Monday, 14 April 2014 09:34

አስገራሚ የምግብ ስያሜዎች

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

የህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን ሶስተኛ ዓመት ክብረበዓል ለመታደም ከበርካታ የሙያ አጋሮቼ ጋር ጉዞ ወደ ግድቡ ተጀምሯል፡፡
ምንም እንኳን አብዛኛው ጋዜጠኛ ጉዞው በአሶሳ በኩል እንዲሆንለት ሃሳብ ቢያቀርብም ከመብራት ሃይል ተመድበው የመጡት አስተባባሪዎች እጅ ጥምዘዛ ግን ጉዟችን በጐጃም መንገድ እንዲሆን አደረገን፡፡ ጉዟችን ቀጥሎ ምሳ ደብረ ማርቆስ ሆነ፡፡ ተወላጆቿ “ዴንማርክ” እያሉ የሚጠሯት የቀድሞዋ “መንቆረር” የአሁኗ ደብረማርቆስ ስንደርስ አዳርም እዚያው መሆኑን አወቅን፡፡ ታዲያ የአዳር እና የመመገቢያ ቦታም የሚመረጥልን በእነዚሁ አስተባባሪዎች ነበር፡፡
ምሳ ሐበሻ ምግብ ቤት እንድንመገብ ቢነገርም እኔና ሌሎች ጓደኞቼ አልጋ ከያዝንበት “ዴሉክስ ገስት ሀውስ” ጀርባ ወደሚገኘው ፓራዳይዝ ሬስቶራንት አመራን፡፡ ምሳ ለማዘዝም የምግብ ዝርዝር የለበትን ሜኑ አነሳን፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር አስገራሚውን የምግብ ስም ዝርዝር ያየሁት፡፡ ከሁሉም በላይ ያስገረሙኝን ምግቦች ስም ዝርዝር እና የስሞቹን ምክንያት ለማወቅ ጉጉቴ ጨመረ፡፡ ህዳሴ ሽሮ፣ ኑሮ በዘዴ፣ ባትኖርም ትኖራለህ፣ ፍቅር ሽሮ፣ አፋታሽኝ፣ ማይ ቾይዝ እያለ ይቀጥላል… የምግቡ ዝርዝር፡፡
እኛ ርቦን ስለነበር ለሶስት ሰው አሳምሮ ይበቃል የተባለለትን “ማይ ቾይዝ” የተሰኘ ጣፋጭ የፆም ምግብ አዘዝን፡፡ ተመግበን ከጨረስን በኋላ በሚገርም ቅልጥፍናና ትህትና ተፍ ተፍ እያለ ያስተናገደንን ወጣት ቢኒያምን ጠርቼ ስለምግቦቹ አሰያየም እንዲያወጋን ጠየቅሁት፡፡ ወጣት ቢኒያም ጌታቸው እድገቱ አዲስ አበባ በተለምዶ ዳትሰን ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ ሰሜን ሆቴል ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ በአስተናጋጅነት መስራቱን ይናገራል፡፡ “ህዳሴ ሽሮ”
እንደ ቢኒያም ገለፃ፣ ህዳሴ ሽሮ በፓራዳይዝ ሆቴል ስፔሻል ተብሎ ከሚጠራው “ማይ ቾይዝ” ቀጥሎ ተወዳጅ ምግብ ነው፡፡ ከህዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ መጣል በኋላ ህዝቡ ስለ ህዳሴው ግድብ በስፋት ያወራ በነበረበት ጊዜ ስም የወጣለት ልዩ ጣዕም ያለው ምግብ እንደሆነ አጫውቶኛል። በፓራዳይዝ ሬስቶራንት ብቻ ይሰራል የተባለው “ህዳሴ ሽሮ”፤ አሰራሩ እና አቀራረቡ የህዳሴውን ግድብ ዲዛይን የተከተለ መሆኑ ይበልጥ አስገራሚ ያደርገዋል፡፡ በትሪ የተዘረጋ እንጀራ ላይ ዙሪያውን ሽሮ ይደረግበታል፡፡ ከዚያም መሀሉ ህልበት (ስልጆ/የተሰኘው የፆም ምግብ ማባያ ይጨመራል፡፡ እንደወጣቱ ገለፃ፤ ሽሮው ዙሪያውን መሆኑ የግድቡን ዙሪያ የሚያሳይ ሲሆን፤ ነጩ ህልበት(ስልጆ) ውሃውን የሚያመላክት ነው፡፡ በተጨማሪም የአበሻ ጐመን፣ ቃሪያ፣ የተቀቀለ ድንችና ሰላጣ ዙሪያውን ለአይነት የሚጨመርበት ሲሆን፤ በምግቡ አራት ቦታዎች ላይ አራት ኮለኖች አሉት፡፡ ይህም የግድቡን አራት ማዕዘናት ለማሳየት ነው፡፡
አራቱ የምግቡ ኮለኖች በቲማቲም በቅርፅ የተሰሩ ናቸው፡፡ ይህ ምግብ ጣዕም ብቻ ሳይሆን ጥበብም የተሞላበት በመሆኑ በተመጋቢዎች ተመራጭ እንደሆነ ቢኒያም ይናገራል፡፡ “በየወቅቱ በሚከሰቱ ሁነቶች ብዙ የልብስ፣ የምግብና መሰል ቁሳቁሶች ስያሜ ይወጣል” የሚለው ወጣቱ አስተናጋጅ፣ በምሳሌነትም ከኢትዮጵያ ሚሌኒየም ጋር ተያይዞ የወጡ የቡቲክ፣ የምግብ ቤት፣ የውበት ሳሎኖችና ሌሎች ድርጅቶችን ጠቅሷል፡፡ ኦባማ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሆነው ሲመረጡ፣ አንዳንድ የንግድ ሱቆች በስማቸው መሰየማቸውን ያስታወሰው አስተናጋጁ፤ ከነዚህም መካከል ባህርዳር ከተማ ውስጥ የሚገኘውን “ኦባማ ካፌ”ን በምሳሌነት አንስቷል፡፡

“ባትኖርም ትኖራለህ”
በሜኑው ላይ ትኩረትን ከሚስቡት የምግብ አይነቶች አንዱ “ባትኖርም ትኖራለህ” የተሰኘው የምግብ አይነት ነው፡፡ ለምን ስያሜው እንደተሰጠው የጠየቅሁት ቢኒያም፤ “እንደምታውቂው እዚህ አገር ላይ በጣም ሀብታም እንዳለ ሁሉ በጣም ድሀ የሆነም በገፍ አለ፡፡ ይሁን እንጂ የምግቡ አይነት ቢለያይም ሀብታሙም ድሀውም ሳይበሉ አያድሩም” ይላል፡፡ “ባትኖርም ትኖራለህ” የተሰኘውም ምግብ ከድንች ቅቅልና ከተወቀጠ ተልባ የሚሰራ ሲሆን ዋጋው በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የሚዘጋጅ እንደሆነ ገልፆ፤ ይህ ስያሜ “ባይኖርህም ትኖራለህ፤ ሳትበላ አታድርም” ለማለት እንደተሰየመ አጫውቶኛል፡፡

“ኑሮ በዘዴ”
ይህ የምግብ ዓይነትም ኢኮኖሚን መሰረት ያደረገ ስያሜ የተሰጠው መሆኑን አስተናጋጁ ይናገራል። ምግቡ በአገልግል ተዘጋጅቶ እንደ በየአይነቱ የሚቀርብ ሲሆን ዋጋው በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ። ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች የሚያዘወትሩት ነው። ዋጋው ዝቅተኛ ቢሆንም ግን ጥራቱን የጠበቀ በመሆኑ ተወዳጅም ነው፡፡ “ሰው ኑሮው እየከበደው ስለመጣ እነዚህን ምግቦች በመመገብ ኑሮውን በዘዴ ለማለፍ ይጠቀምበታል” ብሏል - አስተናጋጁ፡፡

“ማይ ቾይዝ”
“ማይ ቾይዝ” ለእኔና ለሁለት ጓደኞቼ ቀርቦልን ለሶስት ያጣጣምነው ግሩም ጣዕም ያለው ምግብ ነው፡፡ የሚሰራው በአካባቢው ከሚገኙ እንደ የአበሻ ጐመን፣ ድንች ቲማቲምና መሰል አትክልቶች ነው። በጣም ጣፋጭና በከተማዋ በፓራዳይዝ ሆቴልና በሆቴሉ ሼፍ ብቻ የሚዘጋጅ መሆኑን ቢኒያም ጌታቸው ያስረዳል፡፡ “እስካሁን ከመጣችሁ ጀምሮ ለዚህ ሁሉ ሰው ሳቀርብ የነበረው ማይ ቾይዝንና ህዳሴ ሽሮን ነው” የሚለው አስተናጋጁ፤ ምግቡ ጣፋጭና መጠኑም በርከት ያለ በመሆኑ፣ በአብዛኛው ሁለትና ሶስት ሆነው የሚመጡ ቤተሰቦችና ጓደኛሞች እንደሚያዘወትሩት አጫውቶናል፡፡

“ፍቅር ሽሮ”
በአብዛኛው የምግብ ገበታ ላይ በመቅረብ እንደ ሽሮ እድለኛ የለም ባይ ነው፤ አስተናጋጁ። ይሁን እንጂ ሁልጊዜ አንድ አይነት ሽሮ ሲቀርብ አሰልቺ ይሆናል፤ ሽሮን ከአሰልቺነት አውጥቶ በፍቅር የሚበላና የሚወደድ ለማድረግ የተዘየደ ዘዴ እንዳለ አጫውቶኛል፡፡ ሽሮው በተዘረጋው እንጀራ ላይ ዳር እስከዳር ከተቀባ በኋላ፣ የተቀላቀለ እና የተቀቀለ አትክልት በሽሮው ላይ ይጨመርበታል። በመቀጠልም በአራት ማዕዘን ቅርፅ እንጀራው ይታጠፍና ይቀርባል፡፡ ጣዕሙም እጅግ ግሩም ይሆናል፡፡ “ይሄን ሽሮ ከአሰልቺነት ተላቃ በፍቅር የምትበላ ትሆናለች” ይላል - ቢኒያም፡፡ በነገራችን ላይ በጥር ወር አካባቢ ለጥምቀት ፌስቲቫል ጐንደር ከተማ በነበርኩበት ጊዜ፣ አፄ በካፋ ሆቴል ውስጥ “ሽሮ በአትክልት” በሚል ስያሜ አንድ ምግብ መመገቤን አስታውሳለሁ፡፡ አሁን ስሟን ቀይራ “ፍቅር ሽሮ” ተሰኝታ በደብረማርቆስ ተገናኘን እንጂ።

“አፋታሽኝ”
አንድ አባወራ ሁሌ ፓራዳይዝ ሆቴል እየመጣ ራት ይመገብ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ሁሌ ከሚስቱ ጋር ይጋጫል፡፡ ምክንያቱም ቤቱ ውስጥ ራት አይመገብም፡፡ ሚስት ክፉኛ ስጋትና ጥርጣሬ ውስጧን ይንጠዋል፡፡ “ባሌ እራት የሚበላበትና የሚያመሽበት ሌላ ቤት መስርቷል” የሚል ስጋትና ጥርጣሬ፡፡ ነገሩ ሲደጋገምባት ሚስት የፍቺ ጥያቄ ታቀርባለች፡፡ ባል ግን ከዚህ ምግብ መላቀቅ አልቻለም፡፡ ሚስት ባል የነገራትን አምና መቀበል ባለመቻሏ ትዳሯን በፍቺ አፈረሰች፡፡ ባልም ብቻውን ቀረ፡፡ ሚስቱን በፈታ በነጋታው ማታ፣ መሀል ላይ ቆሞ “ማነህ አስተናጋጅ፤ ያቺን አፋታሽኝን አምጣልኝ” በማለት ከሚስቱ ያፋታውን ምግብ ያዛል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የምግቡ ስም “አፋታሽኝ” ሆኖ መቀጠሉን አስተናጋጁ አውግቶኛል፡፡ “አፋታሽኝ” ከካሮት፣ ከድብልቅ ሰላጣ፣ በጣም ካልበሰለ ድንችና ሌሎች አትክልቶች የሚዘጋጅ ሲሆን ጣዕሙ አሪፍና ዋጋውም ኪስን የማይጐዳ በመሆኑ በብዙ ተመጋቢዎች ይመረጣል፡፡ በአካባቢው ባሉ ሌሎች ሆቴሎች አስገራሚ ስም ያላቸው ምግቦች ይኖሩ እንደሆነ የጠየቅሁት ቢኒያም፤ ማይ ቾይዝ፣ ህዳሴ ሽሮና አፋታሽኝ በሌሎች የትም ሆቴሎች እንደሌሉ ገልፆ አንድ ሆቴል “አገልግል” የተሰኘውንና በሁሉም ሆቴል የሚገኘውን ምግብ “ማሰሮ” በማለት ስሙን ለመቀየር ሞክረዋል፤ ሆኖም በይዘቱ ላይ ለውጥ አላመጡም ሲል አጫውቶኛል፡፡ 

Read 4580 times