Saturday, 15 March 2014 13:04

“ማሽን ሲቆም ያመኛል፤ ሥራ ሲፈታ ደስ አይለኝም”

Written by  ከጋዜጣው ሪፖርተሮች
Rate this item
(1 Vote)

የጋዜጦች ሕትመት መዘየግት እስከ ነሐሴ ይዘልቃል
ብርሃንና ሰላም ከደንበኞች ጋር የተጠያቂነት ውል ሊፈራረም ነው
የሞባይል ካርድና “ሰላምታ” መጽሔትን ለማተም አቅዷል
ለሰራተኞቹ የ97 በመቶ የደሞዝ ጭማሪ ሊያደርግ ነው

        ወደ ግቢው ስንገባ ሰራተኞች የዕለቱን ሥራ ጨርሰው እየወጡ ነበር፡፡ አካሄዳችን የድርጅቱን ሥራ አስኪያጅ ለማነጋገር ነው፤ ቀጠሮ ግን አልነበረንም፡፡ “ከሥራ ሰዓት ውጪ፣ ቅዳሜና እሁድ፣ በበዓላት ቀናት ጭምር ይሰራሉ፤ ከቢሮ አይጠፉም” ስለተባለ ከፎቶግራፍ ባለሙያችን ጋር በድፍረት 4 ኪሎ ወደሚገኘው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሄድን፡፡  
5ኛ ፎቅ ስንደርስ ቢሯቸው ወለል ብሎ ስላገኘን ወደ ውስጥ ገባን፡፡ በዚያን ሰዓት ሥራ አስኪያጁ፣ ከአንድ የሥራ ኃላፊ ጋር እየተወያዩ ነበር፡፡ ራሳችንን አስተዋውቀን የመጣንበትን ጉዳይ ነገርናቸው፡፡ “ከሥራ አስኪያጁ ቀጠሮ አላችሁ እንዴ? እኔ ቀጠሮ መስጠቴ ትዝ አይለኝም፤ በዚህ ላይ እስቲ ሰዓታችሁን ተመልከቱ! ከሥራ ሰዓት ውጪ ነው’ኮ የመጣችሁት። እንደምታዩት አጣዳፊ ጉዳይ ስላለን ስለእሱ እየተወያየን ነው፡፡ ሥራ ደግሞ በጣም ይበዛብኛል፡፡ ጊዜ የለኝም፡፡ ለማንኛውም፣ ቀጠሮ አስይዛችሁ ብትመጡ ይሻላል፡፡…” የሚል ነበር የጠበቅነው፡፡ ልክ ነዋ! ምክንያቱም ሌሎች ባለስልጣናትና ኃላፊዎች፣ ኧረ ዝቅተኛ ሠራተኞችም እንደዚህ ነዋ የሚሉን፡፡ እሳቸው ግን ትንሽ እንኳን አላቅማሙም፡፡ እኚህ ሰው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተካ አባዲ ናቸው፡፡
ከጥቂት ሳምንት በፊት ድርጅቱ የሕትመት አካዳሚ ላቋቁም ነው፤ የኢትዮጵያንና የሌሎች አፍሪካ አገራት ገንዘብ የማተም አቅም አለኝ፣ … የሚል ዜና በሚዲያ አስነግሮ ነበረ፡፡ በተቃራኒው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ድርጅቱ የሚያትማቸውን ጥቂት ጋዜጦች እንኳ በወቅቱ ማተም አቅቶታል፣ አንድና ሁለት ቀን አዘግይቶ ነው የሚያስረክበው። እንዴት ነው፤ በተግባር የሚታየውና በዜና የገለጻችሁት ነገር አይጋጭም ወይ? አልኳቸው አቶ ተካን፡፡
ሥራ አስኪያጁ ግን ፍርጥም ብለው ይመስላል እንጂ አይጋጭም አሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጋዜጦች እየዘገዩ መሆኑን አምነው ለመዘግየታቸው ግን ሁለት ምክንያቶች እንዳሏቸው ገልፀዋል፡፡ አንደኛ ጋዜጦቹን የሚያትሙት መሳሪያዎች (ማሽኖች) የቆዩ ስለሆነ ቴክኒካሊ አቅማቸው እየወረደ ነው። አቅማቸውን ለመገንባት መለዋወጫ ለመግዛት ቢጠይቁም መሳሪያዎቹን ያመረተው ፋብሪካ ስለተዘጋ  መለዋወጫዎቹን ማግኘት አልቻሉም። ሁለተኛው ደግሞ የብሔራዊ ፈተና ሕትመት ስለተጀመረ ከአንድ ወር ወዲህ ጋዜጦች እየዘገዩ መሆኑንና ችግሩን እንዳጎላው ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ በዚህ የደንበኞች ቅሬታ ላይ ሥር-ነቀል ለውጥ ለማምጣት በማሰብ ከአንድ ዓመት በፊት “ክሪስ ግሩፕ” በተባለ ኩባንያ አንድ ጥናት አስጠንቶ ነበር፡፡ አቶ ተካ አሁን መንግሥት በፈቀደላቸው 558 ሚሊዮን ብር ጥናቱን ተግባራዊ ማድረግ እንደ ጀመሩ ገልፀዋል፡፡ ከጃፓን የገዟቸው ሁለት ማሽኖች እስከ ግንቦት ድረስ ይገባሉ፡፡ አንዱ ለጋዜጣ ሕትመት፣ ሌላኛው ለመጻሕፍት ህትመት ብቻ ዲዛይን የተደረጉ ናቸው፡፡ በአንድ ጊዜ አራት ቀለም የሚያትመው መሳሪያ ገብቶ እየተተከለ ነው፡፡ ሌሎች በጥናቱ የተካተቱ የመፍትሔ ሀሳቦች ትግበራ በሂደት ላይ ነው ብለዋል፡፡
ማተምያ ቤቱ ገንዘብን የሚያህል ነገር ለማተም እየተዘጋጀሁ ነው ማለቱን ብዙዎች በጥርጣሬ ነው የተመለከቱት፡፡ አቶ ተካ ግን “በእኔ ይሁንባችሁ፣ አትጠራጠሩ፣ እናደርገዋለን” እያሉ ነው፡፡ “ገንዘብ በማሳተም ጉዳይ እዚህ ወይም ውጭ አገር ይታተም ብሎ የሚወስነው መንግሥት ነው፡፡ እኛ እያልን ያለው ገንዘብ የማተም አቅሙ አለን ነው፡፡ እኛ ባደረግነው ጥናት የኢትዮጵያም ሆነ የሌሎች አፍሪካ አገሮች ገንዘብ ማተም እንችላለን፡፡ ከ54ቱ የአፍሪካ አገሮች የራሳቸውን ገንዘብ የሚያትሙት ከስምንት አይበልጡም፡፡ የአስሩን አገሮች ብናትም እንኳ ዳጎስ ያለ የውጭ ምንዛሪ እናገኛለን ከሚል አስተሳሰብ የመጣ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ገንዘብ ውጭ አገር ስታሳትም የተለያዩ ወጪዎች አሉ፡፡ የሴኩሪቲ፣ የትራንስፖርት የአስተዳደር፣… ወጪው በጣም ብዙ ነው፡፡ አገር ውስጥ ቢታተም ግን ወጪው በጣም ይቀንሳል፡፡ ለ46 ዓመት ያህል ምስጢራዊ ህትመት ስንሰራ ስለቆየንና ልምድ ስላለን ገንዘብ ማተም እንችላለን ብለን ለመንግሥት ጥያቄ አቅርበናል፡፡
“እኔ የአታሚዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ስለሆንኩ የሕትመት ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚው ዕድገት መጫወት ያለበትን ሚና አልተወጣም እያልኩ ብዙ ጊዜ ለመንግሥት እናገራለሁ፡፡ የሐራጅ ማስታወቂያ፣ ታክስ፣ የጋዜጣ ሕትመት ዋጋ፣ መጽሐፍት ከውጪ ሲገቡ፣… የሚቀረጠው … ዋጋው በጣም ውድ ነው እያልን እንጮሃለን፡፡ ብርሃንና ሰላም ሁሉንም ነገር ማተም እንደሚችል በጥናታችን አረጋግጠናል፡፡ ሁሉም ነገር እዚህ ከታተመና ዋጋው ከቀነሰ ብዙ አንባቢ፣ ብዙ ገቢ ይኖራል፡፡ ያኔ ነው የሕትመት ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚው ድጋፍ ማድረግ የሚችለው፡፡ እኛ ዕቅዳችን አሁን ያሉትን ጥቂት ጋዜጦች በጥራትና በብቃት ማተም ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች 20 እና 30 ትላልቅ ጋዜጦችም ወደ እኛ እንዲመጡ እንፈልጋለን፡፡ መሳሪያዎቹን የሸጡልን ኩባንያዎች እስከ ግንቦት ስለሚመጡ ቦታ አዘጋጁ እያሉ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት መሳሪያዎች መጥተው ሲተከሉ አሁን ያለው ችግር በእርግጠኝነት ይወገዳል፡፡ የመሳሪያዎቹ ችግር እስካሁን ያልተፈታው ማተምያ ቤቱ ያተረፈውን ሁሉ መንግሥት ስለሚወስድበት ነበር፡፡ አሁን ግን መንግሥትም ያለውን ችግር ተገንዝቦ በጀት ስለፈቀደልን፣ መሳሪያዎች ተገዝተው እየገቡ ስለሆነ ትልቅ ለውጥ አለ፡፡ ለውጡ የመጣው ደግሞ የአታሚዎች ማኅበር ባደረገው ጥረት ነው። ዓላማችን ዋጋ ሲቀንስ ብዙ አሳታሚና ብዙ አንባቢ ይኖራል፡፡ ብዙ አንባቢ ሲኖር ብዙ ትዕዛዝ እንቀበላለን፣ ገቢያችን ያድጋል የሚል ነው” ብለዋል - ሥራ አስኪያጁ፡፡
አቶ ተካ ህይወታቸውን ሁሉ ያሳለፉት በማተምያ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ከማተሚያ ቤት ሌላ ሰርተው አያውቁም፡፡ ቀደም ሲል በንግድና አርቲስቲክ ማተሚያ ቤቶች ከለቀማ፣ ከካሜራ፣ ከስትራፕ፣… አንስቶ ደረጃ በደረጃ እስከ ሥራ አስኪያጅነት የደረሱ በመሆናቸው፣ ሁሉንም ሥራ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ሌላው ባህሪያቸው ሥራ ወዳድነት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ “ማሽን ሲቆም ያመኛል” ይላሉ፡፡ ከአገራችን ሥራ አስኪያጆች በተለየ መልኩ ወደተለያዩ ክፍሎች እየሄዱ ከሰራተኛው ጋር በመስራት፣ ድርጅቱ ያለበትን የአሰራር ችግር በመፈተሽ መፍትሄ በመዘየድ ይታወቃሉ፡፡ ይህ ባህሪያቸው የብርሃንና ሰላም ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲመጡም አልተዋቸውም፡፡ ቅዳሜና እሁድ ወይም የበዓል ቀን ሳይሉ የሥራ ካፖርታቸውን ለብሰው ወደ አንዱ ክፍል ሄደው ይሰራሉ፤ ሰራተኛውን ያነጋግራሉ፡፡
ቀደም ሲል የነበሩት ሥራ አስኪያጆች፣ከቢሮ ወጥተው ከሰራተኛው ጋር ስለማይሰሩ፣ ጥቂት ሰራተኞች አቶ ተካ ካፖርት ለብሰው አብረዋቸው ሲሰሩ ያልለመዱት ነገር ስለሆነባቸው መፍራትና መበርገግ፣ አዲሱ መዋቅር ተሰርቶ ተግባራዊ ሲሆን እንቀነሳለን (እንባረራለን) በማለት መስጋት ጀመሩ። ሥራ አስኪያጁ ያቀዱት ለውጥ ስላልገባቸው እንዳልወደዱትና ጉምጉምታ እንደጀመሩም ሠራተኛው ይናገራል፡፡
የእያንዳንዱን ሰራተኛ ሐሳብ ማወቅ ይቸግራል ያሉት አቶ ተካ፤ ሰራተኛውን የሚያገኙት በመረጠው የሙያ ማኅበሩ ተወካዮች ስለሆነ ከእነሱ ጋር ያላቸው ግንኙነት ጥሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ “ስለሰራተኛው መብትና ጥቅማ ጥቅሞች ከማኅበሩ አመራር ጋር እየተነጋገርን ነው የምሰራው፤ የውስጡን ባላውቅም በሰራተኛው ፊት ላይ የማየው ነገር ጥሩ ነው፡፡ ሰራተኛው የሚፈልገው ነገር ወይም ችግር ካለበት ከማኅበሩ ጋር የምንወያይባቸው መድረኮች ስላሉ እዚያ ላይ አፈታቱ እንዴት ይሁን? በሚለው ነጥብ ላይ እንወያያለን እንጂ ከ800 በላይ ከሆነ ሰራተኛ ጋር ያለን አግባብ እንዲህ ነው ብሎ መናገር ይከብዳል፡፡ ከሰራተኛው ጋር የምንሰራቸው ፕሮጀክቶችም አሉ። እዚያ ላይ የማየው ነገር በጣም ጥሩ ነው፡፡
“የእኔ አመራር የማይመቻቸው ጥቂት ሰራተኞች ካሉ የራሳቸውን ስሜት ሊያንፀባርቁ ይችላሉ። አንድ ሰው ከለመደው አካባቢ ወደ ሌላ ሲሄድ የማያውቀው አካባቢ አቀባበል ጥሩ ላይሆን ይችላል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን እየተሻሻለ ይሄዳል። ሌላው እንደመጣሁ ያደረግሁት ነገር ይኼው እንደምታየው ቢሮዬን ለማንኛውም ሰራተኛ ክፍት ነው፡፡ ሰራተኛው በማኅበሩ በኩል ከሚያቀርበው ጥያቄ በተጨማሪ ለእኔ ማቅረብ ያለበት ነገርና ሐሳብ ካለው ሰተት ብሎ ገብቶ፣ተወያይተንና ተግባብተን ይመለሳል። አርቲስቲክም እያለሁ ኃይለኛ ነበር የምባለው። ይኼ የሆነው ደግሞ ሥራ ስለምወድ እንጂ ማንንም ሰው ለመጉዳት ፈልጌ አይደለም። እዚህም አብሬአቸው ስሰራ ሀሳቤን ያልተረዱ ሰራተኞች ሊፈሩና ሊሸማቀቁ ይችሉ ይሆናል፡፡ አንድ ጋዜጣ ላይ፣ ማኔጅመንቱ ሰራተኛውን ወዛደር ሊያደርግ አብሮት ይሰራል፣ አብሮ ይሸከማል ብሎ ጽፏል፡፡ የእኔ ሀሳብ ግን እንደዚያ አይደለም፤ ቤተሰባዊ አመራር ለመፍጠር ነው፡፡ አብሬአቸው ብበላ፣ ብጠጣ፣ ብሰራ… እንዳይፈሩኝና እንዲቀርቡኝ ለማድረግ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ’እንዲህ ቢሆንስ ምን ይመስልሃል?’ የሚል ሀሳብ አንስተው ልንወያይበትና ሌላ ቦታ የማይጠይቁትን ጥያቄ ሊያነሱ… ይችላሉ። እንዲያውም ባለፈው እሁድ እኔ ሳልጠይቃቸው በገዛ ፈቃዳቸው ነፃ የሥራ ዘመቻ አድርገዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ከእኔ ጋር ወይም ከአመራሩ ጋር ያላቸው አቀራረብ ጥሩ መሆኑን ነው፡፡
“አመራሩ ያላሰበውን ነገር ሁሉ ‘ይኼ ነገር ለምን እንዲህ ይሆናል? እንዲህ ቢደረግስ? ምን ይመስላችኋል?’ በማለት ለቅርብ አለቃቸው ሐሳብ በማቅረብ፣ የማስተካከያ እርምጃ የምንወስድበት ጊዜ አለ፡፡ ይህ “ድርጅቱ የእኔ ነው” የሚለውን ስሜት ስለሚያሳየኝ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ሰራተኛው ደስተኛ ያልሆነበት የቆየ የደሞዝ ስኬል አለ፡፡ ከሌላው ድርጅት ጋር ሲታይ ደሞዛቸው በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ በአርቲስቲክ ማሽን ኦፕሬተር 3652 ብር ደሞዝ ሲያገኝ፣ እዚህ ግን 3001 ብር ነው የሚያገኘው፤ የ600 ብር ለውጥ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ደሞዝ እንዲስተካከልላቸው ቦርድ ላይ አንስተን ተወያይተንበታል፡፡ ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ የደሞዝ ስኬል ይሰራል የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡ ያኔ ደሞዛቸው 97 በመቶ ያድጋል ማለት ነው፡፡
“እንደዚህም ሆኖ የስራ ውጤታቸው ጥሩ ነው፤ ከአምናው ይሻላል፡፡ ስለዚህ ጥሩ ተቀብለውኛል የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡ ኃይለኛ ነው የሚባለው ግን እውነት ነው፡፡ ማሽን ሲቆም ያመኛል፡፡ ይኼ ምንም ላደርገው የማልችለው ልማድ ነው፡፡ ሥራ ሲፈታ ደስ አይለኝም፡፡ የኃይለኝነቴ ማጠንጠኛ በቃ ሥራና ሥራ ብቻ ነው” በማለት አብራርተዋል፡፡
አቶ ተካ፤ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ለወደፊት ያቀዳቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ ይናገራሉ። አዲሱ ፕሮጀክት ትልቅ፣ ሰፊና ዘመኑ በደረሰበት የቴክኖሎጂ ውጤቶች የተደራጀ በመሆኑ ውጭ አገር የሚታተሙ ነገሮች በሙሉ እዚህ ተመልሰው እንዲታተሙ የሚያደርግ ነው፡፡ ለምሳሌ የአየር መንገድ “ሰላምታ” መጽሔት፣ የቴሌኮም ቅድመ ክፍያ የሞባይል ካርድ… ህትመትን እዚሁ የሚያስቀር ትልቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ አየር መንገዱ በዓመት ሦስትና አራት ጊዜ ኬንያ እየላከ ነው የሚያሳትመው፡፡ ለዚህም ብዙ ገንዘብ ያወጣል፡፡ በፊት እዚያ የሚሄደው ጥራት ያለው መሳሪያ ስለሌለን ነበር፡፡ አሁን መሳሪያውን ስለገዛን እዚህ ቢታተም ወጪው በጣም ይቀንሳል፡፡ እኛ ያለንን አቅም ለመንግሥት አሳውቀናል፤ ውሳኔው ግን የመንግሥት ነው፡፡
ለወደፊት ያሰቡት ትልቁና ዋንኛው እቅድ ከደንበኞች ጋር የሚገቡት የተጠያቂነት ቻርተር ነው፡፡ “ለምሳሌ አዲስ አድማስ ወይም ሌላ አሳታሚ ድርጅት፣ ጋዜጣው የታተመበትን ዋጋ ባይከፍል ድርጅቱን ከስሰን የሰራንበትን ዋጋ እናስከፍላለን፡፡ እኛ ህትመት ብናዘገይ፣ ጋዜጣውን ወይም መጽሔቱን ከሁለትና ከሶስት ቀን በኋላ ብናትም፣ ጥራት ብናጓድል፣ እስካሁን በነበረው አሰራር በተለያዩ ምክንያቶች አንጠየቅም፣ አንከሰስም፡፡ በቢዝነስ ዓለም አንዱ የሚጠየቅበትና ሌላ የማይጠየቅበት አሰራር ትክክል አይደለም፡፡ ለምሳሌ እናንተ ጋዜጣ ላይ የወጣ ሰው ፎቶግራፍ ቢበላሽ፣ ግለሰቡ እናንተን ይጠይቃል፣ እናንተ ደግሞ በሶስተኛ ወገን ተጠያቂነት እኛን መጠየቅ አለባችሁ፡፡ ሁሉም ወገን ባጠፋው ነገር ወይም በሰራው ስህተት መጠየቅ አለበት፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥቃቅን የሚመስሉ የአሰራር ድክመቶች መወገድ አለባቸው፡፡ ስለዚህ መጋቢት 9 ቀን 2006 ዓ.ም ቃል የምንገባበት የተጠያቂነት ውል (ቻርተር) አዘጋጅተናል፡፡ ይህ የአመራሩ ውሳኔ ብቻ አይደለም፡፡ የሰራተኛ ማህበሩን “ቃላችንን ባናከብር፣ ህትመት ብናገዘይ፣ ጥራት ብናጓድል፣… ደንበኞቻችን እንዲጠይቁን የሚያደርግ ውል ልንገባ ነው” ብለን ነገርናቸው፡፡ እነሱ ደግሞ ለሰራተኛው ነገሩ፡፡ የህልውና ጉዳይ ስለሆነ በአንድ ድምፅ ነው የተቀበሉት” ብለዋል።
ዋናው ችግር የአቅም ማነስ ነው ይላሉ - አቶ ተካ። “ይህ ችግር መፈታት አለበት፤ጋዜጦች አንዳንዴ አርፍደው ይወጣሉ፣ አንድና ሁለት ቀን የሚዘገዩበትም ጊዜ አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ደንበኞቻችን ’አዲስ ዘመን የመንግሥት ስለሆነ አስቀደማችሁት፣ እኛ የግል ስለሆንን አሳደራችሁ፣…’ ይሉናል፡፡ እውነቱን ለመናገር ይኼ የወገንተኝነት ጉዳይ አይደለም፤ የአቅም ማነስ፣ የማተሚያ መሳሪያዎች እርጅና ነው፡፡ ይህ ችግር በቅርቡ ስለሚፈታና ስለሚስተካከል የደንበኞቻችንን እሮሮና ቅሬታ ለማስቀረት እየሰራን ነው” ብለዋል፡፡
ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፣ ለዘመናት ሲያንገላታው የኖረውን የአሮጌ መሳሪያ አቅም ማነስ፣ አዲስና ዘመናዊ መሳሪያዎችን በመግዛት፣ በቅርቡ ከችግሩ እንደሚወጣ ተገልጿል፡፡ እነዚህን መሳሪያዎች ለማንቀሳቀስ፣ ሲበላሹ ለመጠገን፣… መሳሪያዎቹን የሚያውቅ ባለሙያ ያስፈልጋል፡፡
“የዘመናዊ መሳሪያ ባለቤት መሆን በራሱ የመጨረሻ ግብ አይደለም፡፡ የማንኛውም መ/ቤት የመጨረሻ ግብ፣ የተማረና የሰለጠነ የሰው ኃይል ሀብት ነው፡፡ በዚህ በኩል የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት የህትመት ኢንዱስትሪ አካዳሚ ለመክፈት ባለ 7 ፎቅ ህንፃ ለመገንባት ተወስኖና በጀት ተመድቦ፣ ህንፃው የሚሰራበትን ቦታ ማስተካከል ተጀምሯል፡፡
“አዳዲስ ለተገዙት ዘመናዊ መሳሪያዎች፣ ሠራተኞች ውጭ አገር ልከን በአጫጭር ኮርሶች እናሰለጥናለን፡፡ የመሳሪያዎቹ ዋጋ ላይ ባለሙያዎችን የሚያሰለጥኑበትን ዋጋ እንዲጨምሩ አድርገን ነው የተዋዋልነው፡፡ ስለዚህ ባለሙያዎች፣ መሳሪያው ወደ ተገዛበት አገር ተልከው ይሰለጥናሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መሳሪያዎቹን አምጥተው ሲተክሉም ሰዎችን ያሰለጥናሉ፡፡ እኛ የምናደርገው ነገር የሚሰለጥኑ ሰዎችን ማቅረብ ነው። እነሱ ስልጠናውን የመቀበል ችሎታና ዝንባሌያቸውን ለማወቅ ፈተና ይሰጧቸዋል፡፡ ከዚያም የወደቁትን ትተው ያለፉትን ያሰለጥናሉ፡፡ እንደዚህ ነው ያሰብነው።”
ሰራተኛ ማኅበሩም፣ በአቶ ተካ ሀሳብና እቅድ ሙሉ በሙሉ ይስማማል፡፡ ሳምንታዊ ጋዜጣ በወቅቱ ማተም አቅቶት እየታየ ገንዘብ፣ ሞባይል ካርድ፣ ሰላምታ መጽሔት፣… የማተም አቅም አለን ትላላችሁ? እንዴት ይሆናል? አልናቸው፡፡
“የጋዜጦች መዘግየት እውነት ነው” አለ፤ አንድ የማኅበሩ አባል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ማተሚያ መሳሪያው አርጅቶ ጥርሱ በመበላሸቱ ነው፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ አሳታሚዎች ጋ ያለ ችግር ነው፡፡ በፍላሽ ወይም በወረቀት የሚያመጡት ጽሑፍ፣ የጥራት ወይም ሌላ ችግር ኖሮት አስተካክላችሁ አምጡ ስንላቸው በጊዜ አያቀርቡም፣ በዚህም ይዘገያል፡፡ ጋዜጦች ተደራርበው መምጣታቸውም እንዲሁ የመዘግየት ምክንያት ነው ብሏል፡፡
ሰራተኛው ከአቶ ተካ ጋር አልተስማማም፣ ቅሬታ አለው የሚለውን መረጃ ማኅበሩ በፍፁም አይቀበለውም፡፡ እሳቸው ከመጡ ቅርብ ጊዜ ቢሆንም ተስማምተው እየሰሩ እንደሆነ ነው የሚናገሩት። “ማንኛውም አዲስ ሰው ሲመጣ፣ ባህርይው እስኪታወቅ ለመላመድ ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ ይኼ ታዲያ ያለመግባባትን አያመለክትም፡፡ ሰራተኛው የሥራ ሰው መሆናቸውን ስለተረዳ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያለ አንዳች ቅሬታ ለለውጥ እየሰራን ነው፡፡ እሳቸው ብዙ የተበላሸ ነገር ስለነበር በኃይለ ቃል ይስተካከል፤ እንስራ አሉ፡፡ ሰራተኛው ደግሞ እኛ አውቀን የምንሰራ ሰዎች ነን፡፡ እንዴት ኃይለ ቃል ይናገሩናል? በሚል የተፈጠረ ትንሽ ቅሬታ ነበር፡፡ አሁን ግን ሁሉም በለውጥ መስመር ውስጥ ስለገባ ምንም ችግር የለም” ብሏል ማህበሩ፡፡
ሌላው አባል ደግሞ ጋዜጣ በጊዜ ማውጣት ሳትችሉ እንዴት ገንዘብና ሌላ ነገር እናትማለን ትላላችሁ? ለሚለው ጥያቄ በሚገባ እንችላለን ብሏል። “ገንዘብና ውጭ አገር የሚሰሩ ነገሮችን ለማተም የሚያስፈልገው መሳሪያ ነው፤ በአንድ ጊዜ አራት ቀለም የሚያትም መሳሪያ ገብቷል፡፡ ሌሎችም በቅርቡ ይገባሉ፡፡ ሌላው የሰው ኃይል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከ90 ዓመት በላይ ልምድ ያለው ሰራተኛ አለ፡፡ ሁለቱ አስፈላጊ ነገሮች ከተሟሉ እንዴት ነው የማንችለው?” በማለት ጠይቋል፡፡ ይቋቋማል ስለተባለው አካዳሚም ሲናገር፤ እስካሁን ድረስ አንድም የህትመት ተቋም በአገሪቷ የለም፡፡ ለዚህ ተጠያቂው መንግሥት ነው፡፡ አሁን ግን እኛ ቅድሚያውን ወስደን የህትመት አካዳሚ ለማቋቋም ዝግጅት ጀምረናል፡፡
“እኛ እንደማኅበር ምንቃወመው የሀብት ብክነት ነው፡፡ እኛ ማንኛውንም ነገር የማተም ብቃትና አቅም እያለን ለምን ሌላ ማተሚያ ድርጅት ይፈለጋል? ግልጽ ለማድረግ አገር አቀፍ የፈተናዎች ድርጅት ፈተና ለማተም (ተቃጠለ እንጂ) ማሽን አስመጥቶ ነበር። ብሔራዊ ባንክ፤ አርቲስቲክ ማተሚያን ሊገዛ ነው እየተባለ ይወራል፡፡
ንግድ ባንክ ቦሌ ማተሚያን ገዝቷል፡፡ እያንዳንዱ ድርጅት የራሱን የሚያትም ከሆነ የሀብት ብክነት ነው” ባንኮቹ የገንዘብን ስርጭትና እንቅስቃሴ መቆጣጠር፣ ትምህርት ሚ/ርም ማስተማር እንጂ ህትመት ውስጥ ምን አገባቸው? ሁሉም እንደተቋቋሙበት ዓላማ ቢሰሩ የሀብት ብክነት ይቀራል፣ እኛም ውጤታማ እንሆናለን፣ አገርም ትጠቀማለች ነው የምንለው” ብሏል- የማህበሩ አባል፡፡



Read 3330 times