Monday, 14 April 2014 09:47

የዶክተር ጌታቸው “የሕልም መኪና”

Written by  ከባየህ ኃይሉ ተሠማ bayehhailu@gmail.com
Rate this item
(3 votes)

       በ1966 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተነሳው ሕዝባዊ አመጽ ከዳር እስከዳር እንደሰደድ እሣት በድንገት ተዛምቶ፣ አሮጌውን የዘውድ መንበር ከሥሩ ክፉኛ ነቀነቀው፡፡ ሕዝባዊ ዐመጹ በመንግሥት ዘንድ የፈጠረው እንቅጥቅጥ (Shock) በጣም ብርቱ ከመሆኑ የተነሳ፣ በወርሀ የካቲት የጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድንና የካቢኔያቸውን ስንብት አስከተለ፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ልጅ እንዳልካቸው መኮንን የሰየሙት ካቢኔ፣ አዲስ የሥራ ፕሮግራም ነድፎ በተቃውሞ በተወጠረ የፖለቲካ መድረክ ላይ ጉዞውን ጀመረ፡፡ የአዲሱ ካቢኔ አባላት አሮጌውን የአገዛዝ መንገድ ለመከተል ባለመወሰናቸው ወይም ባለመፍቀዳቸው የተነሳ በአንዳንድ ዘርፎች መንግሥት የነበረው ጽኑ ቁጥጥር እንዲላላ ምክንያት ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ ቀንበራቸው ከላላላቸው እሥረኞች አንዱ የመጻሕፍ ነጻነት ነበር፡፡
በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ መንግስት ያስተዳድራቸው የነበሩት ዕለታዊዎቹ “አዲስ ዘመን” እና “Ethiopian Herald” ጋዜጣ እንዲሁም ሳምንታዊው “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ” ጋዜጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ከውስጥ ገጾቻቸው “የሕዝብ ነጻ አስተያየት መድረክ” ከፈቱ። አዳዲሶቹ የጋዜጣ መድረኮች የታፈነ ብሶት የሚተነፈስባቸው፣ አዲሱ ለውጥ የሚወደስባቸው፣ መጪው ዘመን ይዞት የሚመጣው ተስፋና በረከት ወይም እልቂትና ውድመት የሚተነበይባቸው ዓይነቶች የሀሳብ መለዋወጪያ መሣሪያዎች ሆኑ፡፡
ነጻነትን በጥቂቱ መለማመድ ይበልጥ ነጻነት መሻትን ማስከተሉ አይቀርም፡፡ እነዚህ አዳዲስ ነጻ መድረኮች የተከፈቱ ሰሞን ይቀርቡ የነበሩት ጽሁፎች ያተኮሩት የየካቲትን ድል በማወደስ፣ ስልጣኑን የለቀቀውን ካቢኔ በመጠኑ በመተቸት ቢሆንም እየዋለ እያደረ መሬት ላራሹን የመሳሰሉ አንኳር ጥያቄዎች አንግበው አደባባይ ወጡ። ጊዜው ፈጣንና ተለዋዋጭ ከመሆኑ የተነሳ ፋታ ያልተገኘበት ሆነ እንጂ ይህ መድረክ የተከፈተበት ወቅት የሰከነ ቢሆን ኖሮ፣ በእነዚህ ጋዜጦች ላይ በነጻነት የሚቀርቡት የበሰሉ ጽሁፎች፣ መንግሥት አገዛዙን ለማስተካከል በተጠቀመበት ነበር፡፡
በዚህ ዘመን ከቀረቡት መጣጥፎች መካከል፤ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበሩት፤ ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ መጋቢት 18 ቀን 1966 ዓ.ም ታትሞ በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ “ሹመት” በሚል ርዕስ ያቀረቡት ጽሁፍ በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ እጅግ የተለየ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ደራሲው በዚያን ጊዜ የዘውድ ሥርዓት ወደማይቀረው ፍጻሜ በለውጥ ኃይሎች በፍጥነት በመገፋት ላይ መሆኑን አጢነው፣ መጪውን ጊዜ ለመቀበል መደረግ ከሚገባቸው የአስተሳሰብ ለውጦች መካከል አንዱ ስለ “ሹመት” ያለውን የተዛባ አመለካከት መቀየር ነው ሲሉ በጽሑፋቸው አትተዋል፡፡
ዶክተር ጌታቸው በዚህ ጽሁፋቸው ስለ ሹመ ት በሿሚው፣ በተሿሚውና በህዝቡ ዘንድ የነበረው ጎታች አስተያየት በአዲስ ለውጥ እና ከወደፊቱ ብሩህ ተስፋ አንጻር መቃኘት አለበት ብለዋል፡፡ “… አንድ ሰው በመሾሙ ምክንያት ክብር ከተጨመረለት፣ የተሾመባቸውም ሰዎች ከሰገዱለት፤ በተጨማሪም በሹመት የተሰጠውን ሥራ ለማከናወን የሚያደርገውን ማስተናበርና ማስተባበር እንደማዘዝ ከቆጠረው፤ ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር አርአያ ነውና ተሹሞ ጌታ አድራጊ ፈጣሪ ለመሆን ይጥራል። “ኢታምልክ ባዕደ አምላክ ዘእንበሌየ፤ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አታምልክ” የሚለውም ስለሚሰማው እሱ ተሸሮ በሱ ምትክ ሌላ ሰው ተሹሞ ሲሰገድለት ሊያይ አይፈልግም…” በማለት ስለ ሹመት ያለው ነባር አስተያየት መቀየር አለበት ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው በሰፊው ፅፈዋል፡፡
ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ የአማርኛና የግዕዝ ቋንቋዎች ሊቅ እንደመሆናቸው፣ ይህ ስለ ሹመት የሚያትተው ጽሁፋቸው፤ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው በተዋበ አማርኛ የቀረበና ለዛ ያልተለየው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ የአንድ መጣጥፍ መደምደሚያ እንደሆነ በሚታወቀው የመጨረሻ አንቀጽ ላይ ዶክተር ጌታቸው አዲስ ሀሳብ በማንሳት ነው ጽሁፋቸውን የሚያቆሙት፡፡ ይህ አቀራረብ ለተለመደው የጽሁፍ ደንብ እንግዳ ቢሆንም ይሁነኝ ተብሎ በደራሲው የተሰናዳ ዘዴ መሆኑን ለመረዳት የሚቻለው የአንቀጹን ፍሬ ሀሳብ ስንረዳ ነው፡፡ ይህ በመጣጥፍ የመጨረሻ አንቀጽ ላይ የቀረበው አዲስ ሀሳብ፤ “ሹመት” ተብሎ በቀረበው ሰፊ መጣጥፍ በዘዴ ተሸፍኖ የቀረበ ቅመም ነው፡፡
ዶክተር ጌታቸው በመጣጥፋቸው የመጨረሻ አንቀጽ ያቀረቡት ሀሳብ እንዲህ ይነበባል፡- “… በበኩሌ ለውጡ ህልም ነው የሚመስለኝ። በህልሜም ቆማ የኖረች አንዲት መኪና ትታየኛለች። ሁለት ጓደኞች አንዱ ከኋላ ተቀምጦ አንዱ መሪዋን ይዞ ይጫወታሉ፡፡ አንድ ሶስተኛው ሰው በቁጣ መጥቶ፣ የሁለቱን ቦታ ያለዋውጥና መኪናዋን ወደፊት ይገፋታል፡፡ ወዲያው መኪናዋ የቆመችበትን ቦታ ለቅቃ ትንቀሳቀሳለች፡፡ አሁን መኪናዋ የምትሄደው ሞተሯ ስለተነሳ ይሁን ወይም ያ ሶስተኛው ሰው ገፍቷት ወደ ጉዳዩ ስለተመለሰ ይሁን አላውቅም። ሞተሯ አልተነሳ እንደሆን ተመልሳ ትቆማለች፡፡ ቁርጡ የሚታወቀው ከስድስት ወር በኋላ ነው፡፡ ሶስተኛው ሰው የመንጃ ፈቃድ ስለሌለው፣ እሱም ቢሆን እንዲነዳ የፈለገ የለም፡፡ ቁጣው ካልበረደለት ግን ተለማምዶባት የመንጃ ፈቃድ ያወጣባት ይሆናል፡፡ ከምትቆም ይሻላል ማለት ነው እንጂ የወታደር አነዳድ ስም የወጣለት ነው፡፡
ብዙኃኑ የተማረው ክፍል በአገሩ በተነሳው የለውጥ ንፋስ ተወስዶ ያለፈውን እና የአሁኑን ከማየት በስተቀር መጪውን መገመት ባልቻለበት በዚያ ተለዋዋጭ ጊዜ ያለፈውንና የአሁኑን በቅጡ መርምረው ወደፊቱን መመልከት የቻሉ በጣም ጥቂቶች መሆናቸው እሙን ነው፡፡ ከነዚህ ጥቂቶች መካከል ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ ጎልተው ይታያሉ። እኒህ ታላቅ ሰው በዚህ “ህልማቸው” ጥርት አድርገው የተመለከቱትም ብሩህ የሆነውን እና ሕዝብ የጮኸለትን የአዲስ ተስፋ ሕያውነት ሳይሆን በጨቋኝ ወታደራዊ አገዛዝ የሚታጀበውን መራሩን የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ነበር፡፡
ሕልም እንደፈቺው ነው ቢባልም በዚህ “ህልም” የቆመችው “መኪና” ኢትዮጵያ ስትሆን መኪናዋ ውስጥ ተቀምጠው የሚጫወቱትን ሁለት ጓደኛሞች ሳይጠሩትና ሳይጋብዙት በቁጣ ቦታቸውን እንዲለዋወጡ አድርጎ “መኪናዋን” ወደፊት የሚገፋት ሶስተኛው ሰው፣ ያው ወታደር ነው - የወታደር አገዛዝ አምሳያ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ወታደር ከቁጣ በቀር “የመንጃ ፈቃድ” (ልምድ፣ ችሎታና ብቃት) የለውም፡፡ የሚሄድበትን ሥፍራም የሚያውቅ አይመስልም፡፡ ተሳፋሪዎቹም ሹፌርነቱን አልወደዱትም - ራሱም ጭምር፡፡ የሕልሙ ባለቤት ይህ ወታደር “በመኪናዋ” ተለማምዶባት መንጃ ፈቃድ ያወጣባት ይሆናል ብለዋል፣ ለማጅ የያዘው “መኪና” እንዴት እንደሚንገላታ ለሚያውቅ፣ በእርግጥ እውነታው መራር ሐቅ ነው፡፡
ብዙዎች የአፍሪካ አገሮች ከነጻነት በኋላ እየደጋገመ የደቆሳቸው ጨቋኝ ወታደራዊ አገዛዝ በኢትዮጵያም አመቺ ጊዜ አግኝቶ ሥልጣን ሊነጥቅ እያደባ መሆኑን ዶክተር ጌታቸው ከማንም አስቀድመው ተገንዝበውታል፡፡ ደራሲው ይህንን “ሕልም“ በተመለከቱበት ጊዜ በኢትየጵያ እዚህም እዚያም ብልጭ ድርግም ይል የነበረው የተበታተነ አመጽ፣ በዘውድ መንግሥት ላይ ተነስቶ ደሞዝ ከማስጨመሩ በቀር፣ ይህ ነው የሚባል የተደራጀ ወታደራዊ እንቅስቃሴ አልነበረም። ደርግ የሚቋቋመው ሰኔ 20 ቀን 1966 ዓ.ም ስለሆነ “ህልሙ” ራሱ ደርግን በሶስት ወር ያህል ይቀድመዋል፡፡ እንዲያውም ዶክተር ጌታቸው በህልማቸው “ቁርጡ የሚታወቀው ከስድስት ወር በኋላ ነው” እንዳሉት እውነትም ከስድስት ወር በኋላ ወታደራዊ “አነዳድ” በሙሉ ኃይሉና ጉልበቱ በመላዋ ኢትዮጵያ ላይ ሰፍኖ ለአስራ ሰባት ዓመታት ይቆያል፡፡
ይህ ጽሑፍ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ከታተመ ከ34 ዓመት በኋላ በወጣው ግለ ታሪካቸው (በግል ሕይወቴ ካየሁትና ከታዘብኩት አንዳፍታ ላውጋችሁ፤ 2000 ዓ.ም፤ ኮሌጅቪል፣ ሚኒሶታ) ዶክተር ጌታቸው ይህንን መጣጥፍ ለማቅረብ ምን እንዳነሳሳቸው እንዲህ ገልጸውት ነበር:-
“… እሱ (ልጅ እንዳልካቸው መኮንን) ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ሳለ፤ ያደቡ ወታደሮች አጠገቡ አሉ። አገሪቱን የሚያስተዳድራት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሁን ሌላ ኃይል ሳይታወቅ፤ ይመሻል ይነጋል። ወታደሮቹ ሥልጣኑን ለሲቪሎች እንደማይሰጡ ስጠረጥር ደነገጥኩ፤ ሰው ለውጥ ለውጥ ማለቱን እንጂ፤ ለውጡን ወታደሮች ሊይዙት እንደሚችሉ፣ ቢይዙትም የሚያሰጋ መሆኑን የሚያመለክት ድምጽ አይሰማም፡፡ … ወታደሮች በሌላ አገር ያደረጉትን ሳስብ ፈራሁ፤ ግን እኔ ማን ነኝ? ማንም ብሆን ለአገሬ መፍራት ብሔራዊ ግዴታዬ ነው… በዚህ ጊዜ እኔም ተሽቀዳድሜ “ሹመት” በሚል ርዕስ ፍርሃቴን ለሕዝብና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አሰማሁ” ብለዋል፡፡
ይህን የዶክተር ጌታቸውን ፍርሃት ሊወድቅ ጥቂት ወራት የቀሩት የዘውድ መንግሥትም ሆነ እንዲወድቅ የሚገፉት አብዮተኞች በቅጡ ተመልክተው አልተጠነቀቁበት ኖሮ፣ ያ ብዙ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ሕዝባዊና ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተጠልፎ፣ አገሪቱ አይታ በማታውቀው ጨቋኝና ጨካኝ ወታደራዊ አገዛዝ ሥር ወደቀች፡፡
የሐቀኛ ምሁራን ሚና ከሰፊው ሕዝብ ጋር በስሜት ጎርፍ አብሮ መጉረፍ ሳይሆን ያለፈውን በቅጡ ተመልክቶ ዛሬን ዳስሶ መጪውን መተንበይና ሕዝብን ማንቃት መሆን እንደሚገባው የዶክተር ጌታቸው ጽሑፍ አበክሮ ያስረዳል፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮት የተነሳበትን 40ኛ ዓመት ስንዘክር፤ በሀገራቸው ፍትሕና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን የታገሉትን ሠላማዊ ዐርበኞች በማሰብ ብቻ ሳይሆን ይህ ብሩህ ተስፋ እንዳይላሽቅና እንዳይሰረቅ አስቀድመው ነቅተው ያስጠነቀቁትን እንደ ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ ያሉትን አርቆ አስተዋይ ታላላቅ ምሁራን በማስታወስ ጭምር መሆን አለበት፡፡

Read 2425 times