Monday, 07 April 2014 15:23

ቭላድሚር ፑቲንና ራሺያን የማስፋፋት ዘመቻቸው

Written by 
Rate this item
(7 votes)

         የራሺያ የጦር ሃይል የዩክሬንን ድንበር ሰብሮ፣ ክረሚያ የመግባቱን ሰበር ዜና ድፍን ዓለሙ የሰማው በድንጋጤና በመገረም ነበር፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የራሺያ ድርጊት ምንም አይነት አስደንጋጭም ሆነ አስገራሚ ነገር አልነበረውም፡፡ የራሺያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ላይ የፈፀሙትን አይነት ድርጊት ምቹ ጊዜና አጋጣሚ ካገኙ ከመፈፀም እንደማይመለሱ ያዘጋጁትን እቅድ እንደ ሀገር ምስጢር ጨርሶ ደብቀውት አያውቁም፡፡
ከዛሬ አስራ አምስት በፊት ነሐሴ 16 ቀን 1999 ዓ.ም በፕሬዚዳንት ቦሪስ የልሲን የራሺያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ቭላድሚር ፑቲን፤ አዲሱን ሹመታቸውን ባፀደቀላቸው የራሺያ ዱማ (ፓርላማ) ፊት ቀርበው ንግግር አድርገው ነበር፡፡ ያኔ ያደረጉት ንግግር ለወጉ ያህል የሚደረግ ተራ ንግግር ሳይሆን በስልጣን ዘመናቸው ሊያከናውኑት የሚፈልጉትን ዝርዝር የስራ እቅዳቸውን የሚጠቁም ነበር፡፡
ቭላድሚር ፑቲን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተሾሙበት ወቅት ራሺያ ውቃቤ ርቋት ነበር፡፡ መቸም ቢሆን ለማንም በምንም አይረታም እየተባለ ይነገርለት የነበረው የራሺያ ጦር፣ ጠቅላላ ህዝቧ ራሺያ ካሰማራችው የጦር ሃይል ብዛት በእጅጉ በሚያንሰው በቺቺኒያ በአሳፋሪ ሁኔታ ተሸንፎ ነበር።
ቀደም ባለው ጊዜ የራሺያ ዋነኛ አጋርና የዋርሶ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት አባላት የነበሩ ሶስት የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት፣ የኔቶ አባል ሀገር በመሆናቸው የምዕራቡን አለም ህብረት ክልል አፍንጫዋ ስር አድርሰውት ነበር፡፡ ራሺያን ከፍ ያለ ችግር ውስጥ የከተታትን ይህን ምስቅልቅል በቁርጠኝነት በመታገል እልባት ያበጁለታል ተብለው በከፍተኛ ተስፋ የተጠበቁት ፕሬዚዳንት ቦሪስ የልሲንም የመሪነት ነገር አለሙን ሁሉ እርግፍ አድርገው ትተው፣ ገና ሰማይና መሬት በቅጡ ሳይላቀቅ፣ ቮድካ በመጨለጥ ጥንብዝ ብሎ መስከርን ስራዬ ብለው የያዙበት፣ በዚህም የተነሳ ጤናቸው ክፉኛ ተቃውሶ ጐምላላው ሞት ከዛሬ ነገ ወሰድኳቸው እያለ የሚያስፈራራበት ወቅት ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ፑቲን ግን ለዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ችግር መፍትሔ ይሆናል ያሉትን መላ አበጅተው በልቦናቸው ይዘው ነበር፡፡ እናም የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ስልጣናቸውን በሙሉ ድምጽ ባፀደቀላቸው የራሺያ ዱማ ፊት ቀርበው ባደረጉት ንግግር እንዲህ አሉ፤ “መንግስት መስራት ያለበትን ስራዎች ሁሉ በዚህ ንግግሬ ዘርዝሬ አልጨርሰውም፡፡ የሆኖ ሆኖ አንድ ነገር ግን በእርግጠኝነት አውቃለሁ፡፡ ከላይ ወደታች ያለው የእዝ ሰንሰለት ሳይጠናከር፣ በመላው ራሺያ መሰረታዊ ስርአት ሰፍኖ ጥብቅ የሆነ ስነምግባር ሳይጠበቅ፣ አንዱ ስራ እንኳ ይሰራል ማለት ዘበት ነው፡፡”
ጠቅላይ ሚኒስትር ፑቲን የሀገራቸውን የራሺያን ነገር ሲያስቡ በእጅጉ የሚቆጩበት ሌላም ጉዳይ ነበራቸው፡፡ ቭላድሚር ፑቲን የሶቪየት ህብረት ዝናና ተፈሪነት ሰማይ በነካበት ዘመን የተወለዱ የሶቪየት ህብረት ወርቃማው ዘመን ልጅ ናቸው። ያኔ እሳቸው በተወለዱበት በ1952 ዓ.ም ሶቪየት ህብረት በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት የናዚ ጀርመንን ጦር ሃይል እንዴት እንዳሸነፈች ዝናዋ አለመጠን ገዝፎ የሚተረክበት ጊዜ ነበር፡፡
ያ ወቅት ሶቪየት ህብረት ስፑትኒክ የተባለችውን መንኮራኩሯን ወደ ጠፈር ያመጠቀችበት፣ ሃይድሮጅን ቦንብን መስራት የቻለችበት፣ ዩሪ ጋጋሪን የተባለውን ጠፈርተኛዋን ወደ ጠፈር በመላክ በዓለም ቀዳሚ የሆነችበት፣ ላይካ የተባለውን ውሻም ወደ ጠፈር በመላክ ከአለም አንደኛ የተባለችበት ወርቃማ የዝናና የክብር ጊዜ ነበር፡፡
በቀጣዮቹ አመታትም በ1956 ዓ.ም በሀንጋሪ፣ በ1968 ዓ.ም ደግሞ በቼኮዝሎቫኪያ የተቀሰቀሰውን “ፀረ - አብዮት” አመጽ፣ ዝነኛውን ቀዩን ጦሯን አለአንዳች ማወላወል አዝምታ ሰጥ ረጭ በማድረግ፣ ባለብረት ክንድ ሀገር መሆኗን ያስመሠከረችበት ወቅት ነበር፡፡
ቭላድሚር ፑቲን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተሾሙበት ወቅት የነበረችው ሀገራቸው ግን በዓለም አቀፉ መድረክ የነበራት ቦታ ከድሮ ዝናና ክብሯ በእጅጉ የራቀ፣ እዚህ ግባ የማይባል ዝቅተኛ ቦታ ነበር፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ፣ በወቅቱ የአለማችን የፖለቲካ መድረክ ራሺያን ከመሪ ተዋንያኖች ተራ አውጥቷት፣ የአለም ህዝብም ረስቷት ነበር፡፡
ለጠቅላይ ሚኒስትር ቭላድሚር ፑቲን እንዲህ ያለው የራሺያ አለማቀፋዊ ሁኔታ መቸም የማይበርድ የእግር እሳት ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እስከተሾሙበት ጊዜ ድረስም ይህን ሁኔታ ለመለወጥ የሚችሉበትን “ቅዱስ አጋጣሚና ቀን” ለዘመናት ሲመኙ ኖረዋል፡፡
ልክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እንደተሾሙም ያ ሲመኙት የኖሩት ቀን እንደመጣላቸው በልባቸው አመኑ፡፡ እናም አንዳችም ጣጣ ሳያበዙና በዲፕሎማሲያዊ አነጋገር ነገር ሳያወሳስቡ ለዱማው እንዲህ በማለት እቅጩን ተናገሩ፣ “ራሺያ ለአያሌ ዘመናት ገናናና ታላቅ ሀገር ሆና ኖራለች፡፡ ወደፊትም ትኖራለች፡፡ የራሺያ የግዛት አንድነት ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ  አይደለም፡፡ የግዛት አንድነታችንን በሚዳፈር በማንኛውም አካል ላይ ጠንካራ እርምጃ እንወስዳለን፡፡ በቀድሞው የሶቭየት መሬትም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ላይ ህጋዊ የሆነ የብሔራዊ ጥቅም ጥያቄ ሁሌም ቢሆን አለን፡፡ በዚህ ረገድ የብሄራዊ ጥቅም ማስጠበቂያ ክንዳችን ለአፍታም ቢሆን መዛል የለበትም፡፡ እኛ የምናቀርበው ጥያቄም ሆነ አስተያየት በሌሎች ዘንድ ተንቆ ችላ እንዲባል መቸም ቢሆን መፍቀድ የለብንም፡፡”
ይህ ንግግር ቭላድሚር ፑቲን የራሺያን የውስጥና የውጪ ችግሮች ያስወግዳል ብለው አምነውበት ያወጡት እቅድ ዝርዝር መግለጫ ነው፡፡ ይህንን ንግግራቸውን ያደረጉትም በምስጢርና ለቁልፍ የስራ ባልደረቦቻቸው ብቻ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ለመላው ዓለምም ጭምር እንጂ፡፡
ይህ የፑቲን እቅድ በእጅጉ የተስማማት የመሰለችው የራሺያ የስልጣን አድባርም ከፍ ባለ ልግስና ፊቷን አዙራላቸዋለች፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ወደ ፕሬዚዳንትነት ስታሸጋግራቸው የመንፈቅ ጊዜ እንኳ አልፈጀባትም፡፡ ከ2008 እስከ 2012 ዓ.ም በፕሬዚዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ የስልጣን ዘመን ለሁለተኛ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከማገልገላቸው በቀር እነሆ ዛሬም ድረስ የፕሬዚዳንትነት ስልጣኑን ባርካላቸዋለች፡፡
ቭላድሚር ፑቲን በንግግራቸው በግልጽ እንዳስቀመጡት፤ የሀገር ውስጥ ፖሊሲያቸው በምድረ ራሺያ መረጋጋትን ማስፈንና ጠንካራ ከላይ ወደታች የሚፈስ የእዝ ተዋረድን ማረጋገጥ ላይ ሲያተኩር፣ የውጭ ፖሊሲያቸው ደግሞ በዋናነት ራሺያን ወደ ቀድሞ ገናና ዝናና ክብሯ በመመለስ፣ በዓለም አቀፍ የፖለቲካ መድረክ መሪ ተዋናይነት ዳግመኛ መመለስን ዋነኛ ግቡ ያደረገ ነው፡፡
መላው ዓለም ያኔ እንዲያ በግልጽና በዝርዝር የወደፊት እቅዳቸውን ያቀረቡበትን ንግግር በጥሞና አዳምጧቸውና አስታውሶት ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ ጦራቸውን ወደ ዩክሬን ሲያዘምቱ አይቶና ሰምቶ ክፉኛ ባልደነገጠ ነበር፡፡
ቭላድሚር ፑቲን ግን የስልጣን ዘመናቸውን አሀዱ ብለው ከጀመሩበት በነሐሴ 16 ቀን 1999 ዓ.ም ጀምሮ፣ ከመስከረም 11 ቀን 2001 ዓ.ም የአሜሪካ የሽብር ጥቃት እስከ አሁኑ የዩክሬን አብዮት ድረስ ከላይ የጠቀስኳቸውን የሀገር ውስጥና የውጭ ፖሊሲያቸውን ለማሳካት፣ ታሪክ የፈጠረላቸውን አጋጣሚዎች ሁሉ አለአንዳች ማመንታት ለመጠቀም ሞክረዋል፡፡ ስልጣናቸውን ለመቀናቀን ሞክረዋል ከተባሉት የቀድሞው የራሺያ ቁጥር አንድ ከበርቴ ሙሚካኤል ኮዶሮቭስኪ እስከ የቸቺኒያ አማጺያን ድረስ ያሉትን “አፈንጋጮች” እንደ ብረት በጠነከረው ክንዳቸው ልክ በማስገባት የሀገር ውስጥ መረጋጋት ፈጥረዋል፡፡
በዓለም አቀፍ የፖለቲካ መድረክ ላይም ከሁለተኛው ዙር የኢራቅ ወረራ እስከ ሶሪያ ህዝባዊ አመፅ ድረስ በተካሄዱት አለምአቀፍ የፖለቲካ መድረኮች፣ ራሺያ ከመሪ ተዋንያኖች አንዱ ሆና መተወን ችላለች፡፡
ይህ ሁሉ ግን የቆፍጣናውና የብሔርተኛውን የፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ልብ ሊሞላው አልቻለም፡፡ የታላቁ አባት ሀገር የሲቪየት ራሺያ ግንባታ በፖለቲካው ብቻ ሳይሆን በግዛትም በደንብ መካሄድ ይኖርበታል፡፡ “በቀድሞው የሶቪየት መሬትም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ላይ ህጋዊ የሆነ የብሔራዊ ጥቅም ጥያቄ ሁሌም ቢሆን አለን። በዚህ ረገድ የብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቂያ ክንዳችን ለአፍታም ቢሆን መዛል የለበትም፡፡” ይህን የቭላድሚር ፑቲን ታሪካዊ ንግግር መቼም ቢሆን ልንረሳው አይገባም፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ የአሜሪካንና የአውሮፓ ህብረትን ዛቻና ማዕቀብ ከምንም ሳይቆጥሩ የዩክሬን አካል የነበረችውና ትውልደ ራሺያውያን የሚበዙባት የክረሚያ ግዛት፣ የታላቁ አባት ሀገር ሶቪየት ራሺያ አባል እንድትሆን ያደረጉት ለምን እንደሆነ በወጉ ልንረዳው የምንችለው ይህን ንግግራቸውን በሚገባ ማስታወስ ከቻልን ብቻ ነው፡፡
እንግዲህ ግራም ነፈሰ ቀኝ፣ ፕሬዚዳንት ፑቲን በዩክሬንና በክሚያ ላይ የፈፀሙት ድርጊት፤ ከዚህ በፊት የአፍሪካ ችግር ብቻ ተደርጎ ይቆጠር የነበረው በተለያዩ ሀገራት ተከፋፍለው የሚኖሩ አንድ አይነት ህዝቦች፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ተጠቃለው ለመኖር የሚያደርጉት ትግል፣ (irridentism) አዲሱ የአለማችን የ21ኛው ክፍለ ዘመን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ሆኖ በዓለም አቀፍ የፖለቲካ መድረክ ላይ ብቅ እንዲል አድርገውታል፡፡
ይህ ጉዳይ ደግሞ በተለይ በባልቲክ ሀገራት ዘንድ ከፍተኛ ጭንቀትን ፈጥሯል፡፡ ይህ ደግሞ አለምክንያት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ላቲቪያና ሊቱዋኒያ ከጠቅላላው በጠቀወላላው ህዝባቸው 30 በመቶ የሚሆኑት ትውልደ ራሺያውን ሲሆኑ በኢስቷኒያ ደግሞ ቁጥራቸው 25 በመቶ ይሆናል። አሁን ትልቁ ጥያቄ የፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቀጣይ እርምጃና የእነዚህ አገሮች እጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚለው ነው፡፡

Read 7249 times