Monday, 07 April 2014 15:21

ፑቲንን በአጭሩ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ፕሬዚደንት ቭላድሚር ቭላድሚሮቪች ፑቲን፤ የፋብሪካ ሠራተኛ ከነበሩት እናታቸው ማርያ ኢቫኖቫ ፑቲና እና የሶቪየት ህብረት ባህር ሃይል ወታደር ከነበሩት አባታቸው ቭላድሚር ስፒሪዶኖቪች ፑቲን ቀድሞ ሌኒንግራድ በመባል በምትጠራው ቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ እ.ኤ.አ ጥቅምት 7 ቀን 1952 ዓ.ም ተወለዱ፡፡
ከመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ በሚገኘው የባስኮቭ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ሌኒንግራድ ዩኒቨርሲቲ አመሩ፡፡ በዚህ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት፣ የአለም አቀፍ ህግና ኢኮኖሚክስ ትምህርታቸውን ከተከታተሉ በኋላ በ1975 ዓ.ም ተመርቀው ወጡ፡፡
ቭላድሚር ፑቲን፤ አባታቸው ያገለግሉበት በነበረው የሶቪየት ህብረት የባህር ሃይል ውስጥ ኬጂቢ ተብሎ ከመቋቋሙ በፊት ኤንኬቪዲ በሚል ይጠራ በነበረው የሶቪየት ህብረት የደህንነትና የስለላ ድርጅት ውስጥ አባል እንደነበሩ ከልጅነታቸው ጀምሮ በሚገባ ያውቁ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የአባታቸውን ፈለግ በመከተል ሰላይ ለመሆን ምንም አይነት ፍላጐት አልነበራቸውም። ያኔ የነበራቸው ከፍተኛ ፍላጐት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ ጀምረውት አለመጠን ፍቅር ባሳደረባቸው የጁዶ ስፖርት በመግፋት፣ በምድረ ሶቪየት ህብረት ከፍተኛ ዝናን መጐናፀፍ ነበር፡፡
የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ በነበሩበት ወቅት ግን እንዲህ ሆነ፡፡ የሶቪየት ህብረት የማስታወቂያ ሚኒስቴር የስለላ ታሪክ ያለው ተከታታይ ፊልም ለህዝቡ በቴሌቪዥን ማቅረብ ጀመረ። እንደማንኛውም የሶቪየት ህብረት ዜጋም ወጣቱ ቭላድሚር ፑቲን ይህንን ፊልም ስራዬ ብለው መከታተል ጀመሩ፡፡ ሳያስቡት ግን በወቅቱ በሶቪየት ህብረት ታዋቂ የፊልም ተዋናይ የነበሩት ቪያችስላቭ ቲኮኖቭና ጆርጂ ዚህዞኖቭ ይተውኑት በነበረው የሰላይ ገፀ - ባህርያት በከፍተኛ ፍቅር ወደቁ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በፊልም እንዳዩዋቸው ሰላዮች መሆን የቀንም ሆነ የለሊት ህልማቸው ሆነ፡፡
በ1975 ዓ.ም ከሌኒንግራድ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው በወጡ ልክ በሁለተኛ ወራቸውም የሶቪየት ህብረት የስለላ ድርጅት ኬጂቢን በጀማሪ ሰላይነት ተቀላቀሉ፡፡ ቭላድሚር ፑቲን ምርጥ ሰላይ ለመሆን የነበራቸው ከፍተኛ ምኞትና ህልም እንዲሁ መና አልቀረባቸውም። በብዙ የኬጂቢ ሰላዮች ዘንድ እምብዛም ባልታየ ሁኔታ የስለላ ብቃታቸውን ማስመስከር የቻሉት ፑቲን፤ ባጭር ጊዜ ውስጥ ትከሻቸውን ለኮሎኔልነት ማዕረግ አበቁት፡፡ ሰውየው በዚህ ብቻ አላበቁም። በ1986 ዓ.ም በያኔዋ ምስራቅ ጀርመን የኬጂቢ ቢሮ ሃላፊ በመሆን ለመሾም ችለዋል፡፡
በ1990 ዓ.ም የያኔዋ ሶቪየት ህብረት ስትፈራርስ፣ ለ16 አመታት በከፍተኛ ብቃት ያገለገሉበትን ኬጂቢን በጡረታ ተሰናብተው በመውጣት፣ በራሺያ የፖለቲካ መድረክ የእጣ ፈንታቸውን ለመሞከር ጓዛቸውን ቀርቅበው ወደ ትውልድ ከተማቸው ወደ ቅዱስ ፒተርስበርግ አቀኑ፡፡
ቭላድሚር ፑቲን የፖለቲካውን አለም ለመቀላቀል ወስነው፣ በ1990 ዓ.ም ማብቂያ ላይ ወደ ሌኒንግራድ ወይም ቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ ያመሩበት እግራቸው እርጥብ ነበር። እዚያ እንደደረሱ በመጀመሪያ ያገኙት በሌኒንግራድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበሩበት ወቅት አስተማሪያቸውና ዋና ወዳጃቸው የነበሩትን አናቶሊ ሶብቸክን ነበር፡፡ ሁለቱ በተገናኙበት ወቅት ደግሞ የቀድሞው መምህራቸው ፕሮፌሰር አናቶሊ ሶብቸክ የቅዱስ ፒተርስበርግ ከንቲባ ነበሩ፡፡ ከአራት ቀናት በኋላም ከንቲባ አናቶሊ ሶብቸክ፣ ቭላድሚር ፑቲንን የአለም አቀፍ ጉዳዮች ዋና አማካሪያቸው አድርገው ሾሟቸው፡፡ ከንቲባ አናቶሊ ሶብቸክ በ1996 ዓ.ም በተደረገው የከንቲባነት ምርጫ በድጋሚ ለመመረጥ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ በመሸነፋቸው ቭላድሚር ፑቲን የአማካሪነት ስራቸውን ለመልቀቅ ተገደው ስራ ፈት ለመሆን በቁ፡፡
ቭላድሚር ፑቲን በስራ ፈትነት ሁለት ወራት ካሳለፉ በኋላ ግን በክሬምሊን ቤተመንግስት የፕሬዚደንታዊ ንብረቶች አስተዳደር መምሪያ ሃላፊ የነበሩት የፓቬል ቦሮዲን ምክትል በመሆን እንዲያገለግሉ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ባስቸኳይ ወደ ሞስኮ እንዲመጡ፣ ፕሬዚደንት ቦሪስ የልሲን ጥሪ አቀረቡላቸው፡፡ መጋቢት 26 ቀን 1997 ዓ.ም ፕሬዚደንት የልሲን፤ ቭላድሚር ፑቲንን ምክትል የቢሮ ሃላፊ አድርገው ሾሟቸው፡፡
በቀጣዩ አመት ሐምሌ 25 ቀን 1998 ዓ.ም ቭላድሚር ፑቲን ከኬጂቢ በኋላ እንደ አዲስ የተቋቋመውና ኤፍኤስ ቢ በመባል የተሰየመው የራሺያ የደህንነትና የስለላ ድርጅት ሃላፊ እንዲሆኑ በፕሬዚደንት ቦሪስ የልሲን ተሾሙ፡፡
በዚህ ሃላፊነት እስከ መጋቢት 29 ቀን 1999 ዓ.ም ድረስ ካገለገሉ በኋላ፣ ነሐሴ 9 ቀን 1999 ዓ.ም እንኳን ሌሎች ራሳቸው ቭላድሚር ፑቲንም ጨርሶ ባላሰቡትና ባልገመቱት ሁኔታ በቮድካ ጨላጭነታቸው የታወቁትና ጤናቸው ከመቸውም ጊዜ በላይ አላወላዳ ያላቸው ፕሬዘደንት ቦሪስ የልሲን፤ የራሺያ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው ሾሟቸው፡፡ ቭላድሚር ፑቲን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተሾሙ አምስት ወር እንኳ ሳይሞላቸው ታህሳስ 27 ቀን 1999 ዓ.ም ድንገት ስልጣናቸውን የለቀቁትን ፕሬዚዳንት ቦሪስ የልሲን በመተካት የራሺያ ጊዜአዊ ፕሬዚደንት ለመሆን ቻሉ፡፡ የፕሬዚዳንትነት ስራቸውን አሀዱ ብለው የቀደሱትም በዚሁ እለት የቀረበላቸውንና ፕሬዚደንት ቦሪስ የልሲን ከነቤተሰባቸው በምንም አይነት የወንጀል ክስ እንዳይጠየቁ የሚደነግገውን ፕሬዚዳንታዊ አዋጅ በፊርማቸው በማጽደቅ ነበር፡፡

Read 3630 times