Monday, 31 March 2014 10:55

“አዲስ ትውልድ ፓርቲ” የተቃዋሚ ፓርቲዎች ብሔራዊ ጉባዔ ሊያካሂድ ነው

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(0 votes)

      አዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) የተቃዋሚ ፓርቲዎች ብሔራዊ ጉባዔ በቅርቡ ለማካሄድ ያቀደ ሲሆን ተቃዋሚዎች ልዩነታቸውን አቻችለው ጠንካራ ስብስብስ መፍጠር እንደሚችሉ እምነቱን ገልፆ አገር አቀፍ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጉባኤው ላይ እንዲሳተፉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡ ፓርቲው ሚያዚያ 30  የተቃዋሚ ፓርቲዎች ብሄራዊ  ቀን ተብሎ እንዲሰየምም ጠይቋል፡፡
በጉባኤው ላይ ተቃዋሚዎች በህብረት፣ በጥምረትና በቅንጅት ለመሥራት ያልቻሉባቸው ምክንያቶች እንደሚፈተሹ የጠቆመው ፓርቲው፤ ልዩነቶችን በማጥበብ ጠንካራ የተቃዋሚዎች ስብስብ መፍጠር ይቻላል ብሎ እንደሚያምን  ገልጿል። ከተመሠረተ ጥቂት ዓመታትን ያስቆጠረው አዲስ ትውልድ ፓርቲ፤   ተቃዋሚዎች ልዩነቶችን በማቻቻል በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥያቄ ለመመለስ ይችሉ ዘንድ ለ23 ዓመታት ሊፈጥሩት ያልቻሉትን ጠንካራና አማካይ የተቃዋሚዎች ስብስብ ለመፍጠር ማለሙን አስታውቋል፡፡
በተቃዋሚ ፓርቲዎች ብሔራዊ ጉባዔው ላይ 21 በሚደርሱ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ፅሑፎች እንደሚቀርቡ የጠቆመው አዲስ ትውልድ ፓርቲ፤ ከርእሰ ጉዳዮቹም መካከል “የተሳካና የሰለጠነ የተቃውሞ ፖለቲካ የትግል ስልት እንዴት ይመጣል?”፣ “በኢትዮጵያ ብሄራዊ እርቅና መግባባት እንዴት፣ መቼና የት ይካሄዳል?”፣ “ዲሞክራሲያዊ የመንግስት ለውጥና ሽግግር በኢትዮጵያ መቼና እንዴት ይካሄዳል?”፣ “በኢትዮጵያ ለተቃውሞ ትግል ስኬት የሚበጀው አንድ ጠንካራ ውህድ ፓርቲ? ወይስ የፓርቲዎች ህብረት? ግንባር ወይስ ቅንጅት?” የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በጉባኤው ላይ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በርእሰ ጉዳዮቹ ላይ ጥናታዊ ፅሁፎችን ማቅረብ እንደሚችሉ የገለፀው ፓርቲው፤ በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ ምሁራንም ጥናታዊ ፅሁፎችን እንዲያቀርቡ  ጋብዟል፡፡
አዲስ ትውልድ ፓርቲ፤ ለ22 አገር አቀፍ ፓርቲዎች የውይይት ጥሪ ያቀረበ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ  የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ(መድረክ)፣ አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ(አንድነት)፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) እና ሰማያዊ ፓርቲ እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 2321 times