Monday, 14 April 2014 09:23

በግብረሰዶም አስከፊነት ላይ ዛሬ ውይይት ይደረጋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

በአዲስ አበባ ወጣቶች ፎረም እና በማኅበረ ወይንዬ አቡነ ተክለሃይማኖት አስተባባሪነት ግብረ  ሰዶማዊነትን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ሚያዚያ 18 በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን በዛሬው እለትም በግብረ ሰዶም አስከፊነት ላይ ውይይት ይደረጋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል አዳራሽ ለግማሽ ቀን በሚካሄደው ህዝባዊ ውይይት ላይ የመንግስት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ጋዜጠኞች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት ተቋማትና ሌሎች የህብረተሰቡ ክፍሎች የሚሳተፉ ሲሆን የተለያዩ ባለሙያዎች ለውይይት መነሻ የሚሆኑ በግብረ-ሰዶም አፀያፊነት ላይ የሚያጠነጥኑ ፅሁፎች እንደሚያቀርቡ የመድረክ አስተባባሪ ኮሚቴው ገልጿል፡፡ ከፍተኛ የባህል ጥናት ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ አዳነች ካሣ፣ በግብረ ሰዶም ምንነት እና በመጤ ባህሎች ተፅዕኖ ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፍ እንደሚያቀርቡ የተገለፀ ሲሆን የህክምና ባለሙያው ዶ/ር ስዩም አንቶንዮስ በበኩላቸው፤ ድርጊቱ በጤና ረገድ የሚያስከትለውን መዘዝ ያስገነዝባሉ ተብሏል።
ቅዳሜ ሚያዚያ 18 ቀን 2006 ዓ.ም እንዲካሄድ ከአስተዳደሩ እውቅና ያገኘው የፀረ-ግብረ ሰዶማዊነት ሰላማዊ ሰልፍ፣ ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት እስከ ረፋዱ 5፡00 ሰዓት መነሻውን ተክለሃይማኖት አደባባይ አድርጎ፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በኩል በማቋረጥ ማጠቃለያውን ኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት አደባባይ ላይ የሚያደርግ ሲሆን የግብረ-ሰዶምን አስከፊነት የሚያቀነቅኑና ግንዛቤ የሚያስጨብጡ መፈክሮች እንደሚስተጋቡ ታውቋል፡፡ በሰልፉ ላይ መንግስት በግብረ-ሰዶማዊነት ላይ የማያወላዳ እርምጃ እንዲወስድ ይጠየቃል ብለዋል - የተቃውሞ ሰልፍ አዘጋጆቹ፡፡
በቅርቡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለግብረ-ሰዶማዊነት ይቅርታ በማያሰጠው የይቅርታ አዋጁ ላይ ተወያይቶ፣ለተጨማሪ ውይይትና የማጠናከሪያ ሃሳብ ለቋሚ ኮሚቴው የመራ ሲሆን ረቂቁ እንደገና በተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል፡፡ ኡጋንዳ ግብረ-ሰዶማዊነትን የሚከላከልና በድርጊቱ የተሳተፉትን በሞት የሚያስቀጣ ህግ በቅርቡ ያፀደቀች ሲሆን በርካታ ተጠርጣሪዎችም እየታደኑ እንደሆነ ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡
አንዳንድ ወገኖች ህጉን በመቃወም ለተለያዩ ለጋሽ ሃገራት አቤቱታቸውን እያሰሙ ሲሆን በቅርቡም አንዲት የግብረ-ሰዶማዊያኑ መብት ተከራካሪ ወደ ጀርመን አቅንታ፣ የጀርመን መንግስት ለኡጋንዳ መንግስት የሚሰጠውን እርዳታ እንዲቀንስ በመጠየቅ፣ “ሃገሬ ብመለስ በቀጥታ የስቅላት ፍርድ ተግባራዊ ሊደረግብኝ ይችላል” በሚል ጥገኝነት እንደጠየቀች ተዘግቧል፡፡


Read 2267 times