Saturday, 19 April 2014 12:01

ጎሳዬ አዲስ አልበም ሊያወጣ ነው አጭር የስልክ ቃለምልልስ

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(3 votes)

እንኳን አደረሰህ …
እንኳን አብሮ አደረሰን። .ለአዲስ አድማስ የዝግጅት ክፍልና ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም በዓል እመኛለሁ።
ፆም እንዴት ነበር?
በጣም አሪፍ ነበር። አሁን ደግሞ..የህማማት ሳምንት ነው።  ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ ነው።
‹‹ጎሳዬ ዘፈን አቆመ›› የሚል ነገር ሲናፈስ ቆይቷል። እውነት ነው እንዴ?
ለስራዬ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ማህበራዊ ድረ ገፆችን አልጠቀምም። በፈረንጆች ኤፕሪል መጀመሪያ አካባቢ ነበር ይሄ ወሬ በፌስ ቡክ መናፈሱን ወዳጆቼ የነገሩኝ። በኋላ ላይ እኔም ራሴ ፌስ ቡክ ላይ አየሁት። እነዚሁ ‹‹ዘፈን አቆመ፣ ሀይማኖቱን ቀየረ›› ብለው ያስወሩ ሰዎች መልሰው ‹‹ኤፕሪል ዘ ፉል ነው›› አሉ። ችግሩ ግን “ኤፕሪል ዘ ፉልን” የማያውቅ ሰው ይኖራል። ነገሩ አድናቂዎቼን የሚያሳዝን ስለነበረ፣ በወቅቱ በጣም ተበሳጭቼ ነበር።
ወሬው ሲናፈስ የት ነበርክ? አውስትራሊያ እንደነበርክ ሲነገር ነበር…
ይኼም የተሳሳተ መረጃ ነው። በወቅቱ እዚሁ ሀገር ውስጥ ነበርኩ። ከአንድ ዓመት በፊት አውስትራሊያ የሄድኩት። መረጃዎች ለምን እንደዚህ እየተዛቡ እንደሚቀርቡ አላውቅም። ነገር ግን እኔ ለአሉባልታና ለወሬ ቦታ አልሰጥም።
ጎሳዬ “አደራ” በተሰኘውና ከመሃሙድ ር ባወጣው  ነጠላ አልበም ላይ የገባውን ቃል አልፈፀመም፤ ከሙዚቃ ሥራ ጠፍቷል የሚሉ ወገኖች አሉ …  
ከታላላቆቹ  ከምንወዳቸውና ከምናከብራቸው ድምፃውያን ..የሙያ ቅብብሎሹን በርግጥም ተቀብለናን። እኔም አደራዬን ለመወጣት እየሰራሁ ባለበት ጊዜ ነው ጭራሽ አንገት የሚያስደፋ አንዳንድ ስም የማጥፋት ዘመቻዎች የተደረጉት። እንዲያም ሆኖ በአዲስ ስራና በአዲስ መንፈስ  ከአድናቂዎቼ ጋር ለመገናኘት ሌት ተቀን እየሰራሁ ነው። ከአንጋፋ ሙዚቀኞች ጋር ነው አዲሱን አልበሜን የሰራሁት። በአሁኑ ጊዜ ቀን ከሌት እየሰራሁ ያለሁት አዲሱን አልበሜን ነው። ምን አልባትም በቅርቡ አንድ ነጠላ ዜማ ከሙሉ አልበሜ ቀንሼ ልለቅ እችላለሁ።
የዓመት በዓል ኮንሰርቶችስ ይኖሩሃል?
የመጨረሻውን ኮንሰርት የሰራሁት የዛሬ ዓመት አውስትራሊያ ነበር። በአሁኑ ሰዓትም ከካናዳ፣ አሜሪካና የተለያዩ አረብ ሃገራት ጥሪዎች እየመጡ ነው - የበዓል ኮንሰርት እንዳቀርብ። እስካሁንም ብዙ ኮንሰርቶችን ደጋግሜ ስለሰራሁና በቆየ ስራ በተደጋጋሚ መታየት ስላልፈለግሁ ነው እንጂ ጥያቄዎች ነበሩ። የዓመት በዓል ኮንሰርት ለማዘጋጀት ሁኔታ ደግሞ በአዲሱ አልበሜ ስለተጠመድኩ አልቻልኩም። አዲሱ ስራዬ ወጥቶ በህዝቡ ውስጥ በደንብ ከተደመጠ በኋላ ግን ወደ ኮንሰርት ሥራ ልገባ እችላለሁ።
በናይት ክለቦችም መስራት ትተሃል?
የትም የለሁም፤ ምክንያቱም ቀንም ተሌት የምሰራው አዲሱን አልበሜን ነው። አድናቂዎቼ በአዲሱ አልበሜ እንዲጠብቁኝ ነው የምጋብዛቸው። 

Read 2975 times