Monday, 31 March 2014 11:05

“የሞኝ እጁን እባብ ሁለት ጊዜ ነከሰው…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(8 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ዘንድሮ ብሶት የማይሰማበት፣ አቤቱታ የሌለበት፣ ችግር የማይነገርበት ቦታ ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ ነገሮች ለምን በሦስትና በአራት እጥፍ ፍጥነት እየባሰባቸው እንደሚሄዱ ወደ እንቆቅልሽነት እየተቃረበብን ነው። ዓመት አልፎ ዓመት በመጣ ቁጥር “ከተከታዩ ዓመት ይሻላል…” ከማለት አዙሪት መውጣት አለመቻላችን አይገርማችሁም!
አልናገር ችዬም አልናር
የዘመኑን የዘንድሮን ነገር፣
ከመጨነቅ ከመጠበብ በቀር
ያገኘሁት የለም ሌላ ነገር፣
ተብሎ ከዓመታት በፊት የተዘፈነው ልክ ላለንበት ዘመን ሳናውቀው የከረመ ንግርት ቢጤ ይመስላል፡፡
እናላችሁ… በህትመት ሆነ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ከምናነባቸውና ከምንሰማቸው ነገሮች አብዛኞቹ የተለያዩ ችገሮች ናቸው.፡ ሰዋችን እኮ በሚዲያ በኩል… “ኽረ የአገር ያለህ…” የሚለው “ችግርህን አዋየኝ…” የሚለው ሰሚ ሲያጣ፣ “ምነው የአገሬ ልጅ ከፋህሳ!” የሚል አቃፊ ደጋፊ ሲያጣ ነው። እሱን ሊያገለገሉ የተቀመጡት ከ‘እነመፈጠሩም’ ሲረሱት ባገኛት ቀዳዳ…
ጩኸቴን ብትሰሙኝ
ይኸው አቤት አቤት እላለሁ
በደል ደርሶብኝ እጮሀለሁ፣
እያለ ነው፡፡ ሰዋችን…
መሳቁን ይስቃል ጥርሴ መች አረፈ
ልቤ ነው በጣሙን እጅግ ያኮረፈ፣
እያለ ነው፡፡ ይህንን መገንዘብ አሪፍ ነው፡፡ “የምስቀው ለማህበራዊ ኑሮ ብዬ ነው እንጂ ልቤ ቆስሏል…” እያለ ሰሚ ጆሮ ምነው ጠፋሳ!  
እናማ…አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ነን፡፡ ብዙ ነገሮች ከሀዲዳቸው እየለቀቁ የሄዱ ይመስላል፡፡ “ኸረ በቡሩ ሀዲዱን ስቷል፣ ወዳልተሰፈረንበት እየወሰደን ነው…” ሲባል ነገሬ ብሎ የሚሰማ ጠፍቷል፡፡
ከውሀ ብጠጋ ባሀሩ ነጠፈ
ከዛፉ ብጠጋ ቅጠሉ ረገፈ
እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ፣
ተብሏል፡፡ እና አሁንም የሚይዝ የሚጨብጠው ጠፍቶበት፣ ሁሉም ነገር ጫፏን እንኳን መያዝ እያቃተው፣ በሄደበት አቅጣጫ ችግር አድፈጦ እየጠበቀው… አለ አይደል… “እንደ ምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ…” እያለ ነው፡፡ እናማ…ሰዋችን ይሄን ያህል እየተማረረ ምነዋ ሰሚ ጠፋሳ!
የምር ግን እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ስንቱ ሰው አገር ቆርጦ የሚሄደው፣ በመርከብና በጫካ ከአውሬና ከተፈጥሮ ጋር እየታገለ እትብቱ ለተቀበረባት ምድር ጀርባውን ሰጥቶ እየነጎደ ያለው ሁሉም ‘ስለጠገበ’፣ ‘መሥራት እየቻለ ስለሰነፈ’፣ በሰው አገር ‘የሚጠበቀውን መከራና ስቃይ ስላላወቀ’ ብቻ እንዳልሆነ ልብ ይባልልንማ! በአገሩ ላይ እንደ ‘ባለ አገር’ መታየቱ ሲበቃ፣ ነገሮች ሁሉ ከሁለተኛ ዜግነት በታችም ሲያወርዱት…ሲያደናቅፈው “እኔን…” የሚል፣ ሲወድቅ “አይዞህ” ብሎ ደግፎ የሚያነሳ ሲጠፋና ገድገድ ሲባል ጭራሽ ከኋላ የሚገፋ ሲበዛ…ያላየው አገር ቢናፈቀው ምን ይገርማል!
ወሰወሰው፣ ወንዝ እያሻገረ ወሰወሰው፣ አባይ እንዳፈሩ፣ ወሰወሰው፣ ተበትኖ ቀረ ወሰወሰው፣  በየሰው ሀገሩ፣
ተብሏል፡፡ በየሰዉ አገር ተበትኖ የቀረው የመንከራተት አዚም ስላለበት… “የሀበሻ ልጆች እስከ ሦስተኛው ሺህ ዘመን እንደተንከራተታችሁ ትኖሯታላችሁ…” የሚል ‘ይግባኝ የማይጠየቅበት’ እርግማን ስላለበት አይደለም። ችግር ቢበዛበት ነው። መከራ ቢበዛበት ነው፡፡ ‘ባለ አገርነቱ’ ባይከበርለት ነው፡፡
እናላችሁ… ውሀውም ‘እየነጠፈበት’፣ ቅጠሉም ‘እየረገፈበት’ እንደምንም ብሎ “ይሄስ ቀን ባለፈ…” የሚለው ህዝብ ቁጥሩ እየጨመረ ብቻ ሳይሆን እየተባዛ ነው፡፡ ታዲያላችሁ…ችግሩም ሲበዛ፣ ትከሻመ መሸከም ሲያቅተው፣ ጉልበትም ሲደክም…
ሰዋችን…
ሺህ ዘመን አልኖርም እየተጨቃጨቅሁ
ዛሬስ ሲብስብኝ አመረርኩኝ ጨከንሁ፣
የሚል ደረጃ ላይ ይደርሳል፡፡ ነገርዬው…“ካቃተሽ መዋደዱ ያውልሽ መንገዱ…” ነው፡፡
የተሰጠንን አደራ ያልተወጣን፣ ለምናገለግለው ህዝብ ታማኝ ያልሆንን… “ያውልህ መንገዱ…” መባያችን ጊዜያችን በዓመታት ያለፉ መአት አለን፡፡
እናላችሁ…ህዝባችን ወደፊት እንዴት ‘አፍሪካን እንደምናስከነዳ’… ድፍን ዓለም እንዴት ወደ እኛ እንደሚጎርፍ… በተአምራዊ ግስጋሴ የዓዳም ልጆችን እንዴት “ጉድ!” እንድምናሰኝ … ሲነገረው… አለ አይደል… “የዛሬውስ!” እያለ ነው፡፡  
የምር እኮ ኮሚክ ነገር ነው…መሠረታዊ አገልግሎቶች ማግኘት እያቃተን፣ የባክቴሪያ መፈንጫና ‘ነጻ ግዛት’ የሆነው ጨጓራችን የአሲድ ዶፍ እየዘነበበት…ከዓመት ዓመት በእንቁልልጭ ሊያባብሉን ሲሞክሩ አሪፍ ነገር አይደለም፡፡
ግን እኮ ከተነቃቃን ከረምን! “ማሙሽዬ አሁን ዳቦ ስላላገኘህ አታልቅስ፣ ከነገ ወዲያ ቸኮላት ይገዛለሀል…” አይነት ከዓመት ዓመት በ‘ሪሳይከሊንግ’ የሚቀርብ ማባበያ ቀልብ መሳቡ መቅረቱ ይታወቅልንማ!
እናላችሁ…እዚሀ አገር በርካታ ‘መግለጫ ሰጪዎች’ ሊያወቁ ያልቻሉት ሰዉ ስለ ነገ ቸኮላት ለማሰብ የዛሬውን ዳቦ ማግኘት እንዳለበት ነው፡፡
እንግዲህ…ይሄኔ ነው ‘የሚያስብ አእምሮ’ና ‘የማያስብ ጡንቻ’ የሚለየው፡፡ ‘የማያስብ ጡንቻ’ “ውልፍት በላትና የዶሮ ጠባቂ አደርግሀለሁ!” አይነት ቀረርቶ ውስጥ ይገባል…‘የሚያስብ አእምሮ’ ደግሞ “ለካስ ይሄን ያህል ስህተት ውስጥ ገብቻለሁና፣ ይቅርታ…” ብሎ ያበላሸውን ሊያስተካክል ይሞክራል፡፡
የእውነት መንገድ ተሳስቼ
ተቀጣሁ በእውነት ተመርቼ
እውነት ማሪኝ እላለሁ
ይቅርታ እለምናለሁ፣
እንደተባለው…እውነትን “ማሪኝ” ብለን ይቅርታ መጠየቅ የሚገባን ብዙ ነን፡፡ ‘እውነት’ የሚባለው ነገር…አንጻራዊ በሆነበት ዘመን የፀሐይ በምሠራቅ ወጥቶ በምዕራብ የመግባት እውነት የሚሠራው እኛ እስከፈለግን ብቻ በሆነበት ዘመን…
እውነት ማሪኝ እላለሁ
ይቅርታ እለምናለሁ፣
የማለት ድፍረቱን አንድዬ ይስጠንማ!
እናላችሁ…ይሄ የችግርና የብሶት አዙሪት የሆነ ቦታ ላይ ቆሞ፣ ያዘመመው ሁሉ ተቃንቶ፣ የደከመው ሁሉ ተጠናክሮ… አለ አይደል…
ምነው ምነው የአገሬ ልጅ ምነው
ምነው ምነው የእናቴ ልጅ ምነው፣
ወገን መሀል ባይበላስ ምነው
ፍቅር ካለ ትንፋሽም ቀለብ ነው፣
የሚባልባት አገር እንድትሆን… የሚባልለት ዘመን እንዲመጣ እየናፈቅን ነው፡፡
እማሆይ፣ እማሆይ፣ እማሆይ
ፀሎትሽ ተሰማልሽ ወይ
እማሆይ፣ እማሆይ፣ እማሆይ
ስለትሽ ሰመረልሽ ወይ፣
ሲባል… አለ አይደል… አገርም “አዎ ፀሎቴ ተሰምቶለኛል…” “አዎ ስለቴ ሰመሮልኛል…” የምትልበትን ጊዜ እንናፈቃለን፡፡
አባቶቻችን “የሞኝ እጁን እባብ ሁለት ጊዜ ነከሰው፣ አንዴ ሳያይ ሁለተኛ ሲያሳይ” የሚሏት ነገር አለች፡፡ እናማ ሰዋችን አንዴ ‘ሳያይ’ ተነክሶ ይሆናል። ግንላችሁ…‘እያሳየ’ የሚነከስ ሞኝ አለመሆኑን መገንዘብ አሪፍ ነው፡፡ ነገርዬው…
መሳቁን ይስቃል ጥርሴ መች አረፈ
ልቤ ነው በጣሙን እጅግ ያኮረፈ፣
ነው፡፡ ህዝባችን ‘ልቡ በጣም ማኩረፉን’ ማወቁ፣ ጨጓሯው መቁሰሉን መገንዘቡ…
አንተም ላትበጀኝ፣ እኔም ላልበጅህ
አትድረስብኝ፣ አልደርስም ደጅህ
በምንም ነገር አትደልለኝም
እኔን አታስብ አታገኘኝም፣
ብሎ እስከወዲያኛው ‘ከመቆራራጥ’ ያድናል፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ (ዛሬ ‘ስነዘፍን’ ዋልናትሳ!)
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4417 times