Saturday, 22 March 2014 11:56

ከ600 ሚ. ብር በላይ የፈጀው ካስቴል ወይን ጠጅ ፋብሪካ ዛሬ ይመረቃል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(5 votes)

          የቢጂአይ ኢትዮጵያ እህት ኩባንያ ካስቴል ወይን ጠጅ ፋብሪካ (ካስቴል ዋይነሪ) በኢትዮጵያ ያመረታቸውን ሰባት ዓይነት የወይን ጠጅ መጠጦች ዛሬ በዝዋይ ያስመርቃል፡፡
የድርጅቱ የሽያጭና የገበያ ማናጀር ወ/ሪት ዓለምፀሐይ በቀለ በተለይ ለአዲስ አድማስ እንደገለጸችው፤ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ካስቴል ዋይነሪ፣ ከእርሻው የለቀመውን የወይን ምርት ለመጀመሪያ ጊዜ በመጥመቅ 1.1 ሚሊዮን ጠርሙስ ወይን ጠጅ አምርቷል፡፡
የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ በ2007 ዓ.ም በፈረንሳይና በሰሜን አፍሪካ በወይን እርሻና መጠጥ ታዋቂ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ የቢጂአይ ኢትዮጵያና የካስትል ቢራ ፋብሪካዎች ባለቤት የሆኑትን ፈረንሳዊ ሚ/ር ካስቴልን በኢትዮጵያም በወይን ጠጅ ዘርፍ እንዲሰማሩ እንደጋበዟቸውና ባለሀብቱም በጠቅላይ ሚ/ር ሐሳብ ስለተስማሙ ፕሮጀክት ተቀርፆ ወደ ሥራ መገባቱን ማናጀሯ ገልጻለች፡፡
በቀጣዩ ዓመት ከፈረንሳይ የመጡ የወይን እርሻና ጠመቃ ባለሙያዎች፣ ከተመለከቷቸው የተለያዩ ቦታዎች ዝዋይ ለወይን እርሻ የተሻለች መሆኗን በማመናቸው፣ 498 ሄክታር መሬት በሊዝ በመውሰድ፣ ከፈረንሳይ የመጡ የተለያዩ ምርጥ የወይን ዘሮች መተከላቸውንና የወይን ጠጅ ማምረቻ ፋብሪካም እዚያው መቋቋሙ ታውቋል፡፡
ዓለም አቀፍ ቫራይቲ የተባሉት ምርጥ የወይን ዝርያዎች ካቤርኔ ሶቪኞ፣ ሲራ እና ሜርሎ የተባሉት የቀይ ወይን ዝርያዎች ሲሆኑ የነጩ ወይን ደግሞ ሻርዶኔ የተባለ ዝርያ መሆኑ ታውቋል፡፡ የወይን ጠጆቹ መጠሪያ አኬሽያ (ግራር) እና ሪፍት ቫሊ (ስምጥ ሸለቆ) ሲሆን በአኬሽያ ስም ሚዲየም ስዊት ሬድ፣ ሚዲየም ስዊት ኋይት እና ድራይ ሬድ ወይን ጠጆች ይመረታሉ፡፡ በደረጃው ከፍ ያለውና በሪፍት ቫሊ ስም የሚጠመቁ ካቤርኔ ሶቪኞ፣ ሲራ፣ ሜርሎ እና ሻርዶኔ ሲባሉ፣ በአጠቃላይ ሰባት ዓይነት ወይን ጠጆች እንደሚመረቱ ማናጀሯ አስረድታለች።   
ከወይን ጠጆቹ ምርት ግማሹ አገር ውስጥ፣ የተቀረው ግማሽ ደግሞ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ነው፡፡ ከትላልቆቹ የውጭ ገበያ አሜሪካና ቻይና ዋናዎቹ ሲሆኑ ከአውሮፓ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣… ከጎረቤት አገሮች ወደ ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ጅቡቲ፣ ታንዛኒያ፣ ለመላክ ታቅዷል፡፡
የወይን ተክል ምርት የሚሰጠው በሦስት ዓመት ነው፡፡ በ2011 እና በቀጣዩ ዓመት ምርት ቢሰበስቡም መጠኑ በቂ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ጠምቀው፣ ጥራቱ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላ መሆኑን አረጋግጠዋል። “ያለፈው ዓመት ምርት ለምንፈልገው ጠመቃ በቂ ስለሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ 1.1 ሚሊዮን (አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺ) ጠርሙስ ወይን ጠጅ አምርተን ዛሬ እያስመረቅን ነው፡፡ ወይን ጠጁ ገበያ ላይ የሚውለው ግን በጋው ውስጥ ነው” ብላለች ወ/ሪት ዓለምፀሐይ በቀለ፡፡
ለወይን እርሻው፣ ለፋብሪካው ተከላ፣ ለጠመቃ፣ … ብዙ ካፒታል ወጪ ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ 25 ሚሊዮን ዩሮ (ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ) መውጣቱን የጠቀሰችው ዓለምፀሐይ፤ ለ250 ቋሚና ከ500 ለሚበልጡ ጊዜያዊ ሰራተኞች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግራለች፡፡  
ካስቴል ወይን ጠጅ ፋብሪካ ለብዙ ዓመታት በመንግሥት ይዞታነት የተለያዩ የወይን መጠጦችን ሲያመርት ቆይቶ ወደ ግል ከዞረው አዋሽ ወይን ጠጅ ፋብሪካ ቀጥሎ በኢትዮጵያ የወይን መጠጦች በማምረት ሁለተኛው የግል ድርጅት መሆኑ ታውቋል፡፡

Read 3396 times