Saturday, 08 March 2014 13:07

ያልተዘመረላቸው የአድዋ ጀግኖችና አውደ-ውጊያዎች

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)
  • በችላ ባይነታችን የአድዋ ድል ተረት እንዳይሆን ያሰጋል
  • የእቴጌ ጣይቱ የጦርነት ገድል አለመነገሩ ብዙዎችን አሳዝኗል
  • ለአዲሱ ትውልድ ስለ አድዋ ድል ምን ታሪክ ልናስተላልፍለት ይሆን?

ገሠሦ፣ ምንድብዳብ፣ (በትግርኛ የተቆራረጠ ማለት ነው) ኪዳነ ምህረት ገሠሦ፣ ማርያም ሸዊት፣ ራዕዮ፣ እንዳባገሪማ ገዳም፣ ሶሎዳ፣ … ምንድናቸው ቢባል፣ ስንቶቻችን በትክክል እንመልስ ይሆን? እርግጠኛ ነኝ ከታሪክ ምሁራን በስተቀር፣ ብል ያለማጋነን ብዙዎቻችን አናውቀውም፤ ግን ደግሞ አይፈረድብንም፡፡ ምክንያቱም ስለእነዚህ ስሞች የሚገልጽ አንዳች ምልክት በአካባቢያቸው አልተደረም፡፡ ታሪካቸው በሚዲያ ሲነገርም አይሰማም፡፡ ነገር ግን  አጥንት ተከስክሶና ደም ፈስሶ ከኢትዮጵያዊ ማንነታችን ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ታሪካዊ ትስስር አላቸው፡፡
ከላይ እንደፈተና የዘረዘርኩላችሁ ስሞች የሚገኙት በትግራይ ክልል በአድዋ ከተማ ዙርያ ሲሆኑ ሁሉም የተራራ ስሞች ናቸው፡፡ ተራ ተራሮች ግን አይደሉም-ይለያሉ፡፡ የነፃነትና የድል ተራሮች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ፣ የኩራት ተራሮች ሊባሉ ይችላሉ፡፡  
የአውሮፓ አገራት፣ ከኢትዮጵያና ከላይቤሪያ በስተቀር በርካታ የአፍሪካ አገራትን ወርረው ቅኝ ተገዥ እንዳደረጉት ሁሉ፣ የጣሊያ ወራሪ ፋሺስት ጦርም፣ አልተሳካለትም እንጂ ኢትዮጵያን ወርሮ ለማስገበር ሞክሮ ነበር፡፡ ጀግኖቹ አያት ቅድመአያቶቻችን፤ ወንድ ሴት፣ ወጣት ሽማግሌ ሳይሉ “እምቢኝ ለአገሬ! በሕይወት እያለሁ አገሬን ጠላት አይገዛትም! ..” ብለው፣ ረሃብና ችግር ሳይበግራቸው በዱር በገደሉ ለአምስት ዓመት መሽገው ጠላትን ተፋልመዋል፡፡
የማታ ማታም መጋቢት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ዘመናዊ የጦር መሳሪያ፣ መድፍና መትረዬስ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የጣሊያን ወራሪ ጦር ተጋፍጠው (ያውም በጥቂት ኋላ ቀር ጠመንጃዎች፣ በጦር፣ በጋሻና ጐራዴ) በጀግንነት በመፋለም አጥንታቸውን ከስክሰውና ደማቸውን አፍስስው ነፃ ሀገር፣ ነፃ ኢትዮጵያን ያስረከቡን በእነዚህ ተራሮች ላይ ተዋግተው ነው፡፡
የአድዋ ሰንሰላታማ ተራሮች፣ አገራቸውን የወረረውን የኢጣሊያ ጦር ለመውጋት ከየክልሉ ተጠራርተው መጥተው ጦርነቱ በድል ሲያበቃ፣ እዚያው በቆሙበት የቀሩ ይመስላል፡፡ ታዲያ ምን ያደርጋል! ለወገን ጦር መሸሸጊያና መከታ፣ ለጠላት ጦር አበሳና ፈተና የሆኑት እኒያ የተፈጥሮ ተራሮች እውቅና ተሰጥቷቸው መከበር፣ መዘከርና መወደስ ቢገባቸውም፣ ዞር ብሎ ያያቸው እንኳ የለም፡፡ “የጣሊያን ወራሪ ጦር የተሸፈነበት ስፍራ” የሚል ጠቋሚ ምልክት እንኳ ስለሌለ የዛሬውና መጪው ትውልድ በቃል ከሚተላለፍለት “የአድዋ ጦርነት ድል” የሚል “ታሪክ” በስተቀር ትክክለኛ ስፍራው የት እንደሆነ ለማወቅ ያዳግተዋል፡፡ በዚህ አያያዛችን  ከቀጠለማ የ “አድዋ ድል” ተረት እንዳይሆን ያሰጋል።
እጅግ የሚያሳዝነው ነገር፣ የተፈጥሮ ጀግኖቹ መዘንጋት ብቻ አይደለም፡፡ ከመላ አገሪቱ የተውጣጡ እጅግ በርካታ የነፃነት አርበኞች ውድና ክቡር ሕይወታቸውን ቢሰጡም፣ ነገሬ ብሎ ያስታወሳቸው የለም፡፡ ለምሳሌ ከአድዋ ጦርነት እጅግ አሰቃቂና ከሁለቱም ወገን ብዙ ሺዎች ያለቁበት የምንድብዳብ ውጊያ ዋና ተዋናይ የነበሩት ወጣቱ ጄነራል ፊታውራሪ ገበየሁ ምንም የሠሩት ገድል እንዳልተነገረላቸው የእንዳአምባ ትራቭል ኤጀንሲ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሳየ ታረቀኝ ተናግረዋል፡፡ “ደረታቸውን ሰጥተው የጠላትን ጦር መግቢያ መውጪያ በማሳጣት  ሲተገትጉ፣ በጥይት ተመትተው ሞቱና እዚያው ምንድብዳብ ተቀበሩ፡፡ በመቃብራቸው ላይ ምልክት ስላልተደረገ በትክክል የት እንደተቀበሩ እንኳ አይታወቅም፤ በተቃራኒው ግን ጣሊያኖች ጀኔራል ዳቦርሜዳ ሞቶ በተቀበረበት ሥፍራ በድንጋይ ላይ ስሙን ጽፈው ስለተው፣ አሁን ድረስ ታሪኩ ይታወሳል” ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ጦር አሰላለፍ በአራት አቅጣጫ እንደነበር አቶ አሳየ ይናገራል፡፡ ሶሎዳ ተራራ ስር፣ ከሸዋ የመጡ 400 የኦሮሞ ፈረሰኞች መሽገው ነበር፡፡ 2ኛው ከአድዋ መውጫ፣ 3ኛው የራስ አሉላና የራስ መኮንን ጦር፣ እምባ መላክ ወይም ውጊያው በተካሄደበት ኪዳነምህረት ገሠሦ፣ በእቴጌ ጣይቱ የሚመራው 4ኛ ጦር፣ ከኪዳነምህረት ገሠሦ ጀርባና ጐን መሽጐ ነበር፡፡ የኢጣሊያም ጦር በአራት አቅጣጫ ነው የመጣው፡፡ በአራት አቅጣጫ የመጣው ባሻ አውአሎምና ሌሎች የስለላ (እንተለጀንስ) ሰዎች አሳስተው በነገሯቸው መሠረት እንደሆነ ይነገራል፡፡
ባሻ አውአሎም ሐረጐት ካልተነገረላቸው የአድዋ ጀግኖች አንዱ ናቸው፡፡ ባሻ አውአሎም በኤርትራና በትግራይ የሚመላለሱ ነጋዴ ነበሩ፡፡ ቀደም ሲል ራስ አሉላ ኢጣሊያኖችን እየሰለሉ እንዲግሯቸው፣ የኢትዮጵያን ጦር ምስጢር ደግሞ አሳስተው እንዲጠቁሟቸው ከባሻ አውአሎም ጋር ተስማምተው ነበር፡፡ በዚያው መሠረት፣ ባሻ የኢትዮጵያ ጦር ከኪዳነምህረት ገሠሦ ጀርባ ባለ ተራራ ላይ መመሸጉን ለጣሊያኖቹ ይነግራሉ፡፡ ስለዚህ ጀኔራል አርሞንዲ ጦሩን እየመራ ኪዳነምህረት ገሠሦ ተራራ ላይ ይመሽጋል፡፡ በዚህ ጊዜ እነ ራስ አሉላ በጀርባው ቆርጠው ገብተው መድፍ ሲተኩሱ ከአድዋ 10 ኪ.ሜ ወደ ኋላ መሆኑን አርሞንዲ አያውቅም ነበር፡፡ ስለዚህ፣ ለተቀረው ጦር “ገብቻለሁ” ሲል በተመሳሳይ ሰዓት ከሦስቱም አቅጣጫ ተኩስ ተከፈተበት፡፡ ጄነራል አርሞንዲ የሞተበት ውጊያ በሶስት አቅጣጫ የሚከፈል ነው፡- ኪዳነምህረት ገሠሦ፣ ምንድብብና ማርያም ሸዊት ነው፡፡ (የቦታ ስምና አቅጣጫ ስገልጽ ከተሳሳትኩ ለመታረም ዝግጁ ነኝ፡፡) ጄነራል ዳቦርሜዳ የሞተው ማርያም ሸዊቶ በተባለው ተራራ ላይ ነው፡፡ ጄነራል ባራቶሪ ደግሞ የተገደለው ራዕዮ ተራራ ላይ ነው፡፡ ጄነራል አልባርቶኒ ያመለጠው ደግሞ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ ገብቶ ተደብቆ ነው። የኢትዮጵያ ወታደሮች ከቤተክርስቲያኑ አውጥተው ያልገደሉት፣ ለቤተክርስቲያን ክብር ብለው እንደነበር ይነገራል፡፡ ጄነራል ኤሌናም በጦርነቱ ተገድሏል፡፡
ይህን በአንድ ጊዜ ሦስት የወራሪው ጄኔራሎች የተገደሉበትን፣ አንዱ ጀነራል የተማረከበትን ጦርነት ነው እኛ ኢትዮጵያውያን ችላ ብለን የዘነጋነው፡፡ የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝቦችም ጭምር ነው፡፡ እስከ አፍንጫው ድረስ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀና የማይሸነፍ የሚመስለው የአውሮፓ ቅኝ ገዥ በጦርና በጐራዴ የተሸነፈበትና የተዋረደበት በመሆኑ ክብር ተሰጥቶት ለቀጣዩ ትውልድ ታሪኩ በቅጡ መሸጋገር ነበረበት፡፡ ግን ምን ያደርጋል በእጅ ያለ ወርቅ ሆነ እንጂ!
ዘንድሮ በአድዋ ከተማ የተከበረው የድል በዓል እጅግ ደማቅ ነበር፡፡ ያደመቁት ደግሞ ከአዲስ አበባ ከእቴጌ ጣይቱ ሆቴል ተነስተው 1000 ኪ.ሜ 43 ቀናት በእግራቸው ተጉዘው አድዋ ከተማ የደረሱት አምስት ተጓዦች ናቸው፡፡
ተጓዦቹ ብርሃኔ ንጉሤ፣ መሐመድ ካሣ፣ ኤርምያስ ዓለሙ፣ ሙሉጌታ መገርሳና (ደብሊው) ዓለምዘውድ ካሳሁን በአድዋ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ ሠራዊት የተጓዘባቸውን መንገዶች ተከትለውና ታሪካዊ ስፍራዎችን ጎብኝተው፣ ባለፈው እሁድ በ118ኛ የአድዋ ድል በዓል መታሰቢያ ዕለት በሶሎዳ ተራራ አናት ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አውለብልበው በዓሉ ወደሚከበርበት የተራራው ግርጌ ሲወርዱ “ሰልፍ ሜዳ” ተሰልፎ ይጠባበቅ የነበረው የአድዋ ከተማና አካባቢው ህዝብ፣ አባት አርበኞች፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ተማሪዎች በከፍተኛ እልልታና ጭብጨባ ተቀብለዋቸዋል፡፡ ተራራው አናት ላይ ወጥተው የተቀበሏቸውም ብዙዎች ናቸው፡፡
የዚህ ጉዞ ዓላማ ምንድነው? ሐሳቡስ እንዴት መጣ? … አንገታችንን ቀና አድርገን፣ ደረታችንን ነፍተንና አፋችንን ሞልተን እንድንናገር ምክንያት ለሆነን ለአድዋ ድል ክብርና ዋጋ የሚሰጡ ሰዎች አሉ። አባቶቻችን ባዶ እግራቸውን ተጉዘው እንዴት ነው ይህን ክብር ያጎናፀፉን? ድካማቸው ምን ይመስላል? እንዴትስ ይገለፃል? .. የሚሉ ጉጉ የአዲስ ትውልድ አባላትም አይጠፉም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሀሳብ ካላቸው ሰዎች መካከል አንዱ ሙሉጌታ መገርሳ (ደብሊው) ነው፡፡ ወደ አድዋ ደርሶ መልስ ጉዞ በእግሩ በማድረግ የአባቶቻችንን ድካምና እንግልት በተግባር ለማየት ወስኖ ነበር፡፡
ሙሉጌታ የፊልም ባለሙያ በመሆኑ የብርሃኔ ንጉሤ አጭር ፊልም ቀረፃ እንዳለ ይነገረዋል፡፡ “አሁን አልችልም፤ አድዋ እሄዳለሁ” ይላቸዋል፡፡ ይህንን ሐሳብ የሰሙት ጉዞውን አብረውት ለማድረግ ይስማሙና አምስት ሆነው፣ ቀን ቆርጠው፣ የአድዋ ድል በዓል በሚከበርበት ዕለት ከስፍራው ለመድረስ ጉዞ ጀመሩ፡፡ ይኼው ነው መነሻው፡፡
ተጓዦቹ በጉዞአቸው ወቅት የኢትዮጵያ ጦር ከተጓዘበት መንገድ ወጣ እያሉ ታሪካዊ ቦታዎችን አይተዋል፣ አስደሳችና አሳዛኝ ነገሮች እንዳጋጠማቸውም ይናገራሉ፡፡ ተጓዦቹ በጣም ካዘኑባቸው ነገሮች አንዱ ለአድዋ ጦርነትና ድል መነሻ የሆነው የውጫሌ ውል የተፈረመበት “ይስማ ንጉሥ” የተባለ ስፍራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “ይስማ ንጉስ” የተባለው ስፍራ ባይኖር ኖሮ የአድዋ ጦርነት አይደረግም ነበር፤ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አፍሪካውያንና የዓለም ጥቁር ህዝቦች የሚኮሩበት የአድዋ ድልም አይኖርም ነበር፡፡ በድሉ ቦታ ምንም መታሰቢያ እንደሌለው ሁሉ በይስማ ንጉስም እቴጌ ከተቀመጡበት ድንጋይ በስተቀር ምንም ነገር ባለመሰራቱ በጣም አዝነናል” ብሏል ጋዜጠኛና የፊልም ባለሙያው ብርሃኔ ንጉሤ፡፡ ለመሆኑ ይስማ ንጉሥን ስንቶቻችን እናውቃለን? የቱሪስት መስህብስ የሚሆነው መች ይሆን?
ሌላው ተጓዦቹ ያዘኑበት ነገር በአድዋ ጦርነት ትልቅ ሚና ተጫውተው ብዙም ያልተወራላቸው ጀግኖች መኖራቸው ነው፡፡ ከእነዚህ ጀግኖች አንዷ እቴጌ ጣይቱ ብጡል ናቸው፡፡ እቴጌ የውጫሌን ውል ሲቃወሙ፣ “እኔ ሴት ነኝ፤ ጦርነት አልወድም፡፡ ግን እንደዚህ ዓይነት ውል ከምቀበል ሞትን (ጦርነትን) እመርጣለሁ” በማለት አፄ ምኒልክን ለጦርነት አነሳስተው በጦርነቱ ቦታ ስለፈጸሟቸው በርካታ ገድሎች ያለመነገሩ አሳዝኗቸዋል፡፡ ሴቶች በጦርነቱ ላይ የነበራቸው ሚና በጣም ከፍተኛ ነበር፡፡ ቀኑን ሙሉ ዕቃ ተሸክመው ይጓዛሉ፤ የወንዶቹ ጉዞ ሲያበቃ የሴቶቹ አያበቃም፤ እራት ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል። ይህ ብቻም አይደለም፤ ግማሾቹ ሚስቶች ናቸው፡፡ ሌሊት ተነስተው ቁርስ ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስለዚህ እቴጌ ጣይቱን ማክበርና ማድነቅ በዚያ ጦርነት ላይ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱትን ሴቶች ሁሉ ማክበርና ማድነቅ ስለሚሆን እቴጌይቱን የሚዘክር ነገር መሰራት አለበት ብለዋል፡፡
ብዙም ያልተነገረላቸው ሌላው የአድዋ ጀግና ባሻ አውአሎም ሐረጎት ናቸው፡፡ የእሳቸው ሚና ባይኖር ኖሮ የአድዋ ጦርነት ምን ዓይነት መልክ ይኖረው እንደነበር መገመት አይቻልም፡፡ እሳቸውም እንደ እቴጌ ሁሉ ምንም አልተነገረላቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ጦርነቱን በድል እንዲያጠናቅቅ ስለተጫወቱት ሚና ወጣቱ ትውልድ ማወቅ አለበት፡፡ ባሻ አውአሎም ትልቅ ታሪክ እያላቸው የተረሱ ጀግና ስለሆኑ ስለእሳቸው በሚገባ መሠራት እንዳለበት መታዘባቸውን ተጓዦቹ ተናግረዋል፡፡
የአድዋ ድል ተገቢውን ክብር እንዳላገኘም ይናገራሉ፡፡ በተለይ ሙሉጌታ መገርሳ አድዋ ድል በፍፁም ተገቢውን ክብር እንዳላገኘ ሲናገር “ብራዚል ከእግር ኳስ ሌላ በሳንባ ዳንስ (ካርኒቫል) ፌስቲቫል ትታወቃለች፤ የዓለም ህዝቦችም ሳንባ ዳንስን ለማየት ወደዚያ ይሄዳሉ፡፡ ስፔይን ደግሞ በቲማቲም የመደባደብ ባህል፣ ከኮርማ ጋር የመሯሯጥ ዓመታዊ ካርኒቫል ስላላት የዓለም ታዋቂ ሚዲያዎች ሽፋን ይሰጡታል፡፡ እዚህ ግን ለዓለም ጥቁር ህዝቦች ትልቅ ኩራት የሆነው የነፃነት መካ መዲና፣ ክብርና የሚገባውን ዋጋ ስላልሰጠነው ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሽፋን አልሰጡትም፡፡
ይህ የነፃነት በዓል ክብርና ትኩረት አግኝቶ ቢሆን ኖሮ ከሳንባ ዳንስና ከቲማቲም መደባደብ የበለጠ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ሽፋን ያገኝ ነበር፡፡ የአድዋ ሰንሰለታማ ተራሮችም የማይደፈር የሚመስለው የቅኝ ገዥ ኃይል አከርካሪው የተሰበረበት ዓውደ ውጊያ በመሆናቸው፤ ኢትዮጵያውያንና አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆኑ፣ የዓለም ነፃነት ወዳድ ህዝቦች ሁሉ እንደ መካመዲና ሊሳለሙትና ሊያዩት ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን “ባለቤቱ ያቃለለውን አሞሌ …” እንደሚባለው ሆነና የሚገባውን ክብርና ትኩረት አጣ” ብሏል፡፡
የአድዋ ጉዞ ይቀጥላል ወይስ በዚሁ ያበቃል? በቀጣይስ የአድዋ ድል ተገቢውን ክብርና ትኩረት እንዲያገኝ ምን ይደረጋል?... የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው የአድዋ ተጓዦች መልስ ሰጥተዋል፡፡   
ተጓዥና የጉዞሰው አስተባባሪ በመሆን ሲሰራ የነበረው ያሬድ ሹመቴ ከአሁን በኋላ የአድዋ ጉዞ በየዓመቱ የሚቀጥል መሆኑን ተናግሯል፡፡ ቀጣዩ ጉዞ የሚቀራረቡ ጓደኛማቾች ሚያደርጉት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን፣ አፍሪካውያን፣ ጥቁርና ነጭ የዓለም ነፃነት ወዳድ ህዝቦች፣የቻሉት የአድዋ ጀግኖች ባለፉት መንገድ በመጓዝ፣ ያልቻሉት ደግሞ በተለያዩ መጓጓዣዎች አድዋ ደርሰው ውጊያው በተካሄደባቸው ተራሮች ተገኝተው ድሉን እንደሚያከብሩት ያሬድ ተናግሯል፡፡
ጉዞውን ለማስቀጠል፣ አቅም ጊዜና ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እኛ ከዚህ ስንመለስ ወደየግል ስራችን እንመለሳለን፡፡ ስለዚህ ፕሮጀክት ተቀርፆ ጉዞውን የሚያስተባብርና ተግባራዊ የሚያደርግ አንድ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡
ኮሚቴው ሙሉ ጊዜያቸውን እዚያ ላይ አድርገው የሚሰሩ ሰራተኞች ቀጥሮ ያሰራል። ዓለም አቀፍ እውቀትና የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ ለማድረግ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ይጠይቃል፡፡ ዘንድሮም ከተለያዩ ሚዲያዎች የተውጣጡ ጋዜጠኞች በስፍራው ተገኝተው እንዲዘግቡ የተደረገው አንድ ባለሀብት ስፖንሰር በማድረጋቸው ነው፡፡ ባለሀብቱ አቶ ዳዊት ገ/እግዚአብሔር ይባላሉ፡፡ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ፣ ዓለም አቀፍ እውቅናና የሚዲያ ሽፋን ለማግኘት ከፍተኛ ድካም ብዙ ካፒታልና ጥረት የሚጠይቅ ነው፡፡ ፕሮጀክቱን ለመጀመር አቶ ዳዊት ለጊዜው አንድ ሚሊዮን ብር ለመስጠት ቃል በመግባታቸው ለአገራቸው ሉዓላዊነት መከበር ሲሉ ደማቸውን ባፈሰሱ፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ህይወታቸውን መስዋዕት ባደረጉ የአድዋ ጀግኖች በመላው ዓለም ነፃነት ወዳድ ህዝቦች ስም እናመሰግናቸዋለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለዚህ ክቡር ዓላማ መላው ህዝብና ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን ብሏል አስተባባሪው ያሬድ ሹመቴ፡፡
አድዋ ላንድ ማርክ የተባለ ድርጅት ደግሞ 10 በ15 በሆነ ሰሌዳ ላይ በአማርኛና በእንግሊዝኛ “አድዋ” የሚለውን ቃል በሰሎዳ ተራራ ላይ ጽፎ ለመስቀል ቦታ መረከቡን አስታውቋል፡፡
ከመንግሥትም ሆነ ከአገር ወዳድ ዜጐች ብዙ ይጠበቃል፡፡ ምንስ ቢሆን ህይወታቸውን ሰውተው ነፃ አገር ያስረከቡን ጀግኖች ታሪክ መዘከርና ለአዲሱ ትውልድ ሃቁን ማስተላለፍ ያቅተናል እንዴ? ጐበዝ! ያልተዘመረላቸውን የአድዋ አርበኞችን እንዘምርላቸው!! አውደ ውጊያዎቹንም ስፍራ እንወቃቸው!!  

Read 2647 times