲ ስንል ጥንካሬውን ማለታችን ነው። ለረዥም ጊዜ ምንም ሳይሆን ይሠራል? ሰርቪስ ላደርገው ወይም ቢበላሽ ላሠራው እችላለሁ? የሚለው ነው።
ማማርም አንዱ የጥራት መለኪያ ነው። አንዱ፣ ይህን ነገር እወደዋለሁ ይላል። ለምን ወይም በምን ወደድከው? ሲባል ምክንያት የለውም። “በቃ እወደዋለሁ” ነው መልሱ። ሌላው ደግሞ ብዙዎቹን የጥራት መመዘኛዎች ቢያሟላም “ይህን ነገር አልወደውም” ሊል ይችላል። የሚጠላበትን ምክንያት ግን አያውቀውም። እንግዲህ በእነዚህ መመዘኛዎች ለክተን ነው አንድን ነገር ከፍተኛ ጥራት ያለው ወይም ጥራቱ ዝቅተኛ ነው ማለት የምንችለው። ጥራት ምንድነው? ስትለኝ ጥያቄው ቀላል መልሱ ግን ሰፊ ነው ያልኩህ ለዚህ ነው። እኛ ስለጥራት (ኳሊቲ) ሁለት ኮርስ ነው የምንሰጠው። በ15 እና 20 ደቂቃ ስለጥራት አውርተን አንጨርስም። ታዋቂው የዓለማችን ሳይንቲስት አልበርት አነስታይን፤ “አንድን ነገር በቀላሉ ለመንገደኛ ሰው ማስረዳት ካልቻልክ ሥራህን አታውቀውም ማለት ነው” እንዳለው እንዳይሆንብኝ እፈራለሁ።
ህብረተሰቡ ስለጥራት ያለው ግንዛቤ ምን ይመስላል?
ኅብረተሰብ የሚለዋወጥ (ዳይናሚክ) ስለሆነ ብዙ ጊዜ ይቀያየራል። ከባላገር ልነሳ፤ የጥራት ፅንሰ ሐሳብ (ኮንሰፕት) አላቸው ወይ? አዎ! በሚገባ አላቸው። ቤታቸው ንፁህ ነው፤ የተቀደደ ልብስ በመርፌ ጥርቅም አድርገው ሰፍተው ነው የሚለብሱት፤ ቤታቸውን አዛባ ለቅልቀው ነው የሚኖሩት። መደብ አለች፣ ጓሳ ትነሰነሳለች፤ በሳምንቱ ተጠርጐ ይስተካከላል፤ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋሉ። ጥራት (ኳሊቲ) ፎቅ ቤት ውስጥ መኖር ማለት አይደለም። ከብቶቻቸውን ጧት በጊዜ ያስወጣሉ፤ ማታ በጊዜ ያስገባሉ። እሳታቸውን በጊዜ ያዳፍናሉ፤ ጧት ደግሞ በጊዜ ተነስተው ያነዳሉ። እነዚህን ባለሙያ እንላቸዋለን። በባላገር ሚስት ስትመርጥ፣ በጧት ጭስ ከሚጨስበት ቤት ምረጥ ነው የምትባለው። እናቲቱ ባለሙያ ከሆነች ልጅቱም ባለሙያ ትሆናለች ነው ሃሳቡ። ባላገር ውስጥ የጥራት ፅንሰ ሐሳብና አመለካከት (ኮንሰፕት) አለ። ይህ አመለካከት ግን ማደግ አለበት።
ከተማ ውስጥስ እንዴት ነው? ከተማ ውስጥ የጥራት ፅንሰ ሐሳብ በጣም ትንሽ ነው። ሁሉም ሰው የጥራት ፅንሰ ሐሳቡን መንግሥት ላይ ጥሎታል። ደጁ ላይ ቆሻሻ እያየ መንግሥት ይጥረገው ብሎ ያልፋል። አጠገቡ ያለ ቦይ ተደፍኖ እያየ “የመንግሥት ሠራተኞች ይጥረጉት” ብሎ ይሄዳል። ከቤቱ ጠርጐ ያወጣውን ቆሻሻ ፊት ለፊቱ ባለ ቦይ ውስጥ ይጥላል፤ ውሃ የጠጣበትን መያዣ የትም ይወረውራል። ኧረ ብዙ ጉድለት ይታያል። መሠራት ያለበት ነገር አልተሠራም።
ጥራት የሚቆምባቸው ሁለት ምሰሶዎች አሉ። አንደኛው መሠረታዊ ሐሳብ “Keep and try the first time and every time”  ይላል። አንድን ሥራ ከመጀመሪያ አንስቶ በትክክል መሥራት የሚል ነው መሠረተ ሐሳቡ። ለስህተት ምንም ዕድል ያለመስጠት። “ቆይ በኋላ አስተካክላለሁ” ማለት በፍፁም አይገባም። ሁለተኛው የጥራት መሠረተ ሐሳብ፣ “There is always a way for improvement” የሚል ነው። ለመሻሻል ሁልጊዜ ዕድል አለ ማለት ነው። ዛሬ ከምሠራው ሥራ፣ ነገ የምሠራው የተሻለ መሆን አለበት። እነዚህ መሠረታዊ ሐሳቦች ሲጣመሩ፣ አንደኛ ጠንቃቆች እንሆናለን፤ ጊዜም ሳናባክን እንሠራለን።
ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በታሪኩ የቴክኒክ ችግር ገጥሞት አያውቅም፤ የምንኮራበት አየር መንገድ ነው። ነገር ግን ብዙ ጊዜ በመዘግየት ይታማል። መዘግየት አለ ማለት ነው። ለምንድነው የሚዘገየው? ብለን ስንጠይቅ They do it the second time ማለት ነው። በመጀመሪያው ጊዜ በትክክል ሠርተውት ቢሆን ኖሮ መዘግየት አይፈጠርም ነበር። መጀመሪያ ቴክኒሻኑ ይሠራል፣ ከዚያም ተቆጣጣሪው ይመጣና “ይኼ ትክክል አይደለም” ይላል። ቴክኒሻኑ “ኦ ለካስ ይህቺ አልተስተካከለችም” ይልና ያስተካክላል። ስለዚህ በመጀመሪያውና በሁለተኛው ማስተካከል መኻል ያለው ጊዜ መዘግየትን ይፈጥራል። መዘግየት ደግሞ ጥራትን ያስተጓጉላል።
ሁለተኛው ምሰሶ ለመሻሻል ዕድል መስጠት ነው። ይህም ሁልጊዜ ከሌላው መማር እንደሚችልና እንደሚሻሻል የሚያሳይ ነው። ከአንተ ጋር ስንነጋገርና “ይህ ሰው በዚህ ጉዳይ ላይ የተሻለ ሐሳብ ሊኖረው ይችላል” ብዬ ማሰብ ስጀምር፣ አከብርሃለሁ። ደንበኛዬ ነህና ካንተ እውቀት እወስዳለሁ። ዛሬ ከአንተ ጋር ስለዋልኩ እውቀት አግኝቼ እሄዳለሁ ማለት ነው። እነዚህ ሁለቱ የጥራት ዋነኛ መሠረተ ሐሳቦች፣ ምሰሶዎች (ፒላርስ) ናቸው።
እነዚህ የጥራት ምሰሶዎች በአገራችን አሉ? ከተባለ፣ የሉም ማለት ይከብዳል። አሉ፣ ግን በጣም በጥቂቱ ነው ያሉት። በሥራዬ አጋጣሚ ብዙ አገሮች ዞሬአለሁ። በአሜሪካና በአውሮፓ የትም አገር ሽንት ቤት ውስጥ “ከተጠቀማችሁ በኋላ ውሃ ልቀቁ” የሚል ጽሑፍ አይቼ አላውቅም። ወደ አገራችን ስንመጣ ግን “ትልቅ” የተባለ ሆቴል ውስጥ ይሄ ማሳሰቢያ ተጽፎ ይታያል። ምን ማለት ነው? እኔ ሽንት ቤቱን ከተጠቀምኩ በኋላ ቀጥሎ የሚመጣ ሰው ደንበኛዬ ነው። እኔ ሽንት ቤቱን በምጠብቅበት ሁኔታ እሱም እንደሚጠብቅ አውቄ እሱን ማክበር አለብኝ። በምዕራብ አገሮች ይህ ስለገባቸው በት/ቤት መፀዳጃ ቤቶች ውስጥ እንኳ አይጻፍም። እኛ አገር ለምን ይጻፋል? ለጥራት ያለን ግንዛቤ ዝቅተኛ ስለሆነ  ነው። ይህን ይህን ሳይ “ምን ይሻላል?” የሚለው ብዙ ጊዜ ያሳስበኛል። አዲሱ ትውልድ ስለጥራት ያለው ግንዛቤ እንዲያድግ ካስፈለገ ያለን አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ መለወጥ አለበት።
ለምሳሌ እኔና አንተ ደንበኞች ነን። እኔ አንተን ለማስደሰት፣ እኔ እሱን ብሆን ኖሮ እንዴት እንዲሆንልኝ እፈልጋለሁ? ሰዓት እንዲያከበርልኝ እፈልጋለሁ። ጥያቄዬ ሁሉ በቅንነት እንዲመለስልኝ እፈልጋለሁ… በማለት ማሰብ አለብኝ። ይህን ካደረግሁ አንተ ደስ ይልሃል። በሁሉም ቦታ ደንበኞቻችንን ማስደሰት ስንፈልግ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “እናንተ እንዲደረግላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም አድርጉላቸው” የሚለውን ማሰብ ያስፈልጋል። ይሄ አባባል የጥራት ዋነኛ መመሪያ ነው። ይሄንን መመሪያ መተግበር ወሳኝ ነው። እንግዲህ የጥራት ፅንሰ-ሃሳብ እንዲተገበር ከታች ከጽዳት ሠራተኛው እስከ ላይኛው ባለሥልጣን ድረስ የልቡና ውቅር (ስትራክቸር)፣ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ (የፓራዳይም ሺፍት) መደረግ አለበት።
ለጥራት ያለ የአመለካከት ለውጥ (ፓራዳይም ሺፍት) እንዴት ነው የሚመጣው?
እንደ ዕንቁላልና ዶሮዋ የተሳሰረ ነው፤ ጥራትና ምርታማነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው። ጥራት ከሌለ ተወዳዳሪነትና ዕድገት የለም። በመጀመሪያ በኅብረተሰቡ ውስጥ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል። ሰው ሁሉ እንዲያውቀው ማድረግ የግድ ነው። ጋዜጦች፣ ቴሌቪዥኖች፣ ሬዲዮኖች፣ በአጠቃላይ ሚዲያው፣ የጥራት ሐሳብ በኅብረተሰቡ ውስጥ በሚገባ እንዲሰርጽ በብዛት መሥራት አለባቸው። እኔ እግር ኳስ በጣም ስለምወድ በየሬዲዮ ጣቢያው ስለኳስ ሲያወሩ በጣም ደስ ይለኛል። ነገር ግን ለስፖርቱ የተሰጠው ጊዜ ግማሽ ያህል እንኳ የጥራትን መሠረተ ሐሳብ ለማስረፅ ቢውል አገሪቷ የት በደረሰች።
መጀመሪያ ግንዛቤ መፍጠር ነው፤ ቀጥሎ እርምጃ መውሰድ። ሰው ግንዛቤ ካገኘ በኋላ እያንዳንዱ ግለሰብ መለወጥ አለበት። በሶስተኛ ደረጃ ራሱን እያሻሸለ ሳለ መታገል አለበት። ለምሳሌ ታክሲ ውስጥ ተደራርባችሁ ተቀመጡ ሲባል ትክክል ስላልሆነ መቃወም አለበት። “ፋዘር ወይም ማዘር ጠጋ በሉ” ማለት ከጥራት መሠረተ ሐሳብ ጋር አይሄድም። ስለዚህ መቃወም አለበት። በየትም ቦታ ቢሆን እያንዳንዱ ግለሰብ ትክክል ያልሆነ ነገር ሲያይ ዝም ማለት የለበትም። ህብረተሰቡ መምራት አለበት። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ግንዛቤው መዳበር አለበት። ትያትረኞች ጸሐፊዎች፣ ገጣሚዎች፣ አርቲስቶች፣ …. ጥራት ላይ መሥራት አለባቸው። ትያትር በህብረተሰቡ ውስጥ የበለጠ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችለው በጥራት ላይ ሲሰራ ነው። ስለ ጥራት ማስተማርያ የአየር ሰዓት መኖር አለበት። ስለ ጥራት ካስተማርን በኋላ እርምጃ መውሰድና ሮል ሞዴሎች (አርአያዎች) መፍጠር አለብን።
ለምሳሌ አበበ ቢቂላን ብንወስድ በሩጫ ጥሩ ሮል ሞዴል ነው። ግን ለቢዝነሱ ጥሩ ሞዴል አይደለም። ከአበበ በኋላ ኃይሌ ገ/ሥላሴ መጣ። ኃይሌ ጥሩ የቢዝነስ ሞዴል ስለሆነ ከእሱ በኋላ የመጡት በሆቴልና በሌላ የቢዝነስ ዘርፍ ተሰማሩ። በጥራትም ሮል ሞዴሎች ስለሚያስፈልጉን መሸለምና ማበረታታት ያስፈልገናል። ለዚህ ደግም የሽልማት ድርጅት ያስፈልገናል። ይህ ነገር በህብረተሰቡ ውስጥ ሲደጋገም ባህል ይሆናል። ይህቺ አገር ምን ያሳድጋታል ብትለኝ፣ ጥራትና ምርታማነትን ማሳደግ…  ነው የምለው።
በዚህ ረገድ አዲሱ ትውልድ (ወጣት፣ ሕፃናት፣ ሴቶች) ላይ መሠራት አለበት።  ለሴቶች ቦታና ዋጋ መስጠት ይገባል። በት/ቤቶች ደግሞ አሁን ያሉት መምህራን ከጥራት ግንዛቤ ውጭ ስለሆኑ፣ የአሰልጣኞች ስልጠና ፕሮግራም ያስፈልጋል። የትምህርት ካሪኩለሙም መቀየር (የፓራዳይም ሺፍት ማድረግ) ይኖርበታል። የሽምደዳ ካሪኩለም መቀየር አለበት።
ልጆች፣ ተፈጥሮን ወደዋትና ተንከባክበው እንዲይዟት ማበረታታት ያስፈልጋል። እፅዋት ከተንከባከቡ በውስጡ ለሚኖሩት ነፍሳት አክብሮት ይሰጣሉ። ተፈጥሮን የሚወዱ፣ ደንበኞቻቸውን የሚያከብሩና የሚደራደሩ ወጣቶችን ማፍራት አለብን። መደራደር ስል እናቶችን ማስተማር ያለብን አንድ ነገር አለ። ልጆቻቸው እንዲያጠኑ ሲፈልጉ፤ “አጥኑ፤ ያለበለዚያ ትመታላችሁ” አይደለም ማለት ያለባቸው።
እናት፤ “አጥኑ፣ ካላጠናችሁ ቴሌቪዥን አይከፈትም”
ልጆች፤ “ስንት ቀን ነው የምናጠናው?”
እናት “በሳምንት ስድስት ቀን”
ልጆች “አራት ቀን”
እናት፤ “የለም! አምስት ቀን”… እየተባባሉ መደራደርን መልመድ አለባቸው። ከልጅነታቸው ጀምሮ መደራደር ካላስተማርናቸው አድገው የፓርቲ መሪ ሲሆኑ አይደራደሩም። “ወይ እሞታለሁ፤ ወይ እገለብጣለሁ” ነው የሚሉት። የጥራት ጉዳይ ይህን ያህል ጥልቅ እንደሆነ አንባብያን እንዲረዱልኝ እፈልጋለሁ።
በአገራችን የሚታየውን የምርትም ሆነ የአገልግሎት ጥራት ማነስ እንዴት ይገልጹታል?
 በእኛ አገር አብዛኛውን ጊዜ ሰራተኛው ችሎታ የለውም ሲባል እንሰማለን። ነገር ግን ከ80 እስከ 90 በመቶ የጥራትና የምርታማነት ችግር ሲስተሙ (አሰራሩ ላይ) ነው። ስለዚህ ሲስተሙ መለወጥ አለበት። ሲስተሙ ትክክል ሲሆን ሠራተኛው ትክክል ይሆናል። ለምሳሌ፣ ውልና ማስረጃን ያየን እንደሆነ ሰራተኞቹ አልተቀየሩም። ወይም ፈረንጅ አልመጣም። ሲስተሙ ስለተስተካከለላቸው፣ ሁለት ቀን የሚፈጀውን ሥራ በ30 ደቂቃ ይሠሩታል። ነገር ግን ሲስተሙ ተስተካክሎ ብቻ መቆም የለበትም። ልምድና ባህል መሆን አለበት። አንድ ሰው ቆሞ እንዲህ አድርግ፣ አታድርግ ማለት የለበትም። ያለበለዚያ ወደ ኋላ ይመለሳል።
ፋብሪካዎችም የሲስተም ችግር አለባቸው። እሱንም ማስተካከል ያስፈልጋል። ከዚህ ጋር ሌላው አስፈላጊ ነገር ስልጠና ነው። በተለይ ስለ ጥራትና ምርታማነት ስናወራ ከስልጠና ውጭ ሊሆን አይችልም። የስልጠና ክፍለ ጊዜ ያላቸው ድርጅቶች ስንት ናቸው? ስንል በጣም ጥቂት ናቸው። አቶ ታዲዮስ ሐረገወርቅ ምክትል ሚኒስትር ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ዩኒቨርሲቲዬን እየወከልኩ በስልጠና ጉዳይ ስለምሰራ ብዙ ድርጅቶችን አይቻለሁ። አብዛኞቹ የስልጠና ክፍለጊዜ የላቸውም። ምናልባት አንድ ሰው “የሥልጠና ኃላፊ” ተብሎ ሊቀመጥ ይችላል። ነገር ግን ጥራት ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎች ሲወጡ፣ የሥልጠና ክፍል ኖሯቸው መመሪያ አዘጋጅተው፣ ቤተመጻሕፍት አስቀምጠው ሰራተኞቻቸውን የሚያሰለጥኑ ድርጅቶች ጥቂት ናቸው። ቴሌ፣ አየር መንገድ፣ አውራ ጎዳና፣ ከክልሎችም እንዲሁ… ይኼ ምንድነው የሚያሳየው? የጥራት ፍልስፍና ፅንሰ ሐሳብ አልገባንም ማለት ነው። ሥልጠናን ሲስተማችን ውስጥ አላስገባንም።
ማነው ሲስተሙን መቀየር ያለበት?
የሚገርመው ነገር የግሉ ዘርፍ ነበር ቢፒአር የተባለውን የለውጥ ሂደት መምራት የነበረበት። ቢፒአር አተገባበሩ ትክክል ከሆነ መሰረታዊ አሰራሩ ጥሩ ነው፤ አምንበታለሁ። ይህ የለውጥ ሐሳብ ከግሉ ዘርፍ መምጣት ነበረበት። ነገር ግን መንግሥት ቀደመው። ለምን? ቢባል፣ በታዳጊ አገር ያለው የግሉ ዘርፍ ዕድሜ ጨቅላ ስለሆነና ስላልጎለበተ ነው። ስለዚህ ኃላፊነቱን መንግሥት ወሰደ። መንግሥት ይህን ኃላፊነት ሲወስድ ግን ሁሉንም እኔ መስራት አለብኝ ማለት የለበትም። ይህን የሚሰሩ የግል ዘርፎችን አደራጅቶ እየሰሩ ከስህተታቸው እንዲማሩ መልቀቅ ያለበት ይመስለኛል። እርግጠኛ ያልሆንኩት በምርምርና በዳታ የተደገፈ መረጃ ስለሌለኝ ነው።
የጥራት ፍልስፍናን መሠረተ ሐሳብ ተግባራዊ በማድረግ የተለወጠና ለአብነት የምንጠቅሰው አገር አለ?
አዎ! ለምሳሌ ሲንጋፖርን መጥቀስ እንችላለን። ሲንጋፖር እ.ኤ.አ በ1966 ነው ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጣችው። 50 ዓመት እንኳ አልሞላትም። ከዚያን ጊዜ አንስቶ እስከ 1980 ድረስ ሲስተም እያስተካከሉ ቆዩ። ከዚያም ሊ ኳን የተባለ ጠቅላይ ሚኒስትራቸው “ምርታማነት የአዕምሮ መቀየር ነው። ከአሁን ጀምሮ በዚህ አቅጣጫ ነው የምንሄደው” በማለት አወጀ። ይህን የለውጥ ሂደት የሚመራ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚመራ ኮሚቴ አቋቋመ።
ለአምስት ዓመት የህብረተሰቡን የምርታማነትና የጥራት ግንዛቤ ሲያሳድጉ ቆዩ። ቴሌቪዥኑ፣ ሬዲዮው፣ ጋዜጣው፣ መጽሔቱ፣ ዘፈኑ… በየመንገዱ ላይ የሚሰቀሉትና በየግድግዳው የሚለጠፉት ፖስተሮች፣ .. ሁሉ የቆየ አመለካከት መለወጥና አዲሱን የለውጥና የዕድገት ትሩፋቶች ማስተማር ነበር ሥራቸው። ከዚህ በኋላ ወደ ተግባር እርምጃ ገቡና የለውጥ ሂደቱን የሚመሩ የተለያዩ ተቋማትን አቋቋሙ። በዚህ ዓይነት ሲሰሩ ቆይተው የሕዝባቸውን አዕምሮ ቀየሩት። ከ20 ዓመት በኋላ እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም 12 መመዘኛዎች ባሉት ግሎባል ፕሮዳክቲቪቲ ኢንዴክስ በተባለው የምርታማነት መለኪያ ከዓለም አገራት ጋር ተወዳድረው 3ኛ ወጡ። ከዚያ በኋላ ደግሞ ለውጥ ያገኙበትን አሰራር (ሲስተም) የራሳቸው አደረጉት።  የህልውናቸው አካልና መገለጫ ሆነ። በመቀጠል ደግሞ የራሳቸው ባደረጉት ሲስተም አዲስ ነገር ወደ መፍጠር (ኢኖቬሽን) ገቡ።
በሲንጋፖር አንድ ቢሮ አንኳኩተህ የምትፈልገውን ስትጠይቅ፣ የተቀበለህ ሰው ጉዳዩ የማይመለከተው ከሆነ፣ የሚመለከተው ጋ ይወስድሃል ወይም ወደሚመለከተው ሰው ጋ ወደሚወስድህ ሰው ያደርስሃል እንጂ “አይ! እኔ አላውቅም” አይልህም። የአገር ጉዳይ ነዋ! የታክሲ ሹፌሩ ከአየር ማረፊያ ወደምታርፍበት ሆቴል ሲወስድህ፣ ስለአገሩ እያወራልህ ነው። “ይህ ቦታ በፊት እንዲህ ነበር፤ እኛ ነን እንዲህ ያሳመርነውና የለወጥነው። ይህ ደግሞ …” እያለ በማውራት ሆቴል ያደርስሃል። እሱ ምን ሰራ? ብትል በሙያው በአቅሙ “ይህ የመንግሥት ሳይሆን የእኔ ጉዳይ ነው” በማለት በዜግነቱ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ተወጥቶ ይሆናል። ይኼ ነው የምርታማነት ፅንሰ ሀሳብ።  የሚገርመው ነገር እንደ እኛው ኋላቀር የነበረችው ሲንጋፖር እዚህ “ተአምራዊ” የሚመስል ፈጣን ዕድገት ላይ የደረሰችው በ48 ዓመት ነው።    
ድሮ የጃፓን ምርት ጥራት እንደሌለው ለመግለጽ፣ “ኪሽ ኪሽ የጃፓን ዕቃ ወድቆ የማይነሳ” ወይም “አወይ ሞሶሎኒ አወይ ሞሶሎኒ ተሰባብረህ ቀረህ እንደ ጃፓን ሶኒ” ይባል ነበር። አሁን ግን ጃፓን የዓለምን ኢኮኖሚ ከሚመሩት ቀዳሚ አገራት አንዷ ነች። እንዴት ለዚህ በቃች?
ጃፓንም እንደ ሲንጋፖር ምሳሌ የምትሆን አገር ናት። እንደተባለው ምርቷ ጥራት የሌለው ነበር። ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ---------- የተባሉ አሜሪካውያን በአገራቸው ስለጥራትና ስለምርታማነት ጮኸው ጮኸው የሚሰማቸው ቢያጡ፣ ወደ ጃፓን ሄዱ። እዚያም 150 ሥራ አስኪያጆችን ሰብስበው ስለጥራትና ምርታማነት አወሯቸው። “አሁን የነገርናችሁን ተግባራዊ ካደረጋችሁ በአምስት ዓመት ውስጥ ለውጥ ታመጣላችሁ” አሏቸው። እነዚያ ሥራ አስኪያጆች ጠንክረው በመስራታቸው በአምስት ዓመት ሳይሆን በሦስት ዓመት ለውጥ አመጡ። እነጃፓንንና ሲንጋፖርን ከቀየረ፣ የእኛንም አገር ይቀይራል ማለት ነው።
ወደዚያ የሚወስደው ጉዞ ተጀምሯል?
ጥሩ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች አሉ። ካይዘን በጣም ጥሩ ጅምር ነው። እንዲህ ዓይነት ጅምሮችን ማነቃቃትና ማበረታታት፣ ከፍ እንዲሉና እንዲልቁ ማገዝ፤ ሰራተኞቹ ደግሞ በፍፁም የተለወጡ እንዲሆኑ በየጊዜው ሥልጠና፣ እውቅና፣ አክብሮትና ሽልማት መስጠት ያስፈልጋል።

Read 4086 times