Monday, 14 April 2014 09:30

“ለህዳሴው ግድብ ድጋፋችንን እንቀጥላለን”

Written by  ኤልሳቤት ዕቁባይ
Rate this item
(5 votes)


የኢትዮጵያን እና የሱዳንን ግንኙነት እንዴት ይገልፁታል?
የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ማብራሪያ የሚፈልግ ጉዳይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም እየኖርነው ያለ ጉዳይ ነው፡፡ የሁለቱ አገራት ህዝቦች እጅግ የተቀራረበ ታሪክ እና ባህል ያላቸው ናቸው፡፡ ይብራራ ከተባለም ግንኙነቱ ረጅም ዘመናትን የተሻገረ፣ጥልቅ የሆነ እና ብዙ አቅጣጫዎች ያሉት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የሚታየው በፖለቲካዊው ጐኑ ቢሆንም ግንኙነቱ ከዛ ያለፈ ነው፡፡ በታሪክ ትስስር አለ፣በጂኦግራፊ ጐረቤታሞች ነን፣ብዙ የምንጋራቸው ነገሮች አሉን፡፡ በባህል ካየነው የምንኖረው በአንድ ክፍለ አካባቢ ነው፡፡ ወንዝ እንጋራለን፣ በአንድ ሰማይ ስር እየኖርን ነው፡፡ እነዚህ የጋራ የሆኑ ነገሮች ባህሪያችን ላይ ተመሳሳይ እንድንሆን የሚያደርግ ተጽእኖ ይኖራቸዋል፡፡ የአካባቢውን ታሪክ የሚያጠኑ ሱዳን እና ኢትዮጵያ የሚጋሩት የኋላ ታሪክ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ህዝቦቹ የተሳሰሩ ናቸው፡፡
አንቺ እና ልጄን እንደሁለት አገር ዜጋ መለየት ይከብዳል፡፡ አሁን እዚህ ብትሆን በደንብ ትረጂው ነበር፡፡ በቅርቡ አፍሪካ ህብረት ሊፍት ውስጥ አንዲት ኢትዮጵያዊት በአማርኛ አናገረችኝ። ይቅርታ አማርኛ አልችልም ስላት፣ሱዳናዊ ነህ አለችኝ፡፡ በፖለቲካው ካየን ብዙ የምንጋራቸው ጉዳዮች አሉን፡፡ በተለይ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ ጊዜ ጀምሮ ጥሩ ግንኙነቶች አሉ። ፕሬዚዳንት አልበሽር ወደ ኢትዮጵያ ተደጋጋሚ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም አልበሽር ካርቱም ከሚያሳልፉት ጊዜ ይልቅ አዲስ አበባ የሚያሳልፉት ይበዛል ይላሉ፡፡ የሚቀጥለው ሳምንትም የጣና ፎረም ላይ ለመካፈል ይመጣሉ። የፖለቲካ ግንኙነቶቹ በጠንካራ መሠረት ላይ ይገኛሉ፡፡ ስምምነቶችን በተግባር ለማዋል እየሠራን ነው፡፡
ይህ ሁሉ ዝምድና ቢኖርም ቪዛ ግዴታ ነው፡፡ እዚህ ላይ ምን ታስቧል?
ምን ችግር አለ?
ለምሳሌ ኬኒያና ኢትዮጵያ ቪዛ አይጠይቁም----
ጥያቄሽ ሌላ ጥያቄ በውስጡ ከሌለው በስተቀር አሁንም እጅግ የተቀራረበ ዝምድና እና ጉርብትና አለን፡፡ የቪዛ ጉዳይ ከአገር አገር ይለያያል፡፡ ከድንበር ድንበር ይለያያል፡፡ የኢትዮጵያና የሱዳንን ካየን 800 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ድንበር እንጋራለን፡፡ ድንበሩ እስከአሁን አልተለየም፡፡ እንዲያም ሆኖ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማፋጠን በቅርቡም ስምምነት ተደርጓል፡፡ ሁለቱም አገሮች ከልብ እየሠሩ ነው፡፡
በምን መልክ ?
ቀስ በቀስ ቪዛ ማንሳት ላይ እንመጣለን። ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ለያዙ እና ለመንግስት ሃላፊዎች የቪዛ ጥያቄ የለም፡፡ ቢዝነስ ፓስፖርት ያላቸውም ካርቱም ሲደርሱ ቪዛ ያገኛሉ። በአጠቃላይ ቪዛ ማንሳት የሚለውን ግን ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር እየተማከርንበት ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ፍላጐቱ አለ፡፡
ሁለቱን አገሮች በአውራ ጎዳና  ለማገናኘት የታሰበውስ ምን ላይ ደርሷል?
ከገዳሪፍ፣ ጋላባት የሚመጣው መንገድ አልቋል። የሁለቱን አገራት ህዝቦች እያገለገለ ነው፡፡ በየቀኑ ከካርቱም አዲስ አበባ የሚመጡ አውቶቡሶች አሉ። አሶሳ ኩርሙክ በኢትዮጵያ በኩል ስራው አልቋል። ከሱዳን በኩል ከደማዚን ኩርሙክ የሚያገናኘው እየተሠራ ነው፡፡ በቅርቡ ተገናኝቶ ስራ ይጀምራል። ሌላው ከሁመራ የሚያገናኘውም ሲያልቅ በተለያዩ ሶስት አቅጫዎች ኢትዮጵያና ሱዳን በአውራ ጐዳና ይገናኛሉ፡፡ በሶስት የተለያዩ መንገዶች የሚገናኙ የአፍሪካ አገሮች የሉም፡፡ ሱዳንና ኢትዮጵያ ይህን ያሟላሉ፡፡ ይህ ደግሞ የሰዎችን ህይወት የሚለውጥ ነው፡፡ መንገዶቹ ሲገናኙ ኢትዮጵያ ፖርት ሱዳንን መጠቀም በምትችልበት ሁኔታ ላይ ለመስራት እያሰብን ነው፡፡
የሁለቱ አገሮች ድንበር ያልተሠመረ ነው፡፡ ለማስመር እየተሠራ ያለው ስራ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?
ቅድም እንዳልኩት ኢትዮጵያ እና ሱዳን ረጅም ድንበር ተጋሪዎች ናቸው፡፡ የሱዳን አራት ግዛቶች እና የኢትዮጵያ ሶስት አካባቢዎች የዚህ ድንበር አካል ናቸው፡፡ የማካለሉ ጉዳይ በሁለቱ አገሮች መሀል ረጅም ጊዜ የወሰደ ነው፡፡ የጋራ የድንበር ኮሚሽኑ ላይ ሁለቱም አገሮች በብዙዎቹ ጉዳዮች ላይ ተስማምተው ቦታዎች ለማካለል ዝግጁ ናቸው። ያላለቁና ድርድር እና ውይይት የሚፈልጉ የተወሰኑ ቦታዎች አሉ፡፡ ኮሚቴው ስራውን አላጠናቀቀም፣ ፊርማም አልተፈረመም፡፡
በሂደቱ ላይ ያሉ ችግሮች ምንድን ናቸው?
ፖለቲካዊ ሳይሆን ቴክኒካዊ ችግሮች አሉ፡፡
ቴክኒካዊ ችግሮች ምን ማለት ነው?
ጉዳዩ ሁለት ገጽታዎች አሉት፡፡ አንዱ ቲዎሪ ነው፡፡ ሌላው ፖለቲካዊ ነው፡፡ የቴክኒክ  ቡድኑ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የሠራቸውን ስራዎች ቦታው ላይ ወርዶ ለመስራት ሲሞክር፣አንደኛ የቦታዎቹ አቀማመጥ እጅግ አስቸጋሪ ነው፤ ተራራ ይወጣል፣ ሸለቆ ይገባል --- የመሳሰሉት፡፡ ሁለተኛ ቴክኒካሊ ጉዳዩ በጣም ጥንቃቄ የሚፈልግ ነው፡፡ በመርህ ደረጃ ሁለቱም ተስማምተዋል - ለፖለቲካ፣ ለፀጥታ እና ለሌሎች ጉዳዮች፡፡ ስምምነት ባልተደረገባቸው ቦታዎች ላይ አሁንም ውይይቱና ድርድሩ አላለቀም። ሁለቱም ፍቃደኞች ስለሆኑ ይፈታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በተያያዘ በሱዳንም ሆነ በኢትዮጵያ በኩል ያሉ ጉዳዮችን ማስተናገዱ ፈታኝ ነው፡፡ ስራው ገንዘብ ይፈልጋል፡፡ ገንዘብም ችግር ነው፡፡ ነገር ግን ከሁለታችን ውጪ ማንም እንዳይገባ ተስማምተናል፡፡ ሁለቱም አገሮች ፈተናውን ለመወጣት እየሞከሩ ነው፡፡  ከየትኛውም ወገን ማንንም ሳይጎዱ ጉዳዩን ለመቋጨት ፍላጎት አላቸው፡፡
ኢትዮጵያ ለሱዳን መሬት ቆርሳ ሰጥታለች የሚሉ ወገኖች  አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
ለምን ትሰጣለች?
እርስዎ ምን ይላሉ ?
ለምን? ለምን? ኢትዮጵያ ለምን መሬት ትሰጠናለች? በመጀመሪያ ከኢትዮጵያም ሆነ ከሌላ አገር መሬት አንፈልግም፡፡ ጠቅላይ ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተጠይቀው ሲመልሱም ሰምቻለሁ፡፡ እኔም ኢትዮጵያ ለሱዳን መሬት ሰጥታለች የሚለውን አጥብቄ እቃወማለሁ፡፡ በተወራው መሰረት አሁን ሱዳን ሁለት ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር ሆናለች ማለት ነው፡፡ የሱዳን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ አንዱ አላማ መልካም ጉርብትና ነው፡፡ ያለምንም ጣልቃ ገብነት ከጎረቤቶቻችን ጋር መኖር ነው፡፡ በፊትም ሆነ አሁን አንድ ኢንች መሬት አይደለም ከኢትዮጵያ ከሌሎች ጎረቤቶቻችንም አንፈልግም፡፡ ሱዳን የኢትዮጵያን መሬት ፈላጊ አይደለችም፡፡ የረጅም ጊዜ የፖለቲካ ስትራቴጂያችን ከድንበር ባሻገር ማሰብ ነው፡፡ ሁለቱን ህዝቦች ያለምንም የድንበር ልዩነት አንድ ማድረግ ነው። ምንም ነገር በሌለበት ሁኔታ ላይ ይህን የሚናገሩ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ያላስደሰታቸው ናቸው፡፡ በጋራ እንሰራለን ያልነው ስራ ስለማያስደስታቸው ነው፡፡ ይህንን ንግግር ኢትዮጵያዊያንም ሆኑ ሱዳናዊያን ትክክል ነው ብለው እንዳይቀበሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት የናይል ጉዳይ ዋና አጀንዳ ሆኗል። ካርቱም ነጩ ናይል እና አባይ የሚገናኙባት ቦታ ነች። ምን ትርጉም አለው?
ሁለቱ የሚገናኙበት ቦታ ላይ ብዙ ማለት ይቻላል። ለኔ ሁለቱ ናይሎች የሚገናኙባት ቦታ የሱዳንን አንድነት ታሳየኛለች፡፡ የሱዳንን ህዝብ ይወክላል፡፡ ረጅም መንገድ ተጉዘው ብዙ ጎሳዎችን አልፈው ካርቱም ላይ አንድ ይሆናሉ፡፡ በቅርቡም የተካሄደው የሱዳን ስብሰባ የሱዳንን አንድነት የሚያሳይ ነው፡፡ ሌላው የተፋሰሱ አገሮች አንድነት መገለጫም ነው፡፡ አባይ ከኢትዮጵያ ተነስቶ ብዙ ቦታዎችንና  ህዝቦችን አልፎ ካርቱም ይመጣል። ነጩ ናይልም ከመነሻው ብዙ ኪሎሜትሮችን አቋርጦ፣ብዙ ህዝቦችን አልፎ ካርቱም ይመጣና ይገናኛሉ፡፡ በቅርቡ የናይል ቤዚን ኢኒሽየቲቭ ስብሰባ ላይ ህፃናት “አባይ አባይ” እያሉ ሲዘፍኑ ስሰማ ልቤን በጣም ነካኝ፡፡ የዚያ ዘፈን ትርጉም ብዙ ነው። ሁለቱ ናይሎች ካርቱም ላይ ሲቀላቀሉ ለዘመናት ኖረዋል፡፡ እኛ አሁን ለማድረግ የምንሞክረው ያንን ነው፡፡ እኛ ወረቀት ላይ የናይል ተፋሰስ ስምምነት፣ የምስራቅ ናይል ትብብር የመሳሰሉትን እንላለን። ሁለቱ ናይሎች ግን ካርቱም ላይ ተዋህደው ለዘመናት ፈሰዋል፡፡ አሁንም ይፈሳሉ፡፡ እንዲያውም ይህ የተፈጥሮ ውህደት ያነቃን ይመስለኛል፡፡ እዚህና እዚያ ከምትጨቃጨቁ ለምን  አብራችሁ አትጠጡም የሚል ይመስለኛል፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ የሱዳን አቋም ምንድን ነው ?
አታውቂውም?
ከእርስዎ ልስማው----
በመጀመሪያ የግድቡን ጠቀሜታ እንድናውቅ ላደረጉን ለቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ ምስጋና ይግባ፡፡ ከዛ በኋላ ሶስቱ አገሮች ባቋቋሙት ኮሚቴ ውስጥ በመሳተፋችን ግድቡ ኢትዮጵያ ላይ ቢሠራም ተጠቃሚዎቹ ግብጽ እና ሱዳን መሆናቸውን አውቀናል፡፡ ይህ ለአለምም ይጠቅማል። የግድቡ ፍሬ የሚታወቀው ከኢትዮጵያ ውጪ ላለነው ጭምር ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ ግድቡ ኬፕታውን እና መካከለኛው ምስራቅ ድረስ ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ ይህ በግድቡ እንድንተማመን አድርጐናል፡፡  ግድቡ እውን እስኪሆን ድረስ ድጋፋችንን እንቀጥላለን፡፡
ለግድቡ ከግንባታ ጋር የተያያዙ ተሽከርካሪዎች ድጋፍ እንዳረጋችሁ ይነገራል፡፡ እውነት ነው?
  እሱን ፈልጊና ድረሽበት፣ እኛ ግን ድጋፋችንን እንቀጥላለን፡፡ ድጋፋችንን ከመጀመሪያውም ገልፀናል፡፡
የቅኝ ግዛት ውሎቹን  ሱዳን በአሁኑ ወቅት  እንዴት ታያቸዋለች?
የውሎቹ ፈራሚዎች ነን፡፡ የ1929 በቅኝ ግዛት ዘመን፣የ1959ኙን ከነፃነት በኋላ ፈርመናል፡፡ በነዚህ ውሎች አሁንም እንገዛለን፡፡ ነገር ግን አሁን አዲሱን የናይል ቤዚን ስምምነት ለመቀላቀል እያሰብን ነው፡፡
የ1929 እና 1959 የቅኝ ግዛት ውሎችን አብዛኞቹ የተፋሰሱ አገሮች በኢንቴቤ ስምምነት ተክተውታል እኮ?
እሱን ነው የምልሽ፡፡ ለመፈረም እያሰብንበት ነው፡፡
ከኢትዮጵያ የምታገኙት የኃይል አቅርቦት እንዴት ነው?
አንደኛ ይህ ፕሮጀክት የአፍሪካ ህብረት ስትራቴጂ እቅድ አገሮችን በኤሌክትሪክ ኃይል ማስተሳሰር የሚለውን የሚተገብር ነው፡፡ በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ላይም ጥሩ ነገር የጨመረ ነው። ሁለቱ አገሮች ከተፈራረሟቸውና ከተገበሯቸው ፕሮጀክቶች በማሳያነት የሚቀመጥ ነው፡፡ ወደ ጥያቄሽ ስመጣ የኃይል መቆራረጥ ያለ ቢሆንም አንድ መቶ ሜጋ ዋት እየተጠቀምን ነው፡፡
አቢዬ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ቆይታን እንዴት ይገመግሙታል?
በመጀመሪያ በተልዕኮ ላይ እያሉ ህይወታቸውን ላጡ አባላት ቤተሰቦች መፅናናትን እንመኛለን። ይህ መስዋዕትነት በሱዳናዊያን ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡ አቢዬ ሄጄ አይቻቸዋለሁ፣ የሚጠበቅባቸውን በአግባቡ እየተወጡ ነው፡፡ ሁለት ቀን አብሬያቸው ነበርኩ፡፡ አንዳንድ መኮንኖችን አነጋግሬያለሁ፡፡ የሱዳን ህዝብ እነሱን በመምረጡ ፀፀት እንዳይሰማው ያደረጉ ናቸው፡፡

Read 3540 times