Monday, 31 March 2014 11:37

የምድር ገሃነም - ቀን በቀን እየፈረሰች የምትገኘው ሶርያ

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(5 votes)

አልአሳድ “የጠፈር ምርምር ማዕከል አቋቁሜያለሁ” እያሉ ነው!
ዮሐንስ ሰ.

       ከሶስት አመት በላይ በዘለቀው የሶሪያ የእርስ በርስ እልቂት፣ እስካሁን ከ150 ሺ በላይ ሰዎች ተገድለዋል። በአመት ሃምሳ ሺ መሆኑ ነው። በየሳምንቱ ወደ አንድ ሺ ገደማ ሰዎች በእርስ በርስ ጦርነት ይሞታሉ ማለት ነው። ከ23 ሚሊዮን የአገሪቱ ዜጎች መካከል፣ በእርስ በርስ ጦርነቱ የተፈናቀሉ ሶስት ሚሊዮን ያህል ሶሪያውያን ድንበር አቋርጠው ተሰደዋል። ግን፤ እነዚህ ብቻ አይደሉም የተፈናቀሉት። ከስድስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች፣ ቤት አልባ ሆነዋል። በጦርነቱ ያልተለበለበ አካባቢ፣ ያልፈራረሰ ከተማ፣ ያልተበተነ ቤተሰብ ማግኘት ያስቸግራል። ከ10 ሶርያዊያን መካከል አራቱ፣ ወይ አገር ጥለው ተሰደዋል፤ አልያም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው መውደቂያ ፍለጋ የሚባዝኑ ሚስኪኖች ሆነዋል።
መጥፎነቱ ደግሞ የሶሪያውያን ሰቆቃ በዚህ ያበቃ ይሆናል የሚል ተስፋ የለም። በእርግጥ የበሽር አልአሳድ መንግስት ተዳክሟል፤ አውሮፕላኖችንና ታንኮችን ቢያዘምትም አንድ ሶስተኛ ያህል የአገሪቱን ክልል ብቻ ነው መቆጣጠር የቻለው። በደርዘን የሚቆጠሩ አማፂ ሃይሎች፣ በአብዛኛውም ከአልቃይዳ ያልተሻሉ አክራሪና አሸባሪ ድርጅቶች ሌላውን የአገሪቱ አካባቢ ተቀራምተውታል።
ሰሜናዊና ምስራቃዊ የአገሪቱን ክፍል፣ የተለያዩ አማፂ ቡድኖች የተቀራመቱት ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ከስማቸውና አይነታቸው ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለይቶ ለማወቅ የሚያስቸግሩ በርካታ ታጣቂ ቡድኖች፤ በዋና ከተማዋ ደማስቆ ዙሪያ ሳይቀር መንደሮችንና ከተሞችን ተቆጣጥረዋል። ለመዲናይቱ በጣም ቅርብ ከመሆናቸው የተነሳ የፕሬዚዳንቱን መኖሪያ ሰፈር ሳይቀር በሞርታር ይደበድባሉ።
ነገር ግን፤ አማፂ ቡድኖች ድል በድል እየሆኑ ነው ማለት አይደለም። በተቃራኒው፣ ካለፈው አመት ወዲህ ግስጋሴያቸው ቆሟል ማለት ይቻላል። በውጊያ ማሸነፍና የሚቆጣጠሩትን አካባቢ ማስፋፋት አቅቷቸዋል። አሁን አሁን ደግሞ፣ ሽንፈትን ማስተናገድ ጀምረዋል። ከደማስቆ በመቶ ኪሎሜትር ዙሪያ እስከ ሊባኖስ ድንበር ድረስ ለሁለት አመታት ያህል የተቆጣጠሯቸው ቁልፍ የመተላለፊያ ከተሞችን ከጥቃት መካላከል አቅቷቸው በውጊያ ተነጥቀዋል።
አማፂ ቡድኖች እንደሚሉትና የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት እንደዘገቡት ከሆነ፤ የበሽር አልአሳድ መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከደማስቆ በስተሰሜን ድል የቀናው፤ ከኢራቅ እና ከሊባኖስ በመጡ ተዋጊዎች እርዳታ ነው። መንግስትን ለማገዝ ከጎረቤት አገራት ከመጡት 8ሺ ገደማ ታጣቂዎች መካከል፣ ግማሽ ያህሉ ከሊባኖስ የመጡና ሄዝቦላ የሚመካባቸው ተዋጊዎች ናቸው። ግን፣ እልል የሚያስብል ድል አይደለም። ከደማስቆ በስተደቡብ፣ አማፂ ቡድኖች ከሳምንት በፊት ባካሄዱት ዘመቻ በመንግስት ስር የነበሩ ከተሞችን ወረዋል። እናም፤ ከደማስቆ በ300 ኪሎሜትር ርቀት የሚገኙ አካባቢዎችና ከተሞች የመንግስት ጠንካራ ይዞታ ናቸው ቢባሉም፤ የመንግስት ወታደሮች ከከተማ ከተማ እንደልብ መንቀሳቀስ አይችሉም። በየመሃሉ በአማፂ ቡድኖች ቁጥጥር ስር የወደቁ በርካታ አካባቢዎች አሉ - ለደማስቆ ቅርብ የሆኑ። ከደማስቆ ራቅ ያሉ የሰሜንና የምስራቅ አካባቢማ (ከአገሪቱ ጠቅላላ ስፋት ግማሽ ያህሉ) ሙሉ ለሙሉ በአማፂዎች እጅ ገብቷል ማለት ይቻላል።
እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው፤ ፕሬዚዳንት በሽር አልአሳድ፤ ሰሞኑን ታላቅ የምስራች ዜና ይዘው ብቅ ያሉት። ከቅርብ እስከ የሩቁን ሕዋ የሚያጠና የሶሪያ የጠፈር ምርምር ኤጀንሲ እንደተቋቋመ በአገሪቱ የመንግስት ቴሌቪዥን የተዘገበው በታላቅ የፌሽታ ስሜት ነው። የብዙ መቶ ሺ ወይም የሚሊዮን ኪሎሜትሮች ርቀት አቋርጬ ጨረቃንና ፕላኔቶችን ለማጥናት የምርምር ማዕከል አቋቁሜያለሁ የሚለው የአልአሳድ መንግስት፤ ከደማስቆ ጥቂት መቶ ኪሎሜትሮችን ርቆ መጓዝ ያቃተው መሆኑ ነው ነገሩን የቅዥት አለም የሚያስመስለው። በደርዘን የሚቆጠሩት አማፂዎች እርስ በርስ እየተጨፋጨፉለት ቢሆንም፤ መንግስት ይዞታውን ማስመለስ አልቻለም። ምን አለፋችሁ? አገሪቱ ጤና የላትም ቢባል ሳይሻል አይቀርም። ከመንግስት ወታደሮች ጋር የሚዋጉት አማፂ ቡድኖች፤ እርስ በርሳቸውም ይተራረዳሉ።
የአማፂ ቡዱኖቹ ለቁጥር ያስቸግራሉ። አይነታቸውና ስማቸው ብዙ ነው። ከእነዚህ መካከል በደርዘን የሚቆጠሩ አማፂ ቡድኖች፣ በተወሰነ ደረጃ ለመተባበር ግንኙነት ፈጥረዋል - ነፃ የሶርያ ሠራዊት በሚል ስያሜ። ትብብር ውስጥ ሳይገቡ በየፊናቸው የሚዋጉ አማፂ ቡድኖችም ጥቂት አይደሉም። በስተሰሜን ጫፍ የኩርድ ተወላጆች በሚበዙበት አካባቢም በርካታ አማፂ ቡድኖች ተቋቁመዋል። ከእነዚህ በቁጥር የማይተናነሱ ሌሎች ቡድኖች ደግሞ፣ የሃይማኖት አክራሪነት ላይ የተመሰረቱ ናቸው - አንዳንዶቹም በአልቃይዳ የሚታገዙ። በዚያ ላይ፤ ሶሪያንና ኢራቅን በአንድ እስላማዊ ግዛት ለማጠቃለል ታጥቆ የተነሳው አይኤስአይኤስ የተሰኘ እጅግ ነውጠኛ ቡድንም አለ። በቀድሞ የኢራቅ ወታደሮች መሪነት የሚንቀሳቀሰው ይሄው ቡድን፤ በአብዛኛው ከተለያዩ የውጭ አገራት በመጡ አክራሪ ተዋጊዎች የተዋቀረ ነው። እነዚህ ሁሉ፤ ከመንግስት ጋር እና እርስ በርሳቸው ይጨፋጨፋሉ። በዚህም ነው በየሳምንቱ አንድ ሺ ገደማ ሶሪያውያን የሚሞቱት። ይህም ብቻ አይደለም። አማፂ ቡድኖች በየፊናቸው ከጠቅላላ አገሪቱ ስፋት ሁለት ሶስተኛ ያህሉን ቢቆጣጠሩም፤ የምር ሲታይ ግን በመድፍና በቦምብ የተቦዳደሱ ግንቦችን፣ በአውሮፕላን ድብደባ የተቆፋፈሩ ከተሞችን በአጠቃላይ የፍርስራሽ  ክምሮችን ነው የተቆጣጠሩት።
የሶርያ የእርስ በርስ ጦርነት በአለማቀፍ ደረጃ እልባት የሌለው ተስፋ አስቆራጭ እልቂት ለመሆን የበቃው አለምክንያት አይደለም። ከጤናማዎች ተርታ ሊመደብ የሚችል ቡድን ብርቅ በሆነበት አገር፣ ፀበኛ ወገኖችን ለማደራደርና ለማስታረቅ መሞከር ከንቱ ድካም ነው። አንዱን ወገን ከምር አውግዞ ሌላኛውን ወገን ለማገዝ መሞከርም፤ ከእልፍ ሽፍቶችና ነፍሰገዳዮች መሃል ገሚሶቹን እየቀጡ ገሚሶቹን እንደመሸለም ይቆጠራል። ለዚህም ነው፤ አሜሪካና የአውሮፓ አገራት አንዳች ነገር ለመዘየድ ያቃታቸው። መጀመሪያ ላይ እስራኤልንና አሜሪካን፤ ከዚያም የምዕራብ አገራትንና ክርስትያኖችን በጠላትነት በመፈረጅ ራሳቸውን የሙስሊሞች አለቃ አድርገው ለመሾም ሲሞክሩ የነበሩ አፋኝና አምባገነን አልያም አክራሪና አሸባሪ ቡድኖች፤ ዛሬ ዛሬ “ሺአ ሙስሊም” እና “ሱኒ ሙስሊም” በሚል እየተቧደኑ ይገዳደላሉ።
የሃይማኖት አክራሪነት መጨረሻ ይሄው ነው። ከ700 አመታት በፊት “ሙስሊም” እና “ክርስትያን” ብሎ በማቧደን ጦርነቶችን ያስከተለው የክርስትና አክራሪነት፤ የኋላ ኋላ “ካቶሊክ”፣ “ኦርቶዶክስ” እና “ፕሮቴስታንት” ወይም “ሉተራን” ብሎ ወደተቧደነ ግጭትና እልቂት እንዳመራ ይታወቃል። አሁን በዘመናችንም የሃይማኖት አክራሪነት እንደ ድሮው ተመሳሳይ ውጤት ሲያስከትል ይታያል። የሶሪያ አማፂ ቡድኖች፣ ለማመን በሚከብድ ሁኔታ “ሺአ” እና “ሱኒ” የሚለውን ጥላቻ ከማቀጣጠላቸው የተነሳ፤ የሟቾችን አስከሬን እየነከሱ ፎቶ እስከመነሳት ደርሰዋል።
በአልቃይዳ የሚደገፉ አንዳንዶቹ ቡድኖች፤ በውጊያ አንዳች ከተማ ወይም መንደር ሲቆጣጠሩ፤ ለአፍታ ያህል እረፍት ለማድረግ ፈቃደኛ አይደሉም። ነዋሪዎችን ወደ ማሳደድ ይገባሉ። ታዲያ ከሁሉም በፊት ኢላማቸውን የሚያነጣጥሩት በክርስትያኖች ላይ አይደለም - የሺአ ሙስሊሞች ላይ ነው። የሺአ ሙስሊም ብለው በጠላትነት የፈረጇቸውን ሰዎች ከፊሉን ገድለው፣ ከፊሉን አስረው፣ የቀረውን ደግሞ ከመኖሪያው ነቅለው ከአካባቢው ካባረሩ በኋላ ነው፤ ክርስትያኖችን ማሳደድ የሚጀምሩት። ከዚያ በኋላ ደግሞ “ለዘብተኛ የሱኒ ሙስሊሞች” ላይ ይዘምታሉ። ሂዝቦላ ከሊባኖስ የላካቸው ወታደሮችን ጨምሮ፣ ከበሽር አልአሳድ መንግስት ጎን ለመሰለፍ የመጡ ተዋጊዎች ደግሞ፤ በተቃራኒው ኢላማቸውን በቅድሚያ የሚያነጣጥሩት “የሱኒ ሙስሊሞች” ላይ ነው።
እንዲህ ናላው በተቃወሰ አገር ውስጥ ማንን አውግዞ ማንን መደገፍ ይቻላል? ለጤነኛ ሰው አስቸጋሪ ነው። ግን የማይቸገሩ አልጠፉም። በሊቢያና በግብፅ፣ በቱኒዚያና በባህሬን የተካሄዱ አመፆችን በማወደስ ስትደግፍ የነበረችው ኢራን፤ በሶሪያ ዋነኛ የአመፅ ተቃዋሚ በመሆን ለአልአሳድ መንግስት አለኝታነቷን ለመግለፅ ቅንጣት አላመነታችም። ለምን? “የሺአ ሙስሊም” በሚል ስሜት ነው። የሂዝቦላ አሰላለፍም ተመሳሳይ እንደሆነ ይታወቃል። በአረብ አገራት የተካሄዱትን አመፆች በመቃወም የምትታወቀው ሳውዲ አረቢያ ደግሞ፤ በሶሪያ የአማፂዎች ዋና ደጋፊ ሆናለች። ለምን? “የሱኒ ሙስሊም” በሚል ስሜት ነው። የሶሪያ ነገር፣ ከቅዠት አለም ያልተናነሰ እልባት የማይገኝለት ተስፋ ቢስ የእልቂት አለም ነው ቢባል ምን ይገርማል?
ይሄው ቅዠት አልበቃ ብሎ፤ በሽር አልአሳድ ደግሞ ሌላ ቅዠት ጨመሩበት - የጠፈር ምርምር ማዕከል አቋቁሜያለሁ በሚል አዋጅ ፌሽታ ለመፍጠር ሞከሩ። ሌላስ ምን ቀራቸው? አባታቸው ሲሞቱ ተተኪ ሆነው ስልጣን የያዙት በሽር አልአሳድ፤ ፕሬዚዳንት ለመሆን የገጠማቸው ችግር አንድ ነገር ብቻ ነበር - የፕሬዚዳንቱ እድሜ ከ40 በላይ መሆን አለበት የሚለው ህግ። ያንን ችግር ለማስወገድ አፍታ አልወሰደባቸውም። የእድሜ መነሻ ወደ 34 አመት ዝቅ ተደርጓል ተብሎ ታወጀ። ተገጣጠመ። በወቅቱ የአልአሳድ እድሜ 34 ነበር። እናም ፕሬዚዳንት ሆኑ። ለ30 አመት የገዙ አባታቸውን በመተካት፣ ይሄውና አስራ አምስተኛ የስልጣን አመታቸው ላይ ደርሰዋል። ታዲያ በአባትዬው ዘመንም ሆነ በልጅዬው የስልጣን ዘመን፤ ተቀናቃኝ ተቃዋሚ ፓርቲ ኖሮ አያውቅም፤ አሁንም ክልክል ነው። ቢሆንም ግን፤ በሚቀጥለው ሰኔ በሚካሄደው ምርጫ እወዳደራለሁ ብለዋል - ተወዳዳሪ የሌላቸው ፕሬዚዳንት። በሶሪያ፣ አንዳች ውድድር አለ ከተባለ፤ ውድድሩ የመጨፋጨፍ ውድድር ብቻ ነው።

Read 8100 times