Saturday, 15 March 2014 12:28

የቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የአገልግሎት ጥራቱ እየወረደ ነው ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(6 votes)

 ከቻይና በተገኘ የ4.3 ቢ. ብር ብድር የማስፋፊያ ሥራ ይከናወናል  

የአዲስ አበባው ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት፤መንገደኞችን የማስተናገድ አቅሙ እየተጣበበ በመምጣቱ በአሁኑ ወቅት ያለውን የትራፊክ ፍሰት በአግባቡ ማስተናገድ ወደማይችልበት ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑ ተገለፀ፡፡ በህንፃው ውስጥ ያለው ከፍተኛ የመጣበብ ችግር፤ በአየር መንገዱ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጫና በመፍጠር የአገልግሎት ጥራቱን እያወረደው ነው ተብሏል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰሞኑን ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ላይ በቀረበ የብድር መግለጫ ሪፖርት ላይ እንደተገለጸው፤ አየር መንገዱ ያለበት የመጨናነቅ ችግር አስቸኳይ መፍትሔ ካላገኘ የአየር መንገዱ ደረጃ ዝቅ ብሎ ተወዳዳሪነቱን እንዳያጣ ያሰጋል፡፡ አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላቸው የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት መመዘኛዎች አንፃር ሲታይ ጥራቱ ዝቅተኛ የሆነ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ከጊዜ ወደ ጊዜ የአገልግሎት ጥራቱ እየቀነሰ እንደመጣም  ተገልጿል፡፡
ደረጃው ከዕለት ወደ ዕለት እየወረደ የመጣውን የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እና በቀጣይነት ተመራጭ ኤርፖርት ለማድረግ ፕሮጀክት መነደፉን የገለፀው ሪፖርቱ፤ ከቻይና ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ 225 ሚሊዮን ዶላር (ከ4.3 ቢሊዮን ብር በላይ) ብድር መገኘቱን አመልክቷል፡፡ ብድሩ በዓመት የ2% ወለድ የሚከፈልበት ሲሆን  በሃያ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

Read 2843 times