Saturday, 08 March 2014 12:46

የአቶ አለማየሁ አቶምሳ የቀብር ስነስርዓት ዛሬ ይፈፀማል

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(12 votes)

የኦህዴድ ሊቀመንበርና የኦሮምያ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ አለማየሁ አቶምሳ ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ከቆዩ በኋላ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ህይወታቸው እንዳለፈ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የዘገበ ሲሆን የቀብር ስነስርዓታቸው በዛሬው እለት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስትያን ይፈፀማል ተብሏል፡፡
በጳጉሜ 2002 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በተደረገው የኦሕዴድ ስድስተኛ ድርጀታዊ ጉባዔ ላይ አራተኛው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት በመሆን የተመረጡት አቶ አለማየሁ አቶምሳ፤አብዛኛውን የሹመታቸውን ጊዜ በሕመም ቢያሳልፉም ለበርካታ ወራት ለህክምና በሚቆዩበት ሆስፒታል ሆነው ስራቸውን በኢንተርኔት ያከናውኑ እንደነበር ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡  
አቶ አለማየሁ አቶምሳ በፕሬዚዳንትነት ተመርጠው አንድ ዓመት ሳይሞላቸው ባጋጠማቸው ሕመም ምክንያት ከሃላፊነት ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ያስታወሱት ምንጮቻችን፤ጥያቄያቸው ተቀባይነት ሳያገኝ በመቅረቱ ላለፉት ሶስት ዓመታት ህክምናቸውንና ሃላፊነታቸውን ጎን ለጎን ሲያካሂዱ እንደቆዩ ጠቁመዋል፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊም ከህመማቸው ቀደም ብሎ ከሃላፊነታቸው ለመልቀቅ ጠይቀው ፓርቲያቸው እንዳልተቀበላቸው በህይወት ሳሉ መናገራቸው  ይታወሳል፡፡
  ከሁለት ሳምንት በፊት የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የተገኙት አቶ አለማየሁ፤ ከወትሮው በተለየ የህመምና የመጎሳቆል ስሜት ይታይባቸው የነበረ ቢሆንም ስብሰባውን በአግባቡ ሲመሩና ግምገማ ሲያካሂዱ ነበር ብለዋል - ምንጮች፡፡  
አቶ አለማየሁ በቅርቡ ለኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለሁለተኛ ጊዜ ያቀረቡት የሥራ መልቀቂያ ማመልከቻ ተቀባይነት ማግኘቱ የሚታወቅ ሲሆን ሃላፊነታቸውን አስረክበው ብዙም ሳይቆዩ ባደረባቸው ህመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ45 አመታቸው ከትላንት በስቲያ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ኢቴቪ ዘግቧል፡፡ አንዳንድ ወገኖች ግን ኢቴቪ የአቶ አለማየሁን ዜና እረፍት ከማወጁ  ሶስት ቀን ቀደም ብሎ ህልፈታቸውን እንደሰሙ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ የአፄ ምኒልክ ህልፈት ከህዝቡ ተደብቆ የቆየው ብጥብጥ እንዳይነሳ ተፈርቶ እንደነበር ታሪክ ጠቅሰው ያስታወሱት አስተያየት ሰጪዎቹ፤በአሁኑ ዘመን የመንግስት ሹማምንት ህመምና የሞቱበት ቀን ለምን እንደሚደበቅ አይገባንም ይላሉ፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ትክክለኛ የህልፈት ቀን አለመነገሩን በማስታወስም ጉዳዩ  ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ በመሆኑ የታሪክ መዛባት እንዳይፈጠር እርምትና ጥንቃቄ መውሰድ እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎቹ አሳስበዋል፡፡
የኦሮምያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ከመሆናቸው በፊት በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ የሰሩት አቶ አለማየሁ አቶምሳ፤የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ስራ አስኪያጅና የኦሮሚያ ክልል ማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ ሆነው እንዳገለገሉም ይታወቃል፡፡ የመጀመርያ ድግሪያቸውን ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በህግ ትምህርት ያገኙት አቶ አለማየሁ፤ሁለተኛ ድግሪያቸውን ከቤይጂንግ ዩኒቨርስቲ በህዝብ አስተዳደር አግኝተዋል፡፡ ህልፈታቸውን ተከትሎ ኦህዴድ ባወጣው የሃዘን መግለጫ፤ አቶ አለማየሁ ለኦሮምያ ህዝብ ነፃነትና ዲሞክራሲያዊ መብት መከበር ለ24 ዓመታት እንደታገሉ አስታውሶ፤በኦሮምያ ክልል ኪራይ ሰብሳቢነትን በፅናት እንደታገሉና ኢኮኖሚያዊ እድገት እድገት እንዲመዘገብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን አመልክቷል፡፡ አቶ አለማየሁ አቶምሳ ባለትዳርና የ3 ልጆች አባት ሲሆኑ የቀብር ስነስርዓታቸው ዛሬ በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤ/ክርስትያን እንደሚፈፀም ታውቋል፡፡

Read 5198 times