Saturday, 19 April 2014 12:16

ወለጋ ውልደቱ፤ ጎጃም ቅኔ ቤቱ

Written by  ጵርስፎራ ዘዋሽራ
Rate this item
(10 votes)

   “ወለጋ ውልደቱ፣ ጎጃም ቅኔ ቤቴ” በሚል ርእስ ላስነብባችሁ የፈለግሁት ስለታላቁ የቅኔ መምህር ስለገብረ ሥላሴ ክንፉ ሕይወትና ቅኔዎቻቸው ነው። መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ (1963፤ ገጽ 46) በአሳተሙት የቅኔ መጽሐፍ ላይ እንዳሰፈሩት፤ የመምህር ገብረሥላሴ ክንፉ የትውልድ ሀገር ወለጋ ሖሮ ጉድሩ ነው። ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት በዓፄ ዮሐንስ ጊዜ ሕጻን ገብረ ሥላሴን በአጋጣሚ አግኝተዋቸው እንደ ልጅ አድርገው ለማሳደግ ስለ ፈለጉ፣ ከወላጅ እናታቸው ተረክበው ወደ ጎጃም ደብረ ማርቆስ ይዘዋቸው ይመለሳሉ።
ጎጃም ውስጥ ደግሞ ራሳቸውን ንጉሥ ተክለሃይማኖትን በልጅነታው እንደ አባት ሆነው በመንፈሳዊ አስተዳደግ አርመውና ኮትኩተው ያስተማሩዋቸውና ያሳደጉዋቸው መምህር ነበራቸው። መመህሩም መምህር ክንፉ ይባላሉ። መምህር ክንፉ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ሱባኤ ገብተው፣ ጸሎት ይዘው በኀዘን ጭምር ከሚረዱ የበቁና የላቁ ሊቃውንት ውስጥ አንዱ ነበሩ። ተክለሃይማኖት ያመጡዋቸውን ገብረ ሥላሴን እንደ አባት ሆነው በመንፈሳዊ ጥበብ እንዲያሳድጓቸው ለመምህር ክንፉ አደራ ይሰጡዋቸዋል።
መምህር ክንፉም ንጹሕና በድንግልና የሚኖሩ ታላቅ አባት ስለሆኑ፣ ገብረ ሥላሴን በደስታ ተቀብለው፣ የመንፈስ አባት ሆነው እያስተማሩ በመልካም አኳኋን አሳድገዋቸዋል። ክርስትናም አሥነስተው “ገብረ ሥላሴ” ያሰኙዋቸው እርሳቸው ናቸው። በኋላም ገብረ ሥላሴን እንደ ልጅ አድርገው ርስታቸውንና ሪማቸውን አውርሰዋቸዋል። ገብረ ሥላሴ ክንፉ የተባሉትም ከዚህ የተነሣ ነው። መምህር ገብረ ሥላሴም እንደ ቅዱስ ጳውሎስ “ንዋየ ኅሩየ ረሰይኩከ፤ ከመትጹር ስምየ በውስተ አሕዛብ” ብሎ ክርስቶስ የመረጣቸው ሰው ስለነበሩ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በምትገለገልባቸው በጸዋትወ ዜማ፣ በአገባብና በቅኔ፣ በምሥጢረ መጻሕፍት እጅግ የተደነቁና የተመሰገኑ ሆኑ። ለዚህም ከሞላ ጎደል ተመዝግበው የሚገኙት ቅኔዎቻቸው ምሥክሮች ናቸው። ለዚህ የበቁት ከሕጻንነታቸው ጀምረው የመምህር ክንፉ የላቀና የረቀቀ እውቀትና ጥበብ ለመቅሰም በመቻላቸው ነው። መምህር ክንፉ በዘመናቸው በጎጃም ወደር የሌላቸው የቅኔ ሊቅ ነበሩ። በመምህር ገብረ ሥላሴ ቅኔ ውስጥ በዘርፍም በቅጽልም ቢሆን ጥልቅ ምሥጢር ሳይዝ ለሐረግ ማካሄጃ፣ ለቤት መሙያ ተብሎ የገባ ተራ ነገር አይገኝበትም። ሁሉም ሲፈቱት እንደ እንጀራ የሚያጠግብ ምሥጢርን የያዘ ብቻ ነው። በዚህም ሥራ እጅግ የተመሰገኑ ነበሩ። በዚህ ዓይነት በደብረ ገነት ኤልያስ ቤተክርስቲያን ለብዙ ዘመናት ቅኔ ሲያስተምሩ ኖረው በ1938 ዓ.ም ዐርፈዋል።
ለዚህም ነው የመምህር ገብረ ሥላሴ ክንፉ ስም ሲነሣ አብሮ የደብረ ገነት ኤልያስ ቤተክርስቲያን የሚጠቀሰው። አብ ሲጠራ ወልድ፣ ወልድ ሲጠቀስ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ እንደማይቀር፣ መምህር ገብረ ሥላሴና ደብረ ገነት ኤልያስ አብረው ይታወሳሉ። ምነው ቢሉ በስመ ኃዳሪ ይጼዋዕ ማኅደር ስለሚባል ነው። ቤት በባለቤቱ ይጠራል ለማለት ነው። መምህር ገብረ ሥላሴ ጉባዔ ዘርግተው፣ ምሥጢር አስፋፍተው፣ ለብዙ ዘመናት ቅኔ ያስተማሩት ደብረ ኤልያስ ነው።
ደብረ ገነት ኤልያስ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ በምሥራቅ ጎጃም ዞን በደብረ ኤልያስ ወረዳ የሚገኝ ጥንታዊና ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን ነው። ቀደም ሲል በማቻከል ወረዳ ውስጥ የተጠቃለለ ነበር። የደብሩ አለቃ ድማሐ ገነት ይሰኛል። በቤተክህነት ትምህርት አሰጣጥ ረገድ ደብረ ኤልያስ ጎጃም ውስጥ ከሚገኙ ማዕከሎች ቀዳሚው ሊሆን የቻለው፣ ከጥንት ዘመን ጀምሮ በቦታው ታላላቅ ምሁራን ስለተፈጠሩበት ነው።  
“ደብረ ኤልያስ የጥበብ ማዕከል” (1996-ገጽ 23) በሚለው መጽሐፍ እንደተገለጠው፤ አለቃ ገብረ ሥላሴ ክንፉ የደብረ ኤልያስን የቤተክህነት ትምህርት ቤት ታላቅ የትምህርት ማዕከል እንዲሆን ያስፋፉና ለዝና ያበቁ ሰው ናቸው።
አለቃ ገብረ ሥላሴ እስከ 1892 ዓ.ም ድረስ ደብረ ማርቆስ ከመምህር ክንፉ ጋር ኖረዋል። በ1892 ዓ.ም መምህር ክንፉ በመታሰራቸው ምክንያት ብቻቸውን ለመኖር ተገድደዋል። መምህር ክንፉ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን በመድኃኒት ለመግደል ሞክረዋል ተብለው ሲታሰሩ በመምህር ክንፉ ልጆች በእነ መምህር ገብረ ሥላሴና በሌሎች ዘመዶችና ባለሟሎች ላይ ሥቃይና እንግልት ደርሶባቸዋል። መምህር ገብረ ሥላሴ ዓይነ ስውር የሆኑትም በዚሁ ወቅት እንደሆነ ይገመታል። ከዚህ በኋላ አለቃ ገብረ ሥላሴ ወደ ደብረ ኤልያስ ወርደው ቅኔና ሐዲስ ማስተማር ጀመሩ። ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለዩበት እስከ 1943 በአድማሱ ጀምበሬ አገላለጥ፣ በሌሎች እስከ 1938 ዓ.ም ድረስ ደብረ ኤልያስ ኖሩ። ደብረ ኤልያስ ባስተማሩዋቸው ሦስት ዐሠርት ዓመታት በርካታ ተማሪዎችን አፍርተዋል። የአለቃ ገብረ ሥላሴን የቅኔ ትምህርት ለመማር በርካታ ተማሪዎች ወደ ደብረ ኤልያስ ይጎርፉ ነበር። በአንድ ወቅት የቅኔ ተማሪዎቻቸውም ቁጥር ከ300 በላይ ደርሶ እንደነበር ይነገራል። በአንድ ጊዜ የክብር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ በዚያን ወቅት ስለነበረው ሁኔታ ተጠይቀው፤ “በነዚያ ዓመታት (1890-1930) የደብረ ኤልያስ ቅኔ ትምህርት ቤት እንደ ትልቅ ኮሌጅ ይቆጠር ነበር” ብለዋል።
መምህር ገብረ ሥላሴ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ ጽሑፍና ቴአትር እንዲጀመርና እንዲያብብ መሠረት የጣሉ ሰዎችን አፍርተውልን አልፈዋል። ከነዚህ መኻከል ለመጥቀስ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ መላኩ በጎሰውና ሐዲስ ዓለማየሁ ይገኙበታል። ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ አለቃ ገብረ ሥላሴ ከሚያደንቋቸው የያኔ ተማሪዎቻቸው (ደቀ መዝሙሮቻቸው) ቀዳሚው ነበር። ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ የቅኔ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ አለቃ ገብረ ሥላሴ “ተናገር በከንፈሬ፣ ተቀመጥ በወንበሬ” ብለው በማድነቅ እርሳቸውን ተክቶ እንዲያስተምር ፈልገው ነበር። ግን የሕይወት ዕጣ ወደ ሌላ አቅጣጫ መርታዋለች። በተመሳሳይ መልኩ አለቃ ገብረ ሥላሴ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አመራር ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ በርካታ ሰዎችን ያፈሩ ሲሆን ከእነዚህ መኻከል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስና ዶ/ር ኢሳይያስ ዓለሜ ጥቂቶች ናቸው። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን (ቀደም ሲል አባ መልእክቱ ጀምበሬን) አለቃ ገብረ ሥላሴ በተለየ ሁኔታ ይወድዷቸው እንደነበር ይነገራል። አባ መልእክቱ በልጅነታቸው መምህራቸውን አለቃ ገብረ ሥላሴን ይመሩዋቸውና በደብረ ኤልያስ አቅራቢያ ወደ ምትገኘው ጠሸት ወንዝ አብረው በመሔድ ዋና ይዋኙ እንደነበርም ይነገራል።
ለመምህር ገብረ ሥላሴ በርካታ ቅኔዎች አሉዋቸው። መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ፤ “መጽሐፈ ቅኔ ዝክረ ሊቃውንት” ብለው በ1963 እና በ1991 ዓ.ም በአሳተሙዋቸው ሁለት መጻሕፍት ውስጥ በመምህር ገብረ ሥላሴ ስም 72 ቅኔዎች ታትመውላቸል።
ይህም በርካታ ቅኔዎች ተሰብስበው በመልአከ ብርሃን አድማሱ መጻሕፍት ከታተሙላቸው ባለቅኔዎች ውስጥ በቁጥር ብዛት የመምህር ገብረ ሥላሴ ቅኔዎች በአንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በቅኔያቸው ብዛት ሁለተኛውን ደረጃ የሚዙት ዕቡይ ካሣ ዘጎንጅ ናቸው።
ሊቁ ገብረ ሥላሴ የብሉይንና የሐዲስን ምሥጢራት ጠንቅቀው የሚያውቁ በመሆናቸው የቅኔዎቻቸው ይዘት መጽሐፋዊ ነው። በመጽሐፍ ታሪክ ላይ የተመሠረቱ ቅኔዎችን እንደ ዕቡይ ካሣ  ያበዛሉ፣ ያከታትላሉ ማለት ነው። እናም የቅኔያቸው ስልት ታሪክ፣ ሰምና ወርቅ እና ምሳሌ ነው። ቅኔዎቻቸው በማይረሣ መልኩ በሰው አእምሮ ውስጥ ሠርፀው የመኖር ኃይል አላቸው። ለአብነት ያህል ጥቂቶቹን እንመልከት።
1ኛ. ጉባዔ ቃና ዘመምህር ገብረ ሥላሴ ክንፉ ዘደብረ ኤልያስ (አድማሱ ጀምበሬ 1991 ገጽ 65)
ለሰጡህ እክል በላዔሰብእ በመንጸፈ ደይን እንተቦ።
መሰጠቶዖፍ ከመ ለእጓላ ተሀቦ።
ሰም፡ በኩነኔ ምንጣፍ ከደጅ የተሰጣውን እህል በለዔ ሰብእ /ሰወ በላ/፣ ወፍ ለልጅዋ ትሰጠው ዘንድ ነጥቃ ወሰደችው።
ወርቅ፡ እህል በሚሰጣበት ጊዜ ወፍ ነጥቃ በመውሰድ ለልጅዋ እንደ ምትሰጠው፣ በወፍ (ርግብ ሠናይት የዋኂት) የምትመሰለው እመቤታችን ድንግል ማርያም፣ 77 ነፍሳት ያጠፋውን በላዔ ሰብእን በጥርኝ ውሀ አስምራ፣ ወደገነት እንዲገባ እንደተራዳቺው ያመለክታል። (ታሪኩ በተአምረ ማርያም ላይ ይገኛል።)
2ኛ. ጉባኤ ቃና ዘመምህር ገብረ ሥላሴ ክንፉ ዘደብረ ኤልያስ (አድማሱ 1963 ገጽ 129)
አቤልግእዝ ለሞተ ፍጡራን ፊደል።
ወፍጻሜሁ ሳብዕ ሞተ ኤልያስ ድንግል።
ሰም፡ ለፍጡራን ሞት ፊደል አቤል ግእዝ ነው።
ፍጻሜውም የኤልያስ ሞት ድንግል ሳብዕ ነው።
ወርቅ፡ የአቤል ሞት ግእዝ ነው። የኤልያስ ደግሞ ሳብዕ ነው፤ ማለት አቤል የመጀመሪያው ሟች መሆኑን/ ግእዝ መጀመሪያ ማለት ነው)
ኤልያስ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በብሔረ ሕያዋን ሳይሞት ስለሚኖር፣ በኋላ ዘመን ላይ (በፊደሉ መጨረሻ ሳብዕ ተብሎ እንደተገለጠው) የሚሞት መሆኑን የሚገልጥ ቅኔ ነው።
የቅኔው መንገድ ምርምር ነው።
ሌላው ደብረ ኤልያስ ሄጄ በነበረበት ጊዜ የእኒሁ ሊቅ ቅኔ እንደሆነ የተነገረኝ ጉባዔ ቃና የሚከተለው ነው።
3ኛ. ጉባኤ ቃና ዘመምህር ገብረ ሥላሴ ክንፉ
ይቤላ በእግር ተክለ ሃይማኖት ቢጽየ።
ዳእሙ በክንፉ የዐብየኒ ኪያየ።
ሰም፡ በክንፉ ከአልበለጠኝ ተክለ ሃይማኖት ጓደኛዬ ነው አለች ማን? በምርምር ነው የሚፈታው።
ወርቅ፡ አንዳንድ ሰው እገሌ በዚህ ….. ካልበለጠኝ በስተቀር ጓደኛዬ ነው እንደሚል “ላ” ፊደልም በእግር ጓደኛዬ ነው አለች ማለት ነው። ይኸውም የ”ላ” ፊደል የተንጠለጠለች ሲሆን ተክለሃይማኖት ከጸሎት ብዛት የተነሣ አንድ እግሩ የተሰበረና ሐንካስ የነበረ መሆኑን ቅኔው ያመለክታል።
4ኛ. ሚበዝኁ ዘመምህር ገብረ ሥላሴ ክንፉ ዘደብረ ኤልያስ (አድማሱ 1963 ገጽ 260)
    አመ ሰማዕክሙ ቀርነ ውስተ ቤተ ጸሎት ኬብሮን ባሕታውያን ዘገዳም።
በሉ ነግሠ መብልዕ አቤሴሎም።
እስመ አሜሃ ይሰደድ እንተ ልማዱ ብካይ
            ንጉሠ እስራኤል ጸም።
ሰም፡ በቤተ ጸሎት ኬብሮን ውስጥ ከበሮ /የከበሮ ድምጽ/ የገዳም ባሕታውያን ከሰማችሁ ምግብ አቤሴሎም ነገሠ በሉ። ያን ጊዜም ልማዱ ለቅሶ የሆነው የእስራኤል ንጉሥ ጾም ይሰደዳልና።
ወርቅ፡ አቤሴሎም ቀርነ መለከት እያስነፋ በእስራኤል ላይ በነገሠ ጊዜ አባቱ ዳዊት እንደተሰደደ ሁሉ ጾምም የሥጋ መባልዕት (ምግቦች) ሲበዙ ይሰደዳል ይጠፋል እንደ ማለት ነው። ጾምና ቀኖና ደግሞ ለገዳም ባሕታውያን እንደሚስማማቸው፣ የዓለም ነገር እንደማይስማማቸው ያትታል።
5ኛ. ሣህልከ ዘመምህር ገ/ሥላሴ ክንፉ ዘደብረ ኤልያስ (አድማሱ 1963 ገጽ 249)
ሰይፈከ ቅንት ከመ ቀዳሚ፣
ኃያል ኤልያስ ዘውስተ ገነት ቀዋሚ።
ቤተከ ይንሥት እስመ ተንሥአ
ዝናመ ደመና ካልኡ አረሚ።
ሰም፡ እንደ በፊቱ በገነት ውስጥ ቋሚ የሆንከው ኃያሉ ኤልያስ ሰይፍህን ታጠቅ። አረመኔ የሆነው የደመና ዝናም ቤትህን ሊያፈርሰው ተነሥቷልና።
ወርቅ፡ ኤልያስ ሰማዩ ዝናም እንዳይጥል ገዝቶት የነበረ መሆኑን ያመለክታል። የቅኔው ዓይነት ሰምና ወርቅ ነው።
የመምህር ገብረ ሥላሴ ቅኔዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጋር በእጅጉ የተቆራኙ ናቸው። ይህ ዓይነቱ መንገድ ንጽጽር ሆኖ ጽድቅ (Truth without secret) ቅኔ ይሰኛል። የመምህር ገብረ ሥላሴን ቅኔ ለቅምሻ ያህል አሳየሁ እንጂ የርቀቱ ብዛት የምሥጢሩ ስፋት ዐባይን በጭልፋ ዓይነት ነው። ለዛሬ በዚሁ አበቃሁ።  

Read 12482 times