Monday, 14 April 2014 10:28

አንድ ሺ አንድ የሳዑዲ አረቢያ ልዑላን ለአንዲት ዙፋን ይሻማሉ

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(18 votes)

     አብዱልአዚዝ ሳዑድ፣ የዛሬ 90 አመት ግድም ነው፣ ተቀናቃኝ የጎሳ መሪዎችንና የጦር አበጋዞችን በማንበርከክ ዙፋን ላይ የወጡት። የሳዑዲ ቤተሰብ፣ ገናና የንጉሥ ቤተሰብ በመሆን የታሪክ ጉዞውን የጀመረው ያኔ ነው። አገሪቱ በራሳቸው ቤተሰብ ስም “ሳዑዲ አረቢያ” ተብላ እንድትጠራ የወሰኑት አብዱልአዚዝ ሳዑድ፣ ለ20 አመታት ገዝተዋል። ዘኢኮኖሚስት መፅሄት በዚህ ሳምንት እትሙ፣ እንደገለፀው አብደልአዚዝ ብዙ ወራሾችን ትተው ነው የሞቱት - 36 ልጆችን።
ወራሽ ሲበዛ ምን እንደሚፈጠር ይታወቃል። ቤተመንግስትና አገር ይረበሻል። በእርግጥ አብዱልአዚዝ ከመሞታቸው በፊት የበኩር ልጃቸውን በአልጋ ወራሽነት አዘጋጅተውታል። በቀብራቸው ማግስት፣ የስልጣን ሽኩቻ መፈጠሩ ግን አልቀረም። በተለይ በሁለቱ ታላላቅ ልጆች (በሳዑድ እና በፋይሳል) መካከል የነበረው ትንቅንቅ ቀላል አይደለም። ታላቅዬው ወንድም “ሳዑድ አብደልአዚዝ ሳዑድ” ቀደም ሲል አልጋ ወራሽ ተብለው መሰየማቸው ጠቀማቸው። በስንት መከራ የመጀመሪያውን ዙር ትግል አሸንፈው ዙፋኑን ለመቆጣጠር በቅተዋል። ታዲያ፤ ታናሽ ወንድማቸው “ፋይሳል አብዱልአዚዝ ሳዑድ”፣ እጅ ሰጥተው አልተቀመጡም። ተቀናቃኝነታቸው ለአንድም ቀን አልረገበም። እንዲያውም ባሰበት። የሁለቱ ፀብ ለአምስት አመታት ሲባባስ ቆይቶም ነው፤ በ1950 ዓ.ም የፈነዳው። በየራሳቸው ጎራ ተከታይና አጃቢ አደራጅተው፤ የሹም ሽረታቸውን ተፋጠጡ። ሁለተኛው ዙር ግብግብ ልንለው እንችላለን።
ልዑል ፋይሳል፣ ሙሉ ለሙሉ ታላቅ ወንድማቸውን ከስልጣን ፈንቅለው ለመጣል ባይችሉም፤ በዚህ የሁለተኛው ዙር ትንቅንቅ በከፊል ቀንቷቸዋል። “ንጉሡ አገሪቱን በወጉ እያስተዳደሩ አይደለም፤ ገንዘብ አያያዝም አይችሉበትም” በማለት ከፍተኛ ዘመቻ ያካሄዱት ልዑል ፋይሳል፤ ዙፋኑን ቢወርሱ ደስታቸው ነበር። ያ አልሆነም። ነገር ግን፤ በከፊል የንጉሡን ስልጣን ሸርሽረው ለመውሰድ በቅተዋል። በሽኩቻው ልዑል ፋይሳል የበላይነት እንዳገኙ በግልፅ የታየው፤ የአገሪቱ መሳፍንትና የሃይማኖት መሪዎች ተሰብስበው በወቅቱ ያወጧቸው ሁለት አዋጆች በይፋ ከተነገሩ በኋላ ነው። አንደኛ፤ ቀደም ሲል ፅህፈት ቤት ሲባሉ የነበሩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ተብለው እንዲሰየሙ ተወሰነ። ከዚህም ጋር ተያይዞ፤ ልዑል ፋይሳል የአገሪቱ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል ተባለ። ሁለተኛ፤ ንጉሡ፣ ከጥግ እስከ ጥግ ጠቅልለው የያዙትን ስልጣን፣ ለሌሎች ማጋራትና ማካፈል እንዳለባቸው በመሳፍንቱና በሃይማኖት መሪዎች ተሰብስበው ወስነዋል። የመንግስት ስራዎችን በበላይነትና በብቸኝነት የመምራት ስልጣን የነበራቸው ንጉሥ ሳዑድ፣ ስልጣናቸውን ለማን እንዲያጋሩ ይሆን የተወሰነባቸው? ምን ይጠየቃል! ለወንድማቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ፋይሳል ነዋ!
የንጉሡ ገደብ የለሽ “የፈላጭ ቆራጭ” ስልጣን፣ በአዲስ የስልጣን ክፍፍል ተቀየረ ተብሎ ታወጀ። አዲስ ዘመን ተጀመረ ተብሎ ተበሰረ። በእርግጥ፤ ንጉሡ ማንኛውንም ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ የመሻር ስልጣን ይኖራቸዋል። ነገር ግን “ውሳኔ የመሻር” ስልጣንና፣ “ውሳኔ የማስተላለፍ” ስልጣን ይለያያሉ። ውሳኔዎችን የማስተላለፍና የመንግስት ስራዎችን የመምራት ስልጣን፣ ለጠ.ሚ. ፋይሳል ተሰጥቷል። የወንድማማቾቹ ሁለተኛ ዙር ትንቅንቅ፣ በዚሁ አበቃ። ሽኩቻቸው ግን አልቆመም። ወዲያውኑ ወደ ሶስተኛ ዙር ትግል ተሸጋግረዋል። ስልጣን የተቀነሰባቸው ንጉሥ፤ እንደገና ሁሉንም ስልጣን ጠቅልለው ለመውሰድ ሁለት አመት አልፈጀባቸውም። ጠቅላይ ሚኒስትር ፋይሳል ከስልጣን ለቀቁ።
የቤተሰብና የዘመድ ፀብ ቶሎ አይበርድም። ፋይሳል በቃ ተሸነፍኩ ብለው በዚያው አልቀሩም። ለአራት አመታት ቲፎዞ ሲያሰባስቡና ዝግጅት ሲያካሂዱ የቆዩት ፋይሳል፤ ከቀድሞው የላቀ ጉልበት በመያዝ ከሃያሉ ንጉሥ ጋር አራተኛውን የስልጣን ትንቅንቅ ገጠሙ። ይሄኛው ዙር፣ የሹም ሽረት ብቻ ሳይሆን የሞት ሽረት ግብግብ ነው ቢባል ይሻላል። ፋይሳል አልተቻሉም። የቀድሞ ስልጣናቸውን ከንጉሡ በመንጠቅ ብቻም አልተመለሱም። አልጋ ወራሽ ሆነው እንዲሰየሙ ቢደረግም፤ አላረካቸውም። በጥቂት ወራት ውስጥ፣ በ1957 ዓ.ም አልጋ ወራሽ ፋይሳል፣ በሽኩቻው ተሳክቶላቸው ወንድማቸውን ከስልጣን በማባረር ዙፋኑን ተቆጣጠሩ። በንጉሥና በጠቅላይ ሚኒስትር መካከል የስልጣን ክፍፍል እንዲኖር ለአመታት ሲከራከሩ የነበሩት ፋይሳል፣ ሃሳባቸውን ለመቀየር ጊዜ አልፈጀባቸው። ዘውድ እንደደፉ፣ ወዲያውኑ ሁሉንም ስልጣን ለራሳቸው ጠቅልለው ወሰዱት። ስልጣን የሚቀናቀን ጠቅላይ ሚኒስትር የሚባል ነገር እንዲኖር ስላልፈለጉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትርነትን ለራሴ ደርቤ ይዤዋለሁ ብለው ገቢ አደረጉት።
ከዚያ በኋላ፣ ንጉሥ ፋይሳል እንደተለመደው ሌሎች የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ለወንድሞቻቸው አከፋፍለዋል። ከሚኒስትርነት ቦታ በተጨማሪ፣ የጦር ሃይል፣ የክብር ዘብ እና የስለላ ድርጅቶችን በሃላፊነት የሚመሩትም የንጉሡ ወንድሞች ናቸው። አገሬውን በሙሉ በቤተሰባችን ቁጥጥር ውስጥ ገባ ብለው በደስታ የሚፈነጥዙ ከመሰለን ተሳስተናል። በተቃራኒው፤ የሚኒስትርነትና የሃላፊነት ቦታዎችን በተቆጣጠሩ ወንድማማቾች መሃል የስልጣን ሽኩቻው ይበልጥ ይጧጧፋል። በእናት የሚገናኙ ወንድማማቾችና በእናት የሚለያዩ ወንድማማቾች እንዴት እንደሚተያዩ አስቡት።
እንዲያም ሆኖ፣ ፋይሳል ብዙም አልተቸገሩም። ያኔ የነዳጅ ዋጋ እያሻቀበ በነበረት ጊዜ፣ ንጉስ ፋይሳል ተመቻቸው። አገሬውን በድጎማ አንበሸብሸዋለሁ ከማለታቸውም በተጨማሪ፣ ከወንድማቸው ስልጣን ለመንጠቅ ባካሄዱት ረዥም የትግል ወቅት ከጎናቸው ሆነው ላገዟቸው የሃይማኖት መሪዎች ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ እየሰጡ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ወንበራቸውን አደላድለዋል። ንጉሥ ፋይሰል የተደላደለ ዙፋን ላይ አስር አመት ከደፈኑ በኋላ ነው፤ ቤተመንግስታቸው ውስጥ እንደወትሮው ዘመድ አዝማድ የንጉሥ ቤተሰቦችን እያነጋገሩ ሳለ የተገደሉት። የደበቀውን ሽጉጥ እዚያው ከፊት ለፊታቸው አውጥቶ የገደላቸው፣ የወንድማቸው ልጅ ነው - ለዚያውም በሳቸው ስም ፋይሳል ተብሎ የተሰየመ ወጣት ልዑል። በበርካታ ጥይቶች የቆሰሉት አዛውንቱ ፋይሳል፣ ወዲያውኑ  ወደ ሆስፒታል ተወስደው በሐኪሞች ሲከበቡ፤ ወጣቱ ፋይሳል ደግሞ ወደ እስር ቤት ተወስዶ መርማሪዎች በጥያቄ እያፋጠጡት ነበር።  አዛውንቱ ፋይሳል፤ የመዳን እድል አልነበራቸውም። ብዙም ሳይቆዩ ነው የሞቱት። ወጣቱ ፋይሳልም፣ ለረዥም ጊዜ በሕይወት አልቆየም። በእርግጥ ድርጊቱን የፈፀመው፣ ብዙዎች እንደጠረጠሩት መንግስት ለመገልበጥና ዙፋን ለመውረስ ታስቦ በተቀነባበረ ሴራ አማካኝነት አይደለም። ለመርማሪዎች በሰጠው ቃል ፤ “ንጉሡ የሃይማኖት አክራሪነትን እያበረታቱ አገሪቱን ወደ መጥፎ አቅጣጫ እየወሰዷት ነው” በሚል እምነት ግድያውን እንደፈፀመ ገልጿል።
የሆነ ሆኖ፤ ሕይወት ትቀጠላለች። በፋይሳል ምትክ ታናሽ ወንድም ልዑል ካሊድ ዘውድ ወርሰው ነገሡ። ካሊድ፣ እንደሌሎቹ ወንድማማቾች፣ የስልጣን ሽኩቻን የማዘውተር ዝንባሌና ፍላጎት አልነበራቸውም። እንዲያውም፤ በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ በክብር እንግድነት ከመገኘት በስተቀር፤ ከቤተመንግስትና ከስልጣን ያን ያህልም ቅርርብ ዝምድና አልፈጠሩም። ምናልባት ከቤተመንግስትና ከስልጣን ሹክቻ ጋር የተራራቁት፤ ብዙውን ጊዜ ጤንነት ስለማይሰማቸው ሊሆን ይችላል። ከአንድም ሁለት ሶስቴ በጠና ታመዋል። በልብ ህመም ተይዘው፣ ከሞት የተረፉት በቀዶ ህክምና ነው። ይሄ ሁሉ፣ ስልጣን ከመውረስ አላገዳቸውም። በቃ! በሕይወት ካሉት ወንድማማቾች ሁሉ በእድሜ ታላቅ ስለሆኑ ተራ ደርሷቸው ነገሡ። ለካ፤ ንጉሥ መሆንና ሥልጣን መያዝ፣ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ንጉሥ ካሊድ፣ አብዛኛውን ስልጣን ለታናሽ ወንድማቸው ለልዑል ፉዓድ በውክልና የሰጧቸው በወራት ውስጥ ነው። ህመም የተደራረበባቸው ንጉሥ ካሊድ፣ ብዙም ጤና ሳያገኙ ሰኔ 1974 ዓ.ም እንዳረፉ፤ ወዲያው ዙፋኑ ላይ የተተኩትም ልዑል ፉዓድ ናቸው።
ፉዓድ ቀድሞውንም በጠቅላይ ሚኒስትርነት አብዛኛውን ስልጣን ስለተቆጣጠሩ፤ የነገሡ ጊዜ ብዙም የተለወጠ ነገር አልነበረም። አራቱ ወንድማማቾች በየተራ እንደየእድሜያቸው ቅደም ተከተል ስልጣን ላይ የወጡት፤ አባታቸው አብዱልአዚዝ አስቀድመው በተናገሩት ትዕዛዝ መሰረት ነው። ታላቅ ወንድም እያለ፣ ታናሽ ወንድም ንጉሥ እንዳይሆን ተናዝዘው ነው የሞቱት። ተራ ደርሷቸው ስልጣን የያዙት ፉዓድ፣ የክብር ዘብ አዛዥ የነበሩ ታናሽ ወንድማቸው ልዑል አብዱላህ አልጋ ወራሽና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ መሰየም ነበረባቸው - የአባታቸውን ኑዛዜ ላለመሻር እንጂ ከልዑል አብዱላህ ጋር ብዙ አይዋደዱም ነበር።
ንጉሥ ፉዓድ በ60ኛ እድሜያቸው ዋዜማ ዙፋን ላይ ለመውጣት መብቃታቸው፤ እንደ ትልቅ እድል ይቆጠርላቸዋል። ለምን ቢባል፤ በእድሜ ከፉዓድ የሚበልጡ ወንድማማቾች ሁሉ በየተራ ቢነግሱ ኖሮ፤ ፉዓድ እንዲያ በፍጥነት ተራ ባልደረሰባቸው ነበር። ነገር ግን እድል ያላለላቸው ልጆች፣ በመሃል በተለያየ ምክንያት ይሞታሉ። ለዚህም ነው ፉዓድ 11ኛ ልጅ ሆነው ሳለ፤ ስልጣን በመያዝ ግን አራተኛ ናቸው። በዚያ ላይ ከሃያ አመታት በላይ በስልጣን ላይ ለመቆየት ችለዋል - እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ። ያው ፉዓድ ሲሞቱ፤ አምስተኛው ተረኛ ልዑል አብዱላህ ስልጣን ተረክበው፤ ይሄው እስከ አሁን  ዙፋን ላይ ናቸው።
“ወንድማማቾች ዙፋኑን ይፈራረቁበታል!” ብሎ መናገር ቢቻልም፤ በዚያው መጠን ንግሥና አፋፍ ላይ ደርሰው በአካል ለማጣጣም ሳይታደሉ ያመለጣቸው “እድለቢስ” ልዑላን ጥቂት አይደሉም። ለምሳሌ፤ የአብዱላህ ታናሽ ወንድም፣ “ልዑል ሱልጣን”ን መጥቀስ ይቻላል። በእርግጥ፣ ልዑል ሱልጣን፣ ያን ያህልም ስልጣን አነሳቸው የሚባልላቸው አይደሉም። ለአርባ አመታት ያህል በመከላከያ ሚኒስትርነት የቆዩ ናቸው። ከዚያም በተጨማሪ ንጉሥ አብዱላህን ለመተካት፣ አልጋ ወራሽ ተብለው ተሰይመዋል። ግን አልጋ ሳይወርሱ ነው ከዛሬ ከሶስት አመት በፊት የሞቱት። በአገሪቱ ውስጥ ቁልፍ የስልጣን ቦታ ነው በሚባለው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርነት ላይ ከሰላሳ አመታት በላይ የቆዩት ልዑል ናይፍ ደግሞ፣ አልጋ ወራሽ ተብለው በተሰየሙ በአመታቸው ሕይወታቸው አልፏል። በሳቸው ምትክ አልጋ ወራሽ እንዲሆኑ የተደረጉት ልዑል ሳልማን ናቸው።
ነገር ግን የልዑል ሳልማን እጣ ፋንታም ተመሳሳይ ሳይሆን አይቀርም። ንጉሥ ለመሆን ተስፋ ያላቸው አይመስልም። እድሜያቸው ገፍቷል። 78 ዓመታቸውን ደፍነዋል። በዚያ ላይ፣ ከእድሜ ጋር አብሮ የሚከሰት የመርሳት ህመም ሳያጠቃቸው አይቀርም ተብሎ ይገመታል። ለዚህም ይመስላል፤ ንጉሥ አብዱላህ ከሳምንት በፊት፣ በሳዑዲ አረቢያ እስካሁን ታይቶ የማይታወቅ አዲስ አዋጅ ያስነገሩት።
የአዋጁ አዲስነት ምኑ ላይ ነው? አንደኛ፤ ተተኪ አልጋ ወራሽ ለመሰየም አዋጅ ማስነገር የተለመደ ነገር ነው። አዲሱ አዋጅ ከዚህ ይለያል። የተተኪ ተተኪ አልጋ ወራሽ ለመሰየም የወጣ አዋጅ ነው። በሳዑዲ አረቢያ የዘጠና አመት ታሪክ ውስጥ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የተተኪ ተተኪ አልጋ ወራሽ በአዋጅ የተሰየመው። ሁለተኛ፤ እስከዛሬ በነበረው አሰራር፣ ከወንድማማቾቹ መሃል በእድሜ ታላቅ የሆነው ነበር በአልጋ ወራሽነት እየተሰየመ የሚነግሰው። የአሁኑ ግን፤ የእድሜ ቅደም ተከተልን ያልተከተለ ነው። ያለ ምክንያት አይደለም።
ከ36ቱ ወንድማማቾች መካከል 15ቱ አሁንም በሕይወት አሉ። ነገር ግን ብዙዎቹ እንደ ልዑል ሳልማን እድሜያቸው ስለገፋ፣ ንጉሥ የመሆን እድላቸው አነስተኛ ነው። በሕይወት ካሉት ወንድማማቾች መካከል ከእንግዲህ ንጉስ የመሆን እድል የሚኖራቸው የሁሉም ታናሽ የሆኑት የ60 ዓመቱ ልዑል ሙቅሪን ናቸው። ለበርካታ አመታት የአገሪቱን የስለላ ድርጅት በሃላፊነት የመሩት ልዑል ሙቅሪን፣ የእድሜ ቅደም ተከተል ሳይጠብቁ በአልጋ ወራሽነት እንዲሰየሙ ተደርጓል። መቼ እንደሚነግሱ  ባይታወቅም፤ ከግማሽ ምዕተዓመት በላይ ያስቆጠረው የወንድማማቾች የስልጣን ሽኩቻና የዘውድ ቅብብል ወደ ማብቂያው የተቃረበ ይመስላል። እውነታው ግን ከዚህ ይለያል።
ሽኩቻውና ቅብብሉ ወደ ማብቂያው የተቃረበ ይመስላል እንጂ፤ “ገና ምኑ ተጀመረ?” ቢባል ይሻላል። ንጉሥ ለመሆን፣ ወይም ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ ወፍራም ስልጣን ለማግኘት የሚጠባበቁ “ልዑላን”፣ ዛሬ እንደድሮው 36 ብቻ አይደሉም። የአብዱልአዚዝ ልጆች፣ የስልጣን ዘመናቸው ሲያበቃ፤ በቦታው ከአንድ ሺ በላይ የልጅ ልጆች ተተክተዋል። የስልጣን ሽኩቻው፤ በሺህ ልዑላን መካከል ሆኗል።
 የንግሥና ቅብብሎሹ ደግሞ፣ ለሺህ ልዑላን ሊዳረስ አይችልም። ተራው የደረሳቸው ልዑላን፤ በአብዛኛው ከአስር አመት በላይ ነው በንግሥና የሚቆዩት። የአምስት ወንድማማቾች ዘመነ መንግስት ሲደማመር፤ ከ60 ዓመት በላይ ሆኗል። በዚሁ ጊዜ ውስጥ ቀሪዎቹ ወንድማማቾች ብቻ ሳይሆኑ፣ ልጆቻቸውም በእድሜ ገፍተው እያረጁ ነው። ይህም ብቻ አይደለም። የልጅ ልጆች በብዛት መጥተዋል። በጥቂት አመታት ውስጥ፣ የሳዑዲ ልዑላን ቁጥር ወደ ስምንት ሺ ገደማ እንደሚደርስ የጠቀሰው ዘኢኮኖሚስት፤ አንዳንዶቹ ልዑላን ተራ የመጠበቅ ትዕግስታቸው እየተሟጠጠ ሊሆን እንደሚችል ይገልፃል። በሌላ አነጋገር፤ በማንኛውም ቀን ምን እንደሚፈጠር አይታወቅም፡፡
በጥንታዊ የጐሳና የዘር ትስስር ላይ ተሞርኩዞ የተጀመረው የአብዱልአዚዝ ስርወመንግስት፤ ገና በጥዋቱ በቤተሰብ አባላት ወይም በወንድማማቾች ሽኩቻ መወሳሰቡ ሳያንስ፤ ዛሬ  መፍትሔ ወደሌለው የእልፍ ልዑላን የስልጣን ሽሚያ እያመራ ነው፡፡
አንድ በሉ፡፡ የሳዑዲ ንጉሳዊ ቤተሰብ ሌላ ምርኩዝ ሃይማኖት ነው፡፡ ለምን ቢባል፤ በአክራሪነት ዝንባሌ ከሚጠቀሰው የዋሃቢያ አስተምህሮ ጐን በአለኝታነት በመሰለፍ ስልጣን ላይ ለመውጣትና ለመደላደል ችሏል፡፡
ነገር ግን፤ የስልጣን መደላደል ሲሆንላቸው የነበረው የሃይማኖት ነገር፤ ቀስ በቀስ የአደጋ ምንጭ እየሆነባቸው ነው፡፡ ሳዑዲ እነ ኦሳማ ቢን ላደኖችን የምትፈለፍል አገር ሆናለችና፡፡ ሁለት በሉ፡፡
የሳዑዲ ንጉሳዊ መንግስት ሦስተኛው መተማመኛ፤ በመንግስት ቁጥጥር ውስጥ የገባው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ነው፡፡ ነገር ግን በነዳጅ ሃብት ቀዳሚ የሆነችው ሳዑዲ አረቢያ ዛሬ ዛሬ ለዜጐቿ ተስማሚ አልሆነችም፡፡ መንግስት ገንዘብ እያፈሰሰ ድጐማ ማከፋፈል አላቃተውም፡፡ ምን ዋጋ አለው? ተመጽዋችነት፤ በራስ ጥረት ራስን ችሎ እንደመኖር አያረካም፡፡ ለዚህም ነው የሳዑዱ ስራ አጥ ወጣቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቅሬታቸው እየተባባሰ ወደ ቀውስ እያመራ የመጣው፡፡ ሦስት አትሉም፡፡
በአጠቃላይ፤ የሳዑዲ መንግስት እንደመተማመኛ የያዛቸው ሦስት ነገሮች (የጐሳ፣ የሃይማኖትና የድጐማ አቅጣጫዎች) ለአደጋ የሚያጋልጡ የቀውስ ምንጮች መሆናቸው በገሃድ እየታየ ነው፡፡ እነዚህ ሦስት የቀውስ አቅጣጫዎች ሳዑዲን ብቻ የሚያጠቁ ችግር አይደሉም፡፡ አለምን ከዳር ዳር ከሚያናጉ ሦስት የዘመናችን የቀውስ ምንጮች መካከል ሁለቱ የጐሳና የብሔር ጉዳይ እና የሃይማኖት አክራሪነትና የሽብር አቅጣጫዎች መሆናቸውን ባለፈው ሳምንት ጽሑፌ ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ - የብዙ አገሮችን መረጃ በመጠቃቀስ። ከድጐማ ጋር ወደተያያዘው ሦስተኛ የቀውስ ምንጭ ለመሸጋገር ነው የሳዑዲዎቹን ታሪክ በአጭሩ የተረኩላችሁ፡፡ 

Read 6666 times