Saturday, 08 March 2014 13:02

ግዮን (አባይ) በፍልስፍና መነፅር

Written by  ደረጀ ኅብስቱ derejehibistu@jmail.com
Rate this item
(6 votes)

     ቅድመ ሶቅራጥስ ከነበሩ የግሪክ ፈላስፎች መካከል ታለስ የተባለው ፈላስፋ “የህይወት ምንጭ ዋናው አሃድ ውሃ ነው” ይላል፡፡ በእርግጥም ውሃ የህይወት መሰረት ነው፡፡ ህይወት ስንል ግን ሥጋዊ አካላዊውን ህይወትና መንፈሳዊውን ህይወት ማለታችን ነው፡፡ ሰው የምንለው ፍጡር የሥጋና የመንፈስ ውህድ ነው እና ሥጋዊ ማንነቱን ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ህልውነቱን ጭምር ወስደን ለዚህ ጽሑፍ እንዲስማማን እናድርግ፡፡ የፍልስፍና፣ የሃይማኖት እና የተረት አስረጂዎችን በመጠቀም፡፡
ግዮን በጥንታዊያን ስልጡኖች፣ በታላቁ መፅሃፍና በአገር ቤት አፈ ታሪኮች ታላቁ መንፈሳዊ እሴት የሚሰጠው ወንዛችን ነው፡፡ ግዮን ከአፈጣጠሩ አፀደ ነፍስ የሆነችው ገነትን ከሚያጠጡት አራቱ ወንዞች አንዱ ነው/ ኤፌሶን፣ ጤግሮስ፣ ኤፍራጥስ እና ግዮንን አስታውሱ፡፡ ለሥጋዊ ህይወት አስፈላጊ ከሆኑት ውሃዎችም በላይ የነፍስና መንፈስ ማረፊያ የሆነቸውን ገነትን የሚያለመልም ነው። ለወንዝ ወንዝማ ሚሲሲፒም፣ ቮልጋም፣ ፊያም ወንዝ ናቸው፤ ግና ነፍስና ገነትን ማጠጣት ከቶ አይቻላቸውም፡፡ ምክንያቱም ግዮን አይደሉማ! ግዮን እኮ ከዕጸ ህይወት ሥር የሚመነጭ ወንዝ ነው/ባህሪ ሐሳብን ይመልከቱ፡፡ ዕጸ ህይወት ደግሞ ዘለዓለማዊ ህይወትን የምታስገኝ ፍሬ የምታፈራ ዛፍ ናት፡፡
ኢትዮጵያ በራሷም ሆነ በሌሎች አገሮች አፈታሪክ፣ መለኮትና የደቂቅ መለኮት መኖሪያ መሆንዋ የተመሰከረ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን የአማልክት ልጆች መሆናቸውን፣ ኢትዮጵያም የአማልክት መኖሪያ ምድር መሆንዋን ብዙዎች ጥንታዊያን ማህበረሰቦች አጥብቀው ይስማማሉ። ሌሎችም ባይመሰክሩ እንኳ አይክዱም/የግሪክና የግብጽ ጥንታዊ ጽሁፎችን ይመልከቱ/፡፡ የአማልክት መኖሪያ ስንል ምን ማለታችም እንደሆነ ለማሳየት እንዲረዳን የግሪኩን ፈላስፋ አፍላጦንን በአስረጅነት እንጠቀም፡፡ The Republic በሚለው ድርሳኑ ውስጥ ነገረ ህላዌን (ዲበ አካል/metaphysics) ሲያብራራ፣ ሁለት ዓለማት መኖራቸውን ማለትም የመሆን ዓለም  (ዓለመ ህላዌ/world of being) እና ዓለመ አምሳያ (world of becoming) ብሎ ከፍሎ ይገልጻቸዋል፡፡
ሀ) ዓለመ ህላዌ (የመሆን ዓለም/world of being) እውቀት፣ እውነት፣ ፍትህ፣ ውበት፣ መልካምነት ወዘተ አማናዊ፣ ደገኛ፣ አልፋ ኦሜጋ፣ ቀዋሚ ባህሪያት ያሉዋቸው ነገሮች የሚኖሩባት ሲሆን በዓለመ ህላዌ መመሳሰል፣ ቅዠት፣ ጥላ፣ ብዥታ፣ ወዘተ የሚባል ነገር የለም፤ ሁሉም ነገር የምር ነው። የምር በቃ፤ በራሱ እርግጥ የሆነ ነው፡፡ እውነትና እውቀት መኖሪያቸው በዚህ ነው፡፡ የማይለዋወጥ፣ ዘመን የማይሽረው፣ ጊዜና አውድ የማይቃወመው እውነት መገኛው በዓለመ ህላዌ ነው፡፡ በዚህ መሰረት በጸና እውነት ላይ የሚመሰረት እውቀትም እርግጠኛነቱ የታመነ ዘለዓለማዊ፣ ምክንያታዊ፣ ጽኑ እና በሁሉም አመክንዮ ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ ይህ የጠቢባን ልቦና ምጥቀት እና የጥበባቸው ረቂቅነት የሚመረምረው እውነት ነው፤ ለሚተጉት ለሚሹት አስመሳይነት ቦታ የላቸውም፤ ቅዠትና ብዥታም የህይወት ጎዳናቸውን አያስተጓጉለውም፡፡
ትክክለኞቹን ዋነኞቹን የእውቀት፣ እውነት፣ ፍትህ፣ ውበት፣ መልካምነት ወዘተ ምንጮቹን ያውቃል፤ የዓለመ ህላዌ ሰው፡፡ በምክንያት በምርምር፣ በአልቦ መድሎ እና በአልቦ ስሜት ብቻ ይመረምራል አለመ ህላዌ፡፡ ዛሬ ምን እየተካሄደ እንዳለና ነገ ምን ሊመጣ እንደሚችል በእርግጠኝነት፣ በጽኑ እምነት፣ በጠራ እውነት ላይ ተመስርተው ይታወቃሉ፤ ምክንያቱም በዓለመ ህላዌ ያሉት ነገሮች ሁሉ ዘለዓለማዊያን ናቸው፡፡ ይህ ዓለም (ዓለመ ህላዌ በሌላ ታላቅ ፈላስፋ በቅዱስ አውግስጦስ/St. Augustine ደግሞ ሃገረ ኢየሩሳሌም/the city of Jerusalem ይባላል፡፡)
ለ) ዓለመ አምሳያ/ World of Becoming/ ይህ ደግሞ የዓለመ ህላዌ የእውቀት፣ እውነት፣ ፍትህ፣ ውበት፣ መልካምነት ወዘተ ቅጅዎች፣ ጥላ፣ ግልባጭ፣ አምሳያዎች መኖሪያ እንደ ማለት ነው፡፡ የአምሳያ ዓለም እርግጠኝነት አያውቅም፣ እራስን የመሆን ነገር የለውም፣ ዘለዓለማዊነት አልሰረጸውም፣ አመክንዮ አይዛመደውም፣ እውቀት አይዋሃደውም፣ ከእውቀት እጅግ የራቀ ነው፡፡ ንፋስ፣ ወዠቦ፣ ሞገድ የሚያነዋውጠው ዓለም ነው ዓለመ አምሳያ፡፡ መርጋት፣ መቆም፣ ሚዛናዊነት ባህሪያቱ አይደለም፡፡ ሁሉም ነገር ተለዋዋጭ ነው፤ የአፍታ ህላዌ የሚያባክነው ቀልበ ቢስ፣ ከጥላው የተጣላ ዓለም ነው፤ ዓለመ ህላዌ፡፡ መታመንን፣ ማስረገጥን፣ ቋሚነትን፣ ህልውነትን ማሳየት የማይቻለው ዐውዳዊና አስመሳይ ዓለም ነው፤ እውቀትና እውነትን ዓለመ አምሳያ ውስጥ ፈልጎ ማግኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ሁሉም ነገር በድለላና በሽንገላ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው፡፡ ፈላስፋው ቅዱስ አውግስጦስ ሃገረ አቴና/ the city of Athens/ ይለዋል፤ አለመ አምሳያን፡፡ የአለመ አምሳያ እውነት አማናዊ አይደለም፤ ጥላ ነው፤ ብርሃናዊ አይደለም ብዥታ ነው፤ ዘለዓለማዊ አይደለም ጊዜያዊ ነው፤ መልስ የሚሰጥ አይደለም የሚሸነግል ነው፡፡ በጥበብ በምርምር፣ በአመክንዮ ሳይሆን በስንፍና በቧልት፣ በሰበብ ላይ የተመሰረተና የሚመራ፣ በጠቅላላው ስሜት እና ወኔ የሚያደላበት ዓለም ነው፤ ዓለመ አምሳያ፡፡ ለዕለት፣ ለስሜት፣ ለገለፍተኝነትና ለደምፍላት መገዛት ዋና መገለጫ ባህሪው ነው፤ ዓለመ አምሳያ፡፡
ጉዳዩን የበለጠ ግልጽ ለማድረግ አፍላጦን የሁለቱን ዓለማት ልዩነት ለማስገንዘብ የተጠቀመበትን ታሪክ እዚህ ጋር ብንጠቅሰው መልካም ይሆናል፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ በአንድ ዋሻ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ነበሩ፤ ወደ ኋላና ወደ ጎን ማየት እንዳይችሉ በሰንሰለት ታስረዋል፤ ማየት የሚችሉት ፊት ለፊት ብቻ ነው፡፡ ከፊት ለፊታቸው ባለው ዋሻው ግድግዳ ላይ የሚታየው የጥላ ቅርጻ ቅርጾች ናቸው፡፡ ከሰዎቹ ጀርባ ባለው የዋሻው ቀዳዳ በሚገባ ጥቂት ብርሃን አማካኝነት የሚፈጠሩ የጥላ ቅርጻ ቅርጾች፣ ከፊት ለፊታቸው ባለው የዋሻው ግድግዳ ላይ ለሰዎቹ ይታያቸዋል፡፡ በዋሻው ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚያውቁት እውነት እና እውቀት ቢኖር ይሄው ለዘመናት በዋሻው ግድግዳ ላይ ሲፈራረቅ የሚያዩት ጥላ ነው፡፡ ዋሻው ውስጥ ብዙ አመት ያሳለፉት እና ጥላዎችን የሚመራመሩት የጥላዎችን ዑደታዊ እንቅስቃሴ፤ ንግስናቸው፣ ጭፈራቸው ነው (ጎጃሞች ሰተት ብለው ቆመው የሚንቀጠቀጡት እስክስታ ከዓባይ ፏፏቴ የተቀዳ መሆኑን ልብ ይሏል) በአጠቃላይ ግዮን ለኢትዮጵያዊያን ማንነት እና ባህል ሆኗቸዋል፡፡ ተረቶች እና ምሳሌዎችንም ሳንረሳ (ዓባይ አረጀ አሉ ሽበት ቀላቀለ፤ አንድ ሰው ብቻውን ይሻገር ጀመረ)፡፡ ሌላው ይቅርና የዓባይ አካባቢ ሽፍታና የሌላው አካባቢ ሽፍታ ያላቸው ግርማ መደንግጽ እጅግ የተለያየ ነው፡፡
ግዮን ለኢትዮጵያዊያን አድባር፤ የስልጣኔ ምንጭ፤ የልማት ልዑክ ነው፡፡ ግዮን የእህል ውሃ መወሰኛ፤ የኮከብ መቁጠሪያ፤ መንገድ መሪ፤ ዘመን ቀያሪ ቀመራቸው ነው፡፡ የጥም መቁረጫ፣ የሃሳብ መወጠኛ፣ የአልገዛም ባይነት፣ የጀግንነት የታላቅነት ግርማ ነው፤ ለኢትዮጵያዊያን፡፡ የኢትዮጵያዊ ልቡ እንደ ግብረ ጉንዳን ታታሪ፣ እንደ አንበሳ ደፋሪና እንደ ጠቢብ ተመራማሪ ነው፡፡ ጉልበቱን ከክህሎቱ አጣምሮ ለዘላለም ምስክርነት የተከላቸው ውቅርና ትክል ድንጋዮች የታታሪነቱ ምስክር ናቸው (አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጢያ ወዘተን ያስታውሱ)፡፡ ጦሩን ሰብቆ ጋሻውን ነጥቆ አፈር ከድሜ ያበላቸው ጠላቶቹ ለኢትዮጵያዊ ደፋር ልቦና ምስክር ናቸው (ግብጾችና ጣልያንን ልብ ይሏል)፡፡ ፍትህ አዋቂነቱን፣ ተመራማሪነቱን፣ የጽድቅ ፍቅሩን ለማስረገጥ ደግሞ ወደየ ቤተ አምልኳችን ብቅ ማለት ነው፡፡ ዋቂ ፈታ፣ መስጅድ፣ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ሲመሰክሩለት የኖሩት የጠቢባን ልቦና የሚያፈልቀውን እውቀት ነው፡፡
ግዮን እና ኢትዮጵያ ታዲያ በዓለመ ህላዌ ያሉ ምጡቃን ረቂቃን እንጅ፤ በግዘፈ አካል በሚኖርበት ዓለመ አምሳያ ውስጥ ብቻ ያሉ አይደሉም፡፡ ግዮናዊያን ቋንቋቸው ግዕዝ ነው። ረቂቅነታቸውን መግለጫ፣ ህልውነታቸውን ማወጃ፣ ሰማያዊነታቸውን መመስከሪያ መሳሪያቸው ግዕዝ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊና ግዮን መግባቢያቸው፣ ነገዳቸው፣ ብሔራቸው ግዕዝ ነው፤ ምክንያቱም ግዕዝ እንደ ኢትዮጵያና ግዮን ሁሉ ጥንታዊ ነውና፡፡ ኢትዮጵያዊና ግዮን ነፍስና ስጋቸው የሚጣመረው በግዕዝ ነው፡፡ ኢትዮጵዊ እና ግዮን በሁለቱም ዓለማት ህልው የሚሆኑት በግዕዝ ነው፡፡ ኢትዮጵያን እና ግዮንን በዓለመ አምሳያና በዓለመ ህላዌ ለመረዳት የግዕዝ መሰላልን መጠቀም ግድ ይላል፤ በግዕዝ መሰላል ከዋሻው (ጎጥ፣ ቀበሌ፣ ጎሳ፣ ቅራቅንቦ) ሰንሰለቱን በጣጥሶ ሽቅብ ወደ ጸሐይ (ወደ ሰውነት፣ ወደ ንጽህና) ማረግ ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያዊ፤ ታታሪ ደፋሪና ተመራማሪ ልቦናውን በተዋህዶ አንግቦ አንገቱን ቀና ማድረግ ይገባዋል፡፡ ግዮንን በሰቂለ ህሊና፣ በቁመተ አካል ነው መመርመር ያለብን። ስንቀመጥ ነው ሁሉም ነገር ትልቅ መስሎ የሚታየን፡፡ ስንቆም ስንመረምረው እንበልጣለን እንጅ አናንስም፡፡ የተቀመጣችሁ ተነሱ! ወደ ፀሐይ ተመልከቱ!!

Read 3856 times