Saturday, 15 March 2014 12:53

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሌላ የስኬት መንገድ

Written by  ገብረ ክርስቶስ ኃይለ ሥላሴ
Rate this item
(1 Vote)

           የሐዲስ ዓለማየሁ የባሕል ጥናት ተቋም ሁለተኛው ዓመታዊ ዐውደ ጥናት የካቲት 22 እና 23 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም. በደብረ ማርቆስ ከተማ፣ ቤተመንግሥት ትልቁ አዳራሽ ውስጥ ተካሂዶ ነበር፡፡ እኔም ከወደሸዋ በተለይም ከአዲስ አበባና ከሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲሁም ከልዩ ልዩ መ/ቤቶችና የኪነጥበባት ማኅበራት ከተጋበዙ በርካታ ተሳታፊዎች ጋር ታዳሚ ነበርኩ፡፡ አውደ ጥናቱ ያሳደረብኝን ተስፋና የመነቃቃት መንፈስ በአጭሩ ላስቃኛችሁ ወደድሁ፡፡ አስቀድሜ ግን ስለታላቁ ደራሲና ዲኘሎማት ሐዲስ ዓለማየሁ ብታውቁትም እንኳን አንድ ቁም ነገር እነሆ፡፡
እርሳቸው ራሳቸውን ትልቅ የድርሰት ሥራ እንዳለውና አንቱነት እንደሚገባቸው ፈጽሞ ተሰምቷቸው አያውቅም ነበር፡፡ ይኸን ስሜታቸውን ከእኛ ከዘመነኞቹ ጸሐፍት ጋር ላፍታ ሳገናዝበው እጅግ ያስደምመኛል፡፡ እንኳንስ ከዳር እስከ ዳር የሁሉንም ሕዝብ ሕሊናና መንፈስ አለምልሞና በልዩ ትዝታ ሰቅዞ የሚያኖር “ፍቅር እስከመቃብር” መጽሐፍን ያበረከተ ቀርቶ አንዲት አነስተኛ ድርሰት የዶገዶገ ሰው በአንቱነት እንደሚኩራራና እንደሚንጠራራ ማየት በዚህ ዘመን ብርቅ አይደለም፡፡ ሐዲስ ዓለማየሁ ግን በፍቅር እስከመቃብር መጽሐፋቸው መቅድም ላይ የሚከተለውን አስፍረዋል፡፡
«እኔ እዚህ ‹ፍቅር እስከመቃብር› ብዬ ሰይሜ ላንባቢዎች የማበረክታት ልብ ወለድ ድርሰት በታሪኩዋም ሆነ በአጻጻፍ ጥሩ ድርሰቶች የሚባሉት በያዙት ደረጃ እንኩዋንስ ልትደርስ እንደማትቀርብ አውቃለሁ፡፡ ---- በተለይ የኢትዮጵያ አንባቢዎች ሳይሰለቹ በማስተዋል እንዲመለከቱልኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡» (በደንብ ልብ ይሏል የታላቁን ደራሲ ትህትናና አክብሮት፡፡) ወደተነሣሳሁበት ጉዳይ ልመለስ፡፡
ለአውደጥናቱ በእንግድነት እንድንሳተፍ ጥሪ የተደረገልን ሰዎች የካቲት 21 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም. በጠዋት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ግቢ ተገናኝተን በተዘጋጀልን አውቶቡስ ወደ ጉጃም ደብረ ማርቆስ ተጓዝን፡፡ በተለመደው የጉዞ መስመር ጐሐጽዮንን በማቋረጥ ቁልቁል ወደታላቁ የዓባይ ወንዝ ሸለቆ ተቃረብን፡፡ በዚህ ጊዜ ከተጓዦቹ መካከል አቶ አፈወርቅ ዮሐንስ ብድግ ብለው «የታላቁ ሰው የክቡር ሐዲስን መጽሐፍ ፍቅር እስከመቃበርን እናስታውስ! ሰብለወንጌልንና በዛብህን ጭምር!» አሉና ዋሽንታቸውን አንቆረቆሩት፡፡ አርቲስት ወጋየሁ ንጋቱ መጽሐፉን በሬዲዮ ሲተርክ፣ በዋሽንት እጀባ ኃያል መንፈስ ያጐናጸፈው ተወዳዳሪ የማይገኝለት ባለዋሽንቱ አፈወርቅ ዮሐንስ ነበር፡፡ የፍቅር እስከመቃብሩን ንባብ አጃቢ ዋሽንት ተጓዡ እያዳመጠ፣ በሐሳብ እርቆና ተመንጥቆ ነጐደ፡፡ ጥቂቱ እንባውን መቆጣጠር አቃተው፡፡  በ2000 ዓ.ም. መጨረሻ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኀበር «ሕያው የጥበብ ጉዞ ወደ ፍቅር እስከመቃብር ሀገር» በሚል መርሐ ግብር በርከት ያሉ ደራስያንንና የመገናኛ ብዙኃን ሰዎችን እንዲሁም የሥነ-ጽሑፍ ተመራማሪዎችንና መምህራንን በማሳተፍ መጽሐፉ የተተረከባቸውን ቦታዎች አስጐብኝቶ ነበር፡፡ ይኸው የጉብኝቱ ተጓዥ በጐሐጽዮን በመገኘት ሰብለ፣ በዛብህና ጉዱ ካሣ የተቀበሩበትን ቤተክርስቲያን ተመልክቷል፡፡ በዚያን ጊዜ ቀብራቸውን ለማመልከት አብዛኛው ተጓዥ ጥረት በሚያደርግበት ወቅት የሁሉም እንባ ገንፍሎ መንቆርቆሩን ከአፈወርቅ የዋሽንት ጣዕመ ዜማ ጋር በማጣመር እያሰብሁ እኔንም ሳግ ተናነቀኝ፡፡
በዋሽንቱ ዜማ ታጅበን የዓባይ በረሃ ምንም ሳይታወቀን ደጀን አፋፍ ብቅ አልን፡፡ ደብረማርቆስ እንደደረስን ማረፊያዎቻችንን ከያዝን በኋላ፣ በየግላችን ስናወጋ አምሽተን በጊዜ የመኝታ ዕረፍት አደረግን፡፡ በማግስቱ ለአውደ ጥናቱ በተዘጋጀው መርሐ ግብር መሠረት ወደ ደብረ ማርቆስ ቤተመንግሥት ትልቁ አዳራሽ አቀናን፡፡ አዳራሹ በበርካታ ሰዎች ተሞልቷል፡፡ ከኬንያ፣ ከጀርመንና ከኢጣሊያ የታደሙ ተሳታፊዎችም ተገኝተዋል፡፡ የዚህ ታላቅ አውደ ርዕይ መሪ ቃል «Preservation of Ethiopian cultural and Literary Heritages፡ Focusing on Manuscripts and Indigenous knowledge፡ በሀገር በቀል ዕውቀትና ጥንታውያን ጽሑፎች ላይ ያተኮረ፣ የኢትዮጵያውያን የባህልና የድርሰት ቅርሶች ጥበቃ» የሚል ነው፡፡ ለአውደጥናቱ የተለያዩ ጥናታዊ ወረቀቶች ለማቅረብ ከውጭ ሀገራት የመጡ ነጭና ጥቁር እንግዶችም በመኖራቸው አውደ ጥናቱን ዓለም አቀፍ ገጽታ አላብሶታል፡፡  በቅድሚያ ዶ/ር ስማቸው ጋሻዬ፤ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማኀበረሰብ አገልግሎት ም/ኘሬዚዳንት፤ ስለ ሐዲስ ዓለማየሁ የባሕል ጥናት ተቋም አጭር ገለጻ በማድረግ የዕለቱ ኘሮግራም ተዋወቀ፡፡ በመቀጠልም የዩኒቨርሲቲው ኘሬዚዳንት ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ «የጐጃም ምድር ጥበብ የምታፈልቅ፣ የሚቀዳባትና ለሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የምታጠጣ…» የመሆኗን አንድምታ የሚያስረግጥ ምጥንና እጥር ያለ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡
ይህ በእርግጠኝነት የተዋጣ ተግባር ያከናወነው ዐውደ ጥናት፣ በመጀመሪያው ቀን ውሎው ሙዚቃን፣ ዋሽንትንና ቀረርቶ-ፉከራን ጨምሮ ከአሥራ አምስት በላይ ርዕሰ ጉዳዮችን አከናውኗል፡፡ እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች በቀረቡበት መድረክ የታደመው ተሳታፊ፤ ለምሳው ካልሆነ በቀር ከመቀመጫው ንቀንቅ አለማለቱ ለአውደ ጥናቱ ማራኪነትና በሳልነት አይነተኛ ማስረጃ ይሆነኛል፡፡ በእርግጥም በአውደ ጥናቱ ላይ የቀረቡት ርዕሰ ጉዳዮች የመዝናኛውም አቀራረብ ጭምር በእጅጉ ይበል የሚያሰኙ ስለነበሩ፣ ለአንዳንዶቻችን የተቀመጥንበት የእንጨት ወንበር ደልቶን እንደነበር በእውነት መናገር ይቻላል። በዕለቱ ከቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎችና የመዝናኛ ዝግጀቶች ውስጥ አውደ ጥናቱ በመንፈስና በሥጋ ውሕደት ትዝታን ለዘለቄታው የሚያጐናጽፍ እንደነበር ተገንዝቤአለሁ፡፡ ስለ አለቃ ተክለየሱስ ዋቅጅራ የሥነ-ግጥም ሥራዎች በዶ/ር ጌቴ ገላዬ፣ ስለግዕዝ ማኑስክሪኘት (በተለይም አቶምን አስመልክቶ በጥንታዊ የግዕዝ ጹሑፋችን ተካቶ ስለመገኘቱ) በዶ/ር ኃይሉ ሐብቱ፣ በገድለ ሰማዕታት ጽሑፎች ዙሪያ በኢጣሊያዊቷ በዶ/ር አንቶኒ፣ የፍቅር እስከመቃብሩ በዛብህ ለሰብለወንጌል በግጥም የጻፈው ደብዳቤ እንደመነባንብ በአቶ አበረ አደሙ፣ የሰላም አካዳሚ ሕጻናት ተማሪዎች ስለሐዲስ ዓለማየሁ ያቀረቡት መዝሙር፣ ሙዚቃ በሐዋርያ ባንድና ዋሻነት በአፈወርቅ ዮሐንስ የቀረቡት ዝግጅቶች ሊጠቀሱ  የሚገባቸው ናቸው።  በእማሆይ ኅርይት ደባስ እና በርዕሰ ማእምራን ዮሐንስ ታምሩ የቀረቡት የቅኔ ዘረፋ ተግባራት ድንቅ የሚባሉ ርዕሰ ጉዳዮች እንደነበሩ አይጠረጠርም፡፡ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኀበር ኘሬዚዳንት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ፤ የአንድ ጥናታዊ ጽሑፍ አወያይ ወይም አስተናባሪ በመሆን ከመድረክ የሰጡት አስተያየትም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ እርሳቸው የአለቃ ተክለየሱስን /ነገሮ/ እና የሌሎችንም የወለጋ ተወላጆች ሥራ በግዕዝ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ጐልቶ ስለታያቸው «እኔም ይህንኑ መስመር የማስቀጥል ወለጌ ነኝ፡፡» የሚለውና ቁም ነገር አዘል ንግግራቸው መንደርተኝነት ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት የተለየ ዋጋ ሊሰጠው እንደሚገባ የሚያሳይ ነበር፡፡
በዚሁ ዓይነት ሂደት በሁለተኛው ቀን የዓውደ ጥናቱ ውሎ ከአሥር በላይ ርዕሰ ጉዳዮችን አስተናግዷል፡፡ በዕለቱ እጅግ ሠፊና የተለየ ትኩረት ሊቸራቸው የሚገቡ ጥናታዊ ወረቀቶች ቀርበዋል። በዚህም ረገድ ከኬኒያ በተጋበዙ የዩኒቨርሲቲ መምህር (ዶ/ር ፒተር ዋሳምባ) ስለ የቃል ሥነ-ጽሑፍ፣ ስኬት፣ ተግዳሮትና የወደፊት ሂደት ማራኪ ዝግጅት ቀርቧል፡፡ በዚያውም በኬኒያ ወደ ስምንት የሚደርሱና በድርሰት ዙሪያ የሚሠሩ ማኀበራት መኖራቸው መጠቆሙን ልብ ይሏል። የቅኔ ቤት አስተምህሮ በሙያው ተሰማርተው ባሉ ሊቃውንትና ተማሪዎቻቸው፣ ስለሐገረሰብ መድኃኒቶች አትክልትና አዝርዕት፣ ስለአቤ ጉበኛና የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቹ በአቶ አበረ አዳሙ እንዲሁም በተቋሙ አጠቃላይ እንቅሰቃሴና የትኩረት አቅጣጫ የቀረቡት ጽሑፎችና ውይይቶች ከተጠበቀው በላይ ውጤታማ እንደነበሩ መመስከር ይቻላል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ጥናቶች በአማርኛ ቋንቋ ቢቀርቡ የበለጠ ሊደመጡና ሊሠርፁ ሲችሉ፣ በእንግሊዝኛ በመቅረባቸውና አቀራረቡም ለዛ የሌለውና የሚስብ ስላልነበር፣ ድክመት እንደታየባቸው መደበቅ አይቻልም፡፡ ለወደፊቱም ተመሳሳይ ስህተት እንዳይደገም ተሳታፊዎች አስረግጠው ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
ታዳጊው የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣ በታላቁ ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ ስም የባሕል ጥናት ማዕከል በማቋቋም ተቋሙ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ተግባር ያከናውን ዘንድ በሁለት ጊዜያት የአውደ ጥናት ዝግጅቱ ስኬታማ እንደነበር ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
የጐጃም ምድር በተለይም ምሥራቁ  የግዕዝን ቋንቋና ሥነጽሑፍ ጠንክሮ በማስተማር አያሌ ሊቃውንት በመላው አገራችን ተሰማርተው በያሉበት ቦታ ተግባራቸውን እንዲወጡ ለዘመናት እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ፤ በዚህች አጭር ጽሑፍ ሊገለጥ የማይቻል መሆኑ ይገባኛል፡፡ ይሁንና ጉዳዩ ፈጽሞ ሊድበሰበስ የማይችልና ከፍ ተደርጐ ሊወሳ የሚገባው ሲሆን፣ ዘመናዊውን ትምህርት ከነባሩ  የግዕዝ ቋንቋና ሥነ -ጽሑፋችን ጋር በማዛመድ እንደወትሮው ሁሉ በርካታ ሊቃውንትን በማፍራት፣ ለሌሎችም የሀገራችን የትምህርት ተቋማት ግብአት ለመሆን የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ቀዳሚ ኃላፊነት እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡ ይህ ኃላፊነትና ክብር ደግሞ በእኔ አስተያየት የግእዝን ቋንቋና ሥነ ጽሑፋችንን አቅፎና ተንከባክቦ እዚህ ላደረሰ ሕዝብና ምድር በእጅጉ ይገባዋል፡፡  ስለሆነም መላው ባለድርሻ አካላት ለግዕዝ ቋንቋችንና ሥነ ጽሑፋችን ሕዳሴና ትንሳኤ እጅግ መተጋገዝና በርትቶ መሥራት እንዳለባቸው አስባለሁ፡፡
የግዕዝ ቋንቋችንና ሥነ -ጽሑፋችን የጥናት፣ የምርምር፣ የሳይንሰና የቴክኖሎጂ ምንጭነታቸው የማያጠራጥር ሆኗል፡፡ ምናልባትም ይህን ቋንቋና መላ ድርሰቶችን እንዳናውቅ መገደባችን ነባር ከሆነው የሥልጣኔና የታሪክ ቁንጮነታችን አዘቅዝቀን፣ ተዋራጅና ተመጥዋች ምስኪኖች እንድንሆን ከጥንት ጀምሮ ያሉ ተቀናቃኞቻችን ያሴሩት ይሆን? ማን ያውቃል በርትቶ ከተሠራ ይህም በጥናት ይደረስበታል፡፡
በደብረ ማርቆሱ ዐውደ ጥናት የዩኒቨርሲቲው እውነተኛ ጥረት በዝግጅት፣ ተሳታፊዎችን በማስተናበር፣ ዝግጅቱን በመምራትና ለፍሬ በማብቃት፣ በመስተንግዶና በእንክብካቤ የተሳካ እንደነበር በማስመር፣ የወደፊት ሥራውም የበለጠ እንደሚሆን እምነቴን መግለጽ እወዳለሁ፡፡

Read 2776 times