Saturday, 15 March 2014 12:25

ኢትዮጵያዊው ዶ/ር በካናዳ የአየር ንብረት ትንበያ ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

          የ38 አመቱ ኢትዮጵያዊ ዶክተር ፍሰሃ ኡንዱቼ በካናዳ የመሰረተ ልማትና የትራንስፖርት ሚኒስቴር የማኒቶባ ግዛት የአየር ንብረትና የጎርፍ አደጋ ትንበያ ዳይሬክተር ሆነው መመረጣቸውን ዊኒፒንግ ፍሪ ፕሬስ ዘገበ፡፡
የካናዳ የመሰረተ ልማትና የትራንስፖርት ሚኒስትር ስቲቭ አሽተን ዶክተሩን ለመገናኛ ብዙሃን ለማስተዋወቅ በተዘጋጀ ስነስርዓት ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፣ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ በርካታ ባለሙያዎች የተሳተፉበትን ከፍተኛ ውድድር በማሸነፍ ለማኒቶባ ግዛትየአየር ንብረትና የጎርፍ አደጋ ዳይሬክተር ለመሆን የተመረጡት ዶክተር ፍሰሃ፣ ላለፉት 15 አመታት በሃይድሮሎጂና ከጎርፍ አደጋ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች በአሜሪካና በተለያዩ የአውሮፓ አገራት የካበተ የስራ ልምድ አላቸው፡፡
ላለፉት አምስት አመታት የግዛቷ የውሃ ቁጥጥር ስርዓቶች ዕቅድ ከፍተኛ መሃንዲስ ሆነው ያገለገሉት ዶክተር ፍሰሃ፣ ከዚያ ቀደምም ኤኢኮም በተባለ አለማቀፍ የምህንድስና አገልግሎቶች ኩባንያ ውስጥ የውሃ ሃብቶች መሃንዲስ ሆነው ማገልገላቸው ተነግሯል፡፡ ኒዘርላንድ ውስጥ ከሚገኘው ኢንተርናሽናል ሃይድሮሊክ ኢንጂነሪንግ ኢንስቲቲዩት በሲቪል ምህንድስና የሁለተኛ ዲግሪያቸውን የተቀበሉት ዶክትር ፍሰሃ፣ በኖርዌጂያን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳይንስ ኤንድ ቴክኖሎጂ ሌሎች የምርምር ጥናቶችን እንደሰሩ ተጠቁሟል፡፡
ከማኒቶባ ዩኒቨርሲቲ በውሃ ሃብቶች የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከተቀበሉ በኋላም፣ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ከጎርፍ አደጋ ትንበያና ከአደጋ ቁጥጥር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች በውሃ ሃብቶች መሃንዲስነትና በመምህርነት አገልግለዋል፡፡በወቅቱ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ዶክትር ፍሰሃ፣ በውሃው ዘርፍ የጀመሩትን ጥናት አጠናክረው ለመቀጠል የሚያስችሏቸውን የጎርፍ አደጋዎች የሚበዙባቸው አካባቢዎችና በጎርፍ አደጋ ትንበያ ላይ ልዩ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ዩኒቨርሲቲዎች ሲያጠኑ እንደቆዩና ማኒቶባ ግዛት ለዚህ ተመራጭ መሆኗን በማረጋገጥ ወደዚያው ለመሄድ መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ፍሰሃ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ናቸው፡፡




Read 2871 times