Print this page
Saturday, 19 April 2014 12:04

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

እንኳን ለብርሀነ ትንሳኤው አደረሳችሁማ! ያጣናቸው፣ የወደቁብን መልካም ነገሮች ሁሉ ትንሳኤ ያድርግልንማ!
ታላቁ መጽሐፍ ላይ… “ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ያጠለቀ፣ እኔን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ነው፣” ተብሏል። በዚህ ዘመንም፣ በዚች ምድርም እጁን አብሮ በወጭት አጥልቆ አሳልፎ የሚሰጥ መአት ነው። ልክ የሆነ ድንገተኛ ግዝት የወረደብን ይመስል…እሱ ነው/እሷ ነች አይነት የአመልካች ጣት ጥቆማ ዘመን ሆኗል። ባይማማሉም ተማምነው አብረው ያፈሩትን ገንዘብ፣ አብረው ያቀዱትን መልካም ለብቻ ማድረግም በተዘዋዋሪ አሳልፎ መስጠት ነው። ከመላእክት እኩል ጻድቅ በመምስል፣ በታላቅ ትህትና ‘አንገትን በመስበር’ ተለሳልሶ ገብቶ የሰውን ህይወት አቆርፍዶ ፈትለክ የሚል መአት ነው። እናላችሁ…አሳልፎ መስጠት በብዙ መልኩ ይከሰታል።
እናላችሁ…“…እኔን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ነው፣”  እንደተባለው ሁሉ እውነትም
“…የምስመው እሱ ነው ያዙት፣ ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት…” ተብሎም ተጽፏል።
ታዲያላችሁ…ዘንድሮም “የምስመው እሱ ነው…” እያለ የምናስወስድ መአት ነን።
የመተማመን ነገር ጠፍቶ፣ ጥላችንን እየተጠራጠርን…‘ከወዳጆቼ ጠብቀኝ ጠላቶቼን እኔ እጠብቃቸዋለሁ’ የምንለው ‘ስሞ የሚያስወስድ’ በመብዛቱ ነው።
ምሎ ተገዝቶ ‘ነፋስ የማይገባበት ወዳጅነት’ ከተባለ በኋላ… አለ አይደል… ትንሽ ቆይቶ በ“የምስመው እሱ ነው…” አይነት ወደ ቅልጥ ያለ ባላጋራነት ይለወጣል።
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ብዙ ጊዜ እንደምንለው…እዚህ አገር ‘ሪሰርች’ ምናምን የሚባል ነገር የተለመደ ነው ማለቱ ያስቸግራል። እናላችሁ…ዘንድሮ መኖራቸውን እንኳን ነገሬ ሳንላቸውና የግለሰቦች ጉዳዮች ናቸው በሚል ችላ ብለናቸው የነበሩ እኩይ ባህሪያት በአጭር ጊዜ ለምን በዚህ ፍጥነት የተስፋፉበትን ምክንያት አጥንተው የሚነግሩን ሰዎች መጥፋታቸው ያሳዝናል። እናማ…“የምስመው እሱ ነው…” አይነት መከዳዳት ከዋናዎቹ ባህሪያቶቻችን አንዱ የሆነበትን ምክንያት የሚያስረዱን እንፈልጋለን።
እኔ የምለው….እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የ‘ሪሰርች’ ነገር ካነሳን አይቀር ምን መሰላችሁ…በብልቃጦችና በኬሚካሎች የተሞሉ ቤተ ሙከራዎች ውስጥ ባይሆንም እዚህ አገር በእርግጥ ቅልጥ ያለ ‘ሪሰርቾች’ ይደረጋሉ! ልክ ነዋ…“ስማ ባሏ ፊልድ የሚወጣው መቼ፣ መቼ እንደሁ እስቲ ሠፈር አካባቢ አጠያይቅና አጣራልኝ…” “የጫማዋ ቁጥር ስንት እንደሁ ከጓደኞቿ ሰልልኝ…” ሁሉ ‘ሪሰርች’ ነው።
እናላችሁ…በታላቁ መጽሐፍ እንዲህም ተብሏል…
“በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፣ እረኛውን እመታለሁ፣ በጎችም ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና...”
“ዼጥሮስም ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም አለው። እየሱስም፣ እውነት እልሀለሁ ዛሬ በዚች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው።”
እናማ…በአሁኑ ጊዜም… አለ አይደል… “አህያ ወደቤት ውሻ ወደ ግጦሽ በሆነበት ዘመን “ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም” አይነት ነገር እያልን በአፍ ‘ቲራቲር’ የምንደልል መአት ነን። የሚደለለውም መአት ነው።
እናማ…ያሰቡትን እስኪፈጽሙ፣ ‘የልባቸው እስኪደርስ’ ሲምሉ፣ ከርመው የቁርጥ ቀኑ ሲመጣ እንዲህም ይሆናል…
“ከሊቀ ካሀናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፣ ዼጥሮስም እሳት ሲሞቅ አይታ ተመለከተችውና፡— አንተ ደግሞ ከናዝሬቱ እየሱስ ጋር ነበርህ አለችው። እርሱ ግን የምትዪውን አላውቅም፣ አላስተውልምም ብሎ ካደ።”
“አላውቅም አላስተውልምም…” ብሎ ሽምጥጥ አድርጎ መካድ ዘንድሮ የክህደት ሳይሆን ጭርሱን የብልህነት መለኪያ ሆኗል። በዚህም የለፋበትን፣ ላቡን ያፈሰሰበትን የሚያጣ ስንቱ እንደሆነ ቤቱ ይቁጠረው።
 በታላቁ መጽሐፍ እንዲህም ተብሏል…
“ይሁዳ ሆይ በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አዎ፣ አሁንም የምንለው በመሳም አሳልፋችሁ ትሰጡናላችሁን?
በመሳም እሴቶቻችንን፣ ክብራችንን አሳልፋችሁ ትሰጡብናላችሁን?
በመሳም የ‘ፈረንጅ’ መዘባበቻ ታደርጉናላችሁን?
…እንላለን።
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እዚሀ አገር ይሄ ‘ፈረንጅ’ እየተከተሉ ባልታየ ትርኢት ማጨብጨብ፣ ባላስነጠሰው መሀረብ ማቀበል፣ ባላንገዳገደው “እኔን ይድፋኝ!” ማለት፣ ባልዘነበ ዝናብ፣ ባልከረረች ፀሀይ ዣንጥላ መዘርጋት ምናምን ነገር ላይለቀን ነው! (አንዳንዶቻችን እኮ…አለ አይደል… ማጨብጨብ ብቻ ሳይሆን በሊዝ ለ‘ፈረንጅ የተላለፍን’ ይመስለናል!)
የምር እኮ…ግርም የሚል ነገር ነው። ጤፍ አሪፍ ምግብ ለመሆኑ የፈረንጅ ‘ደረቅ ማህተም’ እና ቡራኬ ለምን እንደሚያስፈልገን አይገባኝም።
“ፈረንጅ አደጋችሁ ብሎናል…”
“ፈረንጅ ህዝባችሁ ጨዋ ነው ብሎናል…”
“ፈረንጅ ግሩም ባህል አላችሁ ብሎናል…”
“ፈረንጅ በአክሱም ሀውልት ተደንቄያለሁ ብሎናል…”
“ፈረንጅ ሴቶቻችሁ ቆንጆዎች ናቸው ብሎናል…”
ፈረንጅ!… ፈረንጅ!… ፈረንጅ!…
እናማ…የምድሩንም የሰማዩንም ለፈረንጅ ሰጥተን…እልፍኛችንንና ጓዳችንን ባዶ እያደረግናቸው ነው።
የባህል ልብሶቻችን እርፍና ለመመስከር ለምን በፈረንጅ አንደበት እስኪነገር፣ ለምን በፈረንጅ ወይዘሮ እስኪለበስ እንደምንጠብቅ ግራ ግብት አይላችሁም! ፈረንጅ የሀበሻን ልብስ ወደደው፣ አልወደደው የልብሱን እርፍና አይጨምረው፣ አይቀንሰውም። (ስሙኝማ…ያኔ “አይሞቀንም አይበርደንም…” ይባል የነበረው ነገር…ናፈቀንሳ! ነገርየው እንዴት ሆኖ ይሆን… ነው ወይስ ሁሉም ነገር በሰሜን ዋልታ በረዶ ተውጦ አረፈው!)
እናላችሁ…ለታሪካዊም ሆነ ባህላዊ እሴቶቻችን ደረጃ ለማውጣት የፈረንጅን በጎ አመለካከት ለምን እንደምንጠብቅ ግራ የሚገባ ነው። አሁን፣ አሁን “ለምን መሬት ነክቷችሁ…” እያልናቸው ያሉ የሙዚቃ ሰዎቻችን እኮ ፈረንጅ አገር ሽልማቶች ከማግኘታቸው በፊት እዚህ ለአሥርት ዓመታት አብረውን ነበሩ እኮ! እናማ… ምነው ያኔ ዓይናችን አላያቸው አለ!…ምነው ያኔ የሙዚቃ ሰዎቻችንን ክህሎቶች በእኛው አንደበት ለዓለም መለፈፍ አቃተን!
አሁን ደግሞ “ጤፍ ዓለም አቀፍ ምግብ ልትሆን ነው…” ምናምን እየተባለ እየተቀባበልነው ነው። እንደውም “የጤፍን ዓለም አቀፍ ዝና ማግኘት ምክንያት በማድረግ ጤፍ የኩራታችን ምንጭ…” ምናምን የሚባል ፌስቲቫል እንዳይዘጋጅ ፍሩልኝማ።
እኔ የምለው…በዛ ሰሞን የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ፈረንጅ ይሁን የአገር ሰው ምናምን ሲባል ከረመና…ፈረንጅ ሆነና አረፈው ተብለን ነበር! ፈረንጁ ከመጡ በኋላ ደግሞ ሳይስማሙ ቀረ ተባለ። “ይሁና!” ከማለት ውጪ ምን ማለት ይቻላል! (“ይሁና! ይሁና!” ምናምን የሚለው ዘፈን ግጥሙ ለጊዜው እንዲመች ሆኖ ተስተካክሎ ይዘፈንልንማ!)
እናላችሁ…የፈረንጅ አሰልጣኝ ምናምን ሲባል ምን እንላለን መሰላችሁ…እውን ለኢትዮጵያ ቡድን ደረጃ የሚመጥን ሀበሻ አሰልጣኝ ጠፍቶ ነው! ደግመን ደጋግመን የምንጠይቀው ጥያቄ ነው። (ሀሳብ አለን… ‘ፈረንጅ’ አሰልጣኝ ከተቀጠረ በኋላ … ድንገት ፊፋ የባሰ ቁልቁል ካወረደን… “እኛ እኮ ችሎታው ጥሩ መስሎን ነበር…”   “ቡድናችንን ለሞሮኮ ያደርስልናል ብለን ነበር…” ምናምን አይነት ‘ቀሚስ አደናቀፈኝ’ አይነት ነገሮች ከመስማት ይሰውረንማ! ስሙኝማ…መጥተው የሄዱ የፈረንጅ አሰልጣኞች ሠላሳ ስምንት ምናምን ይሆናሉ ነው የተባለው! ‘የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፈረንጅ አሰልጣኞች’ የሚል ማህበር ለማቋቋም አይበቁም!)
ታዲያላችሁ…
ሰዉ ሁሉ ሲስማማ ሲፋቀር ሲዋደድ
ማታለል ሳይበዛ መዋሸት በገሀድ
በአፍ ቢላዋነት ሳይሆን ሰውን ማረድ
ያ ደጉ ቀን ጠፋ እኛ ሳንወድ በግድ።
ተብሎ ተዚሞ ነበር። የጠፋው ደግ ቀን ትንሳኤን ያፍጥልንማ!
በድጋሚ እንኳን ለብርሀነ ትንሳኤው አደረሳችሁ! የሰላምና የጤንነት የበዓላት ሰሞን ያድርግላችሁ!
“የምስመው እሱ ነው…” ከሚሉ ‘ስሞ አሳላፊ ሰጪዎች’ ይሰውራችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4324 times
Administrator

Latest from Administrator