Saturday, 22 March 2014 12:20

የጉዞ ማስታወሻ ወደ ፀሐይ መውጫዋ ሀገር-ጃፓን

Written by  በደጀኔ ሳኩሜ
Rate this item
(3 votes)

           ጃፓን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትዋ ስር በሚተዳደሩ ኤምባሲዎችዋ እና ቆንስላ ፅ/ቤቶችዋ በዓለም ላይ እስከ 5300 የሚጠጉ ጃፓናዊ ያልሆኑ ተቀጣሪዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ከ39 ሃገራት የተውጣጡ፣ በስራቸው አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡ ተቀጣሪዎች በቅርቡ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ባዘጋጀው ስልጠና ላይ ተሳትፈው ነበር፡፡
የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅም የስልጠናውን አጋጣሚ በመጠቀም በጉዞ ማስታወሻው የከተባቸውን እንደሚከተለው ያስነብባል፡፡
(ይህ ጽሁፍ የጸሃፊው የጉዞ ማስታወሻ በመሆኑ በምንም መልኩ የጃፓን ኤምባሲ ወይም የጃፓን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አቋምን አያንፀባርቅም፡፡)
ግራ ያጋቡኝ ክስተቶች
የጃፓን-ቶኪዮ ጉዞ ከቦሌ እስከ ናሪታ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የበርካታ “ልእለ-ሀገራትን ድንበሮች” ያሻገረኝ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የ13 ሰዓታት በረራ ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ ሰዎች ለሰው ልጅ መገልገያ የፈጠሩት ቴክኖሎጂ፣ የሰው ልጆችን የራሱ ታዛዥ እና አገልጋይ እያደረገ ባለበት ዓለም እየኖርን ይመስለኛል፡፡ ከአዲስ አበባ 40 ደቂቃዎችን እንደበረርን ለዘመናት በእውነትነቱ ሳልጠራጠረው የኖርኩትን “የሀገራት ልእልና እና ብሄራዊ ድንበሮች” ንድፈ ሃሳቦችን እንደጉም እንዲተኑ ያስቻለ ክስተት አጋጠመኝ፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ እኔ የተቀመጥኩት በአውሮፕላኑ የመስኮት ጥግ ስለነበረ ምድርን የማየት እድል ነበረኝ፡፡ ፊት ለፊቴ የነበረው የአውሮፕላኑ ስክሪን ቻነል 21 ላይ ስለነበረ፣ በየሰከንዱ አውሮፕላኑ የት እንደ ደረሰ ያሳይ ነበር። ከ40 ደቂቃ በረራ በኋላ ስክሪኑ ላይ የጅቡቲን ድንበር እያቋረጥን መሆኑን አመለከተ፡፡ ነገር ግን በመስኮት ወደ ምድር ስመለከት እውነታው ሌላ ነው፡፡ እነዚያ መስመሮች በምድር ላይ የሉም፡፡ ሃሳባዊ እንጂ ነባራዊ አይደሉም፡፡ እናት ምድር አንድ ነች፡፡ ከሁለቱ ክስተቶች እውነታው የቱ ነው? ለኔ ሁኔታው አምታቶኛል፡፡  
የጃፓናዊያን ትህትና
ከሁለት ቀናት በረራ በኋላ እጅግ አስገራሚ እና ልዩ የቴክኖሎጂ ባህል አላት የምትባለውን ጃፓን አገኘኋት፡፡ የነገሮች ሁሉ ቅስት እና ውስብስብነት ከዜሮ ቴክኖሎጂ ባህል ወደ ሙሉ ቴክኖሎጂ ባህል መሸጋገሬን አስገነዘበችኝ፡፡ በቆይታዬ በጃፓን ወደ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ባህል የመለወጥ ሂደት ውስጥ ስነ-ምግባር እና መካኒክስ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው የተገነዘብኩ ይመስለኛል፡፡
ከናሪታ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ እስከ ቶኪዮ-ፕሪንስ ሆቴል ድረስ የጃፓኖች የእንግዳ አቀባበል በማጎንበስ ሰላምታ ከመስጠት ጀምሮ ስነ-ስርአቱ እጅግ ልብን የሚነካ ነው፡፡ ጃፓኖች ጨዋ ህዝቦች ናቸው፡፡ ይህ የአጎንብሶ ሰላምታ እኛ ዘንድም በሰፊው የተለመደ ቢሆንም እንደ እነሱ ብሄራዊ ምልክት እስከመሆን የደረሰ አይመስለኝም፡፡ “አሪጋቶ ኦጋይዜማስ” ትርጉሙም ትህትና የተሞላ ”እጅግ በጣም አመሰግናለሁ” ማለት ሲሆን ይሄን ቃል በተደጋጋሚ መስማት የተለመደ ነው፡፡
ከፍተኛው የቴክኖሎጂ ባህል የመጀመሪያ ትውውቄ
የቶኪዮው ፕሪንስ ሆቴል የክፍል ቁጥር 646፣ በህይወቴ ልዩ ቦታ ትይዛለች፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ከከፍተኛ የቴክኖሎጂ ባህል ጋር የተዋወቅሁት በዚህች ክፍል ዲጂታል መፀዳጃ ቤት ውስጥ ነው፡፡
የክፍሉን መብራት ሳላበራ ነበር የሽንት ቤት መቀመጫው ላይ የተቀመጥኩት፡፡ በስተቀኝ በኩል ያሉትን በርካታ ቀይ እና ቢጫ ቀለሞች ያላቸው ትናንሽ ብርሃኖችን ያለእውቀት ዝም ብዬ ስነካካቸው ነበር፡፡ ለካስ የዲጂታል ሽንት ቤት መታዘዥያ ቁልፎች (buttons) ናቸው፡፡ ቀጭን ጠንካራ የውሃ ግፊት መቀመጫዬን በሃይል ሲመታኝ በድንጋጤ ዘልዬ ተነሳሁ፡፡ የውሀው ግፊት ሃይለኛ ስለነበረ የመታጠቢያ ቤቱን ኮርኒስ አበሰበሰ። እንደምንም የመታጠቢያ ክፍሉን መብራት ካበራሁ በኋላ ሁሉንም መታዘዥያዎች ተራ በተራ፣ በፍጥነት ተጫንኳቸው፡፡ በመጨረሻም የማቆሚያ መታዘዥያውን ስነካው ቀጥ አለ፡፡
የመታዘዥያ ምልክቶቹን በጥንቃቄ መረመርኳቸው፡፡ የወንድ፣ የሴት፣ ግፊት ጨምር፣ ግፊት ቀንስ፤ ወዘተ… የሚሉ ናቸው፡፡ ከመነካካቴ በፊት ማንበብ እንደነበረብኝ ተገነዘብኩ፡፡
ውድ አንባቢያን፤ አሁን ደግሞ ስለጃፓን አስደናቂ የቱሪስት ማዕከላት፣ ብሔራዊ ቤተመንግስት፣ ታዋቂውን የኤሌክትሮኒክስ ገበያ (አኪሃባራ) እንዲሁም ስለ ታላቁ ካማኩራ ቡድሃ ሃውልት እና ሌሎች አስገራሚ ጉዳዮችን በወፈፍ በረር ምልከታ ላስቃኛችሁ፡፡
የጃፓን ፓርላማ (ዳይት)
ውቡ የጃፓን ፓርላማ ህንፃ፣ በቺዮዳ ቀበሌ ጉብታ ቦታ ላይ የተገነባ ሲሆን የጃፓኖች የፖለቲካ ማእከል ነው፡፡ ግባታውም በ1920 ተጀምሮ በ1936 ነው የተጠናቀቀው፡፡
የሰሜኑ ክንፍ የአማካሪዎች ምክር ቤት (House of councilors) ሲሆን የደቡቡ ክንፍ የተወካዮች ምክር ቤት (House of representative) ነው፡፡ ሁለተኛው ፎቅ ላይ የህዝብ ታዛቢዎች እና የሚዲያ መቀመጫ ቦታ አለ፡፡ ፖለቲካዊ ክርክሮች ሲኖሩ ማንኛውም ዜጋ ከዚህ ክፍል ውስጥ ሆኖ መከታተል ህገመንግስታዊ መብቱ ነው፡፡
የጃፓን ዳይት (ፓርላማ) ከዋናው መድረክ ዝቅ ብለው በግማሽ ክብ የተደረደሩ 460 መቀመጫዎች አሉት፡፡ ከመድረኩ ከፍ ብሎ የፕሬዚዳንቱ መቀመጫ አለ፡፡ ከፕሬዝዳንቱ መቀመጫ ጀርባ ከፍ ብሎ የተሰራ የንጉሡ ዙፋን አለ፡፡ ግርማዊነታቸው የጃፓን ዳይትን በንግግር የሚከፍቱት ከዚሁ ቦታ ነው፡፡ በእውነቱ ማንነቱን ያልጣለ የሚያኮራ ታሪክ። ጃፓኖች በመሰረቱ የነሱ የሆነውን አሪስቶክራሲ ሳያጣጥሉ፣ ከዘመናዊው የመንግስት አስተዳደር ጋር አጣጥመው ማስኬድ ችለዋል፡፡  
የነገስታት ቤተ መንግስት እና የኒጁባሺ ድልድይ
ወደ ነገስታት ቤተ መንግስት እየሄድን እግረ መንገዳችንን በቶኪዮ ከተማ ውስጥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በሙሉ የሚገኙበት የካሱሚጋሴኪ ዲስትሪክት (ክፍለ ከተማ እንበለው) አለፍን፡፡ ከቤተ መንግስቱ ፊት ለፊት ስንደርስ፣ ልክ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት እንዳለው የዳግማዊ ምኒልክ ሃውልት አይነት የሚያምር ፈረሰኛ ሃውልት አየን፡፡ ይህ ሰው ጃፓንን ያዋሃደ ሰው ነው ተብሎ ይነገራል። ከቤተ መንግስቱ ዙሪያ በአበቦች እና ዛፎች ያማረ ሰፊ አረንጓዴ ቦታ አለ፡፡ እዚህም እዚያም ሰዎች ከልጆቻቸው ጋር እንዲሁም ለብቻቸው ዘና ሲሉበት ይታያል፡፡ ቦታው መጥፎ ሽታ የሚባል ነገር የለውም። በእግር ለመርገጥ እንኳን የሚያሳሳ ነው፡፡ አዲስ አበባችን እንዲህ የምትሆንበትን ጊዜ ናፈቅሁኝ፡፡
የጃፓን ነገስታት ቤተ መንግስት የኢዶ ቤተ መንግስት በመባል ይጠራል፡፡ የኒጁባሺ ድልድይ ወደ ኢዶ ቤተመንግስት መግቢያ ሲሆን ባሕላዊውን የጃፓኖች ጥሩር በለበሱ ሁለት ወታደሮች ይጠበቃል፡፡ የቤተመንግስቱ አጥሮች የተሰሩት በባለ ግራጫማ ቀለም ድንጋዮች ሲሆን መግቢያ በሮቹ እጅግ ውብ ናቸው፡፡
የሴንሶጂ እና አሳኩሳ ቤተ መቅደሶች እና ታላቁ የቶኪዮ ሰማይ ዛፍ (Tokyo sky tree)
በቶኪዮ ሰሜን ምዕራብ የሚገኙ ሴንሶጂ እና አሳኩሳ ቤተመቅደሶችን ላየ ሰው፤ ጃፓኖቹ ምን ያህል መንፈሳዊ ህዝቦች እንደሆኑ መገንዘብ ይቻላል፡፡ የቤተ መቅደሶቹ አመሰራረት እንደሚከተለው ነው፡፡
ከ132 ዓመት በፊት ሶስት አጥማዶች የቡድሃን ቅርፀ-እንጨት አገኙ፡፡ የአካባቢው ባላባትም የቅርፀ-እንጨቶቹን ቅዱስነት በማመን ሴንሶጂን ቤተ መቅደስ አሰራላቸው፡፡ ቅርፀ-እንጨቶቹን ላገኙት ሶስቱ አጥማጆች ክብር ይሆን ዘንድም ከአጠገቡ የአሳኩሳ ቤተመቅደስንም አሳነፁ፡፡
እነዚህ ቤተመቅደሶችን ለማየት ከመላው ዓለም የሚመጡ ቱሪስቶች ቁጥር ቀላል ባይሆንም ከተለያዩ የጃፓን ግዛቶች የሚመጡ ፀሎተኞች ቁጥር ግን የሀገሬን የጥምቀት በዓል አስታወሰኝ፡፡
ከወርቃማው ሴንሶጂ በስተግራ የአሳኩሳ ቤተመቅደስ አለ፡፡ አማኞች በዚህ ቤተ መቅደስ በር ላይ ካለው የጠበል ውሃ በረዥም የእንጨት ማንኪያ ቀድተው እጃቸውን ያነፁበታል፡፡ ፀሎት ካደረሱ በኋላ ፻ መቶ የን ወደ ሙዳዩ ወርውረው፣ ሁለት ጊዜ ብቻ ነው የሚያጨበጭቡት፡፡ በቃ ልዩነቱ ይህ ነው፡፡ ነገር ግን ሁለቱም በአንድ ቤተ መቅደስ ነው የሚገለገሉት፡፡
የቶኪዮ ሰማይ ጠቀስ ዛፍን ስጎበኝ ሰማይን ልነካ የደረስኩ መሰለኝ፡፡ መጀመሪያ ከመሬት ወደ ላይ አንጋጦ ሲታይ ነገርየውን አይን እስኪችል ቢታይ ከርዝመቱ የተነሳ ጫፉ ሰማይ ውስጥ የታሰረ ነው የሚመስል፡፡ በምን ምክንያት እንደዚህ እንደሚሰማ የፊዚክስ ምሁራን ብቻ የሚያውቁት ይመስለኛል፡፡
ታላቁ የካማኩራ ቅርፀ-ነሃስ (The Great Budha of Kamakura)
ቀጥሎ ደግሞ ወደ ዮኮሃማ ልውሰዳችሁ። ጃፓኖች በጣም የሚታወቁት በድልድይ ግንባታ ነው፡፡ በቶኪዮ ወደ ዮኮሃማ ስንሄድ የዮኮሃማን የባህር ላይ ድልድይ ተሻግረን ነው። ከድልድዩ በስተግራ ኒሳን ኩባንያ ለኤክስፖርት ያዘጋጃቸው የተለያዩ መኪናዎች በአይነት በአይነት ተደርድረው ይታያሉ፡፡ አንድ ሰው በመኸር ወቅት ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም ሲሄድ፤ በየሜዳው እንደሚታየው የአርሶ አደሩ የጤፍ ክምሮች እንደማለት ነው፡፡
ዮኮሃማ የትላልቅ ኢንዱስትሪ ባለቤቶች እና ስራ አስኪያጆች የሚኖሩባት ውብ ከተማ ነች፡፡ አሁን ካማኩራ ደርሰናል፡፡ ይህች ከተማ የጥንታዊው የሳሙራይ መንግስት እና ባህል ማእከል ነች፡፡ ታላቁ የካማኩራ ቅርፀ-ነሀስ በዩኔስኮ የተመዘገበ ስመጥር የሰው ልጅ እደ-ጥበብ ውጤት ነው፡፡ ጃፓን በሳሙራይ መንግስት ትተዳደር በነበረበት ወቅት የተሰራ የካማኩራ ከተማ ማእከላዊነት መገለጫ ነው። በወቅቱ ካማኩራ ላይ የከተመው የጃፓን መንግስት በጠንካራ ስነ-ምግባር ይመራ ስለነበረ፣ ዜን የተባለውን የቡድሃ እምነት ምርጫቸው አድርገው ነበር፡፡
ታላቁ የካማኩራ ቅርፀ-ነሀስ 13.35 ሜትር ርዝመት ሲኖረው፣ ክብደቱም 93 ቶን ነው፡፡ በቅርቡ የመሬት መንቀጥቀጥን አስቀድሞ የሚለይ ቴክኖሎጂ ስለተገጠመለት አደጋ አያሰጋውም፡፡
ካማኩራ ጥንታዊ የሺንቶ እምነት ቤተ መቅደስም ይገኝባታል፡፡ እስቲ በፅሩጋኦካ ሃቺማንጉ ቤተ መቅደስ ውስጥ ስለሚገኝ አንድ ሚስጢራዊ ዛፍ ታሪክ ላውጋችሁ፡፡ በሺንቶ እምነት ልክ እንደ ዋቄፈታ እምነት ህይወት ያለው ለምለም ዛፍ ልዩ ቦታ አለው፡፡
እ.ኤ.አ ማርች 10 ቀን 2010 ዓ.ም 4 ሰዓት ከ40 ደቂቃ ላይ ለብዙ ዘመናት የቆየ ተወዳጁ የጊንጊኮ ዛፍ ባልታወቀ ምክንያት ከስሩ ተነቅሎ ይወድቃል፡፡
ዛፉ በወደቀ በዓመቱ ታላቁ የምስራቅ ጃፓን ሱናሚ አደጋ ጃፓንን አጋጠማት፡፡ አደጋው በደረሰ በዓመቱ ደግሞ ዛፉ ከወደቀበት አንድ ሜትር ወደ ግራ ጠጋ ብሎ ማንም ያልተከለው አዲስ የጊንጊኮ ዛፍ ችግኝ በቅሎ ተገኘ፡፡ ይህችን ችግኝ ጃፓኖች የዓለማችን የወደፊት ብሩህ ተስፋ ምልክት ናት ይላሉ፡፡
እግረ መንገዴን ካስደመሙኝ የጃፓን ባህሎች መካከል ቀለል ያለው የቤት አሰራራቸው እና የግቢ ውበት ቀመራቸው ነው፡፡ ጃፓኖች በትንሽ መሬት ላይ ተፈጥሮን በመቀመር (እንደ ድንጋይ፤ አረንጓዴ ተክሎች በተለይ ሸንበቆ) አስደማሚ ግቢዎችን (Japanese Garden) ይፈጥራሉ። ግቢዎቻቸውን ታዲያ ከእይታ እርካታ ባለፈ፤ በስራ እና መሰል ጉዳዮች ሲደክም የዋለውን መንፈሳቸውን አረፍ የሚያደርጉበት ነው፡፡ ለጃፓኖች ግቢ ማለት ራሳቸውን ከዓለማዊ ጣጣ አላቀው ለቀናት ወይም ሰዓታት አረፍ የሚሉበት ቦታ ነው፡፡

Read 2452 times