Monday, 31 March 2014 10:56

ከምዕራብ ሸዋ ዞን መሬት ተቀማን ያሉ የአማራ ተወላጆች ሰሚ አጣን አሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

“ወደ አንድነት ፓርቲ የመጣነው መሬት ያስመልስልናል ብለን አይደለም”
 ስምንቱ በአዲስ አበባ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው አድረዋል  
“ያለ አግባብ የተያዘ መሬት ላይ ሁሌም እግድ ይጣላል” - የዞኑ አስተዳደር
በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን ዳኖ ወረዳ አዋዲ ጉልፋ ቀበሌ፤ የመጡ 29 የአማራ ተወላጅ አርሶ አደሮች “መሬት እንዳናርስ ተከለከልን፤ ቅሬታችንን የሚሰማን አጣን” ሲሉ አማረሩ፡፡ ከ29ኙ ስምንቱ በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ፣ ወረዳ ሰባት ፖሊስ ጣቢያ፣ ረቡዕ ማታ ታስረው ማደራቸውንና ሀሙስ ረፋድ ላይ መለቀቃቸውን አርሶ አደሮቹ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሮቹ አብዛኞቹ ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ ከጎንደርና ከሌሎች የአማራ አካባቢዎች መሸኛ በማምጣት መሬት እንደተሰጣቸው፣ በአዋዲ ጉልፋ፣ በአጂላ ዳሌና በዙሪያው መሬት በማልማት፣ ቤተእምነት በመገንባትና ሌሎት መሰረተ ልማቶችን በመስራት ከ20 ዓመታት በላይ በሰላም እንደኖሩ ገልፀው፣ ከ2004 ዓ.ም ወዲህ ግን በአማራ ተወላጅ አርሶ አደሮች ላይ የመሬት እቀባ እንደተጣለ ተናግረዋል፡፡
አቶ ቢያዝን አበራ የ65 ዓመት አዛውንት ናቸው። ትውልድና እድገታቸው ጎንደር ቢሆንም በመሬት ጥበትና በተፈጥሮ መጎዳት ሳቢያ ወደ ምዕራብ ሸዋ ዞን ዳኖ ወረዳ አዋዲ ጎልፋ ቀበሌ በ1986 ዓ.ም መጥተው መኖር እንደጀመሩ ይናገራሉ፡፡ ላለፉት 20 ዓመታት መሬታቸውን እያረሱ፣ ለመሰረተ ልማት መዋጮ እያዋጡ፣ አካባቢያቸውን እያለሙ ዘጠኝ ልጆቻውን ሲያሳድጉ መኖራቸውን ገልፀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከ2004 ዓ.ም በኋላ ነገሮች እየተቀየሩ፣ የአካባቢው ባለስልጣናት ባህሪ እየተለወጠና በአማራ ተወላጆች ላይ ጫናው እየበረታ እንደመጣ ገልፀዋል፡፡ “በ2004 ዓ.ም የአማራ ህዝብ ከሰፈረባቸው ቀበሌዎች አንዱ በሆነው አጂላዳሌ ቀበሌ፣ ከሰሜን ሸዋ የመጡ የ150 አባወራዎች ቤት በእሳት ጋይቶ ሰዎቹ የት እንደደረሱ ጠፍተዋል” ያሉት አቶ ቢያዝን፤እርሳቸው በሚኖሩበት አዋዲ ጉልፋ ቀበሌም “ለአማራ ተወላጆች ሁለት ሁለት ሄክታር መሬት ይበቃል፤ ቀሪውን ለኦሮሚያ ወጣቶች እንሰጣለን” በሚል መሬታቸውን አርሰው እንዳይበሉ እንዳደረጉዋቸው ተናግረዋል፡፡ “ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከወረዳ ወደ ዞን፣ ከዞን ወደ ክልል አቤት ብለን ሰሚ በማጣታችን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት እና ወደ ፌዴሬሽን ም/ቤት አቤት ብለናል” ያሉት አዛውንቱ፤ “ይህን የሚያደርገው የአስተሳሰብ እጥረት ያለበት ነው፤ ወደ ቦታችሁ ተመለሱ ውሳኔ እንሰጣለን” ብንባልም እስካሁን ምንም ውሳኔ አላገኘንም ብለዋል፡፡ “ጉዳዩ በእንጥልጥል እያለ መጋቢት 8 ቀን 2006 ዓ.ም አንድም በአማራ ተወላጆች የተያዘ መሬት እንዳይታረስና እንዳይዘራ የሚል እግድ ደብዳቤ ወጣብን” በማለት የእግድ ደብዳቤውን በማስረጃነት አቅርበዋል፡፡
ደሳለኝ በላቸው የተባሉት ሌላው የ43 ዓመት ጎልማሳ፤ ከ1978 ዓ.ም ጀምሮ ከአባታቸው ጋር ወደ ናኖ ወረዳ እንደመጡ ገልፀው፣ ከናኖ ወደ ዳኖ የመጡበት ምክንያት በወረዳው ሰዎች በተደረገላቸው የአብረን እንኑር ጥሪ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከደቡብ ጎንደር በልጅነታቸው እንደመጡ የገለፁት አቶ ደሳለኝ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስምንት ልጆችን አፍርተው በሰላም መኖር እንደ ጀመሩ ገልፀዋል፡፡ ከ29ኙ የአማራ ተወላጅ አርሶ አደሮች ጋር በአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ቢሮ ውስጥ በተነጠፈ ጂባ ላይ ተቀምጠው ያገኘናቸው ጎልማሳው፤ በወረዳው ባለስልጣናት ከፍተኛ የመብት ጥሰት እየደረሰ እንደሆነ ገልጸው በአካባቢው ያሉ የመኪና መንገዶችን፣ ቤተ እምነቶችን እና መሰል መሰረተ ልማቶችን ከመሰሎቻቸው ጋር መገንባታቸውን፣ ጠፍ የነበረውን መሬት አልምተው ግብር እየከፈሉ፣ ለመሰረተ ልማትና ለአባይ ግድብ እንደ ማንኛውም ዜጋ እያዋጡ እየኖሩ “አማራ ነህ ፤መሬት አይገባህም” መባላቸውን ተቃውመዋል፡፡
“ትምህርት የሚሰጠው በኦሮምኛ ብቻ በመሆኑ ልጆቻችንን ወሊሶና ወልቂጤ ልከን በስንቅ እናስተምራለን” ያሉት አቶ ደሳለኝ፤ “በወረዳውና በቀበሌው ኃላፊዎች ስብሰባ ተጠርተን ሄደን በኦሮምኛ ተጀምሮ በኦሮምኛ ያልቃል፤ ስብሰባው እኛን የማያሳትፍ ከሆነ ለምን ጠራችሁን ስንል፤ ግዴታችሁ ነው እንባላለን” ብለዋል፡፡
“ይባስ ብለው መሬት ለምን ትቀሙናላችሁ? አብረናችሁ የኖርን፣ አካባቢውን ያለማን ነን ስንል ድብደባና ግርፋት ደርሶብናል” ያሉት አቶ ደሳለኝ፤ በዚህ ሳቢያ ጌጡ ክብረት የተባለ የአጂላ ፉዳሌ ቀበሌ ነዋሪ የአማራ ተወላጅ፣ህግና ፖሊስ ባለበት ተደብድቦ ሞቷል፤ እስካሁን ገዳዮቹም አልተያዙም፤ ክስም አልተመሰረተም” ሲሉ አማረዋል፡፡ ከ20 ዓመት በላይ ኖረን ጥሩ ልማትና ጥሩ ስራ ስንሰራ “ህገ-ወጥ ሰፋሪዎች ናችሁ፤ ወደ ክልላችሁ ሂዱ፤ መሬቱ ለኦሮሞ ወጣቶች ይፈለጋል” ተባልን ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ይሄም ኢትዮጵያዊነታችንን እንድንጠራጠር አድርጎናል ብለዋል፡፡
ለፌዴሬሽን ም/ቤት በተደጋጋሚ አቤት ማለታቸውንና ምላሽ አለማግኘታቸውን የገለፁት አርሶ አደሮቹ፤ በድጋሚም መምጣታቸውን ጠቁመው፤ “የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈጉባኤ ስለሌሉ ወደ ቦታችሁ ተመለሱ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ የመጣችሁት ፌዴሬሽን ም/ቤት ከሆነ እንዴት ወደ አንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት መጣችሁ በማለት ላቀረብነው ጥያቄም፤ “በአገሪቱ መሪ በኢህአዴጋችን ምላሽ በማጣታችን ጉዳያችንን ለኢትዮጵያ እና ለዓለም ሚዲያ እንዲያሰሙልን በሚል ነው የመጣነው” ብለዋል አቶ ደሳለኝ፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአማራ ተወላጅ አርሶ አደሮች ላይ በአካባቢው ባለስልጣናት እየደረሰ ያለው ግፍና በደል ቆሞ፣ መሬታቸውን እንዳያርሱ የተጣለው እግድ ተነስቶ፣ በሰላም መኖር እንደሚፈልጉ የገለፁት አርሶ አደሮቹ፤ይህ ምላሽ የሚገኘውም ከገዢው ፓርቲ እንደሆነ በመጠቆም አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድላቸው ተማፅነዋል፡፡
“ወደ አንድነት ፓርቲ የመጣነው መሬት ያስመልስልናል ብለን አይደለም” ያሉት ሌላው አርሶ አደር፤ በመንግስት በኩል ምላሽ አጥተን መተንፈሻ በማጣታችን ነው ብለዋል፡፡ “የትኛውንም የአካባቢው ተወላጆች የሚያደርጉትን መዋጮ ለአባይ ግድብ፣ ለመንገድ ስራ እያዋጣንና ግብር እየከፈልን ባለበት መሬት እንዳናርስ የታገድንበት ሁኔታ አሳዝኖናል፤ ዜግነታችንና ህልውናችን አደጋ ላይ ወድቋል፤ መንግስት አስቸኳይ መፍትሄ ይስጠን” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ “አሁን ያላችሁበት አካባቢ አትኖሩም ከተባልንም መንግስት ሌላ የምንኖርበት ቦታ ወስዶ እንዲያሰፍረን እንጠይቃለን” ብለዋል፡፡
“በአሁኑ ሰዓት ሰሚ አጥን ስንከራተት የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ተቀብለው ምግብ እና መኝታ እንድናገኝ አድረገውናል፤ ያለ ስንቅ ነበር የመጣነው” ብለዋል፤አርሶአደሮቹ፡፡ ጉዳያቸውን ለጋዜጠኞች አስረድተው ወደ አገራቸው ሲመለሱ፣ አውቶቡስ ተራ አካባቢ ፖሊሶች ለጥያቄ እንፈልጋችኋለን በማለት ቢያዝን አበራ፣ ደሳለኝ በላቸው፣ ኑሮዬ እንድሪስ፣ ፀጋ ዳምጠውና ሌሎች አራት ሰዎችን በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወረዳ ሰባት ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዷቸው የገለፁት አርሶ አደሮች፤ ለምን መጣችሁ፣ ወደ አንድነት ፓርቲ የመራችሁ ማን ነው፣ ከየት ነው የመጣችሁት እና ሌሎች ጥያቄዎች ቀርቦላቸው  መልስ ከሰጡ በኋላ፣ ፖሊስ ጣቢያ አድረው ሀሙስ 3፡30 መለቀቃቸውን  ገልፀዋል፡፡
የምዕራብ ሸዋ ዞን መስተዳድር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቱፋ ቴሶ በበኩላቸው፤ በአማራ ተወላጆች ላይ ደርሷል የተባለውን በደል እንደማያውቁት ገልፀው፣ ችግሮችም ካሉ ለዞኑ ማመልከትና ተበድለናል ያሉት አርሶ አደሮች ተሳታፊ በሆኑበት መንገድ ተወያይቶ መፍታት ይቻል እንደነበር ተናግረዋል፡፡ “ችግሩ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ እንዳለ አላውቅም፣ ወደ ኃላፊነቱ የመጣሁት በቅርብ ነው” ያሉት አቶ ቱፋ፤ ችግራቸውን በተዋረድ ሳያሰሙ ወደ ፌዴሬሽን ም/ቤት መሄዳቸው አግባብ እንዳልሆነና ለዞኑ ያሰሙት ቅሬታ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ “እኛ አማራ ቢሆኑም ከየትኛውም ብሔር ቢመጡም የምናያቸው በወንድምነት ነው“ ያሉት የመስተዳድሩ ጽ/ቤት ኃላፊ፤ አሁንም ቢሆን ችግራቸውን ቀርበው ያወያዩንና በስፍራው ተገኝተን ከወረዳው ኃላፊዎች ጋር ተመካክረን እንፈታዋለን” ብለዋል፡፡
የአማራ አርሶ አደሮች፣ልጆቻችን በአማርኛ ቋንቋ መማር አልቻሉም በማለት ባነሱት ቅሬታ ዙሪያ አቶ ቱፋ ሲመልሱ፤ “በአገር አቀፍ ደረጃ ከአንድ ክልል መጥተው ሌላ ክልል ውስጥ ለሚኖሩ ዜጎች ት/ቤት ተከፍቶ በልዩ ሁኔታ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ እየተደረገ ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን ያለባቸውን ቅሬታ ከዞኑ መስተዳድር ጋር መነጋገር ይኖርባቸዋል” ካሉ በኋላ፣ከዳኖ ወረዳ ወደ ፌደራል መንግስት ቅሬታ ለማሰማት የሄዱ የአማራ አርሶ አደሮች መኖራቸውን የሰሙት በወሬ ደረጃ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
“አርሶ አደሮቹ ከአካባቢው ተወላጅ ተለይተው የሚታዩበት መንገድ የለም” ያሉት አቶ ቱፋ፤ ከመጠን በላይ የያዙት መሬት ካለም ሆነ ያለአግባብ ታግደውና መሬት ተወስዶባቸው ከሆነ፣ ሁሉም በህግና በስርዓት እንደሚታይ ገልፀው፤ ከህግ በላይ የሚሆን ማንም እንደሌለ ተናግረዋል፡፡  
የዞኑ ምክትል መስተዳድር አቶ ከሳዬ ገመቹ በበኩላቸው፤ “የታገደ መሬት ካለም ያለ አግባብና በህገ-ወጥ መንገድ የተያዘ ነው” ካሉ በኋላ ከዚህ ቀደም በዚህ ጉዳይ ቅሬታ ያነሱ ሰዎች እንደነበሩና በዞን፣ በወረዳ፣ በክልል እና ከእምባ ጠባቂ ተቋም ተወካዮች መጥተው ጉዳዩ ውሳኔ አግኝቷል ብለዋል፡፡
በአማራም ሆነ በአካባቢው ተወላጆች ያለአግባብና ከመጠን በላይ የተያዘ ካለ ታይቶ መሬት ለሌለው ይሰጣል፤ የተረፈው ወደ መንግስት የመሬት ባንክ ይገባል ያሉት ምክትል መስተዳድሩ፤ “በህገ-ወጥ መንገድ ያልተፈቀደ መሬት ይዘው ከአማራ ክልል ስለመጡ የተበደሉ አድርገው ማቅረባቸው፣ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨትና ለመከፋፈል ሆነ ብለው የሚያደርጉት ነው ብለዋል፡፡

Read 2936 times