Monday, 07 April 2014 15:17

ለማይስቅ ውሻ ነጭ ጥርስ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ለማይገላመጥ ዶሮ ቀይ ዐይን ይሰጠዋል!
(የሚጬነ ከናስ አቻ ቦታ እሜስ ዴሬቄነ ኩቶስ አይፌ ዞኡዋ እሜስ)
የወላይታ ተረት

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ደቃቃ ጥንቸል፤ እህል ውሃ ፍለጋ በጫካ ውስጥ ስትዘዋወር፤ አንድ ዝንጀሮ ታገኛታለች፡፡ ጥንቸሏ ግዙፍ ስላልሆነች በየቅጠላ ቅጠሉ ውስጥ እየተሹለከለከች መሄድ እንደምትችል ዝንጀሮ ያውቃል፡፡ ሆኖም አንድ ምክር ሊመክራት ፈልጓል፡፡
“እመት ጥንቸል! የረዥም ጊዜ ወዳጅነታችንን መሰረት በማድረግ ምክር ልለግስሽ እፈልጋለሁ” አላት፡፡
ጥንቸልም፤
“ምን ዓይነት ምክር? ስትል ጠየቀችው”
ዝንጀሮም፤
“ይህን ጫካ አትመኝው፡፡ ሰሞኑን አዳኞች መጥተው ለአውሬ ማጥመጃ የሚሆን ትላልቅ ጉድጓድ ሲቆፍሩ እኔ ዛፍ ላይ ሆኜ አይቻቸዋለሁ፡፡ ስለዚህ ጫካው እንደድሮው ሰላም መስሎሽ ወዲህ ወዲያ አትበይ”
ጥንቸልም፤
“አመሰግናለሁ፡፡ የወጥመዱን የሰሩት ለእኔ አይመስለኝም፡፡ እንደ አንበሳ፣ እንደነብር፣ እንደዝሆን ላሉት እንጂ እንደኔ ቀጫጫ ለሆነ ፍጡር አይደለም፡፡ ባጋጣሚ ጉድጓድ ውስጥ ብወድቅም መውጫ ብልሃት አላጣም!” ትለዋለች፡፡
ዝንጀሮም፤
“እንግዲህ የወንድምነቴን መክሬሻለሁ፡፡ ብታውቂ እወቂበት” አላትና ሄደ፡፡
ጥንቸል እየተዘዋወረች ቅጠል መበጠሷን ትቀጥላለች፡፡ ጥቂት እንደሄደች ዝንጀሮ እንደፈራው አንድ በቅጠል የተሸፈነ ትልቅ ጉድጓድ ውስጥ ሳታስበው ትወድቃለች፡፡ ጉድጓዱ በጣም ጥልቀት ያለው በመሆኑ በጭራሽ በቀላሉ ልትወጣ የምትችልበት አይደለም፡፡ ስለዚህ አላፊ-አግዳሚውን እንዲያወጣት ለመለመን ተገደደች፡፡
“እባካችሁ አውጡኝ፡፡ እባካችሁ እርዱኝ!” እያለች መጮህ ጀመረች፡፡ ተኩላ ድምጿን ይሰማና ወደ ጉድጓዱ አፍ ይሄዳል፡፡ አጎንብሶም ወደ ጥንቸሏ ያይ ጀመር፡፡
ጥንቸልም
“አያ ተኩላ! እባክህ ዘወር በል፡፡ ይሄ ጉድጓድ ለሁለታችን አይበቃንም፡፡ አንተ ያለህበት ቦታ እንደበረሀ የሚያቃጥል አየር ነው ያለው፡፡ እዚህ ግን በጣም ነፋሻና ቅዝቅዝ ያለ አየር ነው ያለው፡፡ ለእኔ በጣም ተስማምቶኛል፡፡ ሆኖም ወደዚህ ለመውረድ ብትችልም እንኳን ቦታው አይበቃንም” አለችው፡፡ ተኩላ፤ የጥንቸሏ ንግግር በጣም አጓጓውና፤ “ልውረድስ ብል በምኔ እወርዳለሁ?” ሲል ጠየቃት፡፡
ጥንቸልም
“እዚያ ጉድጓድ አፍ አጠገብ አንድ በገመድ የታሰረ ባሊ አለልህ፡፡ ባሊው ውስጥ ገብተህ በገመዱ ተንሸራተህ መውረድ ትችላለች” አለችው፡፡
ዕውነትም አንድ ባሊ አጠገቡ እንዳለ አየ፡፡ ባሊው ወደታች ሲወርድ ጉድጓዱ ውስጥ ያለው ገመድ ጫፍ ወደላይ የሚወጣ ነው፡፡ እንደ ፑሊ የሚሰራ ገመድ ነው፡፡ ጉድጓድ ውስጥ ያለውን ጫፍ ጥንቸሏ ይዛለች፡፡
አያ ተኩላ ባሊው ውስጥ ገብቶ ቁልቁል ተምዘግዝጎ ሲወርድ ጥንቸል የገመዱን ጫፍ ይዛ ወደ ላይ መጣች፡፡
እሱ እየወረደ፣ እሷ እየወጣች መንገድ ላይ ሲተላለፉ፤ ከት ብላ እየሳቀች፤
“አየህ አያ ተኩላ፤ ህይወት ማለት እንደዚህ ናት፡፡ አንዱ ሲወርድ አንዱ ይወጣል!“ አለችው፡፡
ተኩላ መሬት ሲደርስ ጥንቸሏ ጉድጓዱ አፋፍ ወጣች!
*   *   *
አንዳንድ ሰዎች አንድ ችግር ውስጥ ሲገቡ ሌላውን እዚያ ውስጥ ነክረው እራሳቸውን ማዳን ይችሉበታል፡፡ ተታልለው እዚያ ችግር ውስጥ የሚገቡት ሞኞች የሚሳሳቱት በአልጠግብ ባይነታቸውና እጉድጓዱ ውስጥ እንኳ ያለው ነገር እንዳያመልጠኝ ብለው ሲስገበገቡ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት በርካታ ሰዎች ጉድጓድ ውስጥ ገብተው ቀርተዋል፡፡ ዞሮ ዞሮ ሁለቱም ለሀገርና ለህዝብ አይጠቅሙም፡፡ አደጋን ከሩቅ አይተው የሚያስጠነቅቁ እንደ ዝንጀሮው ያሉ አስተዋዮች ቢኖሩም እህ ብሎ የሚያዳምጣቸው ሰው አያገኙም፡፡ ባንዱ እግር ሌላው እየገባ፣ ህይወት ትቀጥላለች፡፡
ማይ ግሪንፊልድ የተባለ ፀሐፊ፤
“ታሪክ ራሱን ይደግማል፤ ይላል ታሪከኛ ሁሉ
እኔን ያሳሰበኝ ግና፣
ታሪክ በደገመ ቁጥር፣ ዋጋው ይብስ መቀጠሉ” ይላል፡፡ የሚያስከፍለን ዋጋ እየባሰ የሚመጣው እኛ ከታሪክ ለመማር ባለመቻላችን ነው፡፡ የቀደመው የሰራውን ስህተት የኋለኛው ይደግመዋል - ያውም በዚያኛው እየሳቀ፣ እየተሳለቀ! “በእገሌ ጊዜ የተበደላችሁ እጃችሁን አውጡ!” እያለ፡፡ ከንቲባዎች ተቀያረዋል፡፡ አስተዳዳሪዎች ተቀያይረዋል፡፡ ሚኒስትሮች ተቀያይረዋል ወዘተ… ማንም ከማንም አይማርም፡፡ ሁሌ እኔ ከወደቀው የተሻልኩ ነኝ የሚለውን ለማረጋገጥ የቀደመውን እየረገሙ መቀጠል ነው!! በዚህ ዓይነት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እመሰርታለሁ ብሎ ማሰብ ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ ከተነሳው ሹም መውሰድ ያለብንን ደግ ነገር ካላወቅን ከዜሮ እንደ መጀመር የከበደ ነው ጉዟችን፡፡
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጀርመኖች ለንደንን በቦምብ በደበደቡ ጊዜ ሦስት ዓይነት ህዝቦች ተፈጥረው ነበር ይባላል፡፡ 1) የተገደሉ 2) ለጥቂት የተሳቱና 3) በርቀት የተሳቱ፡፡ የተገደሉት ሟቾች ናቸውና ስለአደጋው ወሬ አይነዙም፡፡ ለጥቂት የተሳቱት በሰቀቀንና ስቃዩን በማስታወስ የሚኖሩ ሆኑ፡፡ በሩቅ የተሳቱት ግን ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖቹን ለመዷቸውና ልበ ሙሉ ሰዎች ሆኑ፤ ይለናል ፀሐፊው ማልኮልም ግላድዌል፡፡ ችግርን መልመድ ደፋርና ልበ - ሙሉ ያደርጋል ነው ነገሩ! ከዚህ ተነስቶ ለአገርና ህዝብ መቆርቆር መቻል መታደል ነው፡፡ በዚህ ወቅት ደሞ ማየት፣ በትክክለኛው ቦታ መገኘትና የሚሰሩትን በቅጡ ማወቅ ግዴታ ነው፡፡ ችግርን ለምዶ መተኛት ግን ሌላ ችግር ነው! ሁሉ በጄ ሁሉ በደጄ እያሉ አግባብነት ያለው ተግባር የማይፈፅሙ አያሌ ናቸው፡፡ የተማሩትና የሰለጠኑበት ሌላ የሚሰሩት ሌላ፤ የሆኑም አያሌ ናቸው! ስለግንባታ እያወሩ የማይገነቡ ከአፈረሰ አንድ ናቸው፡፡ መንገድ ሰርቶ በቅጡ ሳንሄድበትና ሳናጣጥመው ከፈረሰ ወይ ሰሪው በቅጡ አላበጀውም፣ ወይ ሂያጆቹ መሄድ አይችሉም፣ አሊያም ሆነ ብለው የሚያጠፉ አሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በቅጡ ራስን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ “የነቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ”ንም ልብ ማለት መልካም ነው፡፡ ሁሉን በውል በውሉ ካላስቀመጥንና ታማኝነትን ብቻ መለኪያ እናድርግ ካልን የተወዛገበ አካሄድ ውስጥ እንሰረነቃለን፡፡ እመጫት እንደ በዛው ፅሁፍ ከዋናው ማረሚያው ይበረክታል፡፡ ከተቃወምንም ዕድሉን ባግባቡ እንጠቀም፡፡ እንዳያማህ ጥራውንም እንተው! በእጃችን ያለውን በወጉ መጠቀም ያስፈልጋል በሁሉም ወገን፡፡ አለበለዚያ “ለማይስቅ ውሻ ነጭ ጥርስ፣ ለማይገላምጥ ዶሮ፣ ቀይ ዐይን ይሰጠዋል” የሚለው የወላይተኛ ተረት ይመጣል፡፡ “ቆሎ ለዘር፤ እንዶድ ለድግር አይሆንም” እንደሚባለው ማለት ነው፡፡    

Read 4609 times Last modified on Monday, 07 April 2014 15:21