Saturday, 08 March 2014 13:27

የኢንዱስትሪው ዘርፍ የተጋፈጣቸው ፈተናዎች

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)
  • የኃይል መቆራረጥና የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ዋና ፈተና ሆኗል
  • ድሬደዋ ጨርቃጨርቅ በሶስት ዓመት ውስጥ ለ402 ቀናት መብራት አላገኘም
  • ድሬደዋ የምግብ ኮምፕሌክስ በመብራት መቋረጥ በቀን 200 ሺ ብር እያጣ ነው


    ባለፈው ሳምንት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ከተለያዩ ሚዲያዎች ለተውጣጡ ጋዜጠኞች የጉብኝት ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር። ጉብኝቱ ከሞጆ ቆዳ ፋብሪካ ጀምሮ አዳማ የሚገኘውን ኤልሲ አዲስ ኢንዱስትሪያል ዲቨሎፕመንት ፒኤልሲ የተባለ የቱርክ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካን ጨምሮ በቀጥታ በድሬደዋ የሚገኙ የጨርቃጨርቅ፣ የሲሚንቶ፣ የምግብና መሰል ፋብሪካዎችን አስቃኝቷል። በዚህ ጉብኝት በተለይ የመብራት መቋረጥና ከእነአካቴውም መጥፋት በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተጋረጠ አብይ ፈተናና አደጋ መሆኑን ታዝበናል፡፡
ሞጆ ቆዳ ፋብሪካ
ሞጆ ቆዳ ፋብሪካ በመንግስት የተቋቋመ ቢሆንም አሁን ግን ወደ ግል ይዞታነት ተቀይሮ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ በ30 ሚሊዮን ብር ካፒታል የሚንቀሳቀሰው የቆዳ ፋብሪካው፤ 85 በመቶ ምርቱን ለውጭ ገበያ የሚልክ ሲሆን 15 በመቶውን አገር ውስጥ ለሚገኙ እንደ አንበሳ እና ካንጋሮ ያሉ ጫማ አምራች ድርጅቶች እንደሚያቀርብ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሬድዋን በዳዳ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዓመት ከዘርፉ 11 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱም ተገልጿል፡፡ በፊት ጥሬ ቆዳ ብቻ ሲልክ የቆየው ፋብሪካው፤ በአሁኑ ወቅት የተዘጋጁና ያለቀላቸው የበግ፣ የፍየልና የበሬ ቆዳዎች ወደ ጣሊያን፣ ቻይናና ሌሎች አገሮች በመላክ ላይ መሆኑን የገለፁት አቶ ሬድዋን፤በቀጣይ የአዞ ቆዳን አዘጋጅቶ ለመላክ መታቀዱንም አብራርተዋል፡፡
ፋብሪካውን በጎበኘንበት ወቅት የተመለከትነው የፋብሪካው ፅዳት ምቾት አይሰጥም፡፡ በፋብሪካው ሽታ ምክንያት ጉብኝቱን አቋርጠው የወጡ፣ ያስመለሳቸውና መረበሽ የታየባቸው ጋዜጠኞች ነበሩ፡፡ አብዛኞቹ ሰራተኞች ይህን ተቋቁመው እየሰሩ ቢሆንም ለአደጋ መከላከያ ተብሎ የተዘጋጀ ልብስ የላቸውም፣ አብዛኞቹ ከወገብ በታች የላውንደሪ ላስቲክ አሸርጠው ነው የሚሠሩት። በአጠቃላይ “safety first” ለሚለው መርህ ፋብሪካው ትኩረት የሰጠው አይመስልም፡፡ ምንም እንኳ የቆዳው መሽተት ተፈጥሮአዊ እና የሚጠበቅ ቢሆንም ጤንነትን በሚያቃውስ ደረጃ መሆኑ ግን ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የፋብሪካው ወለል በአብዛኛው እርጥብ ሲሆን በጥንቃቄ ካልተራመዱ አንሸራቶ በአፍጢም የሚደፋ አይነት ነው፡፡
ለዚህም ነው አስጎብኛችን አቶ ሬድዋን “እንዳያንሸራትታችሁ ተጠንቀቁ” እያሉ በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቁን የነበረው፡፡ ፋብሪካው የሰራተኞቹን የጤና ሁኔታ በምን መልኩ ይጠብቃል በሚል ላነሳነው ጥያቄም ሲመልሱ “ክሊኒክ አላቸው፤ ሲያማቸው ይታከማሉ” በማለት በአጭሩ አልፈውታል፡፡ ይሁን እንጂ በተረፈ ምርት አወጋገድ ከ90 በመቶ በላይ ፋብሪካው የተዋጣለት እንደሆነ አቶ ሬድዋን በተደጋጋሚ ገልፀውልናል፡፡
ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ እንዳይሰራ የግብዓት፣ የገንዘብና የሎጂስቲክስ ችግሮች እንቅፋት እንደሆኑበት የሚናገሩት ስራ አስኪያጁ፤ እነዚህ ችግሮች በተፈለገው ፍጥነትና መጠን ቆዳን አዘጋጅቶ ለመላክ አላስቻሉንም ይላሉ፡፡ የጥሬ ቆዳ አቅርቦት እጥረት እንዲሁም  የኬሚካልና መለዋወጫ እቃዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ስለሚጠይቅ፣ የሚሰራበትን ብር ይይዘዋል ያሉት  አቶ ሬድዋን፤እነዚህን ፈተናዎች ለመፍታት ብድር፣ ሎጂስቲክስና መሰል ጉዳዮች በመንግስት ትኩረት እንዲሰጣቸው አሳስበዋል፡፡
ኤልሲ አዲስ ኢንዱስትሪያል ልማት ፒኤልሲ
ይህ የቱርክ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ እ.ኤ.አ በ2003 አዳማ ላይ በ150ሺ ስኩየር ሜትር ቦታ ላይ የተቋቋመ ነው፡፡ በ160 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ስራ የጀመረው ፋብሪካው፤የበጀቱን ግማሽ ብቻ እየተጠቀመ እንደሆነ ተጠቁሟል። የጥጥ አቅርቦትና የጥራት ማነስ ችግር ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ እንዳይሰራ እንዳደረገው ተገልጿል። ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከመንግስት ጋር በመመካከር፣ ከአዲስ አበባ በአንድ ሺህ ኪ.ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የኦሞ ወንዝ አካባቢ 400 ሺህ ሄክታር መሬት ወስዶ ጥጥ በማምረት ላይ ሲሆን ከሁለት ወር በኋላ ፋብሪካው የራሱ ጥጥ ይኖረዋል። ከሁለት ዓመት በኋላ ሙሉ በሙሉ በራሱ ጥጥ ማምረት የሚጀምር ሲሆን ከአምስት ዓመት በኋላ የሚፈለገው መጠን ያህል የራሱ ጥጥ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ በዚህ ዓመትም 10 ሚሊዮን  ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ ይጠበቃል፡፡ ሁለተኛው ክፍል የፋብሪካው ማስፋፊያ ሲጠናቀቅ የሰራተኞቹ ቁጥር ወደ ስድስት ሺህ እንደሚያድግ ተብራርቷል፡፡
ፋብሪካው በግዙፍና በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተደራጀ ሲሆን ሰራተኞች በእጃቸው የሚነኩት የተወሰነ ነገር ብቻ ነው፡፡ ያን የሚያህል ፋብሪካ እነዛ ሁሉ ማሽኖች ተሰናስለው ያለእንከን ሲሰሩ ማየት ግርምት ይፈጥራል፡፡ በዚያ ላይ የማሽኖቹ ድምፅም ጆሮን የሚረብሽ አይደለም፡፡ ተረፈ- ምርቱ የጥጥ ፍሬ ሲሆን ለዘይት ምርት ግብአትነት የሚጠቀሙ ድርጅቶች እንደሚወስዱት ተገልጿል፡፡
የተማረ ሰው ኃይል፣ የጥሬ ዕቃ አቅርቦትና የኃይል መቆራረጥ በስራው ላይ ችግር እየፈጠረ እንደሆነ የተናገሩት የፋብሪካው ኃላፊዎች፤ በተለይ የተማረ የሰው ኃይል እጥረት ብሎም ከሰለጠኑ በኋላ ፍልሰቱ ፈታኝ እንደሆነበት አልደበቀም፡፡ በፋብሪካው 85 በመቶ ያህሉ ሴት ሰራተኞች ሲሆኑ ይህም ለሴቶች ብዙ የስራ ዕድል በሌለባት ኢትዮጵያ ትልቅ አጋጣሚ እንደሆነ የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ ገልፀዋል፡፡ የሰራተኞቹ ደሞዝም ከሌሎች ፋብሪካ ሰራተኞች የተሻለ እንደሆነ የገለፁ ሲሆን ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው ሰራተኞችም በስራውም ሆነ በክፍያው ደስተኞች እንደሆኑ ነግረውናል፡፡
የፋብሪካው ፕሬዚዳንት በቴክስታይል ዘርፍ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው በመሆኑ በወቅቱ የቱርክ አምባሳደር የነበሩት የአሁኑ የአገሪቱ  ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ ከፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ጋር በመነጋገር ሊከፈት እንደቻለ በጉብኝታችን ወቅት ተገልፆልናል፡፡ 1100 ሰራተኞች ያሉት ኤልሲ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ፤ 95 በመቶ ያህል ሠራተኞቹ ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ ወደፊት ሰራተኞችን በማሰልጠን መቶ በመቶ በኢትዮጵያዊያን ሰራተኞች እንደሚመራም ተገልጿል፡፡ ግቢው ፋብሪካ ሳይሆን የተዋበ የሀብታሞች ሰፈር ነው የሚመስለው። የሠራተኞች ክበቡ ከአንድ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ ሬስቶራንት ጋር ይፎካከራል፡፡ ግቢው በአበባና በተለያዩ ዛፎች ያጌጠ ነው፡፡
ናሽናል ሲሚንቶ (ድሬደዋ)
በአገራችን የመጀመሪያው ሲሚንቶ ፋብሪካ ነው ናሽናል ሲሚንቶ፡፡ በ1936 ዓ.ም የተገነባው ሲሚንቶ ፋብሪካው፤ በቅርቡ ትልቅ ግዙፍ ማስፋፊያ ተገንብቶለት የድሮው ፋብሪካ በጡረታ ላይ ነው። በአሁኑ ሰዓት ምንም እየሰራ ባይሆንም ወደፊት ላይም (ኖራ) ሊመረትበት እንደታቀደ ተገልጾልናል፡፡   
በአዲሱ ግዙፍ የማስፋፊያ ፋብሪካ ለሲሚንቶ ግብአት የሚሆኑ የማይኒንግ ስራዎች ይከናወናሉ፡፡ በፊት በቀን 500 ቶን ያመርት የነበረ ሲሆን አሁን በቀን ሶስት ሺህ ቶን የማምረት አቅም አለው፡፡ የታክስ እፎይታን ጨምሮ ትልቅ ድጋፍ እንደሚያደርግ ኃላፊዎቹ ገልፀዋል፡፡ ፋብሪካው በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን የሲሚንቶ ፍላጎት ከማርካቱም በላይ በሀገሪቱ የደቡብ ምስራቅ ማለትም ሀዋሳና አካባቢዋ እንዲሁም  ወደ ጎረቤት አገራት የመላክ እቅድም አለው፡፡ ፋብሪካው ሙሉ አቅሙን መጠቀም ሲችል  በቀን 40ሺህ ቶን ማምረት እንደሚችልና በሰው ኃይልና በቴክኒክ ችግሮች በሙሉ አቅሙ እየሰራ እንዳልሆነ ተጠቁሟል፡፡
በዋናነት ሲሚንቶ የሚጠቀመው መንግስት በመሆኑ የገበያ እጥረት እንደማያሰጋቸው የፋብሪካው ኃላፊዎች ይናገራሉ፡፡ የባቡር ሀዲድ፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ ሆቴሎች፣ የአውሮፕላን ማረፊያና መሰል መሰረተ ልማቶች ስለሚገነቡ የሲሚንቶ ፍላጎት ይጨምራል የሚል እምነት እንዳላቸው የፋብሪካው ኃላፊዎች ይገልፃሉ፡፡ በተለይም በምስራቁ የአገሪቱ ክፍል የሲሚንቶ ፍላጎት አሁን ካለው ፍላጎት እንደሚጨምር የሚያመለክት ጥናት እንዳለ ኃላፊዎች ገልፀው፣ አሁን ያለው ከገበያ ጋር የተያያዘ ችግር ጊዜያዊ መሆኑንም በጉብኝታችን ወቅት ተገልጿል፡፡ አልፎ አልፎ የኃይል መቆራረጥ ቢኖርም ፋብሪካው ተለዋጭ የኃይል አቅርቦትን ይጠቀማል፡፡ 1ሺህ ሰራተኞች ያሉት ናሽናል ሲሚንቶ፤ 2.1 ቢሊዮን ብር ካፒታል አለው፡፡ እጅግ ግዙፍና ዘመናዊ በመሆኑ ግቢውን ጎብኝቶ ለማጠናቀቅ ብዙ ሰዓት ፈጅቶብናል፡፡
የድሬደዋ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ
ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ዘመን በ1931 ዓ.ም የተቋቋመው የድሬደዋ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ፤ የ76 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ ቢሆንም በተጋረጡበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተነሳ በአሳዛኝ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ ለ45 ዓመታት በውጭና በአገር ውስጥ የጨርቃጨርቅ ሙያ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ፈቃደ ገ/ህይወት ፋብሪካው ስላለበት ሁኔታ ሲናገሩ እንባ ይተናነቃቸዋል፡፡ ድሬደዋ ጨርቃጨርቅ ለሌሎች ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች እናትም አባትም ነው። የሚሉት አቶ ፈቃደ፤ በኃይል አጥረትና ሌሎች ችግሮች ፋብሪካው ለአደጋ መጋለጡን ይናገራሉ፡፡
በተለያየ ወቅት ጣሊያኖች. እንግሊዞች፣ ጀርመኖችና ጃፓኖች አገሮች አስተዳድረውታል፤ ከዚያ በኋላም በደርግ ዘመን በመንግስት ስር ይንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን የሚሊተሪ የደንብ ልብሶችን ማምረት ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር አቶ ፈቃደ ገልፀዋል፡፡ ከደርግ ውድቀት በኋላ በኢህአዴግ የመንግስት ይዞታዎችን ወደ ግል ማዞር በመጀመሩ እ.ኤ.አ በ2007 ወደ ግል ይዞታነት ተዛውሮ መስራት ጀመረ፡፡ ባለሀብቶቹ ሲረከቡት እጅግ በደካማ ይዞታ ላይ እንደነበር ሥራ አስኪያጁ ይናገራሉ፡፡ የፋብሪካው ማሽኖች የ50 እና 60 ዓመት እድሜ ያላቸው በመሆኑ፣ እንዲሁም ጥሬ ዕቃ አቅርቦት (ጥጥ) እጥረትና በኃይል መቆራረጥ ሳቢያ በፋብሪካው ላይ የህልውና አደጋ እያንዣበበት ነው ይላሉ፡፡ በሶስት ዓመታት ውስጥ ለ402 ቀናት መብራት አለማግኘቱን በመጥቀስ የተለያዩ ችግሮች ተደማምረው ምርታማነቱ እየቀነሰ የመጣው ፋብሪካው፤ የገንዘብ ብድሩን መክፈል እነዳቃተውና የወለዱም መጠን እየጨመረ መምጣቱን ስራ አስኪያጁ ይገልጻሉ፡፡ ይህንን የኃይል መቆራረጥ ችግር ፋብሪካው ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በማልከት ጉዳዩ ለጠ/ሚኒስትሩ ቀርቦ የብድር መክፈያ ጊዜው ለሁለት ዓመት ተራዝሞለታል፡፡ ፋብሪካውን ከውድቀት ለመታደግ ከ4 ጊዜ በላይ የብድር ማግኛ ፕሮፖዛሎችን ለልማት ባንክ ማቅረባቸውን ያስታወሱት ስራ አስኪያጁ፤ አንዳቸውም ምላሽ እንዳላገኙ ይናገራሉ፡፡ ፕሮፖዛሉ በዋናነት ትኩረት ያደረገው ያረጁ ማሽኖችን በአዲስ መተካት፣ ከአራት መቶ በላይ ተጨማሪ የሰው ኃይል መቅጠርና ድርጅቱን ምርታማ ማድረግ ላይ ነው ያሉት ስራ አስኪያጅ፤ ብድሩ ተገኝቶ ፕሮፖዛሉ ተግባራዊ ቢደረግ ኖሮ ፋብሪካው በየዓመቱ 29 ሚሊዮን ዶላር ምንዛሪ እንደሚያስገባ ተተንብዮ ነበር ብለዋል፡፡
ከልማት ባንክ የተጠየቀው ብድር ባይሳካም ሌላ ጥረት መደረጉን ሥራ አስኪያጁ ይናገራሉ፡፡
ህንድ ቦምቤይ ከሚገኝ አንድ ባለሀብት ጋር በጥምረት ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሶ ባለሀብቱ ማሽኖች ይዞ ለመምጣት ፍላጎት ማሳየቱን ጠቁመው ለዚህ ፕሮጀክት 30 ሚሊዮን ዶላር እና 1,200 ተጨማሪ ሰራተኞች እንደሚያስፈልጉም ገልፀዋል፡፡ እቅዱ ተሳክቶ ፋብሪካው ስራ ከጀመረም 80 በመቶ ምርት ለውጭ ገበያ እንደሚልክ ተጠቁሟል፡፡ ይህን ሁሉ ፈተና በጉያው ይዞ የሚንገታገተው ፋብሪካው፤ ባለፈው ዓመት ምርትን ኤክስፖርት በማድረግ ውጤታማ ከሆኑ 10 ፋብሪካዎች ሰባተኛ በመውጣት ተሸልሟል፡፡ ዘንድሮም 2 ሚሊዮን ዶላር ምንዛሪ ይጠበቅበታል፤ ይሁን እንጂ “በዚህ ሁሉ አጣብቂኝ ውስጥ ሆኖ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ምንዛሪ ማስገኘት ህልም ነው፤ ያልዘራነውን አናጭድም” ሲሉ ስራ አስኪያጅ ሀዘናቸውን ገልፀዋል፡፡
ፋብሪካውን ከውድቀት ለመታደግ በተለያዩ ጊዜያት ለመንግስት አካላት አቤት ማለታቸውን ጠቁመው፤ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትም ፋብሪካውን እንደጎበኙ ገልፀዋል፡፡ በተወካዮች ም/ቤት የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የፕራይቬታይዜሽን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ኃላፊዎች እና ሌሎችም ጉብኝት አድርገው ችግሩን ቢረዱም እስካሁን የተገኘ መፍትሄ የለም ብለዋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ የስድስት ወራት እንቅስቃሴ አስመልክተው ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት የኢንዱስሪ ሚኒስትር አቶ አህመድ አብተው፤ ፋብሪካው ወደ ግል ሲዛወር የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የመንግስት ንብረት ሲገዙ የሚደረገው ማበረታቻ ሁሉ እንደተሟላለት ገልፀው፤ ፋብሪካው 35 በመቶ ቀድሞ ከፍሎ 65 በመቶውን በአምስት አመት ውስጥ መክፈል ሲገባው ሳይከፍል በመቅረቱ፣ እንዲሁም ለጥጥ መግዣ ከልማት ባንክ የተበደረውን ገንዘብ ባለመክፈሉ ሌላ ብድር የማይፈቅድለት መሆኑን ገልፀው በማገገሚያ ግዜ ውስጥ ገብቶ በሌሎች አማራጮች የሚቀጥልበት ሁኔታ እየተፈለገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ፋብሪካው 1,500 ሰራተኞች ይዞ በአጣብቂኝ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ሰራተኞቹም “ተስፋ ቆርጠናል፤ ጥረታችን ጡረታችንን ለማስከበር ነው” ብለዋል፡፡
ድሬደዋ የምግብ ኮምፕሌክስ
ድሬደዋ የምግብ ፋብሪካ በ1988 ዓ.ም በ55 ሚሊዮን ብር ካፒታል በ300 ሰራተኞች ሰራ እንደጀመረ የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ካህሉ ንጉስ ይገልፃሉ፡፡ ፋብሪካው በ1996 ዓ.ም በ1997፣በ1998 ዓ.ም በአጠቃላይ በ70.2 ሚሊዮን ብር የተለያዩ ማስፋፊያዎችን አድርጓል፡፡ እ.ኤ.አ የካቲት 11 ቀን 2011 ወደ ግል ይዞታነት የተዛወረው ፋብሪካው፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ተወዳጅ የሆነውን እና 80 በመቶ አዲስ አበባ የሚሸጠውን ቬራ ፓስታን በማምረት ይታወቃል፡፡ ወደ ግል ይዞታነት ከተዛወረ በኋላ ፋብሪካው ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ችግሮቹን መለየትና የሰራተኞቹን ጥያቄ መመለስ ቅድሚያ እንደተሰጠው የጠቆሙት ዋና ስራ አስኪያጁ፤ 175% የደሞዝ ጭማሪና የመዋቅር ለውጥ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት በቀን ሁለት ሺህ ኩንታል ዱቄት፣ 600 ኩንታል ፓስታ፣ እንዲሁም 90 ኩንታል ዳቦ ያመርታል፡፡ በፊት ሙሉ በሙሉ የአውስትራሊያ ስንዴን በግብአትነት ይጠቀም የነበረው ፋብሪካው፤ በአሁኑ ወቅት በ2004 ዓ.ም ባሌ ውስጥ 6 የተደራጁ ማህበራት የሚያመርቱትን የአገር ውስጥ ስንዴ በግብአትነት ይጠቀማል፡፡ በቅርቡም በ6.6 ሚሊዮን ብር አጠቃላይ የፋብሪካው የጥገና ስራ መከናወኑ ተገልጿል፡፡ ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት ለሀረር፣ ለድሬደዋና ለሀረማያ ዩኒቨርሲቲዎች በቋሚነት ዳቦ ያቀርባል፡፡ 165 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያለው ድሬደዋ የምግብ ኮምፕሌክስ፤ በ2012 ኢንግላንድ ከሚገኝ ድርጅት በጥራት፣ በቅንጅታዊ አሰራር፣ በምርት አቅርቦት፣ ሰው ኃይልን በአግባቡ በመጠቀም እና ወጪን በመቀነስ፣ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡
ሆኖም የሃይል መቆራረጥ ለፋብካው ፈተና እንደሆነበት ተገልጿል፡፡ በቀን ሁለትና ሶስት ጊዜ የሚቆራረጠው መብራት ለስራቸው እንቅፋት ሆኖብናል ያሉት አቶ ካህሱ፤ “ወዴት ሄደን አቤት እንደምንል ግራ ገብቶናል” ይላሉ፡፡ የሃይል መቆራረጡ ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር የተገናኘ ነው የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ለከተማ አስተዳደሩ ፀረ ሙስና ቢሮ አመልክተው ጉዳዩን እየተከታተለው እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ እስከዚያው ግን በመብራት መቆራረጥ በቀን 200ሺህ ብር ኪሳራ እየደረሰባቸው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ የድሬደዋ ከተማ ከንቲባ አቶ አሳድ ዚያድ በበኩላቸው፤ የፋብሪካው የኃይል መቆራረጥ ከመልካም አስተዳደር ችግር የመጣ መሆኑን አምነው ክትትል እየተደረገበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የጥሬ ዕቃ አቅርቦት የድሬደዋ የምግብ ፋብሪካ ሌላው ፈተና ነው፡፡ በህገ-ወጥ መንገድ ከውጭ የሚገቡ ፓስታና መሰል ምርቶች በፋብሪካው ላይ የተጋረጡ ችግሮች እንደሆኑ ተነግሯል፡፡ እነዚህ ችግሮች ከተስተካከሉና የኃይል መቋረጥ መፍትሄ ካገኘ ዘንድሮ አምስት ሺህ ኩንታል ፓስታ፣ አምስት ሺህ ኩንታል መካሮኒና 10 ሺህ ብስኩቶችን ወደ ውጭ ኤክስፖርት ለማድረግ ታቅዷል፡፡ “ይሁን እንጂ ፋብሪካው ጥራት ያለውና ከኬሚካል የፀዳ ግብአት እየተጠቀመ፣ ለሚያመርተው ምርት ታክስ እየከፈለ ሌሎች ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ግን በህገ-ወጥ መንገድ ታክስ ሳይከፍሉ ፓስታና መካሮኒዎችን ከእኛ እኩልና ከእኛ በላይ በሆነ ዋጋ ይሸጣሉ” ያሉት አቶ ካህሱ፤ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ህገ-ወጦችን እንዲያስቆም፤ ፌደራል መንግስት ኃይል አቅርቦት ላይ አሻጥር የሚሰሩ አካላትን ትኩረት ሰጥቶ እንዲከታተል ጥሪ አቅርበዋል፡፡   
የፋብሪካው ሰራተኞች በቂ የደሞዝ ጭማሪና እድገት እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ የ175% የደሞዝ ጭማሪ መደረጉን የገለፁት ሥራ አስኪያጁ፤ ለአብዛኞቹ ብዙ ልምድ ያላቸው ሠራተኞች የትምህርት ደረጃቸው ባይፈቅድም እንዳደላደሉ ገልፀው፤ መዋቅሩ በትምህርት ደረጃ ይሰራ ቢባል 60 በመቶው ሰራተኛ ተንሳፋፊ ይሆን እንደነበር ተናግረዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ መታየት ያለበት ካለ በቀጣይ የሚታይ ይሆናል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አህመድ አብተው ፋብሪካዎች ላይ ችግር እየፈጠረ ስላለው የሀይል መቆራረጥ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ ብዙ ፋብሪካዎች ያሉት አዲስ አበባ በመሆኑ መብራት ሀይል ቅድሚያ ሰጥቶ የትራንስሚሽንና የዲስትሪቢውሽን መስመሮችን በማደስ፣ በማጠናከርና መስመሮችን በመለየት ስራ ላይ እየተጋ መሆኑን ገልፀው፤ በክልሎችም ተመሳሳይ ስራ ለመስራት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
የመኢሶ ዳዋሌ የባቡር ሀዲድ ዝርጋታ
ድሬዳዋ ከተማን ወደ ቀኝ ትቶ በመልካ ጀብዱ ወደ ጅቡቲ የሚያመራው የመኢሶ ደዋሌ የባቡር ሀዲድ ዝርጋታ ስራም በፍጥነት እየተከናወነ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ 346 ኪ.ሜ የሚሸፍነው  ፕሮጀክቱ፤ ከአጠቃላይ ስራው 35 በመቶው መጠናቀቁን የመኢሶ ደዋሌ የባቡር መንገድ ፕሮጀክት ማናጀር ኢ/ር መኮንን ጌታቸው በጉብኝቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡ 1.4 ቢሊዮን ዶላር የተበጀለት ይህ ፕሮጀክት፤ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ትልቁ ፕሮጀክት እንደሆነ ኢ/ር መኮንን ተናግረዋል፡፡ ስራው ከመጠናቀቁ በፊት 37 ኪ.ሜትር ለሙከራ እንደሚከፈት የገለፁት ኢ/ሩ፤ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ባቡር በሚያልፍባቸው ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ መነቃቃት ይፈጠራል ብለዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ጅቡቲ 676 ኪ.ሜትር ርዝመት ያለው የባቡር መስመር እየተዘረጋ ሲሆን አጠቃላይ 3 ቢሊዮን ዶላር እንደተመደበም ተገልጿል፡፡ 676 ኪ.ሜትሩ የባቡር መንገድ በተለየዩ የባቡር መንገድ ስራ ላይ በተሰማሩ ድርጅቶች እየተሰራም እንደሆነ ታውቋል፡፡

Read 2220 times