Saturday, 19 April 2014 11:48

የፋሲካ ሰሞን ሶስት ወጎች

Written by  በከበደ ደበሌ ሮቢ
Rate this item
(2 votes)

       የፋሲካ ሰሞን ነው። ልክ የዛሬ አንድ መቶ አርባ ስድስት ዓመት። በሚያዝያ ወር መጀመሪያ 1860 ዓ.ም። ሥፍራው በጎንደርና ወሎ መዋሰኛ ግድም እሚገኘው መቅደላ ተራራ።
ከአምሥት ዓመት በኋላ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተመርቆ ሥራ በጀመረ በዓመት ተመንፈቁ ሁለት መቶኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን የምናከብርላቸው ታላቁ ኢትዮጵያዊ ንጉሥ።
መላ ህይወታቸውን በጦርነት እና ሁሌም “ታጠቅ!” በማለት ያሣለፉት ዓፄ ቴዎድሮስ፤ በህይወት ዘመናቸው የመጨረሻውን ጦርነት ያደረጉት መቅደላ ተራራ ላይ ከአውሮጳ የመጡ የእንግሊዝ ወራሪዎችን ጦር በመግጠም ነው። በሠላሳ ሰባት ዓመታቸው ንጉሥ የሆኑት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ፤ ጋፋት ላይ በአውሮጳውያን ባለሙያዎች አስቀጥቅጠው ያሠሩትን ሲጳስቶቦል የተሰኘውን መድፍ በሃያ ሺህ ጎበዝ ወደ መቅደላ ተራራ በማስጎተት በጄኔራል ናፒየር የሚመራውን የእንግሊዝ ወራሪ ጦር ለመግጠም ተሰናድተዋል። ከአክሱም ሥርወ መንግሥት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በደሞዝ የሚተዳደር የሰለጠነ ሰራዊት (Professional Army) ያቋቋሙት ቴዎድሮስ፤ በመጨረሻው ሰዓት ሁሉም ከድቶአቸው ከስልሳ ሺ የሰለጠኑ ወታደሮቻቸው መሃከል አራት ሺህ ብቻ ቀርተዋቸው ነበር። ከጦርነቱ በኋላ ሊረዳቸው የመጣውም ከአምስት ልጆቻቸው ከአልጣሸ ቴዎድሮስ ቀጥሎ ሁለተኛ ልጅ የሆነው ደጃዝማች መሸሻ ቴዎድሮስ ነው።
“የመቅደላ ጦርነት የተደረገው በፋሲካ ሰሞን ሚያዝያ አምስትና ስድስት ግድም ነው። ከነዚህ ቀናት ጥቂት ቀደም ብሎ ንጉሥ ቴዎድሮስ መቅደላ ደርሶ ጦር ለሚገጥማቸው ጄነራል ናፒየር አንድ ሺህ በጎች ላኩለት …” ሲል ፅፏል። ደፋሩና አመፀኛው ደራሢ አቤ ጉበኛ።  አቤ ጉበኛ “አንድ ለእናቱ” ያለው ቴዎድሮስን ነው፤ እርሡ አንድ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ኃያል ንጉሥ … ለማለት። “ከጦርነቱ ፍጻሜ በኋላ የቴዎድሮስ ሞት ለቴዎድሮስ እረፍት ለኢትዮጵያ ሀፍረት ነበር …. ሲልም ገልጿል ደራሲው።
“ክርስቲያን መሆንህን አውቃለሁ፤ ስለዚህ የሁዳዴን ፆም ፍታና (ፈሥክና) እኔን ግጠም …” ከሚል መልዕክት ጋር አንድ ሺህ በጎች የተሠደዱለት ጄነራል ናፒየር፤ መልእክቱንም በጎቹንም ተቀብሎ የሰሜን ኢትዮጵያንና የማዕከላዊ ሰሜን ኢትዮጵያን ከፍተኛና ተራራማ የመሬት ገፆች አቆራርጦ መቅደላ ደረሰና ከጀግናው ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ቴዎድሮስ ጋር ጦር ገጠመ። ሲጳስቶቦል በቴዎድሮስ ትዕዛዝ ሁለት ጥይት ተኮሰና ሶስተኛው ላይ ፈነዳ። ሢጳስቶቦል ሲፈነዳ ቴዎድሮስ በቁጣ በነደደ መንፈሥ ተውጠው ጥርሣቸውን ሲያንቀራጭጩ፤ የጥርሣቸው መንቀራጨጭ በአካባቢው ላሉት ተዋጊዎች ይሠማ ነበር።  በመጨረሻ ቴዎድሮስ ኃይልና ቁጣ የተቀላቀለበት፣ ኢትዮጵያዊ ጀግንነት የተለኮሰበት ቃል ተናግረው፣ ሽጉጣቸውን ጠጡ። ራሳቸውን ሰው። መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ፤ የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ፤ መቅደላ መቅደላ አንቺ ክፉ ጎራ ሴቱን ሁሉ ንቆ ሢኮራ ሲኮራ ወንዱ አንቺን ወደደ ተኛ ካንቺ ጋራ፤ ገደልን እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው ማረክን እንዳይሉ ሰው የለ በጃቸው ምናሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው?...
ጄነራል ናፒየር፡- የቴዎድሮስን የመጨረሻ ሚስት እቴጌ ጥሩወርቅን እና የመጨረሻ ልጃቸውን ህፃኑን ልጅ (ልዑል) ዓለማየሁን ይዞ ወደ አውሮጳ አቀና። እቴጌ ጥሩ ወርቅ አውሮጳ ከመድረሣቸው በፊት መንገድ ላይ አረፈች። ከማረፏ በፊት… ኃያል ጀግና ንጉሥ ባሏን “እጅህን ሥጥ!” … ባለች ጊዜ ከንጉሥ ቴዎድሮስ አንደበት የወጣው የቁጣ ቃል በአእምሮዋ ጓዳ እንደሚደውል ተሥፋ አደርጋለሁ። “እጅ የለኝም የሚሰጥ” ነው ያሉት ንጉሥ ቴዎድሮስ
እጄ እሣት ነው! ኃይለኞችን እንደ ህፃን በክንዱ ጨብጦ የኖረ እንደኔ ያለ ወታደር በጠላት እጅ መያዝን ሊታገሥ አይችልም! ልጅ ዓለማየሁ ለንደን ከደረሰ በኋላ የቤተ መንግሥት ኑሮ አልተመቸውም ነበርና በወቅቱ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ወደነበረችው ህንድ ከአንድ እንግሊዛዊ የጦር መኮንን ጋር ሰደዱት። በዚያም ጤናው በመስተጓጎሉ በአሥራ ሰባት ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ለንደን ከተማ በሚገኘው የልጅ ዓለማየሁ መካነ መቃብር ላይ የአበባ ጉንጉን ያኖረ ኢትዮጵያዊ መሪ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለሥ ዜናዊ አሥረሥ (ክቡር መልከ ፀዲቅ) ነው። በመጨረሻ ጦር ቢገጥሙትም ከቴዎድሮስ የልብ ወዳጆች አብዛኞቹ እንግሊዛውያን ናቸው። በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው የቁንጅና ውድድር የጥምቀት ዕለት ወንዝ ዳር ተደርጎ አሸናፊዋን ቆንጆ ለእንግሊዛዊው ጆን ቤል የዳሩለት ንጉሥ ቴዎድሮስ ናቸው። ጆን ቤልን ኢትዮጵያዊ መጠሪያ አውጥተውና ኢትዮጵያዊ ሹመት ሰጥተው ሊቀ መኳሥ ዮሀንስ በማለት ኢትዮጵያዊ አደረጉት። በደብረ ታቦር ውጊያ ከመሞቱ በፊት ሊቀ መኳሥ ዮሀንስና ቴዎድሮስ በፈረሥ ሲሄዱ ልብሷ በላይዋ ላይ ያለቀ ሴት አገኙ። ቴዎድሮስ ከፈረሳቸው ወርደው ኪሣቸውን ቢዳብሱ አንዳች አጡ። ሊቀ መኳስን አበድረኝ አሉት። አምስት ማርትሬዛ ብር ሰጣቸው። ቴዎድሮሥ አምስቱን ማርትሬዛ ብር ለጎስቋላይቷ ሴት ሲሰጧት በጣሙን ተደሰተች። ሊቀ መኳስ ዮሀንስ በፃፈው ፅሁፍ ላይ እንዳወሳው፡- “ሥንመለሥ አምስት ማርትሬዛ ብር የነበረውን መቶ ማርትሬዛ ብር አድርገው ሰጡኝ” ብሎአል።
*   *   *
የፋሲካ ሰሞን፡- የትንሳኤ ሰሞን ማለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለበትና ከሞት በተነሳበት ሰሞን።
ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ኢየሱስ ክርስቶስ ከመስቀሉ ጥቂት ቀደም ብሎ ከእስር ቤት የተፈታ ሰው ነው በርባን። ህዝቡ በወቅቱ አይሁድን ሲገዛ ለነበረው ለሮማዊው ንጉሥ ጴላጦስ፣ “በርባን የተባለውን ወንበዴ ፍታልንና በምትኩ ኢየሱስን ሥቀለው!” በማለቱ ነው በርባን የተፈታው። በመፅሀፍ ቅዱስ ላይ በዝርዝር ያልተፃፈውን የበርባንን ሁለንታ “በርባን” በሚል ርዕስ መፅሀፍ የፃፈለት ደራሲ ከፍተኛውን ዓለም አቀፍ ሽልማት (Nobel Prize) ተሸልሟል። ይህንን መፅሀፍ ወደ አማርኛ የተረጎመው ኢትዮጵያዊው የፅሁፍ ጥበብ ሊቅ ዓቢይ ደምሤ ነው።
በርባን ከእሥር ቤት ከተፈታ በኋላ “ይሄ በእኔ ምትክ የተሰቀለው ሰው ማነው? እንዴት ያለ ሰው ነው?” ብሎ አርብ ዕለት ከሰዓት በሥቲያ በጎለጎታ ጌተሰማኒ ቀራንዮ መስቀል ላይ ኢየሱስ ክርስቶሥ በሁለት ወንበዴዎች መሃል ሆኖ ሲሰቀል ተደብቆ ተመልክቷል። ይህን ባየ ጊዜ መንፈሡ በጥልቅ ፍቅር ተመታ። ያ እናትና አባቱን የገደለ፣ ባገኘበት ቦታ ሴቶችን እያገላበጠ የሚዳራ፣ በውንብድና አገር ምድሩን የሚያምስ “ከፈሡ የተጣላ ሠው”፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሰቀል ባየ ጊዜ አእምሮው ተለወጠ። ስለዚህ በእርሱ ምትክ ስለተሰቀለው ሰው ሲጠይቅ “ከሶስት ቀን በኋላ ከሞት ይነሣል!” … ብለው ነገሩት። በአንዲት ሴት ወዳጁ ቤት ጭምት ሆኖ ጣሪያ ጣሪያውን እያየ እሁድ ሌሊት እስኪደርስ ተጠባበቀ። እሁድ ሌሊት ለቅዳሜ አጥቢያ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ግድም ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት በተነሳበት ወቅት በርባን ተደብቆ መካነ መቃብሩ አጠገብ ተገኝቶ ነበር። መፅሀፍ ቅዱስ ላይ እንደምናየው ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሣቱን፣ መቃብሩ ባዶ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየችው ማርያም መቅደላዊት ነች። እንዲሁም ደግሞ ሽቶ እጣን ይዘው የመካነ መቃብሩን ቅድሥና ሲንከባከቡ የነበሩ ጥቂት የሚወድዱት ሴቶች። ይሁንና በርባን በዚያ ነበር። የበርባን ህይወት ጨርሶ የተለወጠው ደግሞ ከዚህ በኋላ ነው።
በርባን በመጨረሻ ህይወቱ ያለፈው ሮም ውስጥ እነ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስና ሌሎች የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች በእምነታቸው ሳቢያ በስቅላት ሲቀጡ፤ እርሱም በመሰቀሉ ነው።
በኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያት ከእስራትና ከመሰቀል የዳነው (ድኖ የኖረው) ከብዙ ዓመታት በኋላ በኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያት (ኢየሱስን በማመኑ) በስቅላት ተቀጣ። የጥንት ሮማውያን ጴጥሮሥን ዘቅዝቀው ሠቀሉት። ሌሎች የኢየሡሥ ክርስቶስን ተከታዮች ደግሞ መለመላቸውን በቁማቸው ሠቀሏቸው።
*   *   *
በ1888 ዓ.ም ከአንድ መቶ አስራ ስምንት ዓመታት በፊት የመቀሌ፣ የአምባላጌና የአድዋ ጦርነቶች የተደረጉት በሁዳዴ ፆም ውስጥ ነው። ጀግና የኢትዮጵያ ገበሬ ሰራዊት እህል ባፉ ሳይዞር እየፆመ ይዋጋል። በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ግብፃዊው አቡነ ማቲዎስ አቡኑ ከንጉሡና ከንግሥቲቱ ጋር ሆነው ወደ አድዋ ከሚተምመው የኢትዮጵያ ገበሬ ሰራዊት ጋር ናቸው። እስከ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ድረስ የጥንት የኢትዮጵያ ጳጳሳት ተቀብተው የሚመጡት ከግብፅ አገር አሌክሳንድርያ ከተማ ነበር።
አቡነ ማቲዎስ፤ “አሁን ጊዜው የጦርነት ስለሆነ ሰራዊቱን ይፍቱትና እየበላ እየጠጣ ይዋጋ .. ቢባሉ አሻፈረኝ አሉ። ቢባሉ ቢሰሩ በአሻፈረኝ ባይነታቸው የፀኑ ሆኑ። አልፈታም …አሉ። ስለዚህ የኢትዮጵያ የገበሬ ሰራዊት እየፆመ ለመዋጋት ተገደደ” የሚለን ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” በተሰኘ መፅሀፉ ላይ ነው።
ሰላምዎ ይብዛ! በፍቅር!
Soli-Deo-Gloria!
(ክብር ለእርሱ ይሁን!)

Read 5940 times