Monday, 07 April 2014 15:30

ኢትዮጵያዊቷ የ‘ሞታውን ሪከርድስ’ ፕሬዚዳንት ሆነች

Written by 
Rate this item
(5 votes)

        በአለም አቀፉ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ የካበተ ልምድ ያላት አፍሪካ - አሜሪካዊቷ ኢትዮጵያ ሐብተማርያም፣ የታዋቂው የአሜሪካ የሙዚቃ ቀረጻ ኩባንያ የሞታውን ሪከርድስ ፕሬዚዳንት ሆና መሾሟን ዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ፐብሊሺንግ ግሩፕ ገለጸ፡፡ የአለማችን ትልቁ የሙዚቃ ኩባንያ የሆነው ዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ፐብሊሺንግ ግሩፕ፣ ከዚህ በፊት በስሩ ይተዳደሩ የነበሩትን ዴፍ ጃም ሪከርድስ፣ አይስላንድ ሪከርድስና ሞታውን ሪከርድስን እንደገና በማዋቀርና ራሳቸውን ችለው እንዲሰሩ በማድረግ፣ ኢትዮጵያ ሃብተማርያምን የሞታውን ሪከርድስ ፕሬዚዳንት አድርጎ በዚህ ሳምንት መሾሙን አስታውቋል፡፡እ.ኤ.አ በ2003 ታዋቂውን ዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ፐብሊሺንግ ግሩፕ የተቀላቀለችው ኢትዮጵያ ሐብተማርያም፣ ጀስቲን ቢበርና ክሪስ ብራውንን ጨምሮ አለማቀፍ ዝና ያላቸውን በርካታ ታዋቂ ድምጻውያን፣ የሙዚቃ ደራሲያንና አርቲስቶችን ለኩባንያው በማስፈረም ተጠቃሽ ስራ የሰራች ሲሆን፣ ከ2011 አንስቶም የዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ፐብሊሺንግ ግሩፕ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የኧርባን ሚዩዚክ ሃላፊ በመሆን አገልግላለች፡፡
ዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ፐብሊሺንግ ግሩፕን በምክትል ፕሬዚዳንትነት በመራችባቸው አመታት፣ ሜሪ ጄ ብላይጄ፣ ፊፍቲ ሴንት፣ ኤሚኔየም፣ አሻንቲ፣ አይስ ኪዩብ፣ አር ኬሊና ሌሎች በርካታ የፕላቲኒየምና የግራሚ ተሸላሚ አርቲስቶችን ወደ ኩባንያው በመሳብ፣ ስኬታማነቷን ያስመሰከረችው ኢትዮጵያ ሐብተማርያም፣ ለረጅም አመታት በዘርፉ ተጠቃሽ ስራዎችን ሲያከናውን የቆየውን ሞታውን ሪከርድስ ወደተሻለ ትርፋማነት ታሸጋግራለች ተብሎ ስለታመነባት ነው በፕሬዚዳንትነት የተሾመችው፡፡
ሞታውን ሪከርድስ የማኔጅመንት፣ የማርኬቲንግና የማስታወቂያ ስራ አቅሙን የበለጠ በማሳደግ፣ ራሱን የቻለ አለማቀፍ የሪከርዲንግ ኩባንያ እንዲሆን ፣ ኢትዮጵያ ሐብተማርያም ከፍተኛ ሃላፊነት እንደተጣለባት የዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ፐብሊሺንግ ግሩፕ መግለጫ ያሳያል፡፡
የዩኒቨርሳል ሚውዚክ ፐብሊሺንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሉቺያን ግሬንጅ እንደተናገሩት፣በኢትዮጵያ ሐብተማሪያም የሚመራው ሞታውን ሪከርድስ፣ ተቀማጭነቱን እ.ኤ.አ ከ1972 ጀምሮ ለ25 አመታት ያህል  በርካታ ስራዎችን አሳትሞ ለአድማጭ ሲያቀርብበት በነበረው ሎሳንጀለስ በማድረግ፣ በዘርፉ አያሌ  ስራዎችን ያከናውናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ ሐብተማርያም ከአዲሱ ሹመቷ በተጨማሪ፣ በዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ፐብሊሺንግ ግሩፕ የኧርባን ሚዩዚክ ሃላፊነት ስራዋን ጎን ለጎን እንደምትቀጥል ተነግሯል፡፡

Read 4221 times