Monday, 31 March 2014 11:29

የሰሚ ያለህ

Written by  ድርሰት - John O’Hara. ትርጉም - ፈለቀ የማርውሃ አበበ filmethiopia@yahoo.com
Rate this item
(3 votes)

          ከዊልያም ጋር በአንድ ቢሮ ውስጥ ነበር የምንሰራው፡፡ ሥራ አጥ ከመሆን ብለን የተቀጠርንበትና ክፍያውም በጣም ትንሽ የሆነ መስሪያ ቤት፡፡ ሥራም የለም፡፡ እጃችንን አጣጥፈን ስናዛጋ እንውላለን፡፡ ብዙውን ጊዜ እኔ አነብባለሁ፤ዊሊያም ደግሞ ተሽከርካሪ ወንበሩን ወደኋላ ለጥጦ፤ በጀርባው ተንጋልሎ ሲጋራውን እየማገ፤ጢሱ ቢሮውን እስኪሞላው ያቡለቀልቀዋል። እድሜው ሀምሳ ሁለት ገደማ ነው፡፡
አንድ ቀን፤ እንደልማዱ ያለማቋረጥ ‹‹ኡሁ! ኡሁ!›› እያለ ሲያስል ቆይቶ፤አብሬው ምሳ እንድበላ ጠየቀኝ፡፡ ተያይዘን ሄድን፡፡ ደስ የማይል ምግብ ቤት፡፡ ምሳው ከቀረበልን በኋላ፤ ተመግበን እስክንጨርስ አንድ ሁለቴ ብቻ ነው የተነጋገርነው። ከዚያ ግን በድንገት፤ልክ ቡና ሲቀርብልን፤ዊልያም ወደ ኪሱ ዘው ብሎ የኪስ ቦርሳውን መዥርጦ አወጣ፡፡ ደምወዙ ከእኔም በጣም ያነሰ ነውና፤ ሂሳብ ሊከፍል እንደማይሆን እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ አዎ፤ከኪስ ቦርሳው የተጨመዳደደ አሮጌ ፎቶግራፍ መዝዞ፤ እጥፋቶቹን ዘረጋግቶ ፊት ለፊቴ ጠረጴዛው ላይ ሰተረው፡፡ ‹‹ሚስቴ ናት›› አለ፡፡ ‹‹ጥላኝ ከመሄዷ በፊት የተነሳችው ፎቶ፡፡ አሁንማ ከእሱ ጋር ነው የምትኖረው፡፡›› ሌላም ፎቶግራፍ አቀበለኝ፡፡ ‹‹እሷ ደግሞ የበኩር ልጄ ናት፤ ከሁለት አመት በፊት የተነሳችው  ፎቶ ነው፡፡አሁን አስራ ሁለት አመት ሆኗታል፡፡ ከጀርባው የተፃፈውን አነበብከው? ‹ከፍራንኪ - ለፍራንኪ-በፍቅር!› …ፍራንኪ ብዬ ነበር የምጠራት፡፡ ዋናው መጠሪያ ስሟ ፍራንሴስካ ነው።›› ዊልያም በደከሙ አይኖቹ ፈገግ እያለ፤ሲጋራውን ከአንዱ የከንፈሩ ጥግ ወደሌላኛው አዟዙሮና የፊሊተሩን ጫፍ በበለዙ ጥርሶቹ ነክሶ፤ጢሱን በሀይል ወደ ውስጥ ማገው፡፡ ‹‹እና ይኼ ከሁለት አመት በፊት ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ግን መንገድ ላይ ከእናቷ ጋር ሆና አየኋት፡፡ ሁለቱም ሳያናግሩኝ አልፈውኝ ሄዱ፡፡ ግን ሁለቱም አይተውኛል፡፡ እኔም እነሱን እንዳየኋቸው በደንብ አውቀዋል፡፡››
ዊልያም፤ የነገረኝ ታሪክ የፈጠረብኝን ስሜት ተረድቷል፡፡ ምክንያቱም፤ የተረጋጋ የነበረ ድምፁ በቅጽበት የሀፍረት ቅላፄ ቀላቀለ፡፡ እርግጥ ነው ዊልያም ከንፈር የሚመጡለት አይነት ሰው አይደለም፡፡ ራሱን የቻለና ስለ ህይወቱም አንዳችም የማማረር ቃል የማይወጣው ነው፡፡ አጭር፤ ራሰ በራ፡፡ አልፎ አልፎ፤ መላጣው ላይ ላብ ያለ ይመስል፤ በመዳፉ ጀርባ አናቱን ይሞዥቃል፡፡ ከምግብ ቤቱ እየወጣንም እንዲያ ሲያደርግ አይቼዋለሁ፡፡
በቀጣዮቹ ሁለት ተከታታይ ቀናት፤ ከዊልያም ጋር ከዚህ ቀደም በነበረን የግንኙነት መንገድ ቆየን። ጠዋት ስንገናኝ ‹‹እንደምን አደርክ?››፤ ከስራ ስንወጣ ‹‹ደህና እደር›› መባባል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ምሳ አብሬው እንድበላ ጠየቀኝ፡፡ ‹እኔም በተራዬ ምሳ አብረን እንድንበላ ግብዣ እንዳቀርብለት እየጠበቀኝ ነበር ይሆን?› ብዬ አሰብኩ፡፡
ልክ እንደመጀመሪያው ቀን፤ ተመግበን እስክንጨርስ አንዲትም ቃል አልተነፈስንም። ከምሳ በኋላ፤ ሲጋራውን አቀጣጥሎ፤ ትክ ብሎ እየተመለከተኝ ፈገግ አለና፤ ‹‹ትምህርትህን የት ነበር…ማለት እ…ዩኒቨርሲቲ ገብተሀል?›› ብሎ ጠየቀኝ፡፡
‹‹እንደውም›› አልኩት ‹‹ ኮሌጅ አልገባሁም››
‹‹ኦኦኦ!በጣም ይገርማል! ደህና…ስለዩኒቨርስቲ ጊዜዬ እያሰብኩ ስለነበረ ነው፡፡ ኡሁ! ኡሁ! ኡሁ! አየህ፤ በወጣትነቴ ወልጄ ቢሆን ኖሮ፤ አሁን ልጄ ኮሌጅ ለመግባት እድሜው ይደርስ ነበር፡፡በቀጥታ ዩኒቨርስቲ እንዲገባ ነበር የማደርገው፡፡ያውም እኔ ራሴ የተማርኩበት ዩኒቨርስቲ፡፡ አየህ፤እኔ በጣም ጥሩ በሚባለው ዩኒቨርስቲ ነው የተማርኩት - ዬል፡፡ ቡዙውን ጊዜ በአዕምሮዬ የሚመላለሰው ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ? ዩኒቨርስቲ መግባቴ በህይወቴ ውስጥ ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንዳለው። ኡሁ! ኡሁ! ኡሁ! አየህ፤ እኔ የነበርኩበት ክፍል ከአጠቃላይ የዩኒቨርስቲው ዲፓርትመንቶች ሁሉ ከፍተኛ ነጥብ የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች ያሉበት ነበር፡፡ በዩኒቨርስቲው ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ! መቼም ስለ ፓይኔ ዊትኒ ሳትሰማ አትቀርም፤ልክ ነኝ አይደል? ስለ ፓይኔ ዊትኒማ ላታውቅ አትችልም። እይውልህ ፓይኔ ዊትኒ እኛ ክፍል ነበረ፡፡ ከኔጋ ደግሞ የወንድማማች ያህል ነበርን፡፡ አየህ፤ፓይኔ ዊትኒ እኛ ክፍል መሆኑ ብቻ በራሱ ክፍሉን ከሌሎቹ ክፍሎች ሁሉ የላቀ ብቃት ያለው ክፍል ያደርገዋል። የሚገርመው ግን ሌሎችም በጣም ብዙ ‹‹ዕንቁ›› የሆኑ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ባስመዘገቡት አመርቂ ውጤት ደጋግመው ሽልማት የወሰዱ፡፡ ሄንሪ ኮራን ውሰድ፡፡ ሄንሪ ኮራ ማለትኮ ገና እንደተመረቅን ጋዋኑን ሳያወልቅ ነው ኮንግረስ ጽህፈት ቤት እንዲሰራ ስጋጃ ያነጠፉለት፡፡ አየህ፤እሱም እኛ ክፍል ነበረ፡፡ ኡሁ!ኡሁ!ኡሁ!ሌላ…አሁን ባለፈው ምርጫ ከንቲባ የሆነው ዋድስዎርዝ፤ጃሚ ዋድስዎርዝ፡፡ እ…እናም ደግሞ ሀገረ ገዢው ሞሪስ፡፡ በነገራችን ላይ ሞሪስ ፖለቲከኛ ብቻ አይደለም፤እንዴት ያለ ምርጥ ደራሲም ነው መሰለህ፡፡ ኧረ በጣም ብዙ ናቸው፡፡
ኡሁ!ኡሁ!ኡ…እንዴ!...ሁ!የማይረሳውን ረስቼልህ ነበር አንተ! ኡሁ! ኡሁ!የቤሊ ፌሊፕስን አድናቆት! እሱንማ መቼም በሚገባ ታውቀዋለህ፤ ዊልያም ሊዮን ፌሊፕስ! እና ምን እንዳለን ታውቃለህ ? ከሁሉም ክፍሎች የሚወደው የኛን ክፍል ነበር፡፡ እና በምረቃ ፕሮግራማችን ቀን ምን ብሎ እንደመሰከረ ታውቃለህ ስለ እኛ ክፍል? ‹‹ ዕውቀትን በማስረፅ ቅብብሎሹ ሂደት እንዳስተዋልኩት፤ በተቀላጠፈ ግንዛቤያቸውና በትምህርት ውጤታቸው ላቅ ያሉ፤ በተለይም፤አዎን፤ በተለይም፤በዋናውና የአንድ ሰው ትክክለኛ ዋጋና እውነተኛ ስብእና መገለጫ በሆነው የማያሻማ የጋራ መመዘኛችን፤ በተደጋጋሚ መቻላቸውን ያስመሰከሩበት የውጤታማ ተግባራዊ ተሞክሯቸው ፍጥነት በ‹ሮኬት› የጉዞ ተምሳሌት ሊመሰል የሚችል፤ የሚያስደንቁ ለጋ ምሁራን የታቀፉበት ክፍልና እፁብ ድንቅ የትምህርት ዘመን!!›› እህስ?!አየህ የንፅፅሩን ክብደት?እሺ እንግዲህ፤ በስንትና ስንት ሙከራዎች በታማኝነት ተፈትነህ ስታበቃ፤ በአንድ በህዝብ ዘንድ በእጅጉ በተከበረ ሰው አንደበት ‹‹ሮኬት!›› መሰኘት ቀላል ነገር ነው እንዴ ታዲያ? አየህ ለአላማህ ቆርጠህ የተሰለፍክ መሆንህ እስከተረጋገጠ ድረስ፤ከሁሉም በላይ የወጣትነት እድሜ ዘመን ማንም በከንቱ የሚያባክነውና ሲፈልግ የሚያነሳው ሲፈልግ የሚጥለው የቁማር ህይወት ወይም አጉል ቀልድ አይደለምኮ! ኡሁ! ኡሁ! ኡሁ! እና አየህ፤ በወጣትነቴ ወልጄ ቢሆን ኖሮ፤ አሁን ልጄ ኮሌጅ ለመግባት እድሜው ስለሚደርስ ይህን ሁሉ ዘርዝሬ፤ የአለምን ወረትና የሰዎችን ጤዛ ቃል ትነት፣ እምነትና ክህደት ሁሉ ጨምሬ፣ የጽናትን ብርታት አብጠርጥሬ አስረዳው ነበር፡፡
...እናልህ አ..ዎ! ስመ ጥሩው ዊልያም ሊዮን ፌሊፕስ፤ እንዲህ ብሎ አወድሶን ነበር እልሀለሁ። እሱም ራሱ ህይወትን ለመቀየር የሚያነሳሱና አእምሮና መላ ልቦናን በተስፋ የሚመሉ፤ ነገን በመናፈቅ ለመኖር የሚያማልሉ ልበለው ይሆን? እንዴት እንዴት ያሉ ‹ረቂቅ› ኮርሶችን ሰጥቶን ነበር መሰለህ! ዋ! የዛሬን አያድርገውና!  ስለእውነት!በጊዜው በዩኒቨርስቲው ውስጥ ለመታዘዝ በአይታክቴነቱ… በበዛ  አድናቆት የተንበሸበሸ ክፍል ቢኖር የኛ ክፍል ብቻ ነበር፡፡››
‹አሁን ወሬውን ቋጨ› ብዬ ሳስብ፤ለካ ላፍታ ፋታ መውሰዱ ነበርና ቀጠለ…
‹‹ከዚያ ያ መከራ ሲመጣብኝ… ያው መቸም የገጠመኝን መከራ ታውቀዋለህ አይደል?››
‹‹እንደውም››
‹‹እይውልህ፤ እኔ… ኡሁ!ኡሁ! እስር ቤት ገብቼ ነበር አየህ…!›› አለና ሳቀ፡፡ ለዛ የሌለው፤ ጆሮን የሚቧጥጥ ሳቅ፡፡
‹‹በቼክ ማጭበርበር መዘዝ ወህኒ ወርጄ ነበር፡፡ እምልህ… አሁን ይኼን ነገር በግልፅ ላንተ ስለነገርኩህ ምንም አይሰማኝም፡፡ፓይኔ ዊትኒ፤ ሄንሪ ኮራን  ወይም ሌሎቹ ዝነኛና የተከበሩት ስመ ጥሮች ቢሆኑ ይሰማቸው ይሆን ይሆናል፡፡ እነሱማ አያርግባቸው እንጂ ተወንጅለው ድንገት ተጠፍነገው ቢገቡ፤ያው ክሳቸው ከተራው ሰው ስለሚከብድ እንዲህ በቀላሉ በቶሎ ከእስር ላይለቀቁም ይችላሉ፡፡ እናም እኔም አየህ፤ በመታሰሬ ምክንያት ነው ሚስቴ ጥላኝ የሄደችው እልሀለው፡፡›› ዊልያም ከዚህ በኋላ ቃል አልተነፈሰም፡፡ ፀጥ ፤ እረጭ እንዳልን ወደ ቢሯችን ተመለስን፡፡
ዊልያም፤ ማውራት ባሰኘው ጊዜ ሁሉ፤ ላገኘው ሰው ታሪኩን የመዘክዘክ አባዜ ተጠናውቶታል። የሚያወራለት ሰው ማንም ቢሆን ለእሱ ምንም ለውጥ የለውም፡፡ በሌላ ቀን፤ ለሁለተኛ ጊዜ ምሳ አብረን በበላን ሰሞን፤ ለጸሐፊያችን ለሬሊም እንዲሁ ሲዘበዝብ አየሁት፡፡ በማግስቱ ጠዋት ታዲያ፤ ዊልያም ማለቂያና እርባና የሌለው የትዳሩን ወሬ በመጠረቅ ስራ እያስፈታ እንዳስቸገራት፤የወሬዎቹ አርዕስተ ጉዳዮች ተደጋጋሚነትም ክፉኛ እንዳሰለቻት ነገረችኝ፡፡ የሚብሰው ነገር ደግሞ፤የአስራ ሰባት አመት ቀምበጧ አዲሷ ጸሀፊያችን፤ አብራው ፊልም ቤት እንድትገባ ስለጠየቃት ተበሳጭታበታለች፡፡ ‹‹ይኼ ሀተታም! ኮተታም! ቅዥቢ ሽማግሌ! ቢጩ!!›› አለች፡፡
ዊልያም፤ከሥራ የተባረረ ቀን፤በቀጥታ ወደ እኔ ጠረጴዛ መጣ፤ የእንግዳ ወንበሩ ጫፍ ላይ ቁጢጥ ብሎ ‹‹አሀሀሀ!  ታውቃለህ? ከሥራ አባረሩኝ’ኮ! ኮንትራቴን አቋረጡት፡፡›› አለና፤ ድካምና ተስፋ መቁረጥ በደቆሰው የሀዘን ስሜት ቁና ቁና ተነፈሰ። ከዚያም ለመሰናበት እጁን እየዘረጋልኝ፤ ‹‹ይሁና እንግዲህ፤ ኡሁ! ኡሁ! ኡሁ! አየህ፤ አንተን በማወቄ በጣም ደስ የሚል ጊዜ ለማሳለፍ ችያለሁ። ኡሁ! ኡሁ! ምናልባት ከሰሞኑ ለምን አብረን ምሳ አንበላም ታዲያ?›› አለኝ። ሆኖም፤ የእሱንም አድራሻ አልሰጠኝ፤ የእኔንም አልወሰደ፡፡ ሌላው ቀርቶ፤ ከቢሮ ከመውጣቱ በፊት ወደ ራሱ ወንበርም አልተራመደም፡፡ አራት እጆቹን አንጨፍርሮ ወደተገተረው መስቀያ ሄዶ ባርኔጣውን አነሳና ወጣ፡፡ በቃ፡፡ እርግጠኛ ነኝ ደግሜ አላገኘውም፡፡ ብቻ ግን ዊልያም፤ በሄደበት ሁሉ የሚያገኛቸውን፤ የማያውቃቸውን እንግዳ  ሰዎችም ቢሆን፤አብረውት ምሳ እንዲበሉ መጋበዙን ይቀጥል ይሆናል፤ እናም ያንኑ ለኔ የነገረኝን ታሪኩን ማውራቱን!!
 ምንጭ - Great Short Stories of John O’Hara.
The Man Who Had to Talk to Somebody.

Read 3398 times