Monday, 07 April 2014 15:37

ሦስት መንግሥታትን በቤተመንግሥት ውስጥ

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(7 votes)

አቶ አያሌው  ይመር ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጀምሮ እስከ ኢህአዴግ ዘመን በሦስት መንግሥታት ቤተመንግሥት ውስጥ ሰርተዋል - በኃላፊነት፡፡
በተለይ ጃንሆይ የቤተመንግስቱ ኃላፊ አድርገዋቸው ነበር፡፡ ከንጉሱም ጋር ቅርበት ነበራቸው፡፡
የ84 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋው አቶ አያሌው ስለ ቤተመንግሥት ሥራቸውና ስለንጉሱ ከጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ጋር በስፋት አውግተዋል፡፡ እነሆ፡-

ከአፄ ኃይለስላሴ ጀምሮ፣ በደርግም ሆነ በኢህአዴግ ቤተመንግስት ውስጥ ነበሩ፡፡ እንዴት ነው ቤተመንግስት የገቡት?
በ1952 ዓ.ም ነው  ቤተመንግስት የገባሁኝ፡፡ ጄነራል አበበ ነበሩ ያሳደጉኝ፡፡ አክስቴ 40 ሺ  ሄክታር ቦታ ነበራት፡፡ እዚሁ አሁን ስድስት ኪሎ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ፡፡ አሁንም የምኖረው እዚሁ አካባቢ ነው፡፡ በጣም ሰፊ ነበር፡፡ እኛ የእቴጌ ጣይቱ ወገኖች ነን፡፡ ጎንደር፣ ጎጃም፣ የጁ… የእኛ ነው፡፡ ጠዋት ማታ ጄነራል አበበን ነበር የማስታምመው፡፡ ጄነራል አበበ የታመሙት ቲቢ ነበር፤ ሳንባ በሽታ፡፡ ጃንሆይ መጥተው ሲያይዋቸው ሁልጊዜ ሰላምታ እሰጣቸው ነበር፡፡ “እንዴት ዋልክ” ይላሉ። ሲወጡ ጥጥ በአልኮል ነክሬ በር ላይ እጠብቃቸዋለሁ፡፡ እጃቸውን አልኮል በነካው ጥጥ ጠረግ ጠረግ ያደርጉትና ፈገግ ብለው ያዩኛል፡፡ ጄነራልም ከህመማቸው አላገገሙ እሳቸውን ቀብሬ አክስቴን ልጠይቅ ወደ ስድስት ኪሎ እያመራሁ እያለ… ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሆስፒታል የሚባለው ጋ… አሁን የካቲት 12 ነው መሰለኝ የምትሉት “ጃንሆይ መጡ መጡ” ተባለ፡፡ እንዳጋጣሚ ነው አየት አድርገው ያወቁኝ፡፡ እናም አስጠሩኝ፡፡
“የት ነው ያለኸው?” አሉኝ፡፡
“አክስቴ ጋ” አልኳቸው፡፡ አንገታቸውን ወዝወዝ አድርገው አለፉ፡፡
ቤት ሄጄ የተባልኩትን የሆነውን ሁሉ ለአክስቴ ነገርኳት፡፡ አክስቴም “ምን ይታወቃል… ሊያሰሩህ ይሆናል” አሉኝ፡፡ አንድ ጠዋት የእቴጌ ዣንጥላ ያዥ (ረጅም ነው) ተልኮ ቤታችን መጣ፡፡ “ኧረ ተካ ገዳ… ከመቼ ወዲህ…” አሉ አክስቴ፡፡
“የድሮው ጠጅ የለም እንዴ… እሜቴ?” እያለ እያጨዋወታቸው ወደ ቤት ዘለቀ፡፡
“የጄነራል አበበ አሽከር የነበረውን አምጣ ተብዬ ነው” አላቸው፡፡ ከቤት ይዞኝ ሄደ፡፡ ስድስት ኪሎ ልደታ አዳራሽ በፊት ለፊት በር ይዞኝ ገባ፡፡ ጃንሆይ እጄን ይዘውኝ፤
“ከዛሬ ጀምሮ ከዚህ እንዳትነቃነቅ” አሉኝ፡፡ በቃ! እዚያው ቀረሁ  ቀረሁ፡፡
ቤተመንግስት ውስጥ ምን ነበር የሚሰሩት?
በፊት የመጠጥ ቤት ኃላፊ ነበርኩ፡፡ በኋላ ከመጠጡ ወጥቼ ምክትል የእልፍኝ አስከልካይ ሆንኩ፡፡ ሴት ወይዘሮና መኳንንቱን ከእቴጋ ጋር አገናኝ ነበር፡፡ እቴጌ ቢሮ ነው የሚቀመጡት፡፡ የተበደለውን፣ ፍርድ ጐደለብኝ የሚለውን “ውሰድና ለእገሌ አገጣጥም፣ በቶሎ ፍርዱ ይታይለት” ብለው ያዙኛል፡፡ ጃንሆይም ለብቻቸው ችሎት አላቸው፤ በችሎታቸው ያስችላሉ፡፡ ምሳ ሲደርስ መኳንንቱ ይመጣሉ፤ ጃንሆይ ጋ ምሳ ለመብላት፡፡ ጃንሆይ ያን ምሳ ይጋብዙና ወደ ማረፊያቸው ይገባሉ፡፡ ጠዋት ፆም ከሆነ፣ ፀሎታቸውን ጨርሰው ለባብሰው ነው ቁጭ የሚሉት። ስድስት ሰዓት ሲሆን የህዝብ ችሎት ቀርበው ያሟግታሉ፡፡ ከዛ ቅዳሴ ካለ ተነስተው ይሄዳሉ፡፡  
ቀጠሮ ሲኖር ማስታወሻ እንይዛለን፡፡ “በዚህ ሰዓት እንግዳ ይመጣል” ብለን ለጃንሆይ እንነግራለን፡፡ አስተርጓሚው ይገባሉ፤ እኛ እንወጣለን። እኔ ለእቴጌም ለጃንሆይም ቅርብ ነበርኩ፡፡  መንግስቱ ንዋይ ያንን ካደረገ በኋላ እኮ (መፈንቅለ መንግሥቱን ማለታቸው ነው) የታችኛው ቤተመንግስት የቢሮዋቸው ኃላፊ አድርገውኝ ነበር፡፡ አዛዡ፣ ሊጋባው፣ አጋፋሪው… ብዙ ብዙ ደረጃ ነበር፡፡ ጠቅላዩ ግን የቤተመንግስቱ ሚኒስትር ናቸው፡፡ በእኔ ሥር አስራ አምስት ሰራተኞች ነበሩ፡፡ ጃንሆይ ብሔራዊ ቤተመንግስት ነው የሚበሉትም የሚያድሩትም፡፡ ፈረንጆች አንዳንድ ገፀ በረከቶች ሲሰጡዋቸው፤ ያንን አንስቼ አስቀምጣለሁ፡፡ በኋላ ያዩትና… “ምንም የሚረባ ነገር አይደለም… ብቻ ይሁን” ይላሉ፡፡
እስቲ የጃንሆይን የዕለት ዕለት ተግባር ይንገሩኝ...?
ከጠዋቱ በ12 ሰዓት ላይ ወታደሩ ከአንደኛ በር ተነስቶ፤ በሰልፍ ሂዶ ነው ባንዲራ በጥሩንባ የሚሰቅለው፡፡ የባንዲራ መስቀያው ፊት ለፊት የእሳቸው መኝታ ቤት ነው፡፡ በራቸውን ወለል አድርገው አንደኛ በር ድረስ ያያሉ፡፡ የጠዋት የሙቀት ልብሳቸውን ለብሰው፤ በዛውም ወደ ፀሎት ይሄዳሉ፡፡ የፀሎት ስፍራቸው፣ ከእንጦጦ ማርያም ትይዩ ነው፡፡
ወደ ፀሎት ሲያዘግሙ “እንዴት አደራች” የለም፤ ዝም ነው የሚሉ። ሰው አያነጋግሩም፡፡ ፀሎታቸውን ሲያበቁ ነው የሚያነጋግሩት፡፡ ከላም አላቢዎችና ፈረስ ቦራሾች በቀር በዚያች አካባቢ ዝር የሚል የለም፡፡ ዳዊቱን የሚደግሙት በቃላቸው ነው …ግዕዙን እኮ ነው፡፡ በ12 ሰዓት ጠዋት የቆሙ ሁለት ሰዓት ሲሆን የቆሙባትን መሬቷን ሳም አድርገው ነው የሚነሱት። ከዛ የከብቶቹን ኃላፊ ይጠሩታል፡፡
“ተሰማ … ላሟ ጥጃዋን ስትዋጋት አላየህም … ለምንድነው?” ይላሉ፡፡ ወደ ፈረሶቹ ዘወር ይሉና ደግሞ፤ “ክፍ.. ሲነክሰው ዝም ብለህ ታያለህ፤ አላየሁም መሰለህ … ሁለተኛ ተጠንቀቁ” ይላሉ፡፡  
እስቲ ስለ1953 ዓ.ም. የታህሳስ ግርግር፤ ይንገሩኝ…?
እዚያው ቤተ መንግስት ውስጥ ነበርን፡፡ መንግስቱ ንዋይ እኮ ነው፡፡… ጃንሆይ ፈረንጅ አገር ሄደዋል፡፡ እቴጌ… መኳንንቱ ሚኒስትሮቹ አሉ፡፡ እኛ አላወቅንም፡፡ ማታ 4፡30 ወደ 5 ሰዓት ገደማ ነው- እኔ ወደ ቤቴ የምገባው፡፡
ለምን?
ቁልፍ ይዣለኋ!
የምን ቁልፍ?
የመጠጡን ነዋ! እቴጌም ቢኖሩ ያው እንደ ጃንሆይ ናቸው፡፡ ጃንሆይ የትም ለመሄድ ሲያስቡ ድብቅ ነው፡፡ ያኔም ለህዝብ አልተነገረም፡፡ የሚያውቅ ግን ያውቃል፡፡ ከዚያ እንግሊዝ አገር ሆነ መቀመጫቸው፡፡ ቆይተው ባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን ወሰዱ፡፡ የጃንሆይ አባት ራስ መኮንን፣ እንግሊዝ አገር የሠሩት ቤት አለ - “ፌርፊልድ ቤተመንግስት” ብለዋታል ጃንሆይ፡፡ ከከተማው ወጣ ብሎ ነው የሚገኝ፡፡
እርስዎ የእንግሊዙን ቤተመንግሥት የማየት ዕድል ገጥሞዎታል?
አላየሁትም፡፡ ጃንሆይ ከተመለሱ በኋላ በተራ እንደወስዳችኋለን ብለው ነበር፡፡ እድላችን ሆኖ አልሄድንም፡፡ በፎቶግራፍ ግን አይቼዋለሁ። እና ጃንሆይ እንግሊዝ አባታቸው ቤት ገቡ፤ ልጆቻቸውንም ባለቤታቸውንም ወሰዱ፡፡ ትንሽ የተማሩትን ባለስልጣናትም ወስደዋል፡፡ ሃሳባቸው የጣልያንን ወረራ ለዓለም ከፍተኛው ፍ/ቤት ማቅረብ ነበር፡፡
መንግስቱ ንዋይ መክዳቱን ጃንሆይ አውቀዋል። በስምንተኛው ቀን ቤተመንግስቱ በታንክ ተከቦ… ስራ ልንገባ ስንሄድ አይቻልም አሉለን፡፡ ሚኒስትሮችን ማታ “እቴጌ ታመዋል” ብሎ ጠርቶ አጐራቸው። እቴጌ የራሳቸው ቤት አለ፤ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጐን፤ የእናታቸው ቤት ነው፤ እዛ ገቡ፡፡ ሲነጋ ሄድን፤ ሰውም ዙሪያውን ከበበ፡፡
ወዲያው አልጋ ወራሽ በሬዲዮ “እኔም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሆኜ ለአገሬ ላገለግል በተቆረጠልኝ ደምወዝ…” የሚል ነገር ሲናገሩ ክው አልን፡፡ “አስገድዷቸዋል…” አልነ፡፡
ጠቅል ይህን ሲሰሙ ባሉበት ሆነው ብድግ አሉ።
“ህዝቤን እኔ አውቀዋለሁ፤ ህዝባችን እኛን ይወደናል፤ ግዴለም እኛ ከአንድ ከሁለት ሰው ጉዳይ የለንም” ብለው ገሠገሡ፡፡ አስመራ ሲገቡ የአስመራ ህዝብ “እኛ እንቅደም እርስዎ ይቆዩ” አለ.. “አይ ግዴለም” ብለው መጡ፡፡ ያኔ አውሮፕላን ማረፊያው ጦር ኃይሎች ነበር፡፡ ያን ጊዜ የቦሌው አውሮፕላን ማረፊያ አልተሠራም፡፡ እዚያ ሄደን ንጉሱን ጠበቅናቸው፡፡ መሬቷ አትታይም፡፡ ህዝቡ ለጉድ ነበር፡፡ ጃንሆይ ፈገግ ፈገግ እያሉ ነበር፡፡ አቡነ ባስሊዎስ ከጐናቸው ነበሩ፡ የጦር ሚኒስትሮቻቸው ጀነራል መርድ መንገሻና ጀነራል ከበደ ገብሬ ነበሩ መንግስቱ ንዋይን ድል ያደረጉት፡፡ ሰራዊቱ ተዋጋ፡፡ ለካ ግማሹ ክቡር ዘበኛም አላወቀም፡፡ “እንግሊዝኛ ቆጠርን!!” የሚሉት ናቸው የከዱት። ጃንሆይ ቀጥታ ልዕልት ተናኘ ቤት ነው የገቡት፡፡ ቆዩና ብሔራዊ ቤተመንግስት ገቡ፡፡ ለሊቱን ሙሉ ተኩስ ነበር፡፡ ጃንሆይ  “እባካችሁ ከልክሉ” ይላሉ። አበበ አረጋይም ተው ይላሉ፡፡ ጃንሆይ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሆስፒታል ሄደው ብዙ ሬሳ ተመለከቱ። ሬሳው ሲታይ “እነ ራስ ስዩም፣ እነ አበበ አረጋዊ… ሚኒስትሮች ሁሉ… ነበሩበት፡፡ መንግሥቱ ንዋይ ኩዴታው መክሸፉን ሲያውቅ ቀጨኔ መድሃኒያለም ተደብቆ፣ ሌሊት ወደ ሶማሊ ሲሄድ ዝቋላ ላይ ተያዘ። ተታኮሰ፤ አንድ አይኑን መቱት፡፡ ወንድምየውን ገደሉት፡፡ እሱን ወደ ጃንሆይ አመጡት፡፡ ብርድ ልብስ ለብሶ ባዶ እግሩን ነበር፡፡
“መንግስቱ” አሉት ጃንሆይ፤ አንድ ዓይኑ አያይም “ያ ሻምፓኝ የምትጠጣበት ቤተመንግስት ነው” “አይታየኝም” አላቸው፡፡ ይኸኔ “ውጡ ውጡ” ተባልንና ወጣን፡፡ እሱና እሳቸው ብቻ ቀሩ፡፡ ህክምና ተደረገለትና ለፍርድ ቀረበ፡፡ ያ ሁሉ ደመኛ ዘመድ መጣልሽ፡፡ ከፍተኛ ፍ/ቤት ሰው ግጥም አለ። የሞት ፍርድ ተበየነበት፡፡
ተክለ ሃይማኖት አደባባይ መሰላል መስቀያ ተዘጋጅቶ ለንጋት አጥቢያ ላይ በ12 ሰዓት ህዝቡ ግጥም ብሏል፡፡ መንግስቱ ገበር ጅንስ ሱሪና ከላይ ሸሚዝ ነበር የለበሰው። የመስቀያውን ደረጃ ጢብ ጢብ ብሎ ወጣ፤ ወዲያው መሰላሉን ሸርተት አደረጉት፡፡ በአደባባይ ተሰቀለ፡፡ ከዛ አብረው የኖሩት መርድ መንገሻ ስቅስቅ ብለው አለቀሱ፡፡
ምክትል እልፍኝ አስከልካይ ሆኜ እሰራ ነበር፤ ለእቴጌ መነን፡፡ ጃንሆይ ወታደሩንም፣ ሹማምንቱንም ሰብስበው “የተወለድኩበትን የአባቴን ቤት ለዩኒቨርስቲ አስረክቤዋለሁ” አሉ፡፡ ያ ሁሉ ሚ/ር የተረሸነው እዛ ውስጥ ነው፡፡ ግብዣቸውን አድርገው ብሔራዊ ፍልውሃ ቤተመንግሥት ገባን። ያን ጊዜ እሳቸው ህዝባቸው እንዲማርላቸው፣ ያን ጊዜ ጨለማ ነው፤ ትምህርት የለም፡፡ በየአገሩ፣ በየወረዳው እየሄዱ እንጨት አጣና እየረበረባችሁ ት/ቤት አቋቁሙ አሉ፡፡ መጽሐፉን ሁሉ በመኪና እየጫኑ እየሄዱ ይሰጡ ነበር፡፡
በቅርቡ የወጣ መጽሐፍ፤ ጃንሆይ ጥፋት የፈፀሙ የቤተመንግሥቱ ባለሟሎችን በአለንጋ ይገርፉ እንደነበረ ይገልፃል፡፡ እርስዎ ይሄን ያውቃሉ?
ጃንሆይ!!? (ራሳቸውን ይዘው እየነቀነቁ) ጠርተው “ተው! እንደዚህ አይነት ብልግናህን ተው!” ብለው ነው የሚመክሩት፡፡ ብለው ብለው ሲያቅታቸው “አለንጋ አምጡ” ብለው…ትንሽ ነካ አድርገው ነው የሚተውት፡፡
ይኼው መጽሐፍ ...ስስት አለባቸው ይላል ንጉሡን?
ውሸት ነው፡፡ በልተሸ የጠገብሽ አይመስላቸውም እኮ፡፡ “አንሺ፣ ብይ… ያወጣሽውን ምግብ መጨረስ አለብሽ” ነው የሚሉሽ፡፡ ሴት ወንድ ሳይሉ ይጋብዛሉ፡፡ እሳቸው የሚቆጡት መብራትና ውሃ ያለጥቅም ሲባክን ነው፡፡ “መብራትና ውሃ ማን አባቱ ነው የሚከፍተው? ጥራ ማን ነው የከፈተው ይሄን ውሃ፤ እናንተ አታውቁትም፤ እኛ እናውቀዋለን የውሃን ጡር” ይላሉ፡፡
የጃንሆይ አመጋገብ እንዴት ነበር?
ጃንሆይ የእኛን ሀገር ምግብ ብዙም አይወዱትም ትንሽ አልጫ ነበር የሚወዱት፡፡ በተረፈ ግን የፈረንጅ ምግብ ነው የሚመርጡት ኬክ ከምግብ በኋላ ሳይሆን በ10 ሰዓት ከሻይ፣ ከወተት ጋር ሆኖ ይቀርብላቸዋል፡፡ ራሳቸው የሚፈልጉትን ያህል ቆርጠው ነው የሚበሉት፡፡
እቴጌ ጣይቱ የአፄ ምኒልክ ቀኝ እጅ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ የአፄ ኃይለሥላሴ እቴኔ መነንስ እንዴት ያሉ ነበሩ?
እቴጌ እንኳን ፀሎተኛ ናቸው፡፡ እቴጌ ጣይቱማ በጦሩም ጭምር አሉበት፡፡ እኝህ እቴጌ መነን ፀሎት ብቻ ነው፤ ደግ ሰው ነበሩ፡፡ በፀሎት ጥሩ አድርገው አገራቸውን የረዱ ሰው ናቸው፡፡ መንህፍት ማንበብ፣ ዳዊት መድገም እንጂ ሌላ የሚያውቁት ነገር የለም። ብቻ ከፈረንጆቹ ጋር ቀጠሮ ሲኖራቸው በአስተርጓሚ መልስ ይሰጣሉ፡፡ ጃንሆይን ያልሽ እንደሆነ ደግሞ የደግነታቸውና የአስተዋይነታቸውን ብዛት አልነግርሽም። መኳንንቱ እንደመሰለው ሲፈርድ… እሳቸው ችሎት ቀርበው ጉዳዩ ሲነበብ ልብ ብለው ያደምጣሉ፡፡ “እዚች ጋ ምልክት አድርግ” እያሉ ተነቦ ሲያልቅ.. “እስቲ ቅድም ምልክት ያደረክበትን አንብብ” ይላሉ መልሰው፡፡ ያ ሁሉ ተደርጐ ነው እሳቸው የሚፈርዱት፡፡ ከዚያ “ርስቱን ቀማኸው፤ አያቱ አድዋ ዘምቶ፣ አባቱም ማይጨው ሞቶ አንተ ጣሊያን ሰጠኝ ብለህ የያዝከው መሬት አይደለም… ለእሱ ይገባል” ብለው ይፈርዳሉ፡፡ ልጃቸው ቢሆንም እንኳ ለሃቅ ነው የሚፈርዱት፡፡ ልብ እንደ ጐራዴ ተመዞ አይታይ እንዴት ብዬ ልንገርሽ? ለፍርድ በጣም ይጠነቀቃሉ፡፡ እንደሳቸው ጥንቁቅ ማንም የለም። ጠዋት ማታ ፖለቲካውን አስተዳደሩን… ይከውናሉ። በቀኛቸው ዶሴ በግራም ዶሴ ነው፡፡ የሞት ፍርድ እሳቸው ካልፈረሙበት አይፈፀምም፡፡ የፍርድ ሚኒስትሩ አቶ አካልወርቅ “ጃንሆይ ያን ነገር እባክዎ አዘገዩት” ይሏቸዋል፡፡
እሳቸውም “ሰው ለመግደል ምን ያስቸኩልሃል?” ይሉታል፡፡ ይሄኔ ዝም ይላል፡፡ ሁልጊዜ የሞት ፍርድ ላይ ፊታቸውን አዙረው ፀልየው ነው፡፡ ምን ያድርጉ… ፍርድ ነዋ፤ አይቀር!
ቀደም ሲል በጠቀስኩልዎት “የንጉሱ ገመና” መፅሃፍ ላይ “ሴሰኛ” መሆናቸውና ከቤተመንግሥት የፅዳት ሠራተኞች ጋር ሳይቀር ይቀብጡ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ይሄስ ምን ያህል ሃቅ ነው?
አይ ሰው ከንቱ! ይሄን አለም የተውት ገና ከስደት ሲመጡ ነው፡፡ ግን እሳቸው ምን ቸገራቸው! አየሽ… ባላደረግሽው ነገር ስትታሚ እግዚአብሔር ነው ዋስሽ። እሳቸውን ማንም የሚጠረጥራቸው የለም። ባይሆን እንኳ እነ ልዑል መኮንን… ልጆች ስለሆኑ ጨዋታ ይፈልጉ ይሆናል፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ የተማሩ እኮ ናቸው፡፡ የሊቁን ትምህርት በግዝ ሲነግሩሽ… ሌላ ነው፡፡ አባታቸው ራስ መኮንን ጥሩ አድርገው አስተምረዋቸዋል፡፡ ኦሮምኛ ሲናገሩ ጥርት አድርገው ነው፡፡ በእርግጥ ንጉስ ስለሆኑ በአስተርጓሚ ነው የሚሠሙት፡፡ አንዴ መንገድ ሲሄዱ አንዱ “ጃንሆይ ተበደልኩ” እያለ በኦሮምኛ ይማፀናል፡፡ ጃንሆይም አብሯቸው ያለውን ሰው “ምን አለ?” ብለው ጠየቁት፡፡ እሱ ለካ ኦሮምኛ አይችልም፡፡
“ኧረ እኔ አላውቀውም ጃንሆይ” አላቸው፡፡
“ምን አባክና የአገርህን ቋንቋ አታውቅም” ብለው ገሰፁት፡፡ እሳቸው ገጠሙታ በኦሮምኛ፡፡ አደርኛም አረብኛም ትግርኛም ይሰማሉ፡፡ ንጉስ ስለሆኑ ግን ሁሉንም በአስተርጓሚ ነው፡፡
ከበደ ተሰማን ያውቋቸዋል?
ደጃች ከበደ ተሰማ አብረን ኑረን አይደል፡፡ ጥንት የዘውዲቱ አሽከር ነበሩ፡፡ በምኒልክም ትንሽ ልጅ ናቸው እንጂ መድረስ ደርሰው ነበር፡፡ ጃንሆይ ከነገሡ በኋላ ደጃዝማች ብለው ጠቅላይ ገዢ አደረጉዋቸው፡፡
በፊት አሽከር ነበሩ፡፡ ደጃዝማች ከበደ ተሰማ ለጃንሆይ ቅርብ ነበሩ፡፡ ዕውቀታቸው የሀገር እንጂ የውጪ ትምህርት አልነበራቸውም፡፡ ብልሃተኛ ነበሩ፡፡ እነ ከበደ ተሰማ እየሩሳሌም ተቀምጠው፣ ጃንሆይ እንግሊዝ እያሉ፣ ምስጢር ይነጋገሩ ነበር። ከበደ ተሰማን ጥሩልኝ ብለው ከእየሩሳሌም በፖርት ሰይድ፣ በግብፅ አድርገው እንግሊዝ አገር ገቡ፡፡ የኢትዮጵያ መሬትን ከረገጡማ ጣሊያን ይይዛቸዋል።
በእንግሊዝ ከተገናኙ በኋላ “እንግዲህ አንተን የጠራንህ በኢትዮጵያ ጦርነት ተነስቷል፤ እየቀደምክ ወረቀት እየፃፍክ ለጎንደር፣ ለጎጃም፣ ለሸዋ፣ ለትግሬ፣ ለኦሮሞ… በምስጢር ላክ፤ “ጃንሆይ መጡ ጃንሆይ መጡ” እያልክ አሏቸው፡፡ ከዚያም ጣሊያን እንዳይማርካቸው ከእንግሊዝ ጦር ጋር እየተከተሉ፤ ለጎንደር ህዝብ በአውሮፕላን ወረቀት ተበተነ። እልልታው ፈነዳ፡፡ ያን ግዜ በቤተመንግስት ባንሆንም የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴን “መጣሁልህ አይዞህ” የሚል ወረቀት ስናነብ ለቅሶ ሆንን፡፡
ከዚያ እሳቸው ጎጃም ገቡ... የአርበኛውን ጦር ለማየት እዛው ቁጭ አሉ፡፡ አርበኛው ሁሉ ገብቶ ገብቶ ሰልፉን አሳይቷል፡፡ “በላይ ዘለቀ ነገ ይመጣል” ተባለ፡፡ ጃንሆይ ከመጓጓታቸው የተነሳ ጠዋት በ4 ሰዓት የተቀመጡ አልተነሱም፡፡ በኋላ ምሳ ሰዓት ሊደርስ ሲል መጣ፤ በፈጥኖ ደራሽ በወጣት ጦር ታጅቦ፡፡ “የገሊላው” አሉ፤ የጃንሆይ ወንድም ራስ ካሣ ከጃንሆይ ጎን ተቀምጠው። ሲደነግጡ የሚጠቀሙበት ዘይቤያቸው ነው፡፡ በላይ ዘለቀ መጥቶ ከጃንሆይ ፊት ቆመ፡፡
“በላይ ዘለቀ ማለት አንተ ነህ? እንደ ጆሮህ ትልቅ፤ እንደ አይንህ ትንሽ” አሉት፤ ጃንሆይ። (ዝናህን ስንሰማ ትልቅ ዕድሜ ያለህ መስሎን ነበር ማለታቸው ነው) ልጅ ነው፤ ፈጣን፡፡ እሱም ከጐናቸው ተቀመጠ፡፡ የልጅ ነገር ሆነና በገዛ እጁ ሞተ፡፡ የጎጃም ጠቅላይ ገዥ እሆናለሁ ብሎ ነበር፤ ውስጥ ውስጡን፡፡ ሰው ክፉ ነው አጣሏቸው፤ እዚህ መጥቶ ታሰረ፡፡ ከእስር ቤት ሰብሮ አመለጠ፡፡ ሱሉልታ ላይ መቶ አለቃውን በጥይት ገደለ፡፡ በመጨረሻ ተያዘና ለፍርድ ቀረበ። …ጃንሆይ እንዲሞትባቸው አልፈለጉም ነበር፡፡ በፍትሃ ነገስቱ… “በግፍ የገደለ ይገደል” ስለሚል ተሰቀለ፤ ጎጃም አኮረፈ፡፡
በላይ ዘለቀን በደንብ ያውቁት ነበር?
የአክስቴን ቤት ተከራይቶ ነበር የሚኖር። ጠይም የሚምር ቆንጆ፣ ጀግና ነበር፡፡ አክስቴ ከምግቡም ከቅቤውም ከማሩም ለበላይ ሰራተኞች ውሰዱ ይሉናል፤ ወስደን እንሰጣለን፡፡ ቤቱ ስንሄድ እንደ ገጠር ቤት በየቦታው በገል ጢስ ይጢያጣሳል። ይኼን ሳይ “ምንድን ነው” ብዬ አክስቴን ጠየኩዋት። “በሽታ እንዳይነካው ይሆናል” ብላ ሸፋፈነችለት… ነገሩ እንኳን ሌላ ነው፡፡ አንድ ሁለት ወር ያህል እንደተቀመጠ ቤት ተሰጠውና ወጣ፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ ደሃቸውን የሚወዱ ነበሩ፡፡
ደመወዝዎ ስንት ነበር?
40 ብር ነበር፡፡ በእኛ ግዜ በጣም ብዙ ነበር፤ የትየለሌ ነው፡፡ ባለቤቴ የቤትዋን ጣጣ ትጨርስበታለች ወሩን ሙሉ፡፡ አንዲት ጠቦት በግ ለመግዛት አስራ አምስት ብር እንኳን አይፈጅም ነበር፡፡
በቤተ መንግስት ውስጥ በኃላፊነት ላይ ከነበሩ ሰዎች በተለየ ከነገስታቱና ሹማምቱ ጋር ቁጭ ብለው ፊልም እንዲያዩ ይፈቀድልዎት ነበር ይባላል?
እኔ ቆሜ ነበር የማየው፡፡ ጃንሆይ ካላዘዙ ማንም የሚቀመጥ የለም፡፡ ምግብ የሚያቀርብላቸውን እሸቱን ጠርተው “ከብላታ አድማሱ ጀርባ ለአያሌው ወንበር አስቀምጡና ፊልም ይመልከቱ” ብለው አዘዙ። ራት በልተን ልንወጣ ስንል ተጠራሁና፤ ፊልም ማየት እንደተፈቀደልኝ ነገሩኝ… እጅ ነሳሁና ተቀመጥኩ፡፡
ቤተመንግሥት ምን ዓይነት ፊልሞች ነበር የሚታዩት?
የጀርመን የሁለተኛ የዓለም ጦርነትን ፊልም ነበር የምናየው፡፡ ጃንሆይ ፊልም ሳያዩ አይተኙም፡፡ ስድስት ኪሎም ሆነ ብሔራዊ ቤተመንግስት ረዣዥም ፊልሞችን ይመለከቱ ነበር፡፡ ለእቴጌ የልዕልት ተናኘ ልጅ ሒሩት ከጎናቸው ቁጭ ብላ ታስተረጉማለች፡፡ እቴጌ እንግሊዝኛ አያውቁም፡፡
አፄ ኃይለስላሴ እንግሊዝኛ በደንብ ይችሉ ነበር?
እንዴታ! በደንብ ነዋ! ፈረንሳይኛማ ከልጅነታቸው ጀምረው እንደውሃ የጠጡት ነው፡፡ እንግሊዝኛ ሲናገሩ የዋዛ መሰሉሽ፡፡ ዶ/ር ቴዎድሮስ የሚባሉ የእርሳቸው ሀኪም ማታ ማታ ከአጠገባቸው አይጠፉም ነበር። በ11 ሰዓት የመጡ ማታ ፊልም ሲያልቅ ከጃንሆይ ጋር ተነስተው ነው የሚሄዱት፡፡ ጃንሆይ በፈረንሳይኛ የሚያወሩት ታዲያ ከሀኪማቸው ጋር ብቻ ነበር፡፡
እስቲ ከዙፋናቸው የወረዱበትን ሁኔታ ይንገሩኝ…
የያዝዋቸው ቤተመንግስት ውስጥ ነው፡፡ መንግስቱ ኃይለማርያም የመጣው ሐረርጌ ኦጋዴን የጦር ኃላፊ ሻምበል ሆኖ ነው፡፡  ወደዚህ እንደመጣ ዋና አደረጉት። “ሻምበል መንግስቱ” … “ሻምበል መንግስቱ” አሉት። ጃንሆይን የያዟቸው ጊዜ፤ “ሰማችሁ ለውጥ ያለ ነገር ነው፤ በእኛ ብቻ አልተጀመረም፤ ግን የአስመራን በር መከራ አይተን ያመጣነው ነውና ተጠንቀቁ፡፡ ኦጋዴኑን ተውት ግዴለም፤ ይሄንን ግን ተጠንቀቁ፤ አደራ አገሪቱ እንዳትሞት” ብለው ነው አጅሬ የተናገሩት፡፡ ሁላችንም አለቀስን፡፡ አፄ ምኒልክ ቤተመንግስት አመጧቸው፡፡ ደበላ ዲንሳ የሚባለው… ሰዎች ይዞ መጥቶ የተፃፈ ነገር በክብር አነበበላቸው፡፡ ከዚያም ግርማዊነትዎ፤ “ወደ ተዘጋጀልዎ ማረፊያ እንዲሄዱ ፍቀዱልን” አሏቸው። እሺ አሉ፡፡ ከጎናቸው እራስ እምሩ አሉ፡፡ “ይሄ ያለ ነገር ነው፤ ብቻ የአገራችሁን ነገር አደራ… አደራ” አሉ፡፡ ለረጅም ሰዓት ሰው ሁሉ ተላቀሰ፡፡ አታንሺብኝ እባክሽ። ለምን መጣሽብኝ?… አመት አቆይዋቸውና አንድ ቀን “ግርማዊ ንጉሰ ነገስት ባደረባቸው ህመም አርፈዋል” ብለው ተናገሩ፡፡ አለቀስን፡፡ ከንቱ ነው ይሄ አለም እባክሽ፡፡  
በእስር ቤት እያሉ ያገኙዋቸው ነበር?
የእቴጌ ጣይቱ መኝታ ቤትና የአፄ ምኒልክ መኝታ ቤት ግራና ቀኝ ነበር፡፡ ሁለቱም የሚገናኙት በሰገነት ነበር፡፡
የአፄ ምኒልክ ልጅ ዘውዲቱ ነግሰው አልነበር፤ የጃንሆይ አልጋ ወራሽ ሆነው፡፡ ምድር ቤት እራት የሚበሉበት ስፍራ ነበረች፡፡ እዛ ውስጥ ነው መንግስቱ ለአፄ ኃይለስላሴ ማረፊያ እንዲዘጋጅ ያዘዘው። መንግስቱ ኃይለማርያም… “እርስዎ” እያለ ነበር ትእዛዝ እንኳ የሚያዘን፡፡ ከአፉ “አንተ አንቺ” የሚል አይወጣውም ነበር፡፡ ከሶስት ከአራት ቀን በኋላ… አስጠራኝና “የእስረኞች አዛዥ እርስዎ ነዎት?” አለኝ፡፡
የእነዚያ ሁሉ እስረኞቹ ሃላፊ ነኝ፡፡ በአፄ ምኒልክ አዳራሽ ነበር ያ ሁሉ እስረኛ የታሰረው፡፡ እና ወደ እስረኞች ስገባ መናገር የምፈልገውን ነገርኳቸው። “እኔን ግባ ካላችሁኝ … ስገባ “እንደምን አደራችሁ፤ እግዚአብሔር ያውጣችሁ” እላለሁ፤ ስል “ይሄንንስ ማለት አትችልም” አለኝ አንዱ፡፡
“ይኼን ካላልኩ አልገባም” አልኩ፡፡ ተጠራሁና “ይበሉ” ተብዬ ተፈቀደልኝ፡፡ ሚኒስትሮቹ እነፀሃፊ ትዕዛዝ አክሊሉ፣ መኳንቱ ሁሉ በስሜ ነበር የሚጠሩኝ። እስረኞቹ ከእኔ ጋር አብረው የነበሩ ናቸው፤ ብዙ አገለገልኳቸው፡፡
መንግስቱን ያልሽ እንደሆነ “እንዴት ነበር የምታደርጉት፣ ደሃ አታበሉም ነበር” ሲሉ ይጠይቁኛል።
እኔም የነበረውን ሁሉ አስረዳቸዋለሁ፡፡ የመንግስቱ ጥፋት አንዲት ናት፡፡ ሰውን ካለፍርዱ መግደሉ፤ “ለፍርድ ይቅረብ፣ ፍርድ ያውጣው ቢል” ጥሩ ነበር። እሱ ጥሩ ሰው ነው፤ በዙሪያው ብዙ ቀጣፊዎች ነበሩ የሚያሳስቱት፡፡ ደሃ ሲያይ ይጨነቃል፤ ሀሰት አይወድም። አንድ ቀን ግቢውን ሲጎበኝ ጠራኝ… የብርቱካን ልጣጭ ወድቆ አይቶ… “በሉ የሚመለከተውን ሰው ጥሩና ይሄን አፅዱ አለኝ” አንቱ ብሎ፡፡ ሰውን አክብሮ ነው የሚናገር።
በኢህአዴግ ዘመንስ ቤተመንግሥት ሰርተዋል?
ሁለት ዓመት ሰርቻለሁ፡፡ ብዙም አያዙኝም ነበር። እንደገቡ ፍራሹን ከየክፍሉ አወጡ አሉን፡፡ ለወታደሩ መተኛ አሰናዳን፡፡ መለስ እንደ ኃላፊ ሆኖ መጣ፤ በኋላ ከፍ አደረጉት፡፡ ብዙ ጊዜም ያነጋግረኝ ነበር፡፡ “አጥሩን… በሩን እንደዚህ ያድርጉ፤ የጎደለብዎትን ለእኛ አለቃዎ ይንገሩ” አሉኝ፡፡
አሁን ጡረታ ስንት ያገኛሉ?
400 ብር አገኛለሁ፡፡  
በጡረታ ከቤተመንግስት ከተሰናበታችሁ በኋላ ባልደራስ የቤተመንግስት ጡረተኞች በሚል አንድ ትልቅ አዳራሽ ተከራይታችሁ ምግብ ቤት ከፍታችሁ ነበር…
ሁላችንም በጡረታ ተገለልን፡፡ ባልደራስ ጄነራል ፍሬ ሰንበት የተማረ ልጅ ነው ፓይለት፡፡ ጃንሆይ ናቸው ያመጡት፤ እልፍኝ አስከልካያቸው ነበር… ይወደኛል፡፡
እና “ሆቴል ማቋቋም ፈልገናል፤ ከእኔ ጋር ብትሆን” አለኝ፡፡ አቋቋምንና ሰርግ መስራት ጀመርን፤ ጥሩ ሆነ። ጀነራልም ሞተብኝ… እኔም ደከም ስላልኩ ወጣሁኝ፡፡ አሁን በቤቴ ውስጥ ነው ያለሁት ልጄ፡፡
አንዴ እዚህ ባልደራስ ለሠርግ ተጋብዤ መጥቼ ነበር። ከምግብ አቀራረብና መስተንግዶ ስርዓቱ ጀምሮ እስከ ምርቃቱ ድረስ ለየት ያለ ስርዓት ነበረው፤ ከየት የመጣ ሥርዓት ነው?
ባልደራስ ማለት የጃንሆይ የበቅሎው፣ የፈረሱ ሃላፊ ማለት፡፡ በቤተመንግስት ውስጥ ያለውን ስርዓት ነው በሰርጉም ያየሽው፡፡ ሞሰቡ ሁሉ ቀሚስ ለብሶ ለብሶ ይመጣል፤ ወደ ግብር፡፡ ጃንሆይ በዚህ ስርዓት ጊዜ ይቆማሉ፡፡ ሞሰቡ “እንጀራ ይስጣችሁ፤ እንጀራ ይስጣችሁ” እየተባለ ያልፋል፡፡ አዛዡ አደግድጎ አሸብርቆ ነው፡፡ ለመኳንንቱ በመሶብ ነው የሚቀርብ። ያም ሲሆን ደግሞ በየማዕረጋቸው ነው፡፡ የአንቺን መቀመጫ የሚቀመጥበት የለም፡፡ በእኔ መቀመጫ የሚቀመጥ የለም፤ ይሄ ህጉ ነው፡፡ ከ4-6 ሰው በአንድ መሶብ ከብቦ ይበላል፡፡ እየተፈተፈተ አሳላፊው ያስተናግዳል፡፡ ጃንሆይ “የመኳንንቱን ምግብ አምጣው እስኪ” ብለው መሶቡን ያዩታል፡፡ በመሶቡ ላይ የተቀመጠውን እንጀራ ሰቅ ሰቅ ያደርጉታል፡፡ ይህን የሚያደርጉት አሳንሰውት እንዳይሆን በሚል ነው፡፡ “እንዴት ነው ደህና አድርገህ አጥቅሰሃል?” ብለው በእጃቸው ያያሉ፡፡ በአንድ ሞሰብ ከ20-30 እንጀራ ይቀርባል፡፡ የተረፈው የአሽከር መጫወቻ ነው፡፡ ጃንሆይ በክብራቸው በነ ራስ አበበ፣ በነ ቢትወደድ መኮንን እነ ራስ መስፍን… በጠረጴዛ ዙሪያ ይበላሉ፡፡ ሰርግ ላይ ያየሽው ስርዓት ከቤተመንግስት የመጣ ነው፡፡


Read 7022 times