Monday, 31 March 2014 10:59

“ግመሎቹም ይጓዛሉ ---- ውሾቹም ይጮኻሉ” የአረቦች አባባል

Written by  ኤልሳቤጥ እቁባይ
Rate this item
(15 votes)
  • በውዝግብ ታጅቦ የገሰገሰው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በሦስተኛ ዓመቱ ዋዜማ
  • የግብፅ ግድቡን የማሰናከል ዓለም አቀፍ ጥረት ቀጥሏል

         የአባይ ውሀ ከሰማኒያ አምስት በመቶ በላይ ከኢትዮጵያ የሚመነጭ ቢሆንም፤ አባይ የግብፅ የብቻዋ ሲሳይ እንደሆነ ሲታሰብና ሲነገር  ኖሯል። ከፖለቲከኞች ዲስኩር በተጨማሪ፣ የግብፅ አፈ-ታሪኮችም አባይን “የብቻችን ፀጋ ነው” እያሉ ለህፃን ለአዋቂው እየተረኩና ከትውልድ ትውልድ እየተሻገሩ ለዘመናት ዘልቀዋል፡፡ “ያለ ግብጽ ፈቃድ አባይን የሚነካ አይኖርም” በሚል ከዘመኑ ቅኝ ገዢ ከእንግሊዝ ጋር የተፈራረሙትን ውልም፤ የአገሪቱ ውድ ሰነድ እንደሆነ ተደርጐ ሲቆጠር ምዕተዓመት ተቆጠረ፡፡  
በ1956 የግብፁ ፕሬዚዳንት ጋማል አብዱል ናስር፣ የአስዋንን ግድብ መገንባት እንደጀመሩ ለአገራቸው አበሰሩ፡፡ ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ፤ ይሄውና  ግብፃውያን እስከዛሬ በየአመቱ ከሚያከብሯቸው ታላላቅ ህዝባዊ በዓላት መካከል አንዱ ሆነ፡፡ ከወንዙ ጉዳትን እንጂ ቅንጣት ጥቅም ሳታገኝ የኖረችው ኢትዮጵያ፤ ውሃውን ስራ ላይ የማዋል ወይም ትልቅ ግድብ የመገንባት አቅም አልነበራትም፡፡ ግን ሽንፈትን ተቀብላ አልተቀመጠችም፡፡ በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈረሙት የአባይ ውሎች ላይ ተቃውሞዋን በተደጋጋሚ ገልፃለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአፄ ሃይለሥላሴ ዘመን መንግስት በአባይ ላይ ትልቁን ግድብ ሳይቀር ለመገንባት የሚረዱ ጥናቶች እንዲካሄዱ ተደርጓል። የኢትዮጵያ ተቃዋሞና እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ እየጠነከረና ብልህነትን እየተላበሰ የመጣው ደግሞ ባለፉት 20 አመታት ነው፡፡ ሁሉንም የወንዙ ተጋሪ አገሮች ያላካተተ የቅኝ ግዛት ውል ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ፣ ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ አዲስ ውል እንዲተካ መጣጣር ጀመረች፡፡ በዚህም የአብዛኞቹን የተፋሰሱ አገራት ይሁንታ ያገኘ “የኢንቴቤ ስምምነት” የተሰኘ አዲስ ውል ተፈረመ። በዚህ መሃል ነው፤ እንደ መሞከሪያ የበለስ ሃይል ማመንጫ ግድብ በጣና ሃይቅ ግድም የተገነባው።  በጥቂቱም ቢሆን ለመስኖ የሚያገለግለው የበለስ ግድብ፤  ከንትርክ ባያመልጥም በአለማቀፍ ደረጃ ትልቅ የውዝግብ ርዕሰ ጉዳይ ከመሆን አምልጧል። እንዲያም ሆኖ፣ የግብጽና የኢትዮጵያ ክርክር አልተቋረጠም፡፡ እንዲያውም እየባሰበት መጥቷል፡፡
ግብፃውያን የቅኝ ግዛት ውሎችን ይዘው ይከራከራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በኢንቴቤ ስምምነት መሰረት ፍትሀዊ የውሀ ክፍፍል ይኑር ትላለች፡፡ የሁለቱ አገራት የዘመናት ክርክር ወደ ተጋጋለ አዲስ ውዝግብ የተሸጋገረው በ2003 ዓ.ም ነው፡፡   
ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ጥቅም የሚውል የታላቁ የህዳሴ ግድብን በአባይ ወንዝ ላይ እገነባለሁ  ስትል አስታወቀች፡፡  የግብፅና የሱዳን ጥቅም ላይ ይህ ነው የሚባል ለውጥ አያመጣም ተብሎ የተጀመረው  የግድብ ግንባታ፣ ሰኞ ሶስተኛ አመቱን ያከብራል፡፡ ባለፉት ሶስት አመታት ግብፅ ግድቡን አስመልክቶ የምትይዛቸው አቋሞች፣ የምትሰጣቸው መግለጫዎች እና የምታንኳኳቸው በሮች ድብልቅልቅ ያሉና እርስ በርስ የሚጣረሱ ቢሆኑም፣ ግብፅ አሁንም ግድቡ እውን እንዳይሆን መጎትጎቷን ቀጥላለች፡፡ ከኢትዮጵያ አቋሞች ጋር ባለፉት ሦስት ዓመታት ጐልተው የወጡ የግብፅ አቋሞችንና እርምጃዎችን እንቃኝ፡፡
ታሪካዊ መብት እና የቅኝ ግዛት ውሎች
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በኢትዮጵያ በኩል ይፋ ከተደረገ በኋላ ጐልተው የወጡ ብዙዎቹ የግብጽ መከራከሪያዎች፤ ከዚያም በፊት ሲሰነዘሩ የነበሩ ናቸው፡፡ አባይ ሲነሳ የሚቀርበው መከራከሪያ በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈረሙ ውሎች ናቸው - የተፋሰሱን አገራት ያላካተቱት  ውሎች ቢሆኑም፡፡ “ግብፅ በአባይ ላይ ታሪካዊና ሕጋዊ መብት አላት፡፡ ኢትዮጵያ  በህዳሴ ግድብ ግንባታ የግብጽን መብት ጥሳለች፡፡ ለግብፅ እና ለሱዳን የውሀ ክፍፍል የሚሰጡ የቅኝ ግዛት ውሎችንም ኢትዮጵያ አፍርሳለች” በማለት ግብፆች የግድብ ግንባታውን ለማስቆም ይጥራሉ፡፡  አብዛኛውን ጊዜ የሚጠቀሱት የቅኝ ግዛት ውሎች ሁለት ናቸው፡፡  በ1929 እንግሊዝና ግብጽ የተፈራረሙት ውል አንዱ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ግብጽ እና ሱዳን በ1959 የተፈራረሙት ውል፡፡  ሰሞኑን ደግሞ “ኢትዮጵያም የቅኝ ግዛት ውሎች አካል ነበረች” ለማለት በሚመስል መንገድ፤ “አፄ ምኒልክ በ1902 ከእንግሊዝ ጋር የተፈራረሙት ውል ተጥሷል” በሚል ኢትዮጵያ ወንዙን ያለግብፅ ፈቃድ ምንም ማድረግ እንደማትችል አስረግጠው እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ ይህን ሀሳብ የሚያራምዱት ወገኖች፣ የግድቡ ግንባታ ግብፅ ላይ ጦርነት ከማወጅ የሚተናነስ አይደለም በማለት  ኢትዮጵያ ግንባታውን እንድታቆም ይሞግታሉ፡፡ መሞገት ብቻ አይደለም፤ የግብፅ ባለስልጣኖች በይፋ የሚነገሩ ድርድሮች እና ጉብኝቶችን ከማድረግ በተጨማሪ ይፋ ያልተደረጉ እንቅስቃሴዎችን እያካሄዱ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ጉዳትን መቀነስ
የሕዳሴን ግድብ ግንባታ ለማስቆም ግብጽ የምታካሂደው ዘመቻ ቀላል ባይሆንም፤ ዘመቻው ይሳካል የሚል እምነት የሌላቸው ቡድኖች በበኩላቸው፤ የራሳቸውን አማራጭ ዘዴ አቅርበዋል። በተለይ “የአባይ ተፋሰስ ቡድን” በሚል የተቋቋመው የግብፃዊያን ቡድን፤ በዩኒቨርስቲ የኢንጂነሪንግ እና የግብርና ፕሮፌሰሮችን፣ የቀድሞ የውሀ እና የመስኖ ሚኒስትሮችን  እንዲሁም ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ ባቋቋሙት የኤክስፐርቶች ቡድን ውስጥ የግብፅ ተወካይ የነበሩ ባለሙያዎችን ያካትታል። ግብፅ የግድቡን ግንባታ የምታስቆምበት ደረጃ ላይ አይደለችም የሚለው ይሄው ቡድን፤ አሁን የሚያዋጣን ድርድሩን የግብፅን ጉዳት በሚቀንስ መንገድ ማስኬድ ነው ይላል፡፡ “ከግብፅ ጥቅም አኳያ ትክክለኛው የድርድር አካሄድ የግድቡን ግንባታ ማስቆም መሆን ነበረበት፤ ነገር ግን ይህ አማራጭ አሁን የለም፡፡ ዘግይቷል፤ ጊዜው አልፏል” የሚሉት የቡድኑ አባላት፤ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ከፅንሰ ሀሳብ ወደ ተግባር ለውጣዋለች በማለት ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ የግብፅ ዓላማና እንቅስቃሴ በግድቡ ምክንያት ሊደርስባት የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ያነጣጠረ መሆን እንዳለበት የሚገልፁት የቡድኑ አባላት፤ ለግብፅ የውሀ ፍላጎት ስጋት የሚሆነው የግድቡ መጠን ስለሆነ የግብፅ መንግስት ኢትዮጵያ የግድቡን መጠን እንድትቀንስ ማግባባት፣ ካልሆነም ጫና ማሳደር እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡
የግብፅ የውሀና የመስኖ ሚኒስትር መሀመድ አብዱል ሙጣሊብም፣ ግብፅ ከታሪካዊ መብቷ እና በቅኝ ግዛት ዘመን ከተሰጣት የውሀ  ኮታ አንዲት ጠብታ አሳልፋ አትሰጥም በማለት በየካቲት ወር በሰጡት አስተያየት፤ የኢትዮጵያን የልማት ፕሮጀክቶች ብንደግፍም ከኢትዮጵያ ጋር መደራደር በቃን ብለው ነበር፡፡ ቱርክ ለግድቡ ግንባታ ባለሙያዎችን ለመላክ ተስማምታለች በማለት ተቃውሞአቸውን የገለፁት እኚሁ ሚኒስትር፤ ቱርክ አለማቀፍ ህጐችን በመጣስና የጐረቤት አገራትን ተቃውሞ ቸል በማለት አታቱርክ የተባለ ግድብ ገንባታ፤ የሶሪያና የኢራቅ ህዝቦችን ለውሀ ጥም ዳርጋለች ብለዋል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ቱርክ አይደለችም በማለት የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ሚኒስትሩ ካጣጣሉ በኋላ፤ ግብፅም ሶሪያ ወይም ኢራቅ አይደለችም በማለት ፎክረዋል፡፡ እንደገና በዚያው ወር  ደግሞ  ኢትዮጵያ  ትልቁን ግድብ በማቆም ሁለት ትንንሽ ግድቦችን በመስራት የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጨት ትችላለች ብለዋል፡፡  
የግብፅ የቀድሞ የውሀ እና የመስኖ ሚኒስትር ግን ያን ያህልም ውጤት አይታያቸውም፡፡ የአባይ ተፋሰስ ቡድን አባል የሆኑት እኚሁ የቀድሞ ሚኒስትር፤ የግብፅን ጉዳት መቀነስ በሚለው ሀሳብ ቢስማሙም፤ በቅርቡ በሰጡት አስተያየት የግብፅን መንግስት “ነፈዝ” ሲሉ አጣጥለዋል፡፡ “በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ግብፅ እየተቀደመች ነው፡፡ ውሳኔዋ በእጅጉ የዘገየና  ውጤት የሌለው ነው” በማለት መንግስትን ሲተቹ፤ “የተፋሰሱን አገሮች አስመልክቶ ግብፅ ያላት መረጃ ያልተሟላና ደረጃውን ያልጠበቀ ነው፡፡ በዚህ መስክ የብቁ ባለሙያ እጥረት ገጥሟታል” ብለዋል። እንዲያም ሆኖ፤ የግድብ ግንባታውን ለማስቆም አልያም ለማስተጓጐል በግብጽ የሚካሄደው ዘመቻ እየጠበበ ሳይሆን እየሰፋ፤ እየሰከነ ሳይሆን በየአቅጣጫው እየተወሳሰበ ሄዷል፡፡ ከውስብስብ ዘመቻዎቹ መካከል አንዱ፣ አለማቀፍ ትኩረት ላይ ያነጣጠረው አቅጣጫ ይጠቀሳል፡፡  
ኢትዮጵያን በዓለማቀፍ ተቋማት መሞገት እና የፋይናንስ ድጋፍ  ማሳጣት
የግድቡን ጉዳይ አለምአቀፋዊ ገፅታ የማላበስ አቅጣጫ በመያዝ፣ ግብፃውያኑ በሚያካሂዱት ዘመቻ ኢትዮጵያ ግድቡን ለመገንባት እንዳትችል የገንዘብ ምንጮቿን ለማድረቅ፣ የቴክኒክ ድጋፍ የሚያሰጡ ወገኖችን ለማሳጣት አለምን እያዳረሱ ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የግድቡን ጉዳይ በአጀንዳ እንዲይዘው ለመገፋፋት ከተጀመረው አዲስ ጥረት በተጨማሪ፤ እንደወትሮው አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋሞች ለኢትዮጵያ ገንዘብ እንዳይሰጡ ጫና የማሳደር ዘመቻም አልተቋረጠም፡፡ ሌላው የዚህ ዘመቻ አቅጣጫ፣ በአውሮፓና በአረብ አገራት ላይ በተለይም በሳኡዲ አረቢያ ላይ ያነጣጥራል፡፡
በግብፅ የአለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የአውሮፓ ክፍል ዋና ፀሀፊ የሆኑት አምባሳደር ጋማል ባዩሚ፤ “የግብጽ ጥረት ለህዳሴው ግድብ የቴክኒክ ድጋፍ የሚሰጡ አገሮች ፣ ኮንትራክተሮች እና ዝንባሌ ያላቸው የአውሮፓና የአረብ ወገኖች ላይ ማነጣጠር አለበት” በማለት ሰሞኑን በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመሳተፍ እንዲያስችላቸው በመከላከያው የነበራቸውን ኃላፊነት የለቀቁት የቀድሞው የግብፅ መከላከያ ሚኒስትርና ፕሬዚዳንት ፊልድ ማርሻል አብዱል ፈታህ አልሲሴ በራሺያ ያደረጉት ጉብኝት ተጠቃሽ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በየካቲት ወር ወደ ጣልያን የተጓዙት የግብፅ የውሀ እና የመስኖ ሚኒስትርም፤ የጉብኝታቸው አላማ እንደተሳካ ሲያስረዱ፤ ጣሊያን የግብፅን ስጋት ተረድታለች፤ ጥረታችን በሌሎች የአውሮፓ አገሮችም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ግብፅ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ሳኡዲ አረቢያ እንድታደራድር መጠየቋን ተከትሎ፤ የአረብ የውሀ ምክር ቤት ሃላፊ መሀሙድ አቡ ዘይድ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደር ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡  የሳኡዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና የኩዌት መንግስታት  ኢትዮጵያ ውስጥ ትልልቅ ፕሮጀክቶች እንዳሏቸው የተናገሩት አቡ ዘይድ፤ በእነዚህ መንግስታት በኩል ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳረፍ መሞከር ትልቅ ውጤት እንደሚያመጣ አምናለሁ ብለዋል፡፡ የአል አህራም የፖለቲካ ጥናቶች ማእከል የአፍሪካ ጉዳዮች ስፔሻሊስት ሀኒ ራስላን በበኩላቸው፤ በሳኡዲ አረቢያና በአሜሪካን መካከል ባለው የዲፕሎማሲ ግንኙነት በኩልም ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ጥረት መደረግ አለበት ይላሉ፡፡
ዲሞክራቲክ ፒፕል ፓርቲ ፣ ኢጂፕሺያን አረብ ሶሻሊስት ፓርቲ እና  ጀስቲስ ፓርቲ የተባሉ የግብፅ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ፣ የግድቡ ግንባታ እንዲቋረጥ ዘ ሄግ ለሚገኘው አለም አቀፍ  ፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ በፓርቲዎች የሚቀርቡ አቤቱታዎችን የማየት ስልጣን የለውም፡፡
የፀጥታ እና የደህንነት ስጋት መፍጠር
የግድቡን ግንባታ የፀጥታና የደህንነት ስጋት ውስጥ መክተት፤ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚዎችን ከግብፅ ጎን ማሰለፍ የሚለው የሚገመት ግን ይፋ ይደረጋል ተብሎ ያልተጠበቀው አቅጣጫ ደግሞ መሀመድ ሞርሲ በስልጣን በነበሩበት ወቅት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ለመነጋገር የተጠራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ፣ ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ የማታቋርጥ ከሆነ አገሪቱ በተለያዩ ወገኖች የተከፋፈለች መሆኗን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ፣ እነዚህን ሀይሎች ከግብፅ ጎን ማሰለፍን እንደ አንድ አማራጭ እንደሚያዩ በቴሌቪዝን የቀጥታ ስርጭት ተላልፏል፡፡ ግድቡን ማጥቃት የሚለው በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት መተላለፉን አስመልክቶ የተለያዩ አስተያየቶች መሰጠታቸው የሚታወስ ሲሆን  ይህም ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር ለመገንባት እየሞከረች የነበረውን የመተማመን መንፈስ የሸረሸረ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡  መሀመድ ሞርሲ፤ በዓመጽ እና በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ የግብፅ የመከላከያ ሚኒስትር ለዋሽንግተን ፖስት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤  ሞርሲ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ከመከላከያ ሃይል ይሰጠው የነበረውን መረጃ በደንብ አይከታተልም ነበር፣ የግድቡን አደገኛነትና አጣዳፊነት አልገባውም፤ ግብፅ በናይል ላይ ያላት ቁጥጥር የብሄራዊ ስትራቴጂካዊ ጥቅም ጉዳይ ነው፤ ከመብቷ በተቃራኒ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ሊፈነዳ የሚችል ጥቃት ነው ብለዋል፡፡
ከተፋሰሱ አገሮች ጋር መተባበር እና አዲስ ናይል መፍጠር
የግብፅ ዋና ዋና መከራከሪያዎችና ዘመቻዎች መልካቸው ባይቀየርም፤ ባለፉት ሦስት አመታት አድማጭን ግራ የሚያጋቡ ዝብርቅርቅ ሃሳቦችና መግለጫዎች ተሰጥተዋል፡፡ ግድቡን በጋራ እንገንባ ከሚለው ግብዣ ጀምሮ፤ የግብፅ ባለሙያዎች ግድቡ አካባቢ ቢሮ ተሰጥቷቸው ሁኔታዎችን ይከታተሉ እስከሚለው ጥያቄ ድረስ በየጊዜው ዥንጉርጉር ሃሳቦች ተደምጠዋል፡፡
ሰሞነኛው ርዕሰ ጉዳይ ደግሞ ከተፋሰሱ አገራት ጋር መተባበር እና አዲስ ናይል እንፍጠር የሚል እቅድ ነው፡፡ ከውጭ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደር ያልቻልነው ከተፋሰሱ አገሮች ጋር ጠንካራ ትብብር ባለመፍጠራችን ነው የሚሉ የግብጽ ባለሙያዎች፤ ጣታቸውን በሁስኒ ሙባረክ ላይ ይቀስራሉ፡፡ ሙባረክ በአረብ ሊግና በአረቡ አለም ተሰሚነት ለማግኘት ለመግኘን  ሲጨነቁ፣ የኢትዮጵያ መሪዎች በተፋሰሱ አገራት ዘንድ ይሁንታ ለማግኘት በርትተው በመስራት ውጤታማ ሆነዋል ይላሉ እነዚሁ ባለሙያዎች፡፡ ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎች በኢንቴቤ ስምምነት ተሰርዘዋል ብላ ከአብዛኞቹ የተፋሰሱ አገራት ጋር ስትፈራረም፤ ሙባረክ ግን ስልጣናቸውን ለማን እንደሚያወርሱ እና ምርጫ እንዴት እንደሚያጭበረብሩ በማሰብ ተጠምደው ነበር የሚሉት ባለሙያዎች፤  አሁንም የተፋሰሱን አገሮች ይሁንታ ለማግኘት ግብፅ መታተር አለባት ሲሉ ይመክራሉ፡፡  
ከሰሞኑ ከወደ ግብፅ እየተሰማ ያለ አዲስ እቅድም ከተፋሰሱ አገራት ጋር አዲስ ናይል የመፍጠር ሀሳብ ነው፡፡ ነጩን ናይል ከኮንጎ ወንዝ ጋር በማገናኘት ከእስከዛሬው በላቀ ሁኔታ ግብፅ በአመት 110 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሀ እንድታገኝ ማድረግ ይቻላል በሚል የቀረበው እቅድ፤ የግብፅን የውሀ ስጋት ይቀርፋል ተብሏል፡፡ አዲስ አባይ እንደመፍጠር ነው በተባለለት በዚሁ እቅድ ላይ ሰሞኑን ጥያቄ የቀረበላቸው የግብፅ የውሀ እና የመስኖ ሚኒስትር፤ ፕሮጀክቱን ከቴክኒክ አኳያ እያጤኑት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ እቅዱን ለማሳካት የበርካታ አገራትን ትብብር ማግኘትና በደቡብ ሱዳን ትልቅ ግድብ መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ይህን  እውን ለማድረግ  የሚሰራው ግድብ ከኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የበለጠ መሆኑን በመጥቀስ ትችት የሰነዘሩ ወገኖች፤ ኢትዮጵያ የህዳሴን ግድብ መጠን እንድትቀንስ እየጐተጐተች ያለችው ግብጽ፤ ከዚያ የበለጠ ግድብ ለመገንባት ጥናት እያካሄደች መሆኗ አስገራሚ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ
የህዳሴ ግድብ ግንባታ በየሳምንቱ ሰባቱንም ቀናት፣ በየእለቱም ሀያ አራት ሰአት እየተሰራ ሲሆን ሰላሳ ሁለት በመቶ ደርሷል፡፡ በተለያዩ መንገዶች ከግብፅ ለሚሰነዘሩ አስተያየቶች እና ለሚካሄዱ ዘመቻዎች ባለፉት ሶስት አመታት ከኢትዮጵያ የተሰጡ ምላሾች ተመሳሳይ ናቸው፡፡  ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ ግብፅን እና ሱዳንን እንደማይጎዳ፣ የግድቡ መጠን እንደማይቀንስ፣ ግንባታው ለሰከንድ እንደማይቆም፣ የግንባታው ወጪም በኢትዮጵያውያን እንደሚሸፈን እና የቅኝ ግዛት ውል በኢንቴቤው ስምምነት እንደተተካ በመግለጽ ነው ኢትዮጵያ ስትከራከር የቆየችው፡፡


Read 6752 times