Saturday, 08 March 2014 12:16

ፓትርያርኩ ‹‹ቤተ ክርስቲያን በዩኒቨርስቲ ምሩቃን አትመራም” ማለታቸው ቅሬታ ፈጠረ

Written by 
Rate this item
(13 votes)

ስለማኅበራት የሰጡትን አስተያየት መልሰው እንዲያጤኑት ተጠየቀ
‹‹ማኅበራት በትኩረት ሊመሩና ጉዟቸውም እየተፈተሸ ሊስተካከል ይገባል›› - መንግሥት


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ‹‹ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው ቤተ ክርስቲያንን እንምራ እያሉ ነው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትውፊትና ሥርዓት አላት፤እንዲህ ማለት አይችሉም›› በማለት የሰጡትን አስተያየት መልሰው እንዲያጤኑት በንግግራቸው ቅር የተሰኙ የመንፈሳውያን ማኅበራት አገልጋዮች ጠየቁ፡፡
አገልጋዮቹ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፣ አቡነ ማትያስ ይሄን አስተያየት የሰነዘሩት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ከኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጋር በመተባበር የካቲት 21 እና 22 ያዘጋጁት ሀገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል የምክክር ጉባኤ በተካሔደበት ወቅት ነው፡፡
በምክክር ጉባኤው መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር ‹‹በባዮሎጂና ኬምስትሪ እንቀድስ እያሉ ነው፤›› ያሉት አቡነ ማትያስ፤ ‹‹ምን እያልኹ እንደኾን ይገባችኋል›› በማለት ማንን እንደሆነ የማሳየት ያህል የጠቆሙበት አስተያየት ያልተለመደና ጥቂት የማይባሉ የጉባኤውን ተሳታፊዎች ያሳዘነ እንደነበር የጉባኤው  ምንጮች አመልክተዋል፡፡
በምክክር ጉባኤው ላይ ለውይይት በቀረቡ ጽሑፎች፣ እስከ ሰማንያ ሺሕ የሚገመቱ መንፈሳውያን ማኅበራት በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም በአዲስ አበባ እንደሚንቀሳቀሱ የተጠቀሰ ሲሆን  ቤተ ክርስቲያኒቱ ማህበራቱ በሕግና በሥርዐት የሚመሩበት ደንብ አውጥታ እስካልተቆጣጠረቻቸው ድረስ እየተከሠቱና ሊከሠቱ የሚችሉ ችግሮች በቀላሉ እንደማይታዩ ተመልክቷል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ በበኩላቸው፤በማኅበር ሽፋን ለግል ጥቅማቸውና ፍላጎታቸው የሚሯሯጡ፣ የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ሕጸጽ የሚታይባቸው ማኅበራት የመኖራቸውን ያህል ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው፣ ምእመናንን በማትጋት ለበለጠ ሀብተ ጸጋ የሚያበቁ ጠንካራ ማኅበራትም እንዳሉ ገልጸዋል፡፡  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምክክር መድረክና በቤተ ክህነቱ ጉባኤያት እየታየ ያለው “ማኅበራት አላሰራ አሉን” በሚል በጅምላ የመፈረጅና የመኰነን ዝንባሌ፣ አብዛኞቹ ማኅበራት ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን እያበረከቱ ያለውንና  በቤተ ክህነቱ ቀጥተኛ አቅም ሊሸፈን የማይችለውን ዘርፈ-ብዙ አገልግሎት ያላመዛዘነ ነው ብለዋል -የማህበራት አገልጋዮች፡፡
“በአሁኑ ጊዜ ማኅበራት የአባሎቻቸውንና የበጎ አድራጊ ምእመናንን የገንዘብ፣ የዕውቀትና ሞያዊ አቅም በማስተባበር የገጠር አብያተ ክርስቲያናት፣ ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ት/ቤቶች በተቀናጀ መንገድ እንዲረዱ ያደርጋሉ፤ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ዕድገት የሚጠቅሙ ልዩ ልዩ ጥናቶችን ያካሒዳሉ፤ በጠረፍ የሀገሪቱ ክፍል በሚያከናውኑት የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ምእመኑ በቋንቋው የሚገለገልበትን ኹኔታ ያመቻቻሉ፤ የቅዱሳት መካናት ተሳላሚዎችን ጉዞ በማስተባበር ሕዝቡ ቅርሱንና ባህሉን አውቆ እንዲጠብቀውና እንዲከባከበው ከማስቻላቸው ባሻገር ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም መስፋፋትና መጠናከርም ያላቸው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡” ሲሉ የማህበራትን ጥቅም አብራርተዋል፡፡
ማኅበራቱ አብዛኞቹን ተግባራት የሚያከናውኑት በየደረጃው ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሓላፊዎች ፈቃድ እያገኙና መመሪያ እየተቀበሉ መኾኑን የሚገልጹት አገልጋዮቹ፣ በግንቦት 2004 ዓ.ም. የማኅበራትን ቁጥር ስለመቆጣጠር ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ በነበረው ጥናት መነሻነት ምልዓተ ጉባኤው ራሱን የቻለና ማኅበራቱን የሚያሠራ ሕግ እንዲዘጋጅ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሕግ ባለሞያዎች ያሉበት ደንብ አዘጋጅ ኮሚቴ ሠይሞ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ የማኅበራት አደረጃጀትና የፋይናንስ ቁጥጥር መርሕን ጠብቆ እንደሚወጣ ሲጠበቅ የቆየው ደንብ ከሚገባው በላይ መዘግየቱ ችግሩ ከቤተ ክህነቱ እንጂ ከማኅበራቱ አገልግሎትና ብዛት አለመኾኑን እንደሚያመለክት ይከራከራሉ፡፡
ፓትርያርኩ አድልዎ በሌለው መልኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማስተዳደር በዕለተ ሢመታቸው ቃለ መሐላ መፈጸማቸውን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ በምክክር ጉባኤው ላይ በተጠቀሰው አኳኋን የመናገራቸው ግፊት የተለያየ መነሻ ሊኖረው እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
የመጀመሪያው መንሥኤ፣ የሙስናንና ብልሹ አሠራርን ችግር ለመቅረፍና ለማድረቅ በቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት ለአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የተሠራው የመዋቅር፣የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናት ተቃዋሚዎች የጥናቱ ባለቤት ነው በማለት በሚከሡት ማኅበረ ቅዱሳን ላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ አመራር አማካይነት እንዲፈጠር የሚሹት ጫና ነው፡፡ ኹለተኛው ደግሞ በመንግሥት በኩል፣ ‹‹በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ውስጥ አክራሪነትና ጽንፈኝነት የሚታየው ህልውናቸውና ዓላማቸው ሃይማኖታዊና በሃይማኖቱ የበላይ ጠባቂዎች ይኹንታ በተቋቋሙ የወጣት ማኅበራት አደረጃጀቶች ውስጥ በመሸጉ አካላት ነው፤ ስለዚህም ማኅበራት በትኩረት ሊመሩና ጉዟቸውም እየተፈተሸ ሊስተካከሉ  ይገባል፤›› የሚለው ክሥ በመሪዎቹ ላይ ያሳደረው ማኅበራቱን የመቆጣጠር ጫና ነው፡፡
የአክራሪነትንና ጽንፈኝነትን ምንነትና መፍትሔዎችን በሚተነትኑት የመንግሥት ሰነዶች፣ የሃይማኖት ተቋማትን ለአክራሪነትና ጽንፈኝነት ተጋላጭ ያደርጋቸዋል ከሚባሉት ኹኔታዎች ውስጥ÷ የሃይማኖት ተቋማቱ የሰው ኃይል አስተዳደርና የፋይናንስ ሥርዐት ለተከታዩ ሕዝብ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌላቸው መኾናቸው፣ በሙስናና በአስተዳደር በደል ሳቢያ የሚፈጠር ግጭት፣ የሰው ኃይል አስተዳደር በዘመድ አዝማድና በጉቦ እየኾነ የሥራ ብቃት በሌላቸው ሰዎች የሚሠራበት፣ የኦዲት ሪፖርት ቀርቦ የሚተችበትና አስተያየት የሚሰጥበት ሥርዐት አለመዳበሩ፣ ተከታዮችን አክራሪነትን የሚቋቋም በሃይማኖት ዕውቀት የማስታጠቅ ክፍተት ይገኙበታል፡፡
በመንግሥት ትንታኔ መሠረት፣አክራሪነትን የመዋጊያው ቁልፍ መሣሪያ ልማትንና ዕድገትን በማፋጠን የመልካም አስተዳደር ችግርን መቅረፍ፣ሕዝቡን በሃይማኖታዊ ዕውቀት ማስታጠቅ ነው፡፡ የሃይማኖት ተቋማትን ለአክራሪነትና ጽንፈኝነት ተጋላጭ ያደርጓቸዋል የተባሉት የመልካም አስተዳደርና የብልሹ አሠራር ችግሮች÷ ማኅበረ ቅዱሳን በተቃዋሚዎች አላግባብ በሚከሠሥበት የመዋቅር፣ የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናት ትግበራ በማፋጠን እንዲኹም ማኅበረ ቅዱሳንን ጨምሮ በርካታ ማኅበራት በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ የገዳማትና የአብነት ት/ቤት ማኅበረሰብን በልማትና ተራድኦ ከመደገፍ ጀምሮ በሚያከናውኑት ሐዋርያዊ ተልእኮ ንቃት ሊወገድ እንደሚችል ቅሬታ አቅራቢዎቹ ያምናሉ፡፡ ከዚኽም አንጻር ፓትርያርኩ ንግግራቸውን መልሰው በማጤን ማኅበራት አገልግሎታቸውን አጠናክረው ለመቀጠል የሚያስችላቸው ኹኔታ እንዲያመቻቹ ጠይቀዋል፡፡

Read 7197 times