Print this page
Saturday, 22 March 2014 12:14

የአፄ ምኒልክን ታሪክ ተጭበርብረናል!?

Written by 
Rate this item
(23 votes)
  • በአሜሪካ፣ በፈረንሳይና ቤልጂየም ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ነበራቸው
  • የ25 ሚሊዮን ዶላር ባለፀጋ ነበሩ - ወደ ቢሊዬነርነት ተጠግተዋል    
  • ቤተ-መፅሃፋቸው ራሳቸው ባሰባሰቡት 10ሺ መፃህፍት የተሞላ ነበር

በሳምንቱ ማጠናቀቂያ ግድም “ጮማ” የሆነ መረጃ እጄ ገባ፡፡ አንድ ወዳጅ ነው መረጃውን ከባህር ማዶ በኢሜይል ያሻገረልን፡፡ The New York Times የዛሬ 105 ዓመት፣ አፄ ምኒልክ ሲሞቱ ነው ዘገባውን ያወጣው - ኖቨምበር 7 ቀን 1909 ዓ.ም፡፡ “ንጉስ ምኒልክ እዚህ ኢንቨስትመንት አላቸው” በሚል ርዕስ የቀረበው ፅሁፍ፤ከአቢሲኒያ የተመለሰውን የቤልጂየም አሳሽ ባሮን ዲ ጃርልስበርግ ቃለመጠይቅ በማድረግ የተጠናቀረ እንደሆነ ኒውዮርክ ታይምስ ይገልፃል፡፡ የሚታወቁትን ታሪኮች እየዘለልኩ “ጮማ ጮማ” የሆኑትን መረጃዎች ነው የማቀብላችሁ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ከመዘጋቱ በፊት በዚህ በአዲሱ የአፄ ምኒልክ ታሪክ ላይ ትንሽ ጥናትና ምርምር ቢያካሂድ ትክክለኛው ታሪክ (ያልተጭበረበረው ማለቴ ነው!) ለትውልድ ይሸጋገራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ “የለም! የአፄ ምኒልክን ጉዳይ አጥንቼ ፋይሉን ዘግቻለሁ” የሚል ከሆነም እንዳሻው፡፡ የኒውዮርክ ታይምስ መረጃ ግን የሚያወላዳ ዓይነት አደለም፡፡ ለመሆኑ እኚህ የጥቁር ህዝብ ኩራት፣የአድዋ ጀግና-----አዳዲስ ገድሎች ምን ይሆኑ? (የተጭበረበርነው ታሪክ ማለት ነው!)
ባሮን ዲ ጃርልስበርግ ለጋዜጣው እንደተናገረው፤ ምኒልክ ከሌሎች የአህጉሪቱ ነገስታት ጨርሶ የተለዩ መሪ ነበሩ፡፡ በዲፕሎማትነት፣ በኢንቨስተርነት (ፋይናንሰር)፣ በተዋጊነት የሚስተካከላቸው አልነበረም፡፡ በተዋጊነትና በዲፕሎማትነት ያላቸውን ብቃትና ዋጋ ያስመሰከሩት ጣልያን በአቢሲኒያዎች ድል በተነሳች ወቅት ነበር ይላል - ጃርልስበርግ። በመጨረሻዎቹ የንግስና ዘመናቸው ግን ምኒልክ ይበልጥ   በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴያቸው እንደታወቁ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡  
የንግስና ዘውድ ከመድፋታቸው ቀደም ብሎ በወጣትነት ዘመናቸው የኢንቨስትመንት ዝንባሌ እንደነበራቸው የሚያስታውሰው ዘገባው፤በዚያ እድሜያቸው በፈረንሳይና ቤልጂየም የማዕድን ማምረቻዎች ውስጥ ቀላል የማይባል መዋዕለ ንዋይ አፍስሰው ነበር ይለናል፡፡ ከንግስናቸው በኋላ ግን አገር በማስተዳደር ሥራ በመወጠራቸው ከኢንቨስትመንቱ ተስተጓጉለው እንደነበር የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ ያመለክታል፡፡
“ዛሬ የአቢሲኒያው ገዢ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴያቸውን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በማስፋፋት በአሜሪካ የባቡር ሃዲድ ሥራ ላይ ከፍተኛ የአክስዮን ድርሻ አላቸው” ሲል አሳሹ የንጉሱን ወቅታዊ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ገልጿል፡፡
አፄ ምኒልክ በአሜሪካ እንዲሁም በፈረንሳይና ቤልጂየም ያላቸው አክስዮንና ኢንቨስትመንት ሲደማመር ከ25 ሚሊዮን ዶላር የማያንስ የግል ሃብት እንደነበራቸው ይገመታል ብሏል- አሳሹን ጠቅሶ የዘገበው ጋዜጣው፡፡   
“እኚህን ጥቁር የአቢሲኒያ ገዢ በተመለከተ በእጅጉ የሚያስደንቀው ጉዳይ ሁለ-ገብነታቸው ነው” ሲል የሚያደንቀው የቤልጂየሙ አሳሽ፤ንጉሱ የተዋጣላቸው ቋንቋ አዋቂ ነበሩ ይላል - ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዝኛና ጣልያንኛ አቀላጥፈው ይናገሩ እንደነበር በመጥቀስ፡፡ ሁለመናቸውን ለአገራዊ ጉዳዮች ለመስጠት ቢገደዱም አዲስ የወጡ የአውሮፓ የስነጽሑፍ ስራዎችን ለመቃኘት ግን ጊዜ አያጡም የሚለው ጃርልስበርግ፤ ብዙ ጊዜ አዲስ የአውሮፓ ደራሲ ስም ሲጠቀስ እምብዛም አይደናገራቸውም ነበር ብሏል፡፡
እሳቸውን ከሁሉም በላይ የሚያኮራቸው ራሳቸው ባሰባሰቧቸው 10ሺ መፃሕፍት የተደራጀው ቤተመፅሃፋቸው ሲሆን መፃህፍትን በተመለከተ ዋነኛ ትኩረታቸው በአፍሪካና በእስያ ጥንታዊ ስልጣኔዎች ላይ የሚያጠነጥኑ ሥራዎች ነበሩ ይላል - ለኒውዮርክ ታይምስ ምስክርነቱን የሰጠው ባሮን ዲ ጃርልስበርግ፡፡ ለካስ ምኒልክ ወደው አይደለም-- ትምህርት፣ ቴክኖሎጂ፣ ሥልጣኔ፣ ዘመናዊ አስተዳደር ወዘተ----ሲሉ የኖሩት፡፡ (የንጉሱን ታሪክ ተጭበርብረናል!?)  

Read 6151 times
Administrator

Latest from Administrator