Monday, 31 March 2014 11:11

“ዛሬ ስለ አባይ የሚፃፈው ቁጭት ሳይሆን ተስፋ ነው”

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(8 votes)

         የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሥራ የተጀመረበትን ዕለት ቆጥሮ የመታሰቢያ፣ የማነቃቂያ፣ የማስተባበሪያ መድረክ በማሰናዳት ግንባር ቀደም ተግባራትን በመፈፀም ለሌሎችም አርአያ የሆነ ዝግጀት በማሰናዳት የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ቀዳሚ ነበር፡፡
በ2004 ዓ.ም አንድ ብሎ የጀመረውና የህዳሴው ግድብ የተጀመረበትን ወቅት የሚዘክር መድረክ ዘንድሮም ለ3ኛ ጊዜ ተግባራዊ አድርጓል፡፡
ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ በተከናወነው ሥነ ሥርዓት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርና ከህዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ጋር በመተባበር እንዳዘጋጁት ተገልጿል፡፡ በዕለቱ የተለያዩ ንግግሮች ቀርበዋል፡፡ አዝናኝና አስተማሪ ፕሮግራሞች ነበሩ። ትችት ሊቀርብባቸው የሚችሉ እውነታዎችም ታይተዋል፡፡
“ዕንባችን የታበሰበት 3ኛ ዓመትን በኪነ ጥበቡ ሥራዎች ለማወደስ ነው መድረኩን ያዘጋጀነው” በማለት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ ብዙ ችግሮች እንደገጠሟት፤ የፈተናዎቹ ዋነኛው ምክንያት አባይ ወንዝን ጨምሮ በተፈጥሮ የታደለች በመሆኗ ምክንያት እንደሆነ፤ አገሪቱ ላይ የሚደርሱት ችግሮች ሁሌም ሕዝቡን ለአንድነት እንደሚያነሳሳው፤ ይህ እውነታ በህዳሴው ግድብ ጅማሬም እንደታየ፤ ለአንድነት፣ ለሠላምና ለልማት ቀናኢ የሆኑ የኪነ ጥበብ ሰዎች ይህንን ጅማሬ ከግቡ ለማድረስ የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሆነ በንግግራቸው አመልክተዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የተወከሉት አቶ ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው፤ ባስተላለፉት መልዕክት በዓሉ በየዓመቱ መከበሩ ብቻ ሳይሆን የግንባታ ሥራውም ከዕለት ማግስት ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበ መሆኑ አስደሳች ነው ብለዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ ክቡር ዶ/ር ደ/ጽዮን ገ/ሚካኤል “የአንድን አገርና ሕዝብ ዕድገት ለማፋጠን የኪነ ጥበብ ሥራ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ታላቅ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር አባላት እያከናወናችሁ ባላችሁት ተግባር ልትኮሩ ይገባል፡፡ ዛሬ ስለ አባይ የምትጽፉት ቁጭት ሳይሆን ተስፋ ነው፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ሚናችሁን ከአገርም ባሻገር ለአፍሪካዊያንና ለተቀረው የዓለም ክፍልም ተደራሽ ማድረግን ዓላማ አድርጋችሁ እንድትሰሩ አደራ እላለሁ” በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በዕለቱ በአማርኛ፣ በኦሮሚኛ፣ በትግሪኛና በጉራጊኛ ቋንቋዎች የተፃፉ የተለያዩ ግጥሞች ቀርበዋል፡፡ በግብፆች ዘንድ በባርነት ይገዙ የነበሩትን እስራኤላዊያን ሙሴ ተልኮ ነፃ እንዳወጣቸው ለኢትዮጵያውያንም “አባይ ሙሴያችን ነህ” በሚል ኃይለ ቃል ያቀረቡት ግጥም ብቻ ሳይሆን ንባባቸው ሽለላ የታከለበት ጭምር በመሆኑ ገጣሚ አበረ አዳሙ የዕለቱን ዝግጅት ልዩ ውበት ሰጥተውታል፡፡
ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ስትጀምር ከተቃዋሚዎቹ አንዷ የነበረችው ሱዳን አሁን ባለሀብቶቿ ቦንድ መግዛት ጀምረዋል፡፡ የዛሬ ዓመት 4ኛ ዓመቱን ስናከብር ግብፃዊያንም ቦንድ ገዝተው የልማቱ አጋር እንደሚሆኑ ተስፋ እናደርጋለን በተባለበት መድረክ ግጥም እንዲያቀርቡ ከተጋበዙት አንዱ ተስፋዬ መኩሪያ “ሦስት ግጥም ነው የማነብላችሁ፡፡ ምክንያቱም አንድም ሦስተኛ ዓመት ስለምናከብር፣ ሁለትም ምስክር በሦስት ስለሚፀና። ሦስትም ነገር በሦስት ከፀናና የህዳሴው ግድብ ሦስት ዓመት ከሞላው ከዚህ በኋላ ያለ ምንም ችግር ስለሚጠናቀቅ” ብሎ ግጥሞቹን አቅርቧል፡፡
ባለቅኔ ታደለ ገድሌ “በ1977 ዓ.ም በአገራችን የተከሰተውን የድርቅ አደጋ በውጭ አገር ሳለሁ በሰማሁበት ወቅት አባይን ርዕስ አድርጌ የፃፍኩት ግጥም ነው፡፡ ግጥሙ በኋላ ላይ የካቲት መጽሔትና አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በተጨማሪም ትምህርት ሚኒስቴር ለ8ኛ ክፍል የአማርኛ መማሪያ እንዲሆን ባሳተመው መጽሐፍ ውስጥም ታትሟል” ያሉትን ግጥም በዕለቱ አቅርበዋል፡፡
አበረ አዳሙ፣ ባዩልኝ አያሌው፣ ተስፋዬ ጐይቴ፣ ትቅደም እንደሻው፣ ተስፋዬ መኩሪያ፣ አንዱዓለም አባተ፣ ሰሎሜ፣ ጌታቸው በለጠ፣ ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ፣ መላኩ፣ ታደለ ገድሌ…ግጥሞችን ሲያቀርቡ፤ አዝመራው ሙሉሰው አስመስሎ በመዝፈን ታዳሚውን አዝናንቷል፡፡ የአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር ክፍል ዘመናዊ የሙዚቃ ባንድም ዝግጅቱን አቅርቧል፡፡
በዕለቱ ዝግጅት ለትችት የሚዳርጉ ነገሮች ነበሩ ወዳልኩት ሃሳብ ልሸጋገር፡፡ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር የህዳሴው ግድብ የተጀመረበትን ዕለት መዘከሪያ መድረክ አዘጋጅቶ ዝግጅት ማቅረብ መጀመሩ ለሌሎችም የጥሩ ነገር ምሳሌ መሆን አስችሎታል፡፡ አባይን ርዕሰ ጉዳዩ አድርጐ በብሔራዊ ሙዚየም የቀረበው የስዕል ኤግዚቢሽን አንዱ ማሳያ ነው፡፡ የህዳሴው ግድብ ግንባታ እያደገ በመምጣቱ ብቻ ሳይሆን ለሥራው አድናቆት የሚሰጡ አካላትም እያደጉ መምጣታቸው እየታየ ደራስያን ማህበሩ ለ3ኛ ጊዜ ያዘጋጀው መድረክ ታዳሚዎች ቁጥር አናሳ መሆን ለምንና በምንስ ምክንያት ነው? ያሰኛል፡፡
የአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ መቀመጫዎች ግማሽ ያህሉ ባዶ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን የዝግጅቱን ታሪካዊነትና ታላቅነት ለማጉላት መሰብሰቢያ አዳራሹን ለማሳመር “ልዩ” ሥራ የተሰራ አይመስልም ነበር፡፡ ከመድረኩ በስተጀርባ በስተቀኝ አሮሬ መንደሮችን በስተግራ አዲስ ሕንፃን የሚያሳይ የሸራ ላይ ስዕል ተሰቅሏል፡፡ ከዚህ በተሻለ ከህዳሴው ግድብ ጋር የተያያዙ ፎቶግራፍ ወይም ስዕል መስቀል አይቻልም ነበር?
የዘመናዊ ሙዚቃ ባንዱ አባላት አለባበስ “ጋባዥህ ቤት ስትሄድ ያማረውንና ጥሩውን ልብስ ለብሰህ ሂድ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር የዘነጉ ያስመስላቸው ነበር፡፡ የሙዚቃ ባንዱ የቆመበትን መድረክም በዕለቱ ከተነጠፈለት ሸራ መሰል ጨርቅ በተሻለ ማስዋብ አይቻልም ነበር ወይ? መድረኩ ላይ ሙዚቃ ሲቀርብ እንኳን ለንግግር አቅራቢዎች የቆመውን ሞደም ከተገተረበት ዘወር የሚያደርገው ሰው የጠፋበት ምክንያትስ ምን ይሆን?
የዕለቱን ዝግጅት በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት ለማስተላለፍ ታቅዶ እንደነበር አመላካች ነገሮች ነበሩ፡፡ በመድረክ መሪውም ተጠቁሟል፡፡ የትላልቅ አገራዊ ርዕሰ ጉዳዮቻችንን መልክ የሚያጠፉ እንዲህ ዓይነት ትናንሽ ነገሮች ስለሆኑ የቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭቱ ቢቀርም የሚቆጭ አይሆንም፡፡ ተጀምሮ ነበር ተቋርጧል ሲባል ስለሰማሁ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ገጣሚ አንዱዓለም አባተ “አለክፉ መንፈስ” በሚል ርዕስ በዕለቱ በቀረበው ግጥም እንዳመለከተው “አይችሉትም፣ አይሰሩትም…” እየተባልንም ለአባይ ግድ ለ3 ዓመት ያህል ዋጋ መክፈላችን፤ ከእቅዱም ከአንድ አራተኛ በላይ ሥራ መስራት መቻላችን በእርግጥም አገራችን በህዳሴ ዘመን ላይ መሆኗን እያረጋገጠልን ያለ ይመስላል፡፡   

Read 8948 times