Print this page
Saturday, 08 March 2014 13:09

ፎርብስ የአመቱን የአለማችን ቢሊዬነሮች ይፋ አደረገ

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(6 votes)

              በየአመቱ የአለማችንን ቢሊዬነሮች እየመረጠ ይፋ የሚያደርገው ፎርብስ መጽሄት፣ ዘንድሮም ለ28ኛ ጊዜ የ2014 ቢሊየነሮችን ዝርዝር ሰሞኑን  ይፋ አድርጓል፡፡ የማይክሮሶፍት ኩባንያ መስራቹ ቢል ጌትስ፣ በ76 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት የአመቱ የአለማችን ቁጥር አንድ  ባለጸጋ ሆኗል፡፡ ላለፉት አራት አመታት በሜክሲኳዊው የቴሌኮሙኒኬሽን ኩባንያ ባለቤት በካርሎስ ስሊምን ቀዳሚነቱን ተነጥቆ የቆየው ቢል ጌትስ፣ ዘንድሮ ቀንቶታል፡፡ ካርሎስ ስሊምን ከኋላው በማስከተል መሪነቱን መልሶ ወስዷል፡፡
ፎርብስ ባለፉት 20 አመታት ይፋ ካደረጋቸው የአለማችን ባለጸጎች ዝርዝር ውስጥ፣ በአስራ አምስቱ የአንደኛነትን ስፍራ የተጎናጸፈ ነባር ባለጸጋ ነው - ቢል ጌትስ፡፡ በ72 ቢሊዮን ዶላር የአለማችንን ሁለተኛ ባለሃብትነት ደረጃ የያዘውን ካርሎስ ስሊምን ተከትሎ በፎርብስ ዝርዝር ሶስተኛ ተደርጎ የተቀመጠው፣ ስፔናዊው ባለጸጋ አማንቺዬ ኦርቴጋ ነው - በ64 ቢሊዬን ዶላር ሃብት፡፡  አሜሪካዊው ቢሊዬነር ዋረን በፌ በ58 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር፣ የኦራክል ኩባንያ ባለቤት ላሪ ኤሊሰን በ48 ቢሊዮን ዶላር የአራተኛና የአምስተኛነቱን ደረጃ ይዘዋል፡፡ በዘንድሮው ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት 1ሺህ 645 የአለማችን ቢሊየነሮች፣ በድምሩ 6 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት እንዳላቸው የዘገበው ፎርብስ፣ ይሄን ያህል ቁጥር ያላቸው ቢሊየነሮች ሲመዘገቡ የዘንድሮው  የመጀመሪያው ነው ብሏል፡፡
በፎርብስ የቢሊየነሮች ዝርዝር ታሪክ፣ 2014 በሴት ቢሊየነሮች ቁጥር ክብረ ወሰን የተመዘገበበት ነው፡፡ በዘንድሮው የፎርብስ ዝርዝር ከተካተቱት የአለማችን ቀንደኛ ቢሊየነሮች፣ 10 በመቶ ያህሉ ወይም አንድ መቶ ሰባ ሁለቱ ሴቶች ናቸው፡፡ በአመቱ ዝርዝሩን ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀላቀሉ ሴቶች ቁጥርም ክብረወሰን ተመዝግቦበታል፡፡ 42 አዳዲስ ሴት ቢሊዬነሮች በዝርዝሩ ውስጥ ሊካተቱ ችለዋል፡፡
ከ2014 የፎርብስ ሴት ቢሊዬነሮች ቀዳሚነት የያዘችውና የዎልማርት ኩባንያ ወራሽ የሆነችው ባለ 36 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላሯ ክርስቲ ዋልተን፣ በአጠቃላዩ ዝርዝር ውስጥ ደግሞ የዘጠነኛ ደረጃን አግኝታለች፡፡ የታዋቂው ኮስሜቲክስ አምራች ኩባንያ የሎሪየል ባለቤት ፈረንሳዊቷ ሊላኒ ቤተንኮርት፣ ከሴት ቢሊየነሮች ሁለተኛነትን፣ ከአጠቃላይ ቢሊየነሮች አስራ አንደኛነትን ይዛለች - በ 34 ነጥብ 5 ቢሊዬን ዶላር፡፡ በዝርዝሩ ውስጥ ብዙ ሴት ቢሊዬነሮችን በማስመዝገብ ቀዳሚነቱን የያዘችው አሜሪካ ናት - በ58 ሴት ቢሊየነሮች፡፡ ጀርመን 16 ሴት ቢሊዬነሮችን ስታስመዘግብ፣ ብራዚልም 14 ሴት ቢሊዬነሮችን አስመርጣለች፡፡
በዘንድሮው ዝርዝር ውስጥ በቴክኖሎጂ በተለይ ደግሞ በኢንተርኔት መስክ የተሰማሩ ባለጸጎች በጥሩ ሁኔታ ተወክለዋል ብሏል ፎርብስ፡፡ የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙከርበርግ፣ የአምናውን ጥሪቱን ከእጥፍ በላይ በማሳደግ 28 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር አድርሶ ስለተገኘ፣ ዘንድሮ 21ኛ ደረጃ ተሰጥቶታል፡፡ ዝርዝሩ እንደሚያሳየው፣ የጎግል መስራቾቹ ላሪ ፔጅ እና ሰርጂ ብሪን፣ በ32 ነጥብ 3 እና በ31 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር 17ኛ እና 19ኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ 32 ቢሊዮን ዶላር ያካበተው የአማዞን ዶት ኮም ባለቤት ጄፍ ቤዞስ በበኩሉ፣ በጎግሎቹ ባለጸጎች ጣልቃ ገብቶ 18ኛው የአለማችን ቢሊየነር ተብሏል፡፡ የአለማችንን ቢሊየነሮች ዝርዝር ለመጀመሪያ ጊዜ ከተቀላቀሉት አዳዲስ ባለጸጎች መካከል በቴክኖሎጂ መስክ የተሰማሩም ይገኙበታል፡፡ በዘርፉ ስመጥር የሆነውን ድሮፕቦክስ የተባለ ኩባንያ የሚመራው ድሪው ሆስተን ከእነዚህ አዲስ ገቢ የቴክኖሎጂ ሞጃዎች አንዱ ነው፡፡ የሄውሌት ፓካርድ ኩባንያ ባለቤት ሜግ ዊትማንም፣ በቴክኖሎጂ ዘርፍ በቢሊዬነሮች ዝርዝር ውስጥ ከሰፈሩት ሁለት ሴቶች አንዷናት፡፡
ከሁለት ወራት በፊት የመንግስት ስራቸውን ያቆሙት የቀድሞው የኒውዮርክ ሲቲ ከንቲባ ማይክል ብሉምበርግ፣ በ33 ቢሊዮን ዶላር የ16ኛነቱን ደረጃ መያዙን የሰሙ አንዳንድ ጠርጣራዎች፣ “ይሄ ሰው በተሰጠው ስልጣን ከአጉል ነገር ጋር ሳይነካካ አይቀርም” ብለው ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ፎርብስ ግን፣ “የለም እንዲያ አይደለም!... ሚስተር በሉምበርግ አብዛኛውን ሃብቱን ያካበተው፣ በሌላ ሳይሆን በግሉ ባቋቋመው የሚዲያ ኩባንያ ነው” ብሏል፡፡
‘የአመቱ ከሳሪ’ እና ‘የአመቱ አትራፊ’
ያለፈው አመት የማትረፍ ብቻ ሳይሆን የመክሰር ጭምር ነበር ይላል ፎርብስ፡፡ በሃብት ላይ ሃብት ያፈሩ ብዙዎች ቢኖሩም፣ አይከስሩት ኪሳራ ያስተናገዱም አልታጡም፡፡ ከእነዚህ ከሳሪዎች መካከል ቅድሚያውን የያዘው ደግሞ፣ ብራዚላዊው ባለጸጋ ኤኪ ባቲስታ ነው፡፡ ለታዋቂውና ለትርፋማው የባቲስታ የነዳጅና የተፈጥሮ ሃብቶች አምራች ኩባንያ፣ አመቱ መልካም አልነበረም፡፡ ኩባንያው የወሰደውን ከፍተኛ ብድር መመለስ ተስኖት፣ በቂ ምርት አውጥቶ ለገበያ ማቅረብ አቅቶት ሲንገዳገድ ነው አመቱ ያለቀው፡፡ አመቱ ተጠናቆ ሂሳቡ ተደማምሮ ተቀናንሶ ሲሰላ ታዲያ፣ አስደንጋጭ ውጤት ነበር የተገኘው፡፡  አምና የ10 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ባለቤት የነበረው ብራዚላዊው ባለጸጋ ባቲስታ፣ ዘንድሮ በእጁ ላይ የተገኘው 300 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ ፎርብስም ይሄን ቀን የጣለው ሰው፣ “ይህን ገንዘብ ይዘህ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ምን ታደርጋለህ!” ብሎ ከሰልፉ አስወጥቶታል፡፡
አመቱ ለባቲስታ እንጂ ለዙከርበርግ የኪሳራ አይደለም፡፡ የፌስቡክ መስራቹ ማርክ ዙከርበርግ፣ በአመቱ የሃብት ጭማሪ ካስመዘገቡ ገበያ የሞቀላቸው ባለጸጎች መካከል ቀዳሚው ነው ተብሏል፡፡ በ2013 በእጁ ላይ የነበረውን 13 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ከእጥፍ በላይ አሳድጎ፣ በ2014 የሃብቱን መጠን 28 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር አድርሶታል፡፡ ዙከርበርግ በአመቱ ከፍተኛ ገንዘብ ያፈራው የአለማችን ቀዳሚ ባለጸጋ ተብሏል - በፎርብስ፡፡
የሞጃዎች አገር
በዘንድሮው የፎርብስ የአለማችን ቀንደኛ ባለሃብቶች ዝርዝር ውስጥ፣ በርካታ ዜጎቿን ያሰለፈችው ቀዳሚት አገር፣ ታላቂቷ አሜሪካ ናት፡፡ በ492 የሞላላቸው ቢሊዬነሮቿ ዝርዝሩን ያጥለቀለቀችውን አሜሪካን ተከትላ፣ ቻይና 152 ቢሊየነሮቿን ስታሰልፍ፣ ሩሲያ በበኩሏ 111 ቢሊየነሮቿን በዝርዝሩ ውስጥ አስገብታለች፡፡  አልጀሪያ፣ ሉቲኒያ፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ በዘንድሮው የፎርብስ መጽሄት ዝርዝር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ስማቸውን ያስጠቀሷቸውን  አንዳንድ ቢሊየነሮችን አፍርተዋል፡፡ እነ አሜሪካ ብዙ ቢሊዬነሮችን ባፈሩበት ባለፈው አመት፣ እነ ቱርክ ብዙ ቢሊዬነሮቻቸውን አጥተዋል፡፡ የዋጋ ግሽበት ክፉኛ እየደቆሳት ያለችው ቱርክ፣ አምና ከነበሯት ቢሊዬነሮች አስራ ዘጠኙን ተነጥቃለች፡፡ የመገበያያ ገንዘቧ የመግዛት አቅም ከአሜሪካ ዶላር ጋር ሲነጻጸር ባለፈው አመት 20 በመቶ የወረደባት ኢንዶኔዢያም ብትሆን፣ ስምንት ቢሊየነሮቿን አጥታለች፡፡
ቁማር እና ዶላር
በምድረ አሜሪካ በቁማር ስሙ ለሚጠራው ሼልደን አዴልሰን፣ አመቱ ገዳም ነበር፡፡ ከሰባት አመታት በፊት በዚሁ ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት አስር የአለማችን ቀዳሚ ቢሊየነሮች አንዱ የነበረው አዴልሰን፣ ሃብቱ አሽቆልቁሎበት ደረጃውን ለሌሎች ተረኞች አስረክቦ ነበር የባጀው፡፡  ዘንድሮ ግን የቁማር በለስ ቀንቶት፣ ተጨማሪ 11 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር አፍሶ ተገኝቷል፡፡ እናም ከ2007 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ከአስሩ ቀንደኞች ተርታ ተመልሶ ተቀላቅሏል - በስምንተኛነት፡፡  እንግሊዛዊቷ የድረገጽ ቁማር አጫዋች ዴኒስ ኮቴስም፣ እንዲህ እንደ አዴልሰን በቁማር ቀን ከወጣላቸው የአመቱ ባለጸጎች አንዷ ናት፡፡ በአባቷ ሱቆች ውስጥ በካሸርነት ተቀጥራ እየሰራች፣ ጎን ለጎን ትምህርቷን ትከታተል የነበረችው ኮቴስ፣ በኋላ ላይ ቁማር እንደሚያዋጣት በማሰብ ከወንድሟ ጋር ባቋቋመችው ቤት 365 የተሰኘ አቋማሪ ኩባንያ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር አፍሳ በፎርብስ ዝርዝር ውስጥ ሰተት ብላ ገብታለች፡፡ ካዚኖ ተብሎ በሚጠራው ቁማር ጨዋታ ቢሊዮን ዶላሮችን ካፈሱ መሰል የቁማር ሃብታሞች ሌላው፣ ባለ 22 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላሩ ሉዊ ቺ ው ይባላል፡፡
‘ራስ ሰራሾች’ እና ‘ወራሾች’
በዘንድሮው ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት 1ሺህ 645 የተለያዩ አለም አገራት ቢሊየነሮች ውስጥ፣ ሁለት ሶስተኛ ያህሉን ወይም 1ሺህ 80ዎቹን፣ ‘ራስ ሰራሽ ቢሊየነሮች’ (self-made billionaires) ይላቸዋል ፎርብስ መጽሄት፡፡ ከምንም ተነስተው ጥረው ግረው በመስራት፣ በየተሰማሩበት የሙያ መስክ ስኬት ያስመዘገቡ ባለጠጎች ለማለት ነው፡፡
207 ያህሉ ከእናት ከአባታቸው ወይም ከዘመድ ወዳጅ ጓደኛቸው አልያም ከሌላ አካል ዳጎስ ያለ ሃብት የወረሱ ባለጸጎች ናቸው፡፡ የተቀሩት 352 ቢሊየነሮች ደግሞ፣ ምንም እንኳን የተወሰነውን ሀብት ያገኙት በውርስ ቢሆንም፣ እግራቸውን አጣጥፈው የወረሱትን የሚበሉ ተጧሪዎች አይደሉም ተብሏል፡፡ ፎርብስ እንደሚለው፣ እነዚህኞቹ ባለጸጎች በውርስ ያገኙትን ሃብት መነሻ በማድረግ ጠንክረው የሰሩና የበለጠ ሃብት እያፈሩ ለትልቅ ደረጃ የበቁ ብልሆች ናቸው፡፡
አዲስ ገቢዎች እና ተሰናባቾች
በዘንድሮው የፎርብስ የአለማችን ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ፣ 268 አዲስ ገቢ ቢሊየነሮች ተካተዋል። በርካታ አዳዲስ ቢሊየነሮች በተፈጠሩበትና ክብረወሰን በተመዘገበበት በዘንድሮው አመት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በዝርዝሩ ከተካተቱ አዲስ ገቢዎች መካከል፣ 50ው ከአሜሪካ፣ 37ቱ ደግሞ ከቻይና ናቸው፡፡ ስማቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በፎርብስ ዝርዝር ውስጥ ከተካተተላቸው አዳዲስ ቢሊየነሮች መካከል የምትጠቀሰው፣ ከቢሊየነሮች ሁሉ በዕድሜ ለጋ የሆነችው ፔሬና ኬ ናት፡፡ የሆንግ ኮንግ ዜግነት ያላት ይህቺ የ24 አመት ወጣት፣ በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር በ1ሺህ 284ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች የልጅ ሃብታም ናት፡፡ 1ሺህ 540ኛ ደረጃ የያዘችው የፌስቡክ አጋር መስራች ሸሪል ሳንበርግ እንዲሁም ከሰሞኑ ከፌስቡክ ጋር የ19 ቢሊዮን ዶላር ሽያጭ የተዋዋሉት የዋትዛፕ መስራቾች ጃን ኩም እና ብሬን አክተንም ለዝርዝሩ አዲሶች ናቸው፡፡
ከዚህ በፊት በዝርዝሩ ውስጥ ተካተው የነበሩና ዘንድሮ ግን የተሰናበቱ ጊዜ የጣላቸው ባለጸጎችም አልታጡም፡፡ 47 የእስያ ፓሲፊክ፣ 20 የመካከለኛው ምስራቅና የአፍሪካ አገራት ቢሊየነሮች በዚህ አመት ከፎርብስ ዝርዝር ተሰርዘዋል፡፡ አምና ቢሊየነር ተብለው በፎርብስ ከሰፈሩበት መዝገብ፣ ዘንድሮ ስማቸው የተፋቀባቸው የከሰሩ ባለጸጎች በድምሩ አንድ መቶ ናቸው፡፡ ከእነሱ በተጨማሪ ሌሎች 16 ቢሊየነሮችም ከዚህ አለም በሞት በመለየታቸው ከዝርዝሩ ተሰርዘዋል፡፡ ከከሰሩት በታች ከሞቱት በላይ አንድ ሰው አለ - ከሁሉም በላይ አይከስሩ ኪሳራ የገጠመው ኖርዌጂያኑ ኦላቭ ቶን፡፡ ፎርብስ አሰላሁት እንዳለው፣ አምና 5 ነጥብ 75 ቢሊዮን ዶላር የነበረው ይሄ ባለጸጋ፣ ዘንድሮ ቤሳቢስቲን የሌለው ነጭ ደሃ ሆኗል፡፡
ጥቁር ቢሊየነሮች
በዚህ አመት የፎርብስ ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት 1,645 ቢሊየነሮች፣ ጥቁሮች ዘጠኝ ብቻ ናቸው። ከአህጉሪቱ ብዙ ቢሊየነሮችን በማስመዝገብ ቀዳሚነቱን የያዘችው ናይጀሪያ መሆኗን የፎርብስ ዘገባ ያሳያል፡፡ በናይጀሪያ የመጀመሪያዋ ሴት ቢሊየነር ሆነችው ፎሎሩንሽኮ አላኪጃ በ2ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ዝርዝሩን የተቀላቀለች ሲሆን፣ የአገሯ ልጅ አሊኮ ዳንጎቴም አምና ከነበረበት 20 ያህል ደረጃ በማሻሻል 23ኛ ላይ ተቀምጧል - በ25 ቢሊዮን ዶላር፡፡ ላለፉት አመታት በአፍሪካ አህጉር አንደኛው ቢሊየነር ሆኖ የዘለቀው ዳንጎቴ፣ ዘንድሮም ክብሩን የሚነጥቀው አፍሪካዊ ባለሃብት አልተገኘም፡፡  ናይጀሪያዊቷ ፎሎሩንሽኮ አላኪጃ፣ የአንጎላዋ ኢሳቤል ዶሳንቶስ እና ኦፕራ ዊንፍሬይ በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱ ሶስቱ ብቸኛ ጥቁር ቢሊየነሮች ናቸው፡፡  የኛው ሼክ መሃመድ ሁሴን አል አሙዲ በ15 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር 61ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡

Read 6864 times