Saturday, 08 March 2014 13:28

ተራማጁ ደራሲ ለምን ተገለለ?

Written by 
Rate this item
(10 votes)

የፈጠራ ስራዎች ፀረ-ፊውዳል ድርሰቶች አይደሉም የሚል ምሁር ከመካከላችን ይኖራል? ታዲያ ፀረ-ፊውዳል ታጋዩና የመሬት ላራሹ መፈክር አንጋቢው ተራማጁ የተማሪዎች ማህበር ይህን ህዝባዊ ደራሲ ሳያጎላው ያለፈው ሆን ብሎ ይሆን ወይስ ረስቶት?

ይህን ጽሑፍ ያዘጋጀሁት ስለ አንጋፋው ደራሲ አቤ ጉበኛ አንዳንድ ሃሳቦችን ለመሰንዘር ነው። ጽሑፉ ከምርምርም በሉት ከጥናት ሥራ ጋር የሚመደብ አይደለም፡፡ ወፍ በረር ወይም ወፍ ዘለል ምልከታ አይባልም፡፡ በአጭሩ እኔ ስለአቤ የተሰማኝን የገለጽሁበት መላምታዊ ስሜት ነው፡፡
አቤን እኔ በሚገባ ወይም በቅርበት አላውቀውም፡፡ የአቸፈር ሰው መሆኑን፣ ዳንግላ መማሩን የተረዳሁት በቅርቡ ነው፡፡ የእኛ ዘመን ምሁራን “የየት አገር ሰው ነህ?” ተባብለው በይፋ አይጠያየቁም ነበር፡፡ በትምህርት ቤት ዘመኔ “ሰይፈ-ነበልባል” የተባለውን ድርሰቱን ያነበብሁ ይመስለኛል፡፡ በእኔ የጉርምስና ዘመን፣ በእኔ አካባቢ ስሙ እንደ ሌሎች ደራሲዎች ጎልቶ ሲነገር አልሰማሁም፡፡ ወይም የግንኙነት አድማሴ ጠባብ ነው ወይም በጆሮዬ ተኝቼበታለሁ፡፡ አሁን ይህን እያልሁ ያለሁት በዚያ በእኔ ዘመን ላይ ቆሜ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ አዎ! እንደ ከበደ ሚካኤል፣ እንደ መንግስቱ ለማ፣ እንደ ፀጋዬ ገ/መድህን፣ ሌላው ቢቀር እንደ መንግስቱ ገዳሙ እንኳ በስሙ አይዘመርለትም ነበር፡፡ የፈጠራ ስራው የወረደ ስለሆነ? ፈፅሞ አይመስለኝም፡፡ ሥራዎቹማ! እሳት ጫሪ፣ አነጋጋሪ፣ የአብዮት ማዕበል ጠሪ ነበሩ፡፡ ፀባዩ ከሰው ስለማይገጥም? ይህ በከፊል እውነት ሊሆን ይችላል፡፡ አቤ እከክልኝ-ልከክልህን የማያውቅ በራሱ የሚተማመን የቀለም ሰው ነበር፡፡ ይህን ሁሉ የሆነ ደራሲ ለምን ደመ መራራ ሆነ? መልሱን እኔም አልሰጣችሁም፤ እናንተም እንድትመልሱልኝ አልፈልግም፡፡
በእነዚያ ዘመናት በአቤ ስም ላይ የተጫኑትን ቋጥኞች ከሥር መሰረታቸው ፈልፍሎ ለማወቅ በእርግጥም ጥልቅ ጥናትና ምርምር ይጠይቃል፡፡ እኔ ግን መላምቴን ጎን-ለጎን ባስሔድ ጆሮውን የሚነፍገኝ እንደማይኖር ተስፋ አለኝ፡፡
1. አቤና የአጼው ዘመን
በዚያን ዘመን የነበሩ ደራሲያን፣ አብዛኛዎቹ በቀኝ እጃቸው ብዕር፣ በግራ እጃቸው ሥልጣን የጨበጡ ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት የዘመኑ ሹም የሰራው ብቻ ሳይሆን በሩቁ በማንኪያ የነካው ወጥ ሁሉ ይጣፍጥለታል፡፡ ለምን ቢሉ? ወጡ እንዳይጎረና ዙሪያ ከበው የሚያማስሉለት ብዙ ሌቄዎች ከጎኑ ስላሉ … የዚያ ሁሉ ወጥ አማሳይ እጅ ያረፈበት ወጥ ደግሞ በየትኛውም መመዘኛ ሲታይ ላይጣፍጥ አይችልም፡፡
አቤ በዚያን ዘመን የግሽ-አባይ ጎርፍ ከገጠር አምጥቶ ከቀለጠው ከተማ የዶለው ብቸኛ ፍጡር ይመስለኛል፡፡ በቀኝ እጁም የያዘው ብዕር ብቻ ነው፡፡ ብዕሩም በቅኔ ቤት እንጂ በገነተልዑል ግቢ ውስጥ ገብቶ ያልተሟሸ ነው፡፡ ቃላቱም ቱባ-አገራዊ ሽካራ እንጅ ቤተመንግሥታዊ ለስላሳ አይደለም፤ አስተሳሰቡም ደረቅ-ገጠራዊ እንጅ ከተማዊ-ጮሌ አይመስለኝም፡፡ ገፀ-ባህርያቱም አብዛኛዎቹ ከውጭ አገር የኮረጃቸው ሳይሆን ከአካባቢው በተጨባጭ የፈጠራቸው ናቸው። በፖለቲከኞች ቋንቋ ለመናገር፣ አቤ ለዘመኑ ቢሮክራሲ አጎብዳጅ አልነበረም። (አስር ጊዜ አይመስለኝም… ይመስለኛል… የምለው ያለምክንያት አይደለም፡፡ አንድም ከላይ እንደገለጽሁት ጽሑፉ ጥናታዊ አለመሆኑን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ሁለትም ለዚህ መረጃ የሚሆን ማጣቀሻ የፈረንጅ ስም ለመጥራት ስላልፈለግሁ ነው፡፡ ሶስትም አገራዊ ሊቃውንትን በመረጃነት እንዳላቀርብ የቀሰምሁት ዘመናዊ የፈረንጅ ትምህርት የሚስበኝ ወደ ነጭ ምሁራን እንጂ ወደ እራሴ ሊቃውንት አለመሆኑን ለማስገንዘብ ጭምር ነው፡፡)
ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ልመለስ፡፡ እና! የአቤ ስም በዘመነ አፄ ለምን ገንኖ አልወጣም? ልብ በሉ፤ አቤ በዚያን ዘመን ግራ እጁ ባዶ ቢሆንም ቀኝ እጁ የሚንቦገቦግ የብዕር ሰይፍ ጨብጧል፡፡ ይህ ሰይፈ-ነበልባል የዘውዱን ህዝባዊ የብዕር ሰው ስም በስርአቱ እንዲታፈን መደረጉ ተገቢም ባይሆን የሚጠበቅ ነው፡፡ ያኔ ሥዩመ እግዚአብሔርን መዳፈር ራሱን ፈጣሪን መድፈር ሆኖ ይቆጠራል፡፡ ይህንን የስዩማንን ድፍረት ቅኔ የቆረጠባት ቤተክርስቲያንም ብትሆን በደግ የምትቀበለው አይመስለኝም፡፡ ቀብታ ያነገሰችውን ንጉሥ ከጉያዋ የወጣ ደብተራ፣ በግራ እጁ ስልጣን ያልጨበጠ ብዕረኛ፣ የቁም-ስቅሉን ሲያበላው ቁጭ ብላ አትመለከተውም፡፡ ያኔ! አቤን አውግዢው፤ ወይም የይቅርታ ደብዳቤ አስጽፊው ብትባል አቤን እንዲጽፍ ሳታስገድደው የምትቀር አይመስለኝም፡፡
ንጉሡና በእሳቸው አካባቢ ያሉት መኳንንትና መሳፍንት አቤን የሚመለከቱት እንደ ኮሚኒዝም በጎሪጥ ነው፡፡ በዘመነ አብዮት ቆምጬ፤ “ኢምፔሪያሊዝምን በጎሪጥ ሶሻሊዝምን እንደ በላይ ዘለቀ አያቸዋለሁ” ብሏል አሉ፡፡ ይህ በዘመኑ ቢሮክራሲ የጎሪጥ የሚታይ ሰው፣ ግራ እጁ ባዶ የሆነ፣ ብዕሩ አርፎ የማይተኛ ተንኳሽ፣ በዐይነ-ቁራኛ የሚታይ ሞገደኛ ብዕረኛ፣ እንኳንስ ስም አሞጋሽ፣ አፍ-አካፋች ጓደኛም አይኖረውም፡፡ እንኳንስ በቀኛቸው ብዕር፣ በግራቸው ሥልጣን የጨበጡት ደራሲያን፣ የእነሱ ቅርበት ያላቸውም ንዑስ ደራሲያንም ቢሆኑ አቤን የሚቀርቡ አይመስለኝም፡፡ ከእሱ ጋር መታየት ከእሱ ጋር መፈረጅ ነው፡፡ ከእሱ ጋር መፈረጅ ደግሞ ከእሱ ጋር ግዞት መውረድ ያስከትላል፡፡ በመሆኑም በዘመኑ አቤን የከበቡት ስም አጥፊዎቹ እንጅ ስም አልሚዎቹ አይደሉም ባይ ነኝ፡፡ በቀረው ተመራማሪው ይሙላበት፡፡  
2. አቤና የተማሪው እንቅስቃሴ
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በመላው ተራማጅ ዓለም ህዝቦች ዘንድ አንቱ የተባለ ማህበር ነበር፡፡ ማህበሩ ጥልቅ ተራማጅ ብቻ ሳይሆን የሶሻሊስት ርዕዮት አለም ተከታይ ጭምር ነበር፡፡ እንቅስቃሴውም በአገር ውስጥ የነበረው ተሰሚነት ቀላል አልነበረም፡፡ የዘውዱን ስርዓት ቦርቡሮ የጣለው ይህ እንቅስቃሴ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ምንም እንኳ ዋርዳ ወይም ማማት ወፎች ፈልገው ያገኙትን የሾላ ፍሬ (አብዮት መሆኑ ነው) አንድ ጉራሽ ሳይቀምሱት ዛፉ ላይ ወጥተው ሲንጫጩ፣ የቤተ መንግሥት ጫካ ተንተርሶ፣ እረኛ መስሎ የበግ ለምድ ለብሶ፣ ያደፈጠ ዝንጀሮ የሾላውን ፍሬ ቢቀማቸውም፣ የተማሪው እንቅስቃሴ ለዚያን ጊዜው ለውጥ ያበረከተው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡
ይህ እንቅስቃሴ በላይን ንጉሡ አንቀው ከቀበሩት ጉድጓድ አውጥቶ የታጋይ ካባ ያለበሰ ማህበር ነው። ደጃዝማች ታከለን ፈርጣጭ ንጉሥ አጋች ብሎ ያሟካሸ ነው፡፡ ከዘመኑም ደራሲያን መካከል መርጦ የተቡ ብዕርተኞች ብሎ የካበና የሾመ ነው፡፡ ለ“አልወለድም” ደራሲ፣ በግራ እጁ ባዶ ሆኖ ሥርዓቱን ቀድሞ ለተፋለመ ህዝባዊ የብዕር ሰው፣ ማህበሩ ለምን ያኔ! የጎላ ዕውቅና አልሰጠውም? በግሌ ይህ ተራማጁ የተማሪዎች እንቅስቃሴ በመጽሔቶቹ ላይ ስለ አቤ የፃፈውን ነገር አላነበብሁም፡፡
አቤ በሩሲያ ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ሥራው በተራማጅነት ተፈርጆ ሰፊ መድረክ ሲሰጠው፣ ተራማጁ የተማሪው ማህበር ለምን ስለአቤ ምንም ሳይል አለፈ? አቤ የተማሪው ማህበር የቆመለተን ዓለማ ሙሉ-በሙሉ ያሟላ ብዕረኛ ነው፡፡ የዘውድን ሥርዓት በብዕሩ በጽናት ተፋልሟል፡፡ ለዚህም ድፍረቱ ተግዞ ታስሯል፡፡ ከዘመኑ ብዕረኞች መካከል እንደ አቤ የዘውድ ስርዓትን በብዕሩ በግልጽ የሞገተ ደራሲ እንኳን ያኔ፣ አሁንም ያለ አይመስለኝም፡፡ ታዲያ፣ ጉዳዩ ይህ ሆኖ ሳለ፣ በዓላማ የተሳሰረውን ህዝባዊ ደራሲ፣ ተራማጁ የተማሪዎች ማህበር ለምን ስሙን ሊያገነው አልቻለም? እውን “አልወለድም”ን ባያነብ ነው? ሠይፈ ነበልባልን አንብቦ ባይገባው ነው? ቢያንስ “አንድ ለእናቱ” ብቻውን የአቤን ስም ማግነን ይሳነዋል? የዳኛቸው ወርቁን ብቸኛ ልብወለድ “አደፍርስ”ን በየጥናት ክበባት ያስነበበን የተማሪ ማህበር፣ ለምን ከአቤ ስራዎች አንዱን እንድንወያይበት አላደረገም? የአቤስ የፈጠራ ስራዎች ፀረ-ፊውዳል ድርሰቶች አይደሉም የሚል ምሁር ከመካከላችን ይኖራል? ታዲያ ፀረ-ፊውዳል ታጋዩና የመሬት ላራሹ መፈክር አንጋቢው ተራማጁ የተማሪዎች ማህበር ይህን ህዝባዊ ደራሲ ሳያጎላው ያለፈው ሆን ብሎ ይሆን ወይስ ረስቶት? መልሱን ባውቀውም አልነግራችሁም፡፡ እናንተም እንድትነግሩኝ አልፈልግም፡፡ ለምን ብትሉ መላምት እንጅ ጥናትና ምርምር አይደለምና፡፡
3. አቤና ደርግ
“ሶሽያሊስት ነኝ” ያለው የደርግ መንግሥት ሶሽያሊስት አመለካከት ላላቸው የጥበብ ሰዎች ወዳጅ አልነበረም፡፡ ማርክስ ለማለት ማርቆስ የሚሉትን የደርግ አባላት ያስተካከሏቸው ደብተራቸውን ወርውረው፣ ትምህርታቸውን ጥለው ለዘመናት የታገሉለት አብዮት በእርግጥ የፈነዳ መስሏቸው አገር ቤት የገቡት፣ የተማሪውን ማህበር ሲያንቀሳቅሱ የኖሩት እውነተኛ ተራማጆ ናቸው፡፡ እነዚህም ወጣት ተራማጆች በወጉ ሳይደራጁ አገር ቤት ገብተው ደርግ እርስ-በእርስ ያጨፋጨፋቸውና የተረፉትን እራሱ አርዶ አስፋልት ላይ ያሰጣቸው ናቸው፡፡ በአጭሩ ኮትኩተው-አሰልጥነው፣ መግበው ያሳደጉት ውሻ የበላቸው የዋህ ታጋዮች ናቸው፡፡
ወደ አቤ ስመጣ፣ ደርግ በአብዮት ስም የተረከባት አገር እነአቤ ቀደም ብለው በህዝባዊ ብዕራቸው ያደነቋት፣ የዘመሩላት፣ የተጋዙላት ኢትዮጵያ ናት፡፡ እጅግ በርካታ ህዝቦች አንድ-አንድ ጡብ እየጨመሩ በገነቡት ቤት ላይ ደርግ የመጨረሻዋን ጡብ እንኳ ሳያሰቀምጥ የቤቱ ባለቤት እኔ ነኝ አለ፡፡ በእርግጥም ደርግ ምንም አይነት ጡብ በዚህ የቤት ሥራ ላይ አላኖረም፡፡ በአንፃሩ ግን ደርግ በዘውድ ሥርዐት ታማኝነቱ፣ በአጣና ደብዳቢነቱ፣ በግድያ ፈፃሚነቱ፣ ሕንፃ ገንቢ የሆኑ ተማሪዎችን፣ ምሁራንን በአጠቃላይ ምስኪን ገበሬዎችን አሳዶ ይገድል፣ ህዝባዊ የፈጠራ ሰዎችን ያስር፣ ከግዞት እንዳይወጡ በር ዘግቶ ይጠብቅ የነበረ ዋርድያ ነው፡፡ ይህ ዋርድያ የአገሪቱን ስልጣን ከተረከበበት ቀን ጀምሮ በአፉ ሶሻሊዝም እየሰበከ፣ በተግባር ሶሽያሊስት አመለካከት የነበራቸውን የጥበብ ሰዎች ከኢምፔሪያሊዝም ጋር ደምሮ የጎሪጥ ያያቸው ጀመር፡፡ እንደ አቤ ባይበረታባቸውም መንግስቱ ለማና ሌሎችም የደርግ ጥላቻ ዒላማ ነበሩ፡፡
የአቤ ድርሰቶች ለደርግ የተዋጡለት አይመስልም። ለስልጣን ወይም ለገንዘብ የማይንበረከከው አቤ፤ ከጊዜ በኋላ ብዕሩን ወደ ደርግ እንደሚያዞርበት ገብቶታል፡፡ ደርግ የጀመረውን ትውልድ የማጥፋት ዘመቻውን አቤ ዐይቶ እንዳላየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ በፀጋ የሚቀበለው አይሆንም። በዚህም መሰረት አቤን ከአካባቢው አርቆታል፡፡ የ“አልዋለድም” ደራሲ ጭራሮ-እንጨት ሆኖ ያቀጣጠለውን የአብዮት እሳት ቀርቦ እንዳይሞቅ አግዶታል፡፡ ምንም ዐይነት አስተዋጽኦ እንዳላደረገ ሆን ብሎ ወደ ጎን ገፍቶታል። ዛሬም እንደ ትላንቱ አቤ ከሁሉም የተገለለ ብቸኛ ደራሲ ሆኗል፡፡ ዛሬም እንደ ትላንቱ በጃንዳርም ሰላዮች የሚጠበቅ የብዕር ሰው ተብሏል፡፡ ከአቤ ጋር ቆሞ መታየት ሳይቀር ቀይ ሽብርን የሚጋብዝ አስፈሪ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የእሱን ብዕር ምርኳዝ አድርገው ሥልጣን ላይ የወጡ ደርጎች ለምን የአቤ ስም እንዲቀበር ፈለጉ? በእርግጥም አቤ በወቅቱ የደርግ ስጋት ነበረ? አዎ! ነበረ፡፡ ምንአልባት በወቅቱ የፈለቁት ሕቡዕ ድርጅቶች መልምለውት ይሆን? ጨርሶ አልተጠጉትም፡፡ አቤ ከእነሱ ሁሉ ባላይ አርቆ የሚያስብ ታጋይ ብዕረኛ ነበር፡፡ አሁን አጠገቤ ቢሆን ኖሮ “ማንም ተልካሻ በተጠራበት ስም ታጋይ፣ ተራማጅ፣ አትበለኝ” ብሎ ይገስፀኝ ነበር፡፡ አቤ ያኔ! ወደ አንዱ ጎራ ጠባ ቢልማ ኑሮውና ቀብሩም የውሻ ባልሆነ ነበር፡፡
የተፋለመለትን ህዝብ አምኖ ለህዝብ መብትና ፍትህ እየጮኸ፣ የተጋዘለት ህዝብ ግን ሳይደርስለት ደሙ-ደመ ከልብ ሆኖ ቀረ፡፡
እና! በፈጣሪ ተሰይሞም ሆነ ጠበንጃ አንግቦ ሥልጣን ላይ የወጣ ሹም ሁሉ ለምን አቤን ጠላው? ለምን አሳደደው? ለምን ሊቀበር የማይችለውን ስሙን ለመቅበር ሞከረ? መልሱን እኔም አልነግራችሁም … እናንተም እንድትመልሱልኝ አልፈልግም፡፡ ጥያቄ?

Read 3555 times