Saturday, 22 March 2014 12:15

“ኧረ መላ በሉ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(13 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አዲስ አበባ ያላችሁ ‘ከተሜዎች’… ኑሮ እንዴት እያደረጋችሁ ነው? (‘ከተሜዎች’ የሚለው ቃል በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ የገባው የዘንድሮውን ትርጉም ዘርዝሮ የሚነግረን ሰው እየጠበቅን ስለሆነ መሆኑ ይታወቅልንማ!)
ወይ አዲስ አበባ፣ ወይ አራዳ ሆይ፣
አገርም እንደ ሰው ይናፍቃል ወይ!
ይባልላት ነበር… ይቺዋ አዲስ አበባችን። ዘንድሮ… አለ አይደል… ‘ስልጣኔ’ መጣና፣ ‘ግሎባላይዜሽን ወረረንና’፣ ነገሩ ሁሉ ‘እዛው ፈላ እዛው ሞላ’ ሆነና፣ መፈጠርና መሆን ቀርተው መኮረጅና መምሰል ‘የጥይት ጭንቅላት’ መለኪያ ሆኑና…ከተማችን ለትዝታ እንኳን የሚቀሩ ነገሮቿ እየጠፉ ነው፡፡
የምር እኮ…አለ አይደል… “የካዛንቺስ ልጅ ነኝ…” “የአራት ኪሎ ልጅ ነኝ…” “የቄራ ልጅ ነኝ…”  “የመርካቶ ልጅ ነኝ…” ብሎ ነገር ታሪክ እየሆነ ነው፡፡ ለብዙ ሰፈሮች ‘ልዩ የራሳቸውን አሻራዎች’ ሰጥተዋቸው የነበሩ ነገሮች ሁሉ ከ‘ነው’ ወደ ‘ነበር’ እየተሸጋጋሩ ነው — ‘ነበር’ የሚለውም እስኪጠፋ ድረስ!
ምን አለፋችሁ…ይቺው ስንት ክፉና ደግ እየመጣ ሲሄድባት የኖረች ከተማ… አለ አይደል… “ናፈቀችኝ”… “ትዝታዋ እንቅልፍ ነሳኝ” ምናምን አይነት የሚዘፈንላት ሳትሆን “ኸረ መላ በሉ፣ ከተሜዎች ሁሉ!…” የሚባልላት ከተማ እየሆነች ነው!
ታዲያላችሁ…አዲስ አበባ እንደሚወራላት ‘ዘመናዊ’ ባህሎችና ልምዶች ከሚበዙባት ይልቅ ጭርሱን ትናንት የነበሩ ‘እውነተኛ የዘመናዊነት’ ጅማሮዎች ……………ሁሉ እያጣች ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… አንድ ሚኒባስ ታክሲ ላይ ምን የሚል አየሁ መሰላችሁ…“አፍህን ከምትከፍት አጠራቅምና ሱቅ ክፈት፡፡” “ኧረ መላ በሉ…” ይሏችኋል ይሄ ነው። “አትንጣጪ!” “የቤትሽን ዓመል እዛው” ምናምን ከመባል አልፎ አሁን ደግሞ “አፍህን ከምትከፍት…” ወደሚል ደረስንና አረፈው፡፡ እናላችሁ…አዲስ አበባ ገንዘባችሁን ከፍላችሁ በምትሄዱበት ትራንስፖርት ውስጥ የምትዘለፉባት ከተማ ሆናለች፡፡
ከመደበኛው በላይ አምስት ተጨማሪ ተሳፋሪዎች የተጠቀጠቁበት ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ሌላ ሦስት ሰው ለመጨመር ከተሳፋሪዎች መሀል “ምን አለ ጠጋ ብትሉ…” የሚሉ እወደድ ባዮች፣ በታከሲ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ቦታዎችም፣ በማያገባቸው ጥልቅ የሚሉባት ከተማ ሆናለች፡፡ እናማ… የራሳቸውን መብት ለማስከበር እንደመሞከር የእናንተንም አብረው የሚያስደፈጥጡ እየበዙ ያሉባት ከተማ እየሆነች ነው፡፡ (አንድ ሚኒ ባስ ውስጥ “ባቡር እስኪመጣ፣ ጠጋ ጠጋ በሉ…” ብሎ የለጠፈው ይህንን አይቶ መሆን አለበት፡፡)
እናማ… ከተማችን “ኧረ መላ በሉ…” የሚባልላት ሆናለች፡፡
ስሙኝማ…መቼስ ዘንድሮ ጤና ጎድሎ ህክምና የማግኘት ነገር…ግራ የሚያጋባ ደረጃ እየደረሰ ነው፡፡ መሀላቸውን ጠብቀው፣ ለሙያቸው ታምነው በሀቅ የሚያገለግሉ መአት የህክምና ባለሙያዎች እንዳሉ ሁሉ መሀላቸውን አፈርሰው፣ እንደ ‘ጥጋበኛ ጎረምሳ’ …የፈለጉትን የሚያናግራቸው እየበዙ ነው፡፡
ችግሩ ምን መሰላችሁ…የእነኚህ ሥነምግባር የጎደላቸው ‘ባለሙያዎች’ ሥራ የሀቀኞቹን ሥራ እየሸፈነና ሙያው ላይ አስቀያሚ ጥላውን እያጠላ… አለ አይደል… ህዝቡን ሁሉንም ባለሙያ ቀላቅሎ እንዲጠረጥር እየገፋው ነው፡፡
ይቺን ስሙኝማ… የደም ናሙና ለመስጠት በሥራ ሰዓቷ እንቅልፏን ትለጥጥ የነበረችውን የላቦራቶሪ ባለሙያዋ በር ያንኳኳች ወዳጄ ያገኘችው መልስ ምን መሰላችሁ… “ቤትሽ መሰለሽወይ እንዲህ የምታንኳኪው! … ነገሩ እዚሁ ‘ጦቢያ’ ውስጥ ሆነና ነው እንጂ… ‘ዘመናዊነት’  በ‘ከት ኤንድ ፔስት’ የተሠሩ መስታወት ህንጻዎች ሳይሆን በባህሪይና በሙያ ስነ ምግባር ጥንካሬ በሚመዘንባቸው ቦታዎች የዚች ቢጤዋ ወዲያውኑ ነበር “ሻንጣሽን ይዘሽ ወደ ምትሄጂበት ሂጂ…” ትባል የነበረው፡፡
እናላችሁ…አዲስ አበባ ደሞዛቸውን በምትከፍሉላቸውና እጃቸውን ከፍ አድገው መሀላ በፈጸሙ የህክምና ‘ባለሙያዎች’ የምትዘለፉባት ከተማ እየሆነች ነው፡፡
እናማ… ከተማችን “ኧረ መላ በሉ…” የሚባልላት ሆናለች፡፡
እግረ መንገዴን አንድ ወዳጄ የነገረኝን ስሙኝማ…ሰውየው ለህክምና አንድ የህክምና ተቋም ሄዶ ዶክተር ዘንድ እንዲያቀርቡት እያናገረ ሳለ አንድ ወንድ ነርስ ክብረ ነክ ንግግር ይናገረዋል። ሰውየውም በትእግስት ነርሱ ስርአት እንዲይዝ ይነግረዋል፡፡ ይሄኔ ነርስ ሆዬ፤ ለካ ገና ጮርቃ ቢጤ ኖሮ…ያንን አርባዎቹ ያጋመሰ ሰው…“ከፈለግህ ውጪ እንውጣ!” ይለዋል፡፡ ይሄኔ ሰውየው ብው ይልላችሁና “ውጪ ድረስ ምን አስወጣን፣ እዚሁ እየተቻለ…” ይልና በአንድ ቡጢ መዳፍ የበዛባት ጭብጦ አድርጎት ቁጭ አለላችሁ፡፡
እናማ… አዲስ አበባ በተወሰኑ የህክምና ባለሙያዎች የተበላሸ ስነ ምግባር ተጨማሪ በሽታ የሚሸምቱባት ከተማ እየሆነች ነው፡፡
እናማ… ከተማችን “ኧረ መላ በሉ…” የሚባልላት ሆናለች፡፡
ኮሚክ ነገር ነው…አዲስ አበባ የአሥራ ሦስት ዓመት ወንድ ልጆች፣ የሠላሳ ሰባት ዓመት ባለትዳር እናትን፣ የሰባ ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የአሥራ አራት ዓመት ታዳጊ ሴት ‘የሚለክፉባት’ ከተማ ሆናለች፡፡ በሚገርም ሁኔታ ነገሬ ካላችሁ…አለ አይደል… “ሴት መልከፍ ዕድሜን በሁለት እጥፍ ይጨምራል” የሚል የጥናት ምርምር ተገኝቶ ሁሉም ‘ለካፊ‘ እንዲሆን የተመከረ ነው የሚመስለው፡፡
አዲስ አበባ በአንዳንድ ህዝባዊ የአገልግሎት መስጫ ስፍራዎች…እናንተ ለሁለት ሰዓት ተሰልፋችሁ ፀሀይ ሲያንቃቃችሁ ቆይታችሁ…‘ምርጦች’ በመጡ በሁለት ደቂቃ ውስጥ ጉዳያቸውን ጨርሰው የሚሄዱባት ከተማ ሆናለች፡፡ በእርግጥም … ከተማዋ ‘ገንዘብ አፍ አውጥቶ’ የሚናገርባት ከተማ ሆናለች። የመብትና እኩል አገልግሎት የማግኘት ነገር በአንዳንድ ቦታዎች ከ‘ወርክሾፕ ሰነድ ማወፈሪያነት’ ያለፈ ትርጉም እያጣ ነው፡፡
እናማ… ከተማችን “ኧረ መላ በሉ…” የሚባልላት ሆናለች፡፡
አዲስ አበባ አንድ ካፌ ውስጥ አንድ መቶ ሰው ካለ፣ ዘጠና ስድስቱ እናንተ ላይ እያፈጠጠ ያለ የሚመስልባት ከተማ እየሆነች ነው፡፡ ለ‘ሥራም’ ይሁን ‘ለሌላ ጉዳይ’… አለ አይደል… ሰውን ፍጥጥ ብሎ ማየት በየትኛውም መለኪያ… ሲያንስ የስነ ምግባር ጉድለት፣ ሲበዛም ቅልጥ ያለ ‘እንደወረደ’ መሆን ነው፡፡ እናማ…ዘና ለማለት በሄዳችሁበት ቦታ የሸሻችሁት ድብርት መልኩን ለውጦ ‘አቅሙን አጠናክሮ’ ይመጣላችኋል፡፡
እናማ… ከተማችን “ኧረ መላ በሉ…” የሚባልላት ሆናለች፡፡
እናላችሁ…አዲስ አበባ መንገዶቿ ጎዳና ተዳዳሪዎችና ‘የእኔ ቢጤዎች’ የተጨናነቁባት ከተማ ሆናለች፡፡ (በነገራችን ላይ በልመና የሚተዳዳሩትን “የእኔ ቢጤ…” ማለትም ታሪክ ሆኖ ቀረ አይደለ!) በተለይ ህጻናት ጎዳና ተዳዳሪዎች እንዲህ የበዙበት ምክንያት ግራ ይገባል፡፡
ታዲያማ…እግር ግጥም አድርገው ይዘው “ካልሰጠሽኝ አልለቅም” አይነት የሚቃጣቸው ህጻናትና… ኋላ፣ ኋላ እየተከተሉ “እግዚአብሔር ይስጥዎት…” ሲባሉ የማይሰሙ አዛውንት ‘የእኔ ቢጤዎች’ ከተማዋን የሆነች የፊልም መድረክ እያስመሰሏት ነው፡፡
እግረ መንገዴን፣ የልመናን ነገር ካነሳን አይቀር…በየመንደሩ እየዞሩ የሚለምኑት ድፍን እንጀራ ተሰጥቷቸው ወጥ ካልተጀመረ የማይቀበሉ መአት አሉላችሁ፡፡ አይገርምም! እንደበፊቱ ከቤተሰቡ  የተራረፈ ምናምን ነገር ለመስጠት መሞከርማ…ምን አለፋችሁ…አይታሰብም፡፡ አንድ ጊዜ ፒያሳ መሀል ሃምሳ ሳንቲም የተመፀወተ አንድ የአካል ጉዳተኛ ሀምሳ ሳንቲሙን የመፀወተው ሰውዬ ላይ መልሶ ሲወረውርበት አይተን አዝነናል (‘ብዙ ቁጥር’ የተጠቀምኩት “ከወዳጆቼ ጋር አይተን…” ለማለት ነው እንጂ አራት ኪሎ ናፍቆኝ አይደለም፡ ቂ…ቂ…ቂ…)
እናማ… ከተማችን “ኧረ መላ በሉ…” የሚባልላት ሆናለች፡፡
አዳስ አበባ…የምታውቁትን ሰው፣ የምትሸምቱትን ዕቃ፣ የምትሳፈሩበትን የትራንስፖርት መኪና፣ የምትሰሙትን ዜና፡ የምታነቡትን ‘እውነተኛ’ ታሪክ…የማታምኑባት ከተማ ሆናለች፡፡
አዲስ አበባ…ከጥበቃ ሠራተኛውና ከሥራ አስኪያጁ፣ ዋናው የወሳኝነት ስልጣን የትኛው ዘንድ እንደሆነ ግራ የሚገባችሁ ከተማ ሆናለች፡፡
አዲስ አበባ…ተሳዳቢ ሽማግሌዎች፣ መሀል ጣታቸውን በመኪና መስኮት የሚቀስሩ አዛውንቶች የበዙባት ከተማ ሆናለች፡፡ አንድ ጊዜ…አንዲት ምን የመሰለች ‘ዳያስፖራ—ቀመስ’ የምትመስል ሴት በተወለወለች ሌክሰስ መኪና መስኮት መሃል ጣቷን ስትቅስር ታይታለች። ጥፍር ተሞረደ፣ ቀለም ተቀባ… መሀል ጣት፣ መሀል ጣት ነው! ቂ…ቂ…ቂ…
እናማ… ከተማችን “ኧረ መላ በሉ…” የሚባልላት ሆናለች፡፡
አዲስ አበባ…ሴት ልጅ ከባሏ ወይም ከእጮኛዋ ጋር እየሄደች የምትጠቀስባት ሲብስም የምትጎነተልባት ከተማ እየሆነች ነው፡፡
አዲስ አበባ…“እንደምን አደርክ?” “በረታሽ ወይ?” አይነት ሰላምታ ቀርቶ “ሰፈራችሁ መብራት መጣ?” “ውሀ እናንተ ሰፈር አለች?” ምናምን አይነት ንግግሮች የሰላምታን ቦታ እየተኩባት ያለች ከተማ ሆናለች፡፡
አዲስ አበባ…የትኛው የትራፊክ መብራት ሲበራ እንደሚሄዱ፣ የቱ ሲበራ እንደሚቆሙ ግራ የሚገባቸው የሚመስሉ ስንት ዓመት መሪ የጨበጡ (የመኪና መሪ ለማለት ነው…እያጠራን እንሂዳ!) አሽከርካሪዎች የበዙባት ከተማ እየሆነች ነው፡፡
እናማ… ከተማችን “ኧረ መላ በሉ…” የሚባልላት ሆናለች፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5384 times