Saturday, 15 March 2014 12:41

የ92 ዓመቱ አንጋፋ ማተሚያ ቤት ምሬት በዝቶበታል

Written by  ከጋዜጣው ሪፖርተሮች
Rate this item
(7 votes)

የግል ጋዜጦች፤ ብርሃንና ሰላም  ለኪሳራ እየዳረገን ነው ብለዋል     
ጋዜጣውን “እንዝጋው አንዝጋው” በሚለው ላይ እየተነጋገርን ነው - ኢትዮ ቻናል
ጋዜጣችን ሁለትና ሦስት ቀን ዘግይቶ ስለሚወጣ ዜና መስራት ትተናል - ካፒታል
  ብርሃንና ሰላም የደንበኞች ቅሬታ ለመፍታት እየሰራሁ ነው ብሏል
ብርሃንና ሰላም ከደንበኞች ጋር “ተጠያቂ የሚያደርገኝን” ውል እፈራረማለሁ አለ
የጋዜጦች ሕትመት መዘግየት  እስከ ነሐሴ ድረስ  ሊዘልቅ ይችላል ተባለ

      ከሀረማያ ዩኒቨርስቲ በግብርና ትምህርት ተመርቀው የግብርና ባለሙያ የሆኑት አቶ ፍቃዱ ታመነ፤ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ቋሚ ደንበኛ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ቅዳሜ ጠዋት ጋዜጣውን  ለመግዛት ወደ ፒያሳ በተደጋጋሚ ቢመላለሱም “አርፍዷል፤ አልወጣም” የሚል ምላሽ እያገኙ ባዶ እጃቸውን ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ እሁድ እሁድ ደግሞ ከቤታቸው መውጣት አይወዱም፡፡  በዚህ ምክንያት ጋዜጣውን ካነበብኩ ሰነባበትኩ ይላሉ፡፡ “አዟሪዎችን ስጠይቅ እሁድ ይወጣል ቢሉኝም እኔ ግን ቅዳሜ በትኩሱ ማግኘት ያለብኝን አዲስ አድማስ እሁድ ለመግዛት ሞራል የለኝም፤ ምክንያቱም ያደረ ምግብ ይመስለኛል” በማለት ጋዜጣው ለምን ቀኑን ጠብቆ እንደማይወጣ ይጠይቃሉ፡፡
በአንድ የመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆነውና ስሙ እንዲገለፅ ያልፈለገው  ወጣት፤ አዲስ አድማስ፣ ሪፖርተር፣ ፎርቹን፣ ካፒታል፣ ሰንደቅ… ጋዜጦችንና ሌሎች መፅሔቶችን በደንበኝነት ወደ ቢሮው እንደሚያስመጣ ጠቁሞ፣ ከጥቂት ወራት ወዲህ ግን ጋዜጦች ቀናቸውን ጠብቀው ስለማይወጡና መ/ቤቱ በፈለገው ጊዜ ስለማያገኛቸው፣ ውሉን ለማቋረጥ ማሰቡን ይገልፃል፡፡ የተለያዩ ጨረታዎችን፣መስሪያ ቤቱን የተመለከቱ ዜናዎችንና አጠቃላይ መረጃዎችን በትኩሱ ማግኘት እንደሚፈልግ የተናገረው የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው፤የሚዲያ ድርጅቶች የደንበኝነት ውል የገባንባቸውን ጋዜጦች ለምን በወቅቱ እንደማያቀርቡ ሲጠየቁ “ማተሚያ ቤት ማሽን ተበላሽቶ ነው” የሚል ተመሳሳይ ምላሽ እንደሚሰጡ ጠቁሞ “በዚህ አይነት እስከመቼ ይዘለቃል፤አሳታሚዎች በጉዳዩ ላይ ተመካክረው አንድ ነገር ላይ መድረስ አለባቸው” ሲል ምክሩን ለግሷል፡፡
የጋዜጣ ማርፈድ ችግር የቆየ ቢሆንም ከጥቂት ወራት ወዲህ ግን ተባብሷል ይላል - የካፒታል ጋዜጣ አዘጋጅ ግሩም፡፡ ማርፈዱ ደግሞ ጦሱ ብዙ ነው፡፡ “በአሁኑ ጊዜ በፊት ከምናሳትመው በአስር ፐርሰንት ቀንሷል፤ ስምንት ሺ አዝዘን ከአምስት መቶ እስከ ስምንት መቶ እንቀንሳለን” ያለው አዘጋጁ፤ ኮፒ ብቻ ሳይሆን ገፆችም እንደሚቀንሱ፣ ወደ ክፍለሃገር የሚላኩትም እንደሚቀሩ ገልጿል፡፡ “ከቀናችን ሁለት ቀን ዘግይተን ስለምንወጣም ዜና መስራት ሁሉ ትተናል” ይላል ግሩም፡፡
ለጋዜጣው ማርፈድና ማደር ምክንያቱ የብርሃንና ሰላም ማሽኖች ማርጀት ነው የሚለው የካፒታል አዘጋጅ፤ ይህም የጋዜጣውን ሽያጭ በማስተጓጎል ለከፍተኛ ኪሳራ ዳርጎታል ብሏል፡፡ “አሁን አሁን በቀናችሁ ትወጣላችሁ ወይ ስንባል፣ መልሳችን ‘የብርሃንና ሰላም ማሽን ካልተበላሸ---’ የሚል ሆኗል” ይላል አዘጋጁ፡፡
የሪፖርተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ መላኩ ደምሴ በበኩሉ፤ የማተሚያ ቤት ችግር ከአቅም በላይ እንደሆነ ጠቁሞ፣አሁን ካለው ችግር ይልቅ የወደፊቱ እንደሚያሳስበው ይናገራል፡፡ “ሪፖርተር ጋዜጣ በሳምንት ሶስት ጊዜ ነው የሚታተመው፤ላለፉት 20 ዓመታትም የብርሃንና ሰላም ደንበኞች ሆነን ቆይተናል” ያለው ጋዜጠኛ መላኩ፤ “ሪፖርተር በዓመት እስከ 30 ሚሊዮን ብር ለማተሚያ ቤቱ  ቢያስገባም እንዲህ አይነት መጉላላትና ችግር ሲደርስብን ከአመራሩ ጀምሮ እስከ ሰራተኛው ድረስ ሊያማክሩንና የት ወደቃችሁ ሊሉን ይገባ ነበር እነሱ ግን ምንም አይነት የጥፋተኝነት ስሜት እንኳን አይሰማቸውም” ብሏል፡፡
 ሰሞኑን ብሄራዊ ፈተና እየታተመ መሆኑ እንደ ሰበብ ቢቀርብም ችግሩ ግን ከዚያም በፊት ነበረ ይላል - ጋዜጠኛ መላኩ፡፡ ብርሃንና ሰላም በተደጋጋሚ ማሽን ተሰበረ፣ ቀለም የለም፣ ኬሚካል አልቋል---በሚሉ ሰበቦች መከራ እንዳበላቸው አስታውሶ፤ አሁን እየታተመ ባለው ብሄራዊ ፈተና ሰበብ ደግሞ ለብዙ  ችግርና ኪሳራ እንደተዳረጉ ገልጿል፡፡ ጋዜጣ ባደረና በሰነበተ ቁጥር ስርጭቱ ላይ ከፍተኛ ችግር ከመፍጠርም ባሻገር፣ ባለማስታወቂያዎች በቀነ ገደብ የሚያስነግሯቸው ማስታወቂያዎች ቀናቸውን መሳትና ሌሎች  ከሞራል ጋር የተያያዙ ቀውሶች እንደሚያስከትል ዋና አዘጋጁ ተናግሯል፡፡ “እሁድ በሚወጣ ጋዜጣ ለሰኞ የስብሰባ ጥሪ ማስታወቂያ ያወጣ ድርጅት፤ጋዜጣው ማክሰኞ ሲወጣ ለምን ክፍያ ይፈፅማል?” ሲል የሚጠይቀው መላኩ፤“በተመሣሣይ መልኩ በርካታ ድርጅቶች ክፍያ ላይፈፅሙ ይችላሉ፤እናም ኪሳራው ብዙ ይሆናል” በማለት አስረድቷል፡፡
የጋዜጦች መዘግየት ጋዜጣ አዟሪዎችንም ክፉኛ እየጎዳቸው ነው፡፡ ላለፉት 12 ዓመታት በጋዜጣ አዟሪነት የሰራው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ጎልማሳ፤ “አሁን እንደ በፊቱ ብዙ ጋዜጦች የሉም፤ ያሉትም በቀናቸው ስለማይወጡ ገበያችን እየቀዘቀዘ ነው” ብሏል፡፡ በዚህም የተነሳ አዟሪዎች ፊታቸውን ወደ መፅሄቶች እንዳዞሩ ይናገራል፡፡ “አንዳንድ ጋዜጦች በተመላሽ አይሰጡም፤ እኛ በተመላሽ ካላስረከብን ደግሞ  ለኪሳራ እንዳረጋለን” ያለው ጋዜጣ ሻጭ፤ “ከዚህ ሁሉ ቀናቸውን አሳልፈው ሲወጡ ቁጥሩን ቀንሰን እንረከባለን፤ይሄ በገበያችን ላይ ጉዳት ቢኖረውም ብዙ ጋዜጣ ወስደን ከምንከስር መቀነሱ ይሻላል” ይላል፡፡ የጋዜጦች በቀናቸው አለመውጣት በአሳታሚዎችም ሆነ በአዟሪዎች ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ እንደሆነ የጠቆመው ጋዜጣ አዟሪው፤በአሁኑ ሰዓት በፊት ከሚረከበው የጋዜጣ መጠን በግማሽና ከዚያም በላይ ቀንሶ እየተረከበ መሆኑን ገልጿል፡፡
በዜድ ፕሬስ ስር የሚታተመው ሳምንታዊው ኢትዮ ቻናል ጋዜጣ በቀኑ መውጣት ባለመቻሉ ለከፍተኛ ኪሳራ እየተዳረገ መሆኑን ሳምሶን አድቨርታይዚንግ ባለቤት ሳምሶን ማሞ ተናግሯል፡፡ “በጋዜጣው ላይ ማስታወቂያ የሚያወጡት ድርጅቶች በቀኑ ካልወጣ ክፍያ አይፈፅሙም፤ ስለዚህ ኪሳራው የድርጅታችን ነው” ያለው ሳምሶን ማሞ፤ “የጋዜጣው ህልውና አደጋ ላይ በመሆኑ እንዝጋው አንዝጋው በሚለው ላይ እየተወያየን ነው” ብሏል፡፡
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተካ አባዲ ለጋዜጦች መዘግየት ሁለት ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ፡፡ አንደኛ፤ጋዜጦቹን የሚያትሙት ማሽኖች የቆዩ ስለሆነ አቅማቸው እየወረደ ነው፤ አቅማቸውን ለመገንባት መለዋወጫ ለመግዛት ቢጠይቁም መሳሪያዎቹን ያመረተው ፋብሪካ ስራ በማቆሙ መለዋወጫዎቹን ማግኘት አልቻልንም ብለዋል። ሁለተኛው ምክንያት የብሔራዊ ፈተና ሕትመት መጀመር እንደሆነ አቶ ተካ ተናግረዋል፡፡ ማተሚያ ቤቱ በደንበኞች ቅሬታ ላይ ሥር-ነቀል ለውጥ ለማምጣት ከአንድ ዓመት በፊት “ክሪስ ግሩፕ” በተባለ ኩባንያ አንድ ጥናት ማስጠናቱን ጠቅሰው፤ አሁን መንግሥት በፈቀደላቸው 558 ሚሊዮን ብር ጥናቱን ተግባራዊ ማድረግ እንደ ጀመሩ ገልፀዋል፡፡ ከጃፓን የገዟቸው ሁለት ኦፍሴት ማሽኖች እስከ ግንቦት ድረስ ይገባሉ፡፡ አንዱ ለጋዜጣ ሕትመት፣ ሌላኛው ለመጻሕፍት ህትመት ብቻ ዲዛይን የተደረጉ ናቸው፡፡ በአንድ ጊዜ አራት ቀለም የሚያትመው መሳሪያም ገብቶ እየተተከለ ነው፡፡ ሌሎች በጥናቱ የተካተቱ የመፍትሔ ሀሳቦች ትግበራም በሂደት ላይ ነው ብለዋል አቶ አባይ፡፡
 የአታሚዎች ማህበር ፕሬዚዳንት እንደሆኑ የገለፁት ሥራ አስኪያጁ፤አሁን መንግሥት በፈቀደው በጀት ማተሚያ ድርጅቱን በማጠናከር ያሉትን ጥቂት ጋዜጦች በጥራትና በብቃት ለማተም መዘጋጀታቸውንና ተጨማሪ 20 እና 30 ጋዜጦች ወደ ብርሃንና ሰላም መጥተው እንዲታተሙ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ አሁንም በተፈቀደው በጀት የማተሚያ ማሽኖች ተገዝተው እየገቡ በመሆናቸው መጪው ጊዜ ለህትመቱ ኢንዱስትሪ ብሩህ እንደሚሆን ይናገራሉ፡፡
 የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሠራተኞች ማህበር ተወካይ በበኩላቸው፤ የጋዜጦች መዘግየት እውነት መሆኑን አምነው፤ አሳታሚዎች ዘንድም ችግር እንዳለ ይናገራሉ፡፡ “ማተሚያ መሳሪያው አርጅቶ ጥርሱ በመበላሸቱ መዘግየት ይፈጥራል፤ ሌላው ምክንያት ደግሞ አሳታሚዎች ጋ ያለ ችግር ነው፤ በፍላሽ ወይም በወረቀት የሚያመጡት ጽሑፍ፣ የጥራት ወይም ሌላ ችግር ኖሮት አስተካክላችሁ አምጡ ስንላቸው በጊዜ አያቀርቡም፣ በዚህም ይዘገያል፡፡ ጋዜጦች ተደራርበው መምጣታቸውም እንዲሁ ለመዘግየት ምክንያት ነው ይሆናል” ብለዋል፡፡
አቶ ተካ እንደሚሉት ለወደፊት ያሰቡት ትልቁና ዋንኛው እቅድ ከደንበኞች ጋር የሚገቡት የተጠያቂነት ቻርተር ነው፡፡ “ለምሳሌ አዲስ አድማስ ወይም ሌላ አሳታሚ ድርጅት፣ ጋዜጣው የታተመበትን ዋጋ ባይከፍል ድርጅቱን ከስሰን የሰራንበትን ዋጋ እናስከፍላለን፡፡ እኛ ህትመት ብናዘገይ፣ ጋዜጣውን ወይም መጽሔቱን ከሁለትና ከሶስት ቀን በኋላ ብናትም፣ ጥራት ብናጓድል፣ እስካሁን በነበረው አሰራር በተለያዩ ምክንያቶች አንጠየቅም፣ አንከሰስም፡፡ በቢዝነስ ዓለም አንዱ የሚጠየቅበትና ሌላ የማይጠየቅበት አሰራር ትክክል አይደለም፡፡ ለምሳሌ እናንተ ጋዜጣ ላይ የወጣ ሰው ፎቶግራፍ ቢበላሽ፣ ግለሰቡ እናንተን ይጠይቃል፣ እናንተ ደግሞ በሶስተኛ ወገን ተጠያቂነት እኛን መጠየቅ አለባችሁ፡፡ ሁሉም ወገን ባጠፋው ነገር ወይም በሰራው ስህተት መጠየቅ አለበት፡፡ ቃል የምንገባበት የተጠያቂነት ውል (ቻርተር) አዘጋጅተናል፡፡ ይህ የአመራሩ ውሳኔ ብቻ አይደለም፡፡ የሰራተኛ ማህበሩን “ቃላችንን ባናከብር፣ ህትመት ብናገዘይ፣ ጥራት ብናጓድል፣… ደንበኞቻችን እንዲጠይቁን የሚያደርግ ውል ልንገባ ነው” ብለን ነገርናቸው፡፡ እነሱ ደግሞ ለሰራተኛው ነገሩ፡፡ የህልውና ጉዳይ ስለሆነ በአንድ ድምፅ ነው የተቀበሉት” በማለት ገልጸዋል፡፡
 ከዚህ ቀደም ብርሃንና ሰላም ከአሳታሚዎች ጋር ውል እንፈራረም ሲል መጠየቁን ያስታወሱ አንድ የቀድሞ ጋዜጣ አሳታሚ፤ “ውሉ ጋዜጦች የሚያስጠይቁ ፅሁፎች ይዘው ሲያመጡ፣ብርሃንና ሰላም አላትምም የማለት መብት አለው” የሚል ይዘት እንደነበረውና አሳታሚዎች ሳይቀበሉት እንደቀሩ ተናግረዋል። “በፕሬስ ህግ መሰረት የሚያስጠይቅ ፅሁፍ ቢፃፍ የመጀመሪያ ተጠያቂ ዋና አዘጋጁ፣ ዋና አዘጋጁ ከጠፋ ኩባንያውና አሳታሚው፤ እነዚህ አካላት ከጠፉ ደግሞ አታሚ ድርጅቱ ተጠያቂ ይሆናል” ያሉት አሳታሚው፤ እነዚህን ሁሉ ዘሎ ለሚመጣ ተጠያቂነት ነው ብርሃንና ሰላም አላትምም ያለው ብለዋል፡፡ “ብርሃንና ሰላም አላትምም ሲል የትም መሄጃ አማራጭ አልነበረንም፤ ያም ሆኖ ውሉን አልፈረምንም፣ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ነው ጋዜጦች ማተሚያ ቤት እያረፈዱና እያደሩ መውጣት የጀመሩት” ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡
አቶ ተካ ግን ዋናው ችግር የአቅም ማነስ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ “ጋዜጦች አንዳንዴ አርፍደው ይወጣሉ፣ አንድና ሁለት ቀን የሚዘገዩበትም ጊዜ አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ደንበኞቻችን ’አዲስ ዘመን የመንግሥት ስለሆነ አስቀደማችሁት፣እኛ የግል ስለሆንን አሳደራችሁ፣…’ ይሉናል፡፡ እውነቱን ለመናገር ይኼ የወገንተኝነት ጉዳይ አይደለም፤ የአቅም ማነስ፣ የማተሚያ መሳሪያዎች እርጅና ነው፡፡ ይህ ችግር በቅርቡ ስለሚፈታና ስለሚስተካከል የደንበኞቻችን እሮሮና ቅሬታ ይወገዳል።” ብለዋል፡፡
ሰባት ዓመት በህትመት ላይ የቆየ ጋዜጣቸው በማተሚያ ቤቱ ችግር እንደቆመባቸው የሚናገሩት የቀድሞ አሳታሚ ግን በአቶ ተካ አባባል አይስማሙም፡፡ “ማተሚያ ቤት ገብተን የእኛ ጋዜጣ ህትመት ተጀምሮ ቢሆን እንኳን አዲስ ዘመን ከመጣ የእኛ ተቋርጦ እሱ ይታተማል” በማለት ያፈጠጠ ወገንተኝነት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
ማተሚያ ቤቱ በቅርቡ በብዙ ሚሊዮን ብሮች ዘመናዊ ማሽን ከስዊድን ማስመጣቱን የገለፀው የሪፖርተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ መላኩ ደምሴ፤ለማሽኑ ተስማሚ እውቀትና ስልጠና የወሰዱ ሰራተኞች ስለሌሉ ማሽኑ በአግባቡ መስራት እንዳልቻለ ተናግሯል፡፡ “ድርጅቱ ይህን የሚያህል ዘመናዊ ማሽን ሲያስመጣ ማሽኑን በአግባቡ የሚያንቀሳቅሱ ሰራተኞች ሰልጥነው እንዲመጡ አለማድረጉ ለዘርፉ ትኩረት አለመስጠቱን ያመለክታል” ሲል ወቅሷል፡፡ ከስዊዲን የመጣው ማሽን ትክክለኛ ባለሙያ ቢመደብለት አሁን ያለውን የአሳታሚዎች ችግር መፍታት እንደሚችልም ጨምሮ ገልጿል፡፡
 የማንኛውም መ/ቤት የመጨረሻ ግብ፣ የተማረና የሰለጠነ የሰው ኃይል ሀብት ነው - ይላሉ አቶ ተካ፡፡ “የዘመናዊ መሳሪያ ባለቤት መሆን በራሱ የመጨረሻ ግብ አይደለም፡፡ የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት የህትመት ኢንዱስትሪ አካዳሚ ለመክፈት ባለ 7 ምድር ቤትና 6 ፎቅ ህንፃ ለመገንባት ተወስኖና በጀት ተመድቦ፣ ህንፃው የሚሰራበትን ቦታ ማስተካከል ተጀምሯል፡፡ አዳዲስ ለተገዙት ዘመናዊ መሳሪያዎች፣ ሠራተኞች ውጭ አገር ልከን በአጫጭር ኮርሶች እናሰለጥናለን፡፡” ብለዋል፡፡
 “አሁን ያለው የማተሚያ ቤት ችግር ተስፋ አስቆራጭ ነው” የሚለው የኢትዮ ቻናል ባለቤት ጋዜጠኛ  ሳምሶን፤ ብርሃንና ሰላምም ሆነ መንግስት ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ ካላመጡ በህትመት የምንቆይበት ተስፋ የለም ብሏል፡፡  
የካፒታል ጋዜጣ አዘጋጅ ግሩም እንደሚለው፤ “ጋዜጣችን ሙሉ በሙሉ በማተሚያ ቤቱ ችግር ዘግይቶ እየወጣ ለኪሳራ ስንዳረግ ዝም መባል የለበትም፤ ማተሚያ ቤቱ ሲሆን 100 ፐርሰንት ካልሆነ 50 ፐርሰንት ኪሳራችንን ሊጋራን ይገባል”
ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት መጋቢት 9 ቀን 2006 ዓ.ም ከጋዜጣ አሳታሚ ድርጅቶች ጋር ለመወያየትና የተጠያቂነት ውል ለመፈረም ጥሪ አድርጓል፡፡

Read 4822 times