Monday, 07 April 2014 15:56

ህልመኛው ክንፈኛ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ከትከሻዬ ጫፍ ግራና ቀኝ ካለው፣
ጉቶ የመሳሰለ ብቅ ያለ መሰለኝ፣
ይኸ እንግዳ ነገር እጅጉን ገረመኝ፡፡
የህልም ነገር ሆኖ መች አድሮ መች ውሎ፣
አየሁታ ወዲያው ጉቶው ክንፍ አብቅሎ፡፡
ወደፊት ወድሬ ሁለቱን እጆቼ፣
እግሬን ወደ መሬት ወደታች ዘርግቼ፣
በእነዚህ ረጃጅም ሰፋፊ ክንፎቼ፣
ከፍ ከፍ ወደ ላይ፣
ወዲያ ወደ ሰማይ!
አየሩን ቀዝፌ፣
ሄድሁ ተንሳፍፌ፡፡
ዕድሜዬን በሙሉ መሬት ተጣብቄ፣
አንድ ሜትር እንኳ ከፍ ያላልሁ ርቄ፣
ይኸው አየሩ ላይ ቀጨሁት ዓለምን፣
ያከራርመውና ዕድሜ ይስጥልኝ ህልሜን፡፡
እያደር ግን ኋላ ስካነው መብረሩን፣
ልክ እንደ ጭልፊቷ ሽው እልም ማለቱን፣
ጅው ብዬ ወርጄ ልክ እንደ የሎሱ፣
ወይ እንደ ድራጎን ያየር ላይ ንጉሱ(ሡ)፣
ይመስለኛል ያሰብሁ ልመካ በክንፌ፣
ያሻኝኝ ለመውሰድ ከመሬት ጠልፌ፡፡
አንዳንዱን ክፉ ሰው ላጥ አደርገውና፣
አንጠልጥዬ ወደ ላይ ርቄ እወስደውና፣
እንደ ሥራው መጠን ከድንጋይ ዓለቱ፣
ከጥልቅ ውቅያኖስ አልያም ከጅረቱ፣
ለቅቄ ስተወው ላይመለስ ከቶ፣
እረካለሁ መሰል ሳየው ሲቀር ሞቶ፡፡
ደግሞም ሆዳሙን ሰው ብድግ አደርግና፣
ፊቱን ወደ መሬት ዘቅዝቄ አይና፣
እጥለው መስሎኛል ጭው ካለው መሬት፣
አራዊት አምባ ምድር ሰው ከማይኖርበት፡፡
ይኸ ባለጌውን አለብላቢት ምላስ፣
የባጡን የቆጡን ቀባጥሮ የሚላላስ፣
ሳያስበው ድንገት ሁለት እጁን ይዤ፣
ከሰዎች መካከል ይህን ሰው መዝዤ፣
ወደ ላይ ወስጄው እዚያ ላይ አምጥቄ፣
ያዝ ለቀቅ አድርጌው ነፍሱን አስጨንቄ፣
ለቅቄ ስተወው ከላይ ደመናው ጥግ፣
ወደ ታች ወረደ ሄደ ሲምዘገዘግ፡፡
የሞተ መሰለኝ ምላሱን ጎልጉሎ፣
ብረት ምሰሶ ላይ በልቡ ተተክሎ፡፡
ሃይ የሚል የሌለው ከልካይም ተቆጪ፣
እኔው ራሴ ሆኜ ፈራጅ ዳኛ ቀጪ፣
ክንፎቼ እንዳይረግፉ እየለመንሁ ዕድሜ፣
እየቀጣሁ አለሁ ባለጌውን በህልሜ፡፡
ደግሞስ ማን ደርሶብኝ እንዴት ተነክቼ፣
ሽው ነው ወደ ላይ እብስ በክንፎቼ፡፡
ይህን ህልም እያየሁ ሳልነሳ ካልጋ፣
ሌቱ በረዘመ ጨርሶ ባልነጋ፡፡
ምን እንደ ህልም አለ፣ ከቶ ሌላ የለም፤
ህልመኛው ክንፈኛ አድራጊ ፈጣሪ …
        የሆነበት ዓለም፡፡
ይዘቱም መጠኑም የተስተካከለ፣
እንደዚህ እንደኔው ያለመ ሰው ካለ፣
ወደኔ ብቅ በሉ ሰማችሁኝ ሰዎች?
በጉዳዩ እናውራ የሌት አላሚዎች፡፡
በዝርዝር እንንገር ይህንን ሁኔታ፣
ምስጢሩን ገላልጦ ህልም ለሚፈታ፡፡
    ከአምሳሉ ጌታሁን ደርሰህ
የካቲት 2006 ዓ.ም

Read 3395 times