Saturday, 22 March 2014 11:54

የቁጫ አርሶ አደሮች በወረዳው ባለስልጣናት እየተዘረፍን ነው አሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

“አስር ሳንቲም እንኳን ከአርሶ አደር ገንዘብ አልተሰበሰበም” የወረዳው ፖሊስ
        በደቡብ ክልል በጋሞ ጎፋ ዞን በቁጫ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች የማንነት ጥያቄ በማንሳታችን በወረዳው ኃላፊዎችና ታጣቂዎች በቅጣት ስም ገንዘብ እየተዘረፍን ነው ሲሉ አማረሩ፡፡ እስካሁን ከዘጠኝ ቀበሌዎች ብቻ ከ170 ሺህ ብር በላይ በወረዳው ኃላፊዎችና ታጣቂዎች መሰብሰቡን አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡ በቁጫ ወረዳ የሰላም በር ፖሊስ ፅ/ቤት እስረኞች አስተዳደር የሆኑት ኮማንደር አሰፋ ታፈሰ በበኩላቸው፤ መንግስት ሳያውቀው ያለ አግባብ ከአርሶ አደሩ የሚሰበሰብ አስር ሳንቲም የለም ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎች ግን በቅጣት ሰበብ ገንዘባቸውን ተዘርፈዋል ያሏቸውን የ273 አርሶ አደሮች ስም ዝርዝር፣ የተወሰደባቸውን የገንዘብ መጠንና ገንዘቡን ሰብስበዋል የተባሉትን የቀበሌ አስተዳዳሪዎችና ታጣቂዎችን ስም ዝርዝር መያዛቸውን ይናገራሉ፡፡ “ይህ ሁሉ በደልና ግፍ የሚደርስብን ማንነታችን ይከበር በሚል ጥያቄ በማንሳታችን ነው” ብለዋል፡፡ ለጥያቄያችን ምላሽ ለማግኘት ከዞን እስከ ክልል እንዲሁም እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የፌዴሬሽን ም/ቤት ድረስ አቤት ብንልም እስካሁን ሰሚ አጥተናል ሉት የቅሬታ አቅራቢዎች ተወካዮች፤ይባስ ብሎ እንግልት፣ ግርፋት፣ እስራትና በቅጣት ሰበብ የገንዘብ ዝርፊያ እየተፈፀመብን ነው ሲሉ አማረዋል፡፡
“ገንዘቡን ከአርሶ አደሩ የሚሰበስቡት የማንነት ጥያቄ አንስተሃል፣ መከፋፈልንም ፈጥረሃል፣ስለዚህ ትታሰራለህ ወይስ ገንዘብ ትቀጣለህ በሚል ማስፈራሪያ ነው” ያለው የአካባቢው ወጣት ነዋሪ፣ ህዝቡ እስር ቤት መግባትና መጉላላት ስለማይፈልግ ለፍቶ የቋጠረውን ገንዘብ እያስረከበ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ የቀበሌው ኃላፊዎች ከፖሊስ ጋር እየሄዱ ያለደረሰኝ የሚሰበስቡት ገንዘብ ለምን ጉዳይ እንደሚውል እንደማያውቁ የገለፀው ይኸው ወጣት፤“ገንዘቡንም አንሰጥም፣ አንታሰርምም” ያሉ ነዋሪዎች ከአካባቢያቸው ሸሽተው ወደ አዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች ለመሸሽና ለመሰደድ ተገደዋል ብሏል፡፡  ከቁጫ ሸሽተው ወደ አዲስ አበባ የመጡ ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ የአገር ሽማግሌ እንደሚሉት፤ የቀበሌው ሹሞችና ታጣቂዎች ገንዘብ ሲሰበስቡ ሻል ያለውን ሰው ብዙ ብር የሚጠይቁ ሲሆን  ከተሰበሰበው ገንዘብ እስካሁን ዝቅተኛው 300 ብር፣ ከፍተኛው አስር ሺህ ብር  ነው፡፡ ይህ ሁሉ እንግልት እንዲቆም፣ መንግስት ጣልቃ ገብቶ አንድ እርምጃ እንዲወስድና የቁጫ ህዝብ የማንነት ጥያቄ እንዲመለስ የአገር ሽማግሌው አሳስበዋል፡፡
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉና ከመኖርያቸው ሸሽተው እንደሄዱ የተናገሩ የቁጫ ተወላጅ፤“በሽምግልና ዕድሜ ሰርቼ ከቋጠርኩት ላይ 10 ሺህ ብር ተወስዶብኛል፤በዚያ ላይ ከስራ ተስተጓጉዬ ወላይታ ተደብቄያለሁ” ሲሉ አማረዋል፡፡
ታህሳስ 25 ቀን 2006 ዓ.ም የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ኡሞድ ኡቦንግ ለክልሉ መስተዳደር በፃፉት ደብዳቤ፤ በ23/04/2006 “በቁጫ ወረዳ አመራሮች በደል እና አፈና ደርሶብናል” በሚል ከቁጫ ህብረተሰብ አቤቱታ እንደደረሳቸው ከገለፁ በኋላ፣ “የቁጫ ማህበረሰብ ዘላቂ መፍትሄ ሊያገኝ የሚችለው በክልሉ መንግስት ነው፤በመሆኑም የችግሩን ግዝፈት በማየት የቁጫ ህዝብ የማንነት ጥያቄ እልባት እንዲያገኝ፣ እየደረሰባቸው ያለው ድብደባና እንግልት በክልሉ መንግስት በኩል ታይቶ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ” በሚል የቁጫን ህዝብ የአቤቱታ ደብዳቤ አያይዘው እንደላኩ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጠቁመው ይሁን እንጂ በክልሉ መንግስት በኩል እስካሁን ምንም ምላሽ አላገኘንም ብለዋል።  ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ እስካሁን በአርባ ምንጭ ማረሚያ ቤት ከ280 በላይ ሰዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ፣ሌሎች ተምረው በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ 31 ያህል የቁጫ ተወላጆች የወረዳውን ኃላፊዎች ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በማውገዛቸው “ህገመንግስቱን በሃይል የመናድ ሙከራ አድርገዋል” በሚል ክስ ቀርቦባቸው በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት እየተከራከሩ እንደሆነ ገልፀው፣ ይህ ሁሉ እንግልት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ “አሁንም ቢሆን ቁጫ ቁጫ እንጂ ጋሞ አይደለም፣ፍላጎታችን በተገቢው መንገድ እስኪመለስ ጥያቄያችን ይቀጥላል” ብለዋል ቅሬታ አቅራቢዎቹ፡፡ የቁጫ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት የእስረኛ አስተዳደር ኃላፊ ኮማንደር ታደሰ ታፈሰ በበኩላቸው፤በወረዳው በውንብድና፣ በቤት ቃጠሎ፣ የመኪና መንገድ በመቁረጥ እና ያልተፈቀደ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ተከሰው፣ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ቀርቦባቸው የታሰሩ፣ በቁም እስር ላይ ያሉና በገንዘብ የተቀጡ ሰዎች መኖራቸውን አምነው፣ የማንነት ጥያቄ በማንሳቱ የታሰረና ገንዘብ የተወሰደበት ሰው እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
ለልማት ስራ ከአካባቢው አርሶ አደር ገንዘብ ይሰበሰብ እንደሆነ የጠየቅናቸው ኮማንደሩ፤ “መንግስት የት ሄዶ ነው ከህዝብ ገንዘብ የምንሰበስበው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የአርባ ምንጭ ማረሚያና ማነፅ ተቋም ኃላፊ ኮማንደር አበበ ሀብቴን በዞኑ ማረሚያ ቤት ስለሚገኙ እስረኞች ሁኔታ ጥያቄ አቅርበንላቸው፤  በስልክ መረጃ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ገልፀው፤“አርባ ምንጭ ድረስ በመምጣት ማጣራት ይኖርባችኋል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

Read 2326 times Last modified on Saturday, 22 March 2014 12:00