Saturday, 08 March 2014 12:58

ኢንተርቪው ከዶክተር ሙሉጌታ በቀለ ጋር

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

   የአርሲ ጉዞዬ አስደናቂ ማስታወሻ

“በል እንዳትቀር እፈልግሃለሁ አልኩት፡፡ ትንሽ ቆይቶ ምልክት አደረገልኝ፤ ሞባይሌ ላይ። ደወልኩለት፡፡ ‘አንድ ልነግርህ ፈልጌ የረሳሁት ነገር አለ’ አለ፡፡ ያ ታጣቂ ገበሬኮ ራሱ መጥቶ - ያኔ ያልኳችሁ ስህተት ነው፤ የመጀመሪያው ቦታ ነው ትክክል ብሎ ነገረኝ- አለ … Can you imagine?” (አይገርምህም? እንደማለት) አለ ዶ/ር በመደመም፡፡
“That’s how the muse works! ውቃቢ ሲፈቅድ እንዲህ ነው አየህ!” እንቅልፍ የነሳው ነገር ነበረ ማለት ነው ታጣቂውን፡፡ “አዎ በስህተት ነው - እኔ ምን ሆኜ እንደሆን አላውቅም፤ መጀመሪያ በትክክል ነበርኮ የተናገርኩት’ አለ፤ አለኝ፡፡” “ታጣቂውም Re-affirm አረገ (ዳግመኛ አረጋገጠ) … ይሄ ምን ማለት ነው … ከ38 ዓመት በኋላ … በየጭንቅላቱ ውስጥ የሚሄድ ነገር አለ …”
“Guilt ም (የጥፋተኝነት ስሜት) አለ፤ ጭንቀትም አለ … ምንም ዓይነት ነገር ሊኖር ይችላል … አንድ ወዳጄ ከርቸሌ የነበረ ወዳጄ (ዘመዴም ነው) የአራት ኪሎ አካባቢ ሰው ነው-በዱሮው መንፈስ … አስከሬን እየሸኘን ሳለ ቅዳሜ ለት ቴክስት ልኬለት ነበር- ‘በጥምቀተ-ባህርም ታቦት ሲሸኝ እንዲህ በህዝብ አይጥለቀለቅም’ ብዬ፡፡ እሱ ምን ብሎ መለሰ … “Take photos of the guilt-ridden offsprings of the killers” …
(በወንጀለኝነት ስሜት የሚናወጡትን ገዳዮች ልጅ-ልጆች ፎቶ አንሣ-እንደማለት ነው)
እንግዲህ ሁሉም በየፊናው አዕምሮው ውስጥ የቀረ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ የእኛ ሰዎች እንዲህ ማሰባቸው አይገርምም! በኋላም ከዚህ ዘመዴ ጋር ስናወራ … “የላኩልህን ሚሴጅ ለሙሉጌታ አነበብክለት ወይ?” ብሎኝ ነበር፡፡ “እንዴት ብዬ ዶ/ር ሙሉጌታኮ በወፈ-ሰማይ ህዝብ ተከቦ ነበር” ብዬዋለሁ፡፡ ዞሮ ዞሮ ያው መልዕክቱን አሁን አድርሻለሁ” አልኩት፡፡ ተሳሳቅን፡፡ …
ወደ ሳጉሬ ስንገባ ፈረሰኞቹ በዛ ግርማ-ሞገስ ባለው አጀብ ሲቀበሉን the grandiosity of the moment (የዚያች ቅፅበት ድምቀት-ከግዝፈት) መግለፅ ከምችለው በላይ ነበረ! ለዚህ ነው ቴክስት የላኩለት፡፡ ቀረርቶ፣ ሽለላ፣ ለቅሶ … ድብልቅልቅ ወኔና ዕንባ፤ ከ38 ዓመት በኋላ! በጣም ስሜቴን አጥለቅልቆት ነበር! ማመን አልቻልኩም - ሙሉ ከተማ ሲንቀሳቀስ ማየት … ሲጐርፍ ሲሳብ ሲሰበሰብ፤ በአንድ አይነት የኮቴ-ቅኝት ሲፈስ መመስከር …
“አዎ ተቀነባብሮልናል፡፡ እኛ ከፍቅረማርያም ጋር ያሰብነው አባቴ ከሚካኤል ወደ ሥላሴ ይሂዱና በሰላም ይረፉ ብለን ነው፡፡ ነገሩ እንዴት ነበር መሰለህ? ክፍሌ ዘመድ ወዳጁን ሁሉ፣ በታህሣሥ 26 መሆኑ ነው፤ ሰበሰበና “እንዲህ ተገኝቷል ምን እናድርግ?” አለ፡፡ መቼ ነው ያሰባችሁት?” ሲሉት፤ የካቲት ውስጥ (ጊዜ እንዳንፈጅ ነው ብሏቸዋል)። “የት እንዲቀበር ነው የምትፈልጉት?” ሲሉት እዚያው ሥላሴ ግቢ ውስጥ አላቸው፡፡ “ይሄኮ የእናንተ፣ የአባታችሁ ቀብር ጉዳይ ብቻኮ አይደለም፡፡ የእኛንም ሰዎች ነው የምንቀብረው …”
እኛ እንግዲህ ስላሴ የክፍሌ እናት የተቀበሩበት ለመቅበር ነበር ያሰብነው … ‘በጭራሽ እኛኮ ሙስሊሞች ነን አብዛኛዎቻችን፡፡ … እዛ ቀብራችሁ እንዴት ብሎ ሌላው ዘመድ አዝማድ ይይ? አይሆንም-ፊት ለፊት፤ ሁሉም ሊያይ የሚገባበት ቦታ ነው መቀበር ያለባቸው! የእናንተ ሰው ብቻ ሳይሆን፤ ሌሎችንም ጭምር ያን ጊዜ ያለቁትን ለማስታወስ ነው የምንፈልገው - ብለው አሻፈረኝ አሉ -የአገር ሽማግሌዎቹ! … እኔም ፍቅረ ማሪያምም ሌሎችም ተሟገትናቸው - አይሆንም አሉ! ሁሉም ተቀበለ … ካሰብኩት በላይ ሆነ፡፡ ሁሉም በኋላ ሲያዩ … ቶላ በዳዳ በል፣ መኰንን አካ በል … ትላልቅ ያገር ሰዎች፤ በኋላ ሲያዩት ተደሰቱ ነው እምልህ፡፡ አይሆንም ብለው የነበሩት ሰዎች - በጣም ጥሩ ሆነ አሉ … ዘሪሁን የመቃብር ቤቱን ሥራ ጀምር ተባለ፣ … ሐውልት መሥራትና መጽሔት ማዘጋጀት አዲሳባ ያለው ኮሚቴ ሥራ ነው … ሌላው የአገሬው ኮሚቴ መስተንግዶ ይሥራ ተብሏል፡፡ በዚህ ተከፋፈልን … እኛ ገንዘብ እንደምንም ማከፋፈል ጀመርን-እዚህ ደረስን…
“ብዙ ብር አወጣችሁ?’
“አዎ ሀውልቱ ከ60 እስከ 70ሺ ሳይወስድ አልቀረም፡፡ መጽሔቱ እንደዛው ወጪ አለበት…”
“አንዱ የነካኝ ነገር አብዛኛዎቹ የቀብሩ ታዳሚዎች ሙስሊሞች ናቸው … ይሄንን ማመን አልቻልኩም፡፡ ግራ ቀኙ ሙስሊም ነው … የፕሮግራሙ መሪው የተናገረውን ታሪክ በትክክል ተረድቼው ከሆነ ፊታውራሪ ሱማሌያ ሄደው ነው ቁራን ቀርተው የመጡት ነው ያለው መሰለኝ…”
“አይ፤ እዚሁ ነው፡፡ የሱማሌ፤ ቁራን የሚያውቅ ሰው … ሱማሊኛም ይችላሉ አባቴ -የሚችሉት በዚያ ሱማሌ የተነሳ ነው፡፡ እዚሁ ነበር … እሱን አግኝተውት ቁራን ቀሩ፡፡ የአማርኛ ትምህርት በኋላ ላይ ተማሩ … እንደዚህ እንደዚህ ነው የሆነው
“መጀመሪያ ምን ነበሩ? ክርስቲያን ሆነው ነው ቁራን የቀሩት ማለት ነው?” ብዬ ጠየኩት፡፡   
“መጀመሪያማ በእኛ አካባቢ እስልምና አለ፡፡ እስልምናም ክርስትናም ባንድ አካባቢ ባንድ ዘመን ነው የገባው፡፡ የመጣው፡፡ ሳጉሬ፡፡ አያቴ ሁለቱም ሲመጡ አይተዋል! ያኔ ምናልባት በራስ ዳርጌ ጊዜ ነው - በሚኒሊክ ጊዜ መሆኑ ነው … ኦገቶ አያቴ በሚኒሊክ ጊዜ ነበሩ - ባላባት ናቸው ያን ጊዜ … እስልምናም ክርስትናም ሲመጣ - ከዛ በፊት ያው አዋማ ነው የሚባሉት - ያው በኦሮሞ አይነት አኗኗር ውስጥ የነበሩ ዕምነቶች ያልነካቸው ነበሩ …ኋላ ግን ኦገቶ እስላም ሆኑ፡፡ እስላምን ተቀበሉ። አብዛኛዎቹን የሚስቶቻቸውን ልጆች እስላም አደረጉ፡፡ የአባቴን እናት ልጆች (የሴት አያቴን) እነሱን ደሞ ክርስቲያን አረጓቸው፡፡ አንድ ቱሱራ የሚባል አለ፡፡ ክርስቲያን አልሆንም ብሎ እስላም ሆነ! ሌሎቹ አራቱ ማለት - ተክሌ፣ አበበ፣ በቀለ እና አሹ እምትባል ሴት ክርስቲያን ሆኑ! እንግዲህ፤ በኋላ ለባላባትነት አባቴን መርጠዋል ማለት ነው፡፡ ክርስትና ከተነሳህ ያው ከሥርዓቱ ጋር ቀረብ ትላለህ፡፡ ከሲስተሙ ጋር፡፡ እናቴንም ያገቡት ለዛ ነው፡፡ እናቴ እንግዲህ የማህል ሠፋሪ ልጅ ናት! ባሻ ገድሌ የእናቴ አባት የአንኮበር ሰው ናቸው፡፡ ከራስ ዳርጌ ጋር ሄደው ማህል የሰፈሩ ሰው ናቸው፡፡ አያቴ፤ የእናቴ እናት፣ ጠራ መንዝ ናቸው፡፡
“ስለዚህ አንኮበርና ጠራ ናቸዋ እናትህ?”
“አዎን፡፡ ሚስት ስጡን ቢሏቸው (በዚያን ጊዜ አጠራር) ‘ለጋላ አንሰጥም!” ብለው ነበር፡፡ በኋላ ፎከሩ፡፡ በቀለ ክርስቲያን የመሆን እድል አገኙ …. እስላም ሆነው ነበረ ማለት ነው አባቴ፡፡ … ካሜላ ነው ስማቸው … ሚካኤል ማለት መሰለኝ፡ ከካሜላ በፊት ጨዊቻ ነው እሚባሉት አባቴ፡፡ ጨዊቻ የኦሮሞ ስም ነው! ሌላ የእስላም የቁርዓን ስም ነው … ካሜላ … በኋላ የክርስትና አባታቸውን አውቅ ነበረ … ደጃች ወንድይራድ … እንደዛ ገደማ ናቸው፡፡ ከትልልቆቹ አንዱ፡፡ … ቁራንም ቀርተው፣ ክርስትናን ተነስተው፣ ባላባትነቱንም ተቀብለው ነበር ማለት ነው … አባታቸው ካረፉ በኋላ ባላባትነቱን ተረከቡ፡፡ ብዙ ልጆች ነበሩ ታላላቆችም ነበሩ፡፡ ሦስት ታላላቆች። ብዙ ጊዜ ልምዱ እንደዛ ነው - የመጀመሪያው ልጅ-የበኩር ልጅ ነው የሚወርሰው-ባላባትነቱን፡፡ በአሁኑ ሁኔታ ግን እንደዚያ አልነበረም-ለአባቴ ነበር የተናዘዙላቸው!” አለኝ፡፡
እኔም በመገረም፤ “ከመስጊድና ከቤተክርስቲያን ጋር የነበራቸው ቀረቤታ በጣም ፍላጐት አሳድሮብኛል፡፡ አስገራሚ ዕውነት ነው” “Fundamental to the Ethiopian society የኢትዮጵያ ህ/ሰብ የመሠረት ደንጊያ ነው ብዬ አሰብኩ፡፡ እስካሁን ወሎ ብቻ ነበር ሲጠቀስ የኖረው - አሁን ሳጉሬ መጣ-አርሲ - a very profound aspect of religion- በአንድ አገር ውስጥ መስጊድንም እራሱ አሠርቶ፣ ቤተክርስቲያንንም (በዕውነተኛ ልቡና ሠርቶ) መጓዝ ድንቅ ነገር ነው። ትምህርት ነው፡፡ ከባድ ነው ከ38 ዓመት በኋላ ያገኘነው ማጠየቂያ (Justification)፡፡ ይኸው ሥላሴ ኮረብታ ላይ ታይቷል፡፡ በመሠረቱ የእስላም ሴት ለቅሶ ስትመጣም አላቅም… ግን መዓት መጡ … አለቀሱ … ለቀስተኞቹ በብዛት ሙስሊሞች ናቸው …በብዛት ያለቅሳሉ … በጣም ይገርማል … እንዲህ ያለ ማረጋገጫ አይገኝም - እኔ ከዚህ አኳያ (angle) ነው ያየሁት፡፡
ሌላው የእኔ የግሌ እይታ፤ በእኛ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ዘመን የአርሲ ዕድገት በህብረት ዘማቾችን ደርግ ያላቸውን አስታውሳለሁ … በትክክል ባልጠቅሰውም … “ቅምጥል ንዑስ ከበርቴዎች፣ እጃቸውን የእንጀራ ጠርዝ የሚቀደው … “ጥቁር ወተት ነጭ ኑግ አምጣ እያሉ ገበሬውን ሱሪ ባንገት ሲያስወልቁት ከርመዋል…” በሚል ዓይነት ነበር ዘማቾቹን የሚከስ የሚወቅሳቸው፡፡
“…አንተ በሦስት ማዕዘን የማይታረቅ ቅራኔ ውስጥ ገብተህ ነበረ ማለት ነበርኮ! ፀረ-ፊውዳል የተማሪ እንቅስቃሴ ባንድ በኩል፤ እሳቸው ደግሞ ፀረ-ደርግ ሆነው ይታገሉ፣ ይዋጉ ነበር፡፡ ደርግ ደግሞ በእኛ በዘማቾች ላይ ጥቁር ወተት ነጭ ኑግ እያለ ነው፡፡ በጣም ማራኪ ታሪካዊ ሦስት ማዕዘን ነው የሚታየኝ፤ በጣም ስቦኛል! … Deep inside (ውስጠ-ነገሩን ለመረመረ)   የማህበረሰባችንን አካሄድ የሚያሳይ ስዕልም ያለው ይመስለኛል… ብዙ ነገር በውስጡ የሚያልፍ የህይወት፣ የሞትና የተረፈ-ህይወት ነገር አለው” ትልቅ ፅሁፍ ይወጣዋል ከታሰበበት፡፡ የእስላም-ክርስቲያን ዕምነት ውሁድ (harmony) በኢትዮጵያ ሁሌም የነበረ፣ ያለና እሚኖር ነው፤ የሚለውን ዕሳቤ ፍንትው አድርጐ ያሳየናል፡፡ የአንድነት አገራዊ መገለጫኮ ይሄው ነው … ማሳያ ነው፡፡ አንተስ ይሰማሃል?” አልኩት፤ የኮረኮረኝን ያህል ተናግሬ፡፡  
“እኔማ አውቀዋለሁ፡፡ ድሮውኑ እስላም ክርስቲያን እኮ አንድ ላይ ነው የሚኖረው፡፡ ቆይ ልንገርህ፡፡ ኦገቶ እስላም ሆነ፡፡ እስላም ነው፡፡ አርሲ ኦሮሞ ከብት አርቢ ነው፡፡ አራሽ አይደለም ከአመጣጡ፡፡ ይሄንን እዚህ ባላባት ሆነው ከኃ/ሥላሴ ጋር … ኃ/ሥላሴ ኦገቶን በደምብ ያውቋቸዋል አሉ፡፡ ሲመጡ ከዚህ የሸዋ ኦሮሞዎችን ኑ ባካችሁ ያገሬን ሰው፣ ያገሬን ገበሬ፤ ግብርና አስተምሩልኝ ብለው የአጐቴን የመኰንንን የሰናይትን አያት፤ ሌሎችም ሰዎች እዚህ አምጥተው እንዲሠፍሩ አርገዋል፡፡ ቤት ሰጥተዋል፡፡ ከዛ ምን ሆነ አንድ ጊዜ አንድ ክርስቲያን ሰው ሞተ አሉ፡፡ የመቃብር ቦታ፣ ቤተክርስቲያን፣ የለም፡፡ የት ነው ያለው ወደ ኢቴያ። ቦሩ ጃዌ እሚባል ቦታ … በቃሬዛ፣ በጠፍር አልጋ ተሸክመው ወስደው እዛ ቀበሩ፡፡ በኋላ ኃ/ሥላሴ ጋ ሄደው፤”በል ፅላት ስጠኝ” ብለው መድኃኔ ዓለምን ቆረቆሩ!”  
“እኒሁ ኦገቶ?!” ገርሞኝ ጠየኩት፡፡
“አዎ ኦገቶ፡፡ ጋለማ ሥር ያለች ከተማ እሁድ ገበያ ትባላለች፡፡ እዛ ቆረቆሩ፡፡ ሠንሠለታማው ጋራ ሥር ያለችው እሁድ ገበያ ውስጥ ያለ ቤተክርስቲያን ኖረ ማለት ነው፡፡ አሁንም አሉ፤ የዚያ ቤተክርስቲያን፤ ቀዳሽ ቄሶች፣ ልጅ ልጆች፡፡ እዚያው ሠፈሩን መሬቱን ይዘው ይኖራሉ፡፡ ከዛ ደባል እግዚሃር-አብ አለ፡፡ በጥምቀት ጊዜ ይኬድበታል፡፡ መድኃኔዓለም ከከተማው ወጣ ያለ ነው፡፡ ወደላይ 4ኪ.ሜ ገደማ። እና አንድ አጐቴ ከሌሎች ጋር ሆነው እዚህ ከተማ ውስጥ እግዚሄርአብን ከመድህኔዓለም ደባልነት አውጥተው አሁን እሁድ ገበያ ውስጥ እንዲኖሩ አርገውታል፡፡ እና ኦገቶ ናቸው ቤተክርስቲያን ያሠሩት፡፡ የዚያን ክርስቲያን ሰውዬ መሞትና ኢቴያ ቦሩ ጃዌ ድረስ ሄዶ (50 ኪ.ሜ) መቀበር፤ ካዩ ወዲያ ነው እንግዲህ! ይሄ ዕውነተኛ ታሪክ ነው! እና ለእኔ ዓይነት ሰው እስላም - ክርስቲያን ልዩነት ዓይነት Sense (ስሜት) ምንም የለም፡፡ ምንም ማስተናገጃም የለኝም፡፡”
“ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ የዛሬው ሥነ ስርዓት የፈጠረብህ ስሜት ምንድነው? እንዴት ታየዋለህ? በአጭሩ”
“እኔ አሁን እንደማየው ካሁን ወዲያ፤ የተበጣጠቀው ታሪክ መልሶ መገጣጠም የተጀመረ ይመስለኛል … ምናልባት ካሁን ወዲያ የተሻለ ህይወት ለመኖር እንችል ይመስለኛል እንጂ ካሁን በፊት ያጋጠመኝ የነበረው ስሜት … እንደጠላትነት ነበረ … ደርግ ወድቆ ይሄኛው መንግሥት ሲመጣ ምን ነበረ መሰለህ … በቀለን የገደለ ሰው እናውቃለን ለምንድነው ከሰን የማናሳስረው? ገዳዮቹን ፖሊሶች እናውቃለንኮ ለምንድነው የማናሳስረው ሲባል ነበር … ያ አይነት ስሜት ነበር፡፡ ይሄ ቂም ነው፡፡ ቂም ነው፡፡ አልተዋጠልኝም ነበረ፡፡ የመገፋፋት ሁኔታ ነበረ ልልህ ነው፡፡ እና ታላቅ ወንድሜም እሱን ሰምቶ እንዲህ ይባላል ብሎኝ ነበር፡፡ ቃታ-የሳበ ሁሉ አስተሳሰብ አያስፈልግም እና ተውኩ፡፡ ተው አልኩት፡፡ እዛ ውስጥ አንገባም ተባባልን፡፡ እና ሌላም አጐቴ ነበረ፡፡ በቂም እሚያስብ፡፡ ያጋጥመኝ ነበር … ያኔ ታስታውስ እንደሆን (የዛሬ 26 ዓመት ግድም) ሰላምና መረጋጋት የሚባል ነበረ …”
“እንዴ በደንብ ነው የማስታውሰው!”
“አሰላ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ውስጥ ሲያገለግል የነበረ አጐቴ ሲነግረኝ፤ አለቃው አንድ የቡድን መሪ አድራጊ-ፈጣሪ የነበረና የእኛ አባትን ታሪክ ይሄንን ያወራ የነበረ አለ፡፡ ‘ገዳዮቹ ማናቸው?’ ብሎ ይጠይቃል፤ አለ፡፡ ለምን ገዳዮቹን ሰብስበን እዚህ አንጨርሳቸውም? ከዛ በኋላ ቂማችሁን ተወጥታችኋል ማለት ነው፤ ለምን እንደዚህ አናረግም?’ አለኝ አለ፡፡ እስቲ ቆይ ዕድል ስጠኝ ብዬ በኋላ ተውኩት፤ አለ፡፡ እና እንደዛ እንደዛም ሆኖ ነበር! በዛ ውሰጥ ነው ያለፍነው! ያ ፈሊጥ ነበረ! ጊዜ ወዳንተ ሲያዘነብል ቂም መወጣት ወይም አንተን ወደዘመመበት ለማዝመም የተደረገ ሙከራ ነበረ። ጊዜው ያመቻል፡፡ አጋጥሞኛል፡፡ እሱ 2ኛ ነው፡፡ ሌላም እንደዚሁ ዘመዳችን የሆነ በጊዜው አድሃሪ ምናምን ብሎ ተሳድቧል ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ ባለፈው ቅዳሜ መጣና አየሁት፡፡ ገበሬ ማህበር ደምበኛ አብዮታዊ ባሻሪ የነበረ ነው፡፡ በኋላ ተገናኘን!! እሱኮ እደዚህ ያረገ ነው አሉኝ፡፡ አሁን ሌላ ሆነ! እሁድ ልሄድ አስቤያለሁ - ገጠር!
“ምን ልታደርግ?”
እንዲሁ ዘመዶቼን ልጠይቅ፡፡ ይቺ አሁን የነብር ቆዳ ለብሳ የፎከረችዋን ሴትዮ አላየሁዋትም ነበር፡፡ ሁሌ በሄድኩ ቁጥር እሷን አገኛለሁ …  ደሞ ያጐቴ ሚስት ልጅ አለች እሷንም ሄጄ ላያት፣ ልሰማት እፈልጋለሁ … አብረንም ብንሄድ መልካም ነው እና አሁን በረጋ መንፈስ ምንም ችግር የሌለው፤ ነገር መሥራት ይቻላል…አየህ፤ “ለካ እንዲህ ማድረግ ይቻላል?!” ነውኮ ያልነው! ይሄን ያህል አልጠበቅነውም”
“አገርን ማነቃነቅኮ ነው፡፡ እኔም በጭራሽ ለማመን አልቻልኩም”
“ዕውነት ነው አንድ አፅም ታሪክ እየሰራ ነው! ሰው እንደጉድ ፈሰሰ፡፡
በቪዲዮ በስፋት መቀረፅ ነበረበት! እንደታሪክ፣ እንደ እስላም-ክርስቲያን አንድነት፤ የብዙ ነገር ማሳያ ነው፡፡ በቲቪ መታየት ነበረበት-ለትውልድ ማስተማሪያ! አመለጠን - ብዙ ይዘጋጅ ብለን ነበረ … ታሪክና ሃይማኖት እንዴት የተሣሠሩ እንደሆኑና የመንግሥታት መለዋወጥ የማታ ማታ ንክች እንደማያደርጋቸው ያሳያል!!”
“That’s excellent! አመሰግናለሁ ዶ/ር ሙሉጌታ!”

Read 1821 times