Saturday, 22 March 2014 12:36

“ፀሐይዋ በደመቀች ጊዜ ድርቆሽህን አድርቅ”

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(2 votes)

               መጋቢት 4 ቀን 2006 ዓ.ም ታትሞ በወጣው ስመ ጥሩው የታይም መጽሔት ላይ ማይክል ሹማን የተባለ ጸሐፊ “Forget BRIC, meet PINEs” (የBRIC ሀገራትን፡- ብራዚል፣ ራሺያ፣ ህንድና ቻይናን እርሷቸውና የPINEs ሀገራትን፡- ፊሊፒንስ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ናይጄሪያና ኢትዮጵያን ተዋወቁ፡፡) በሚል ርዕስ የራሱን የኢኮኖሚ ትንታኔ ያቀረበበትን ጽሁፍ ለንባብ አብቅቷል፡፡
ፊሊፒንስ፣ ኢንዶኔዢያና ናይጄሪያ ይህን የማይክል ሹማንን ወቅታዊ የኢኮኖሚ ትንታኔ ጽሁፍ አንብበው ምን እንደተሰማቸው ወይም ምን አይነት አስተያየት እንደሰጡ አላውቅም፡፡
ዘጠና ሚሊዮን ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱት ኢትዮጵያዊያን ያላቸው የቴሌቪዥን ቻናል አንድ ብቻ ነው፡፡ ይሄው አንድ ለእናቱ የሆነው መንግስታዊው “የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን” እና ሌሎች መንግስታዊና ለመንግስት ልዩ ቀረቤታ ያላቸው የዜና ማሰራጫዎች፣ የማይክል ሹማንን ጽሁፍ ያቀረቡት ከፍ ያለ ትኩረት በመስጠትና ከዋና ዋና ዜናዎቻቸው እንደ አንዱ አድርገው ነው፡፡
እነዚህ የዜና ማሰራጫዎች ለጽሁፉ ከሰጡት ትኩረትና ዜናውን ካቀረቡበት ሞቅ ያለ ስሜት አንፃር በመመዘን፣ ማይክል ሹማን በታይም መጽሄት ላይ ያቀረበው ወቅታዊ የኢኮኖሚ ትንታኔ ኢትዮጵያን አስደስቷታል ብለን ብንናገር ዋሾ ልንባል አንችልም፡፡
ማይክል ሹማን ያቀረበው ጽሁፍ በጥቂት አረፍተ ነገሮች አጥሮና ተጠቃሎ ሲቀርብ እንዲህ የሚል ነው። “ከዚህ በፊት BRIC በመባል የሚታወቁት ብራዚል፣ ራሺያ፣ ህንድና፣ ቻይና ሲያስመዘግቡት በቆዩት ከፍተኛ ፈጣን እድገት የድህረ አሜሪካን የዓለም ኢኮኖሚ በዋናነት ይቆጣጠሩታል ተብሎ ተገምቶ ነበር፡፡ ይህ ግምት አሁን አይሰራም፡፡ እነዚህ ሀገራት አሁን እያስመዘገቡት ያለው የኢኮኖሚ እድገት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ከእነዚህ ሀገራት ይልቅ የPINE ሀገራት በሚል አዲስ ስም የወጣላቸው ፊሊፒንስ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ናይጄሪና ኢትዮጵያ በቀጣዩ የዓለም ኢኮኖሚ መድረክና ድህነትን በማስወገድ በኩል እጅግ ጠቃሚ ሚና መጫወት የሚችሉ ወሳኝ ሀገራት በመሆን ብቅ ብለዋል፡፡ ስለዚህ ዓለም የBRIC ሀገራትን ትቶ አዲሶቹን የPINE ሀገራትን ይተዋወቅ፡፡”
ማይክል ሹማን፤ በታይም መጽሄት ላይ ያቀረበው ጽሁፍ አንኳር ፍሬ ነገር ይሄው ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ማይክል ሹማን የBRIC እና የPINE ሀገራትን ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ አስመልክቶ ያቀረበው ትንታኔ በርካታ አቃቂር ለማውጣት እድል የሚሰጥ አይደለም፡፡
ናይጄሪያ በአፍሪካ ከደቡብ አፍሪካ ቀጥላ ሁለተኛዋ ባለትልቅ ኢኮኖሚ ሀገርና በ2050 ዓ.ም ከዓለም አስር ታላላቅ ኢኮኖሚዎች አንዱ ለመሆን ትልቅ ህልም ያለመችና ይህንን ትልቅ ህልሟን እውን ለማድረግ ደፋ ቀና በማለት ላይ የምትገኝ ሀገር ናት፡፡
ትናንትና ከትናንት ወዲያ የከፋ ድህነትን፣ ረሀብንና የእርስ በርስ ጦርነትን ለመላው ዓለም ለማሳየት ዓለማችን ከኢትዮጵያ የተሻለ ወይም ኢትዮጵያን የሚያስንቅ ማስታወቂያ አልነበራትም፡፡ ዛሬ እንዲህ አይነት ኢትዮጵያ የለችም፤ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የትናንት የድህነት፣ የረሀብና የእልቂት ታሪኳን በፈጣን ኢኮኖሚ ባለቤትነት መቀየር ችላለች፡፡
ለአስራ ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያውያንን አስከፊ ፍዳና ስቃይ ያስቆጠራቸውን የደርግን ወታደራዊ አስተዳደር በትጥቅ ትግል ያስወገደው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያን በመምራት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ድርጅት ላለፉት አስራ ስድስትና አስራ ሰባት ዓመታት ያህል የሚመራበት ዋነኛ የርዕዮተ ዓለም መስመሩ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” እንደሆነ ለሚመራቸው የኢትዮጵያ ህዝቦች ይነግራቸው ነበር፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን የርዕዮተ ዓለም መስመሩ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መሆኑ ቀርቶ “ልማታዊ መንግስት” እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ግን የኢህአዴግ የርዕዮተ ዓለም ለውጥ ልዩነቱ ጨርሶ አይታያቸውም፡፡ ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የየእለቱን ህይወታቸውንና የሀገሪቱን ጠቅላላ የፖለቲካ የኢኮኖሚና፣ የማህበራዊ መስኮች በመቆጣጠር ረገድ የመንግስት እጅ እያደር ሲረዝም እንጂ ሲያጥርና ሲሰበሰብ ትናንትም ሆነ ዛሬ ለአፍታም እንኳ አይተው ስለማያውቁ ነው፡፡
በኢህአዴግ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት፤ ላለፉት ዓመታት ያስመዘገበውን የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይ በማድረግ በ2025 ዓ.ም ሀገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ እቅድ ነድፏል፡፡ ለአምስት ዓመት እንዲሆን ተብሎ የተዘጋጀው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሊገባደድ አንድ ዓመት ብቻ ቀርቶታል፡፡ በዚህ እቅድ መገባደጃ ላይ ይገኛል ተብሎ የታሰበውን የአፕል ፍሬ ግን በረሮ ወሮታል። እንደ እውነት ከሆነ አለመጠን የረዘመው የመንግስት እጅ፣ የራሱ ዕቅድ እንዳይሳካ በራሱ በመንግስት ላይ ከፍተኛ እንቅፋት ፈጥሮበታል፡፡ በየትኛውም አይነት ርዕዮተ ዓለም ለሚመራ መንግስት የኢኮኖሚ እድገቱ እንዲሳለጥና የውጭም ሆነ የውስጥ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ከፈለገ፣ ጥራትና ብቃት ያለው አስተማማኝ የመሰረታዊ አገልግሎት መስጠት መቼውንም ጊዜ ቢሆን ግድ ነው። በኢትዮጵያ እንደ ውሀ፣ መብራትና፣ የቴሌኮሚኒኬሽን መገናኛን የመሳሰሉ መሰረታዊ አገልግሎቶች መቶ በመቶ በመንግስት የተያዙ ናቸው፡፡
መንግስት እነዚህን አገልግሎቶች “የሚታለቡት ላሞች” በማለት ይጠራቸዋል፡፡ ነገር ግን አለመጠን የረዘመው የመንግስት እጅ እነዚህን ላሞቹን በሚገባ ማለብና ወተታቸው ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ከቶውኑም አልቻለም፡፡
ዛሬ መንግስት እነዚህን ወሳኝ የሆኑ መሰረታዊ አገልግሎቶች ለህዝቡ በወጉ ማቅረብ ተስኖታል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ኢትዮጵያዊያን ከአምላካቸው ቀጥሎ መንግስታቸውን በመፍራትና በማክበር ይታወቃሉ፡፡ መንግስታቸው እንዲፈጽሙት ያዘዛቸውን ማናቸውንም አይነት ትዕዛዝ ያለ ብዙ ማንገራገር ይፈጽማሉ፡፡ መንግስት በሚያወጣቸው ህጎች ጠማማነትና በአመራሩ ጉድለት የተነሳ ለከፍተኛ የኑሮ ጫናና የመብት ረገጣ ሲጋለጡ እንኳ በቅድሚያ የሚያደርጉት በአመጽ አደባባይ መውጣት ሳይሆን የተጫናቸውን ቀንበር እንዲያቀልላቸውና መልካም ጊዜን እንዲያመጣላቸው አምላካቸውን በፀሎት መማፀን ነው። ከዚህ ባለፈ በችግሮቻቸው ላይ በመቀለድ ራሳቸውን በመጠኑም ቢሆን ዘና ያደርጋሉ፡፡ መንግስታቸው ግን ይህንን እጅግ አስገራሚ ትዕግስታቸውን አብዛኛውን ጊዜ ነገሬ ብሎ ከጉዳይ ጥፎት አያውቅም፡፡
መንግስት አለቅጥ በተጠናወተው የቁጥጥር አባዜ የተነሳ፣ ከመጠን በላይ ያስረዘመው እጁ ያስገኘለት ትርፍ ቢኖር በአስደንጋጭ ሁኔታ እለት በእለት እየተንሰራፋ የመጣውን ንቅዘትና ሙስና ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እጅግ ኮሚክ የሆነው የመንግስት ነገር፣ ራሱ በረጅም እጁ የፈለፈላቸውን ሙሰኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ወገቡን ጠበቅ አድርጎ በድኑ እንደመዋጋት ፈንታ ህዝቡን በታሰረ አንጀቱ ሞጥረህ ተዋጋልኝ ማለቱ ነው፡፡
ማይክል ሹማን በጽሁፉ እንደጠቀሰው፤ ናይጄሪያ በነዳጅ ዘይት ሀብት እጅግ የበለፀገችና ኢኮኖሚዋም በዋናነት በነዳጅ ዘይት ሽያጭ በሚገኝ ገቢ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም ለምሳሌ ከነዳጅ ዘይት ሽያጭ ብቻ 55 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ችላለች፡፡ የናይጄሪያን ነገረ ስራ ጉዳዬ ብለው በጥሞና የሚከታተሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ግን እስኪ ናይጄሪያን በአንድ አረፍተ ነገር ግለፅዋት ሲባሉ፤ ዘና ብለው “ህዝቦቿ እጅግ ደሀ የሆኑ በጣም ሃብታም ሀገር” ሲሉ ይገልጿታል፡፡
ይህን እውነት ማንም ሀሰት ነው ብሎ መከራከር አይችልም፡፡ ለምን ቢባል አንድ መቶ ስልሳ ሶስት ሚሊዮን ከሚሆነው የናይጄሪያ ህዝብ አንድ መቶ አስር ሚሊዮን የሚሆኑት በቀን ከአንድ ዶላር በታች ገቢ በማግኘት ኑሮአቸውን ይገፋሉ፡፡
ናይጄሪያውያን በየዓመቱ ከነዳጅ ዘይት ከነሱ አልፎ ለሌሎች ሊተርፍ የሚችል ከፍተኛ ገቢ ማስገባት ቢችሉም አፕላቸው የበረሮ ሲሳይ ከመሆን አልፎ እነሱ እጅ ላይ ጠብ ለማለት አልቻለም፡፡ ናይጄሪያውያኑ ራሳቸው ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲጠየቁ “ገንዘባችንን ሰይጣኑ ስለሚበላብን ነው፡፡” በማለት አለአንዳች መሰልቸት ያስረዳሉ፡፡ ሰይጣኑ እያሉ የሚጠሩት ሙስናን ነው፡፡
ሙስናን በተመለከተ ኢትዮጵያውያን “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል!” የሚል እድሜ የጠገበ አባባል አላቸው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ያደጉት ይህን አባባል እየተናገሩ አሊያም ሲነገር እየሰሙ ነው። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሙስና በመላ ሀገሪቱ ከምን ግዜውም በበለጠ ሁኔታ ተንሰከፋ በማለት መንግስታቸውን ለአምላካቸው ያሳቅሉታል፡፡ እርስ በርስ ሰብሰብ ብለው ሲጫወቱም በሀሜት ይቦጭቁታል፡፡
ናይጄሪያውያን ደግሞ ሙስናን በተመለከተ፤ “ፀሐይዋ በደመቀች ጊዜ ድርቆሽህን አድርቅ!” የሚል አባባል አላቸው፡፡ ኢትዮጵያውያንም ሆነ ናይጄሪያውያን እነዚህን ሀገርኛ አባባላቸውን በተግባር ላይ አላዋሉትም በማለት ራሱን እንደ ቂል የሚያስገምት ሰው አይገኝም፡፡ የአጠቃቀማቸውን መጠን በተመለከተ ግን ኢትዮጵያዊያኑን ከናይጄሪያውያን ጋር ማወዳደር በእርግጥም አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡
“ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚለውን አገርኛ አባባል እየተናገሩና እየሰሙ ያደጉት ኢትዮጵያዊያን፤ በቅርብ ጊዜ መንግስታቸው በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ጠርጥሮ ካሰራቸው የሀገሪቱ የግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤት ሳንዱቅ ውስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን ብር (ሀምሳ ሁለት ሺ ዶላር) የሚጠጋ ገንዘብ መገኘቱን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲያዩ ተገርመውና ተደንቀው ነበር፡፡
የኢትዮጵያውያኑን መገረምና መደነቅ ያዩት ናይጄሪያውያን ደግሞ “ኢትዮጵያዊያን ሙስና ማለት ምን ማለት እንደሆነ በወጉ አልገባቸውም፡፡” ብለው በተራቸው ሲገረሙ,ኧ ኢትዮጵውያኑን የሙስና ተጠርጣሪዎች ደግሞ “አንድ ጠርሙስ ጥሩ ውስኪ ወይም አንድ ብልቃጥ ስም ያለው ሽቶ ለማይገዛ ብር አጓጉል ተልከስክሰው መንግስታቸውን ስራ አስፈቱት።” በሚል ተሳልቀውባቸዋል፡፡
እቅጩን እንነጋገር ከተባለ ናይጄሪያውያን እውነታቸውን ነው፡፡ የጅጋዋ ግዛት ገዢ ሆነው ባገለገሉበት ጥቂት ዓመታት ውስጥ 218.6 ሚሊዮን ዶላር መዝረፍ የቻሉ እነ ሳሚኑ ቱራኪን የመሰሉ አገረ  ገዥና ከ1993 እስከ 1998 አጋማሽ ድረስ ፕሬዚዳንት ሆነው ናይጄሪያን በመሩበት ወቅት አምስት ሚሊዮን ዶላር የዘረፉ ሳኒ አባቻን የመሰሉ ፕሬዚደንት ላሏቸው ናይጄሪያውያን ሀምሳ ሁለት ሺ ዶላር አይናቸው ውስጥ ቢገባም እንኳ ጨርሶ አይቆረቁራቸውም፡፡
በናይጄሪያ የተንሰራፋው ሙስና አቻ የለሽ መሆኑን ድፍን ዓለም አሳምሮ ያውቀዋል የናይጄሪያ ማዕከላዊ ባንክ በቅርቡ ይፋ ያደረገው መረጃ ግን ሙስናን በተመለከተ በመላው ዓለም ናይጄሪያ የምትገኝበት ምድብ “የአሸናፊዎች አሸናፊ” ምድብ ውስጥ መሆኑን በሚገባ ያረጋገጠ ነው፡፡ የናይጄሪያ ማዕከላዊ ባንክ ገዢ የነበሩት ላሚዶ ሳኑሲ፤ በመስከረም ወር ለፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን በፃፉት ደብዳቤ፤ የናይጀሪያ ብሔራዊ የነዳጅ ኩባንያ ከጥር ወር 2012 ዓ.ም እስከ ሀምሌ ወር 2013 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ፣ ለአለም ገበያ ካቀረበው ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ስልሳ አምስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ቢችልም ወደ ማዕከላዊ ባንኩ ገቢ የተደረገው ግን አስራ አምስት ቢሊዮን ዶላሩ ብቻ ነው፡፡ አርባ ዘጠኝ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላሩ የት እንደገባ እስከዛሬ ድረስ ያወቀ ሰው ስላልተገኘ “ሰይጣኑ እንደበላው” ተቆጠረ፡፡  የዚህን ጉድ ጉዳይ በደብዳቤ ያሳወቁት ሳኑሲ ላሚዶና መሰሎቻቸው ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን የነገሩ ክብደት አስደንግጧቸው ጠንካራ እርምጃ ባፋጣኝ በመውሰድ እንዲያው ሌላው ቢቀር የተወሰነ ቢሊዮን ዶላር ከሰይጣኑ አፍ ማስጣል ይችላሉ ብለው ተስፋ አድርገው ነበር፡፡
በእርግጥም ፕሬዚደንት ጆናታን አፋጣኝ እርምጃ ወስደዋል፡፡ የወሰዱት እርምጃ ግን የናይጀሪያ ማዕከላዊ ባንክ ገዢ የሆኑትንና ይህ አቻ የለሽ ሙስና መፈፀሙን በደብዳቤ በመግለጽ ተገቢውን እርምጃ ባፋጣኝ እንዲወስዱ ያሳሰቧቸውን ሳኑሲ ላሚዶን ከሃላፊነታቸው ማባረር ነው፡፡ ናይጀሪያ የነዳጅ ዘይት ያገኘችው በ1956 ዓ.ም ነው፡፡ እስከዛሬ ካገኘችው የነዳጅ ዘይት ገቢ ውስጥ 400 ቢሊዮን ዶላሩን ሰይጣኑ በልቶታል፡፡  

Read 3584 times