Print this page
Tuesday, 04 March 2014 11:18

የ“ሆላንድ ካር” ባለቤት ችግሩን በመወያየት መፍታት እፈልጋለሁ ይላሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)

ለኪሳራ የዳረገን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው
ፋብሪካው ውስጥ ያሉት ንብረቶች የደንበኞች ናቸው
ችግሩ ከተፈታ በሀገሬ ላይ ኢንቨስት ማድረግ እፈልጋለሁ

ከሁለት ዓመት በፊት የተዘጋው “ሆላንድ ካር” በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ሲሆን በአጭር ዓመታት ውስጥ ባሳየው የስራ “አፈፃፀም የአፍሪካ ምርጥ ኩባንያ ተብሎ መሸለሙ ይታወሳል፡፡ በኢትዮጵያም በወቅቱ ኢንዱስትሪውን እያንቀሳቀሱ ካሉ ፋብሪካዎች አንዱ ነበር፡፡ የኩባንያው መስራችና ባለቤት ለረጅም ዓመታት በሆላንድ ሃገር በትምህርትና በስራ የቆዩት ኢ/ር ታደሰ ተሰማ ሲሆኑ ኩባንያው በሃገሪቱ ታላላቅ ወንዞች የተሰየሙ አባይ፣ አዋሽና ተከዜ የተሰኙ የቤት አውቶሞቢሎችን ከመገጣጠም ባሻገር፣ የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ችግርን ይፈታል የተባለ ተሰካኪ አውቶብስ ለመገጣጠም እንቅስቃሴ ጀምሮ ነበር፡፡ በወቅቱ የተከሰተውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እና የአካባቢ አየር ብክለት ለመቋቋም የሚያስችል የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂንም ለማስፋፋት ጅምር ስራዎች ነበሩ፡፡ በዚህ መሃል ነበር ድንገት ኩባንያው ከስራ ውጪ መሆኑ የተነገረው፡፡ ባለቤቱም ከሃገር ወጥተው ለጋዜጠኞች በስልክ መግለጫ ሰጡ፡፡ በወቅቱ ኩባንያው ስራ ያቆመበት ምክንያት በግልፅ አልታወቀም ነበር፤ ብዙ ያልጠሩ ጉዳዮችም ነበሩ፡፡የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከዘመን ባንክ ጋር የነበራቸው አለመግባባት ለኩባንያቸው መክሰር ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ የሚናገሩት ኢ/ር ታደሰ፤ አሁን ሁሉም ነገር በውይይት ስምምነት ላይ ተደርሶበት፣ ደንበኞች ቀብድ የከፈሉባቸውን ተሽከርካሪዎች የሚያገኙበት መፍትሄ ማበጀት እንደሚሻል ይገልፃሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ከሆላንድ ካር መስራች ጋር በከኩባንያው መዘጋትና ተያያዝ በደንበኞች ንብረት ዙሪያ ካሉበት አገር በስልክ አነጋግሯቸዋል፡፡  

እስቲ ወደ ሌላ ጉዳይ ከመግባታችን በፊት ሆላንድ ካር ኩባንያ እንዴት እንተ ተቋቋመ ይንገሩኝ?
በ1980 ወደ ሆላንድ ገብቼ እዚያው ትምህርቴን ጨርሼ ስራ እየሰራሁ ሳለ፣ መጠነኛ አገልግሎት የሰጡ መኪናዎችን ወደ ኢትዮጵያ እልክ ነበረ፡፡ በዚህ ስራ ትንሽ እንደቆየሁ ያገለገለ መኪና ከማስገባት “ለምን እዚሁ ሃገር ቤት መገጣጠም አይቻልም” በሚል ሃሳቡን ለሆላንድ መንግሥት አቀረብኩ፡፡ የሃገሪቱም መንግሥት የተማርኩበትን ሙያ ከገመገመ በኋላ፣ ከሙያዬ ጋር ስለማይሄድ እውቀት ያለው ማስተር ኩባንያ ፈልግ አሉኝ፤ እኔም አገኘሁ፡፡ “ትሬንቶ” ከሚባል ኩባንያ ጋር ሆነን ለሆላንድ መንግስት አመለከትን፡፡ የሆላንድ መንግሥትም ጥያቄያችንን ተቀበለ፡፡ በ2005 እ.ኤ.አ ከኩባንያው ጋር የጋራ ጥምረት መሰረትን፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ስትመጡ በምን ሁኔታ ተስተናገዳችሁ?  
ድርጅቱን ስናቋቁም እኛ የመጀመሪያዎቹ ስለነበርን ብዙ ችግሮች ነበሩ፡፡ ነገሮች በደንብ እስኪደራጁ ለሁለት አመታት ፊያት መኪናዎችን መሸጥ ጀመርን፡፡ በኋላም ከቻይና ባለሙያዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ በሰው ሃይል ተደራጅተን ወደ ፋብሪካ ግንባታው ልንገባ ችለናል፡፡ መጀመሪያ ላይ በጠቅላላው 40 ሰራተኞችን ብቻ ነበር ወደ ስራ ይዘን የገባነው፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ወደ ቻይና ልከን ሙያውን እንዲቀስሙ አድርገናል፡፡ የሆላንድ ባለሙያዎችን ለ6 ወር አስመጥተንም የእውቀት ሽግግር አድርገናል፡፡ የሰራተኛው ቁጥርም ከ40 ወደ 250 አድጎ ነበር፡፡
ወደ ገበያ ስትገቡ አቀባበሉ እንዴት ነበር?
 ብዙ ችግር ነበረብን፡፡ አንደኛው ችግር ያገለገሉ መኪናዎች በብዛት ወደ ሃገር ውስጥ ስለሚገቡ፤ ህብረተሰቡ ሃገር ውስጥ በኛ ባለሙያዎች በሚገጣጠሙት መኪናዎች ላይ መተማመን አልነበረውም፡፡ በጥራት ደረጃው ላይ አብዛኛው ደንበኛ ጥርጣሬ ነበረው፡፡ እኛ ያንን ለማሳመን ብዙ የፕሮሞሽን ስራ ሰርተናል፡፡ አንዱ የኩባንያችን ግብ የነበረው የህብረተሰቡን አመለካከት በመቀየር፣ በሃገር ውስጥ ምርት የመገልገልን ባህል ማሳደግ ነበር፡፡ በዚህ ተሳክቶልናል፡፡ በኋላም እንዳየነው፣ ከውጭ የሚመጡ ያገለገሉ መኪኖች ቁጥር በጣም ቀንሶ ነበር፡፡ የኛ መኪኖችም በትዕዛዝ ጭምር በወረፋ ይሸጡ ነበር፡፡ ያገለገሉ መኪኖች ወደ ሃገር ቤት አለመግባት ደግሞ በብዙ አኳያ ጥቅም አለው፡፡ በ2 ዓመት አካባቢ ገቢዎችና ጉምሩክ እንዲሁም ኢንቨስትመንት ሚኒስቴር ይፋ ባደረጉት ጥናት፣ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመው ነበር፡፡ በገበያው በኩል ከሄድን፣ እኛ እንደውም ፍላጎቱን ማሟላት አልቻልንም ነበር፡፡ አንድ ደንበኛ ያዘዘውን ምርት ለማግኘት እስከ 7 ወር ድረስ ሁሉ ይጠብቅ ነበር፡፡ ይሄ ምርታችን ምን ያህል  ገበያ ላይ ተፈላጊ እንደነበር ያሳየናል፡፡ ነገር ግን በወቅቱ በነበሩት ችግሮች፣ ጥሬ እቃውን በፈለግነው መጠንና ፍጥነት ወደ ሃገር ውስጥ ማስገባት አንችልም ነበር፡፡
ጥሬ ዕቃውን ወደ ሃገር ውስጥ በፈለጋችሁት መጠንና ፍጥነት እንዳታስገቡ ያገዳችሁ ምን ነበር?
የውጭ ምንዛሬ ችግር ነው፡፡ የምንፈልገውን ያህል ምንዛሬ ከባንክ አናገኝም ነበር፡፡
ፋብሪካው እስኪዘጋ ምን ያህል መኪኖችን ነው ለደንበኞቻችሁ ያስረከባችሁት?
ትክክለኛ ቁጥሩ አሁን እጄ ላይ የለም፤ ነገር ግን በግምት ወደ 3ሺ ይሆናል፡፡
ትርፋማ ከነበራችሁ እንዴት ወደ ኪሳራ ልትገቡ ቻላችሁ?
እንግዲህ እ.ኤ.አ በ2010 አካባቢ የገንዘብ መግዛት አቅም በጣም ተዳከመ፡፡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 30 በመቶ ያህል ነበር የቀነሰው፡፡ ያ በጥሬ እቃ አቅርቦታችን ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ነበረው፡፡ ያጋጠመንን ኪሳራ ደንበኛው ላይ ላለመጫን እኛ ነበርን የምንሸከመው፡፡ ለምሳሌ የ24 መኪናዎች መገጣጠሚያ ስናስገባ 950 ሺህ ብር ነበር ታክስ የምንከፍለው፡፡ ይህ የታክስ መጠን የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከምን ተከትሎ ወደ 2.1 ሚሊዮን ብር ገባ፡፡
በዚህን ወቅት ደንበኛው ላይ ዋጋ ከመጨመር ይልቅ በራሳችን ለመወጣት ወሰንን፡፡ ደንበኛው ቀደም ብሎ የታክስ ዋጋ ሳይጨምር ያዘዛቸው መኪኖች ስለሆኑና ቀደም ብሎ የተገባ የዋጋ ስምምነት ስላለ ጭማሪ ማድረግ አይቻልም፡፡ ትዕዛዞቹን በወቅቱ ለደንበኛው ላለማስረከባችንም ደጋግሜ እንዳልኩት የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ማነቆ ሆኖብን ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ኩባንያው ችግር ላይ ወደቀ፡፡ ያም ቢሆን ኪሳራውን እየተሸከመ ከ300 በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች በስምምነቱ መሰረት መኪናዎችን አስረክቧል፡፡ በወቅቱ ከባንክ እየተበደርን ነበር ኪሳራውን የምንወጣው፤ ምክንያቱም ከችግሩ ፈጥነን እንወጣለን የሚል ተስፋ ነበረን፡፡
በወቅቱ ባጋጠማችሁ ችግር ዙሪያ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር ተቀራርባችሁ ለመነጋገር አልሞከራችሁም?
እኔ በተቻለኝ መጠን ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ለኢንቨስትመንት ቢሮ እና ሌሎች ባለስልጣኖች ችግሩን ደጋግሜ ተናግሬያለሁ፡፡ አሁን ያኔ እኛ ስናነሳው የነበረው አይነት ችግር መከሰቱንና ጉዳዩን የተለያዩ ኩባንያዎች ለመንግሥት አመልክተው፣ በአስቸኳይ እንዲታይላቸው መወሰኑን ሰምቻለሁ፡፡ እኛ ግን በወቅቱ በተደጋጋሚ ተናግረናል፡፡ ለምሳሌ ድርጅቱ በ2010 ላይ ኦዲት ተደርጎ ምንም ገንዘብ እጃችን ላይ አልተገኘም፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ 5 ዓመት ሳይሞላን ኢትዮጵያ ውስጥ ዋና የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ተብለው ከተለዩት 5 ኩባንያዎች  አንዱ ሆነን ነበር፡፡ በወቅቱ ምርጥ ታክስ ከፋዮችም ተብለናል፡፡
ኩባንያው የከሰረው የገበያ ፉክክሩን ስላልቻለው ነው የሚባል ነገርም አለ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?
እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ የደንበኞች ፍላጎት በገለፅኩት መጠን ነበር፡፡ ፈፅሞ የገበያ ችግር አልነበረብንም፤ መኪኖቻችንን በወረፋ  ነበር የምንሸጠው፡፡
አዳዲስ ፕሮጀክቶችም ጀምራችሁ ነበር፡፡ ተገጣጣሚ አውቶብስ የመስራት እና በባዮ ጋዝ የሚንቀሳቀሱ መኪኖችን የማምረት፡፡ እሱስ ጫና አልፈጠረባችሁም?
አውቶብሶቹን ለመስራት ወጪ አውጥተናል፡፡ እኛ ለአዲስ አበባ ትራንስፖርት ችግር መፍትሄ ይሆናል ብለን ያቀረብነው ፕሮጀክት ነበር፡፡ የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮም በጉዳዩ አምኖበት ወደ ስራ የተገባ ቢሆንም በኋላ ላይ ምርቱ ስላልተፈለገ ቆሟል፡፡ በወቅቱ ግን “አሃዱ” የተባለውን የመጀመሪያ ተገጣጣሚ አውቶብስ ለመስራት ወደ 8.5 ሚሊዮን ብር አውጥተናል፡፡ ባዮ ጋዝን በተመለከተ ለማምረት የሚያስችሉን ጥሬ እቃዎችን ከውጭ ካስገባን በኋላ አሁንም ኮንቴይኔር ውስጥ ያለ አገልግሎት ተቀምጧል፡፡ አላማችን የነበረው የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ ስለመጣ ከተማ ውስጥ ካለው ቆሻሻ፣ ባዮ ጋዝ በማምረት፣ በዚህ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን ለገበያ ማቅረብ ነበር፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ የከተማዋን ፅዳት ከመጠበቅ አኳያ ካለው ጥቅም ባሻገር፣ ለነዳጅ የሚወጣውን በመቆጠብ ሃገሪቱንና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ አዋጭ ፕሮጀክት ነበር፡፡ እነዚህን ፕሮጀክቶች መጀመር በራሱ ወጪ ያለው በመሆኑ የተወሰነ ጫና ቢፈጥሩብንም ዋናው ችግራችን ግን የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ነበር፡፡
መጨረሻ ላይ ከዘመን ባንክ ጋር አለመግባባት ውስጥ የከተታችሁ ጉዳይ ምን ነበር?
በ2010 እ.ኤ.አ ኩባንያው ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ላይ ስለወደቀ ደንበኞች ራሳቸው ተሰብስበው ምን መፍትሄ እናምጣ በሚለው ጉዳይ ተወያዩ፤ እነዚህ ደንበኞች እኛ ጋ አስቀድመው የከፈሉት ቀብድ የመኪናውን ዋጋ 30 በመቶ ነበር፡፡ “የቀረውን ገንዘብ ለሆላንድ ካር አንሰጠውም፤ ከዘመን ባንክ ጋር እያንዳንዱ ደንበኛ ስምምነት ፈፅሞ ቀሪው ገንዘብ ባንክ ይቀመጥና ባንኩ ጥሬ እቃውን ከውጭ በማምጣት ለሆላንድ ካር ይሰጥ” የሚል ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ ሆላንድ ካር ደግሞ ገጣጥሞ ያስረክበን ተባለ፡፡
ይህን አፈፃፀም የሚከታተል የደንበኞች ኮሚቴም ተቋቋመ፡፡ ገንዘቡ የሚቀመጥበት ልዩ ሂሳብም ተከፈተ፡፡ በዚህ ሂደት ባንኩ ሆላንድ ካርን ማንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ባንኩ እቃውን የማስገባት ፍቃድ ስለሌለው፣ በሆላንድ ካር ስም ኤልሲ ተከፍቶ በዚያው መሰረት እቃው በሆላንድ ካር ስም ይገባ ነበር፡፡ መኪናዎቹ ከተገጣጠሙ በኋላ እንኳ የትኛው ደንበኛ ይውሰድ የሚለውን የሚወስነው የደንበኞች ኮሚቴ ነው፡፡ መጀመሪያ ላይ ገንዘቡን ሙሉ ለሙሉ የመቆጣጠሩ ኃላፊነት የደንበኞች ኮሚቴ እና የባንኩ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ኩባንያውም እዚህ ውስጥ መግባት አለበት ተብሎ ያሉንን ቋሚ ንብረቶች በሙሉ አስይዘን ወደ 22 ሚሊየን ብር ተበድረን ገባንበት፤ ነገር ግን አሁንም እኛ ገንዘቡን የማስተዳደር ስልጣን አልነበረንም፡፡ በወቅቱ 600 ደንበኞች ነበሩ በዚህ ሂደት መኪናቸውን የሚጠባበቁት፡፡ ከነዚህ ውስጥ ወደ 400 ገደማ ሰዎች ወስደዋል፡፡ ኋላ ላይ 120 ደንበኞች ብቻ ሲቀሩ በባንክ የተቀመጠው ገንዘብ አለቀ፡፡ ለምን ይህ ሆነ ከተባለ በወቅቱ ኮሚቴው እና ባንኩ ተራቸው ለደረሰና ክፍያቸውን ላልጨረሱ ደንበኞች እንደማሟያ ገንዘብ ወጪ ያደርጉላቸው ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ገንዘብ አለቀ፡፡ ለቀሩት 120 ሰዎች የሚያስፈልገው እቃ ሃገር ውስጥ ገብቷል፡፡ ባንኩ ግን ደንበኞች ያስቀመጡት ገንዘብ ስላለቀ እኛን ወደ 20 ሚሊዮን ብር  አምጡ አለን፡፡ በወቅቱ ኩባንያው ያንን ማድረግ ስለማይችል ጊዜ ስጡን አልናቸው፡፡ ሶስት ወር ያህል ጊዜ ቢሰጡን ኖሮ ባንኩም ኩባንያውም፣ ደንበኞችም ችግር ውስጥ አይገቡም ነበር፡፡ በወቅቱ ይህን በሚገባ ደጋግመን ነግረናቸዋል፡፡ እንደውም እኔ ባንኩ ላይ ሊከተል የሚችለውን ኪሳራ ጠቅሼ አስረድቻቸዋለሁ፡፡
ባንኩ ግን በፎር ክሎዠር ምክንያት ድርጅቱን ሸጦ ገንዘቡን የመውሰድ ሃሳብ ነው ያመጣው፡፡ በዚህ ደግሞ ባንኩም፣ ኩባንያውም፣ ደንበኛውም ተጎጂ ይሆናል አልናቸው፡፡ ነገር ግን ይኸው እስካሁን ድረስ እልባት ሳያገኝ ደንበኛውም ንብረቱን ሳያገኝ ሊቆይ ችሏል፡፡
በወቅቱ ባንኩ ለተጠየቀው ገንዘብ የ3 ወር ጊዜ ሰጥቶን ቢሆን ኖሮ ችግር ውስጥ ባልተገባ ነበር፡፡ እኔ ችግሩን ለመፍታት ካለኝ ፍላጎት የተነሳ የግል መኪናዬን ጭምር አስይዣለሁ፡፡ አሁን ደንበኛው ሊያውቀው የሚገባው ነገር ፋብሪካው ውስጥ ያሉት ያልተገጣጠሙ መኪኖች የሆላንድ ካር ንብረቶች አይደሉም፡፡ ንብረቶቹ የደንበኞች ብቻ ናቸው፡፡ ብራቸውን ከፍለውበታል፤ ሊከራከሩ የሚገባቸውም የ“ሆላንድ ካር ነው” ብለው ሳይሆን “የኛ ንብረት ነው ይገባናል” ብለው ነው፡፡
ከዘመን ባንክ ጋር ያለው ችግር ባልተፈታበት ሁኔታ ደንበኛው ማንን ነው መጠየቅ የሚችለው?
አንደኛ ንብረቱን በተመለከተ ውሳኔ እንዲሰጡ የተሾሙትን ዳኛ፤ ውላቸውንና የከፈሉበትን ደረሰኝ አሳይተው “ይሄ ንብረት የሆላንድ ካር አይደለም፤ የኛ ነው” ብለው መጠየቅ አለባቸው፡፡ ባንኩ ንብረቱ የሆላንድ ካር ስለሆነ ሸጬ እወስዳለሁ የሚለው ነገር ትክክል አይደለም፡፡ የባንክ ንብረት አይደለም፤ የደንበኞች ነው፡፡ ባንኩ በስሙ ከውጭ ሃገር እቃ ማምጣት አይችልም፤ በኩባንያው ስም ነው እቃው የመጣው፡፡ የኛ ኃላፊነት የነበረው የደንበኞችን ንብረት ገጣጥመን ማስረከብ ነው፡፡
በወቅቱ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ችግሩን አሳውቃችሁ ነበር?
ይሄንማ ደንበኛው ነው ማድረግ የነበረበት፡፡ ውሉ ያለው በባንኩ እና በደንበኞች መካከል ስለሆነ ማለት ነው፡፡ ደንበኞች በወቅቱ ወደ ባንክ ያስገቡት የገንዘብ መጠን 43 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ እኛ 22 ሚሊዮን ብር አስገብተናል፡፡
ይሄን ለምን አስቀድማችሁ ለደንበኞች ማስረዳት አልቻላችሁም?
እኛ ደንበኛውን የማግኘት እድል አልነበረንም፡፡ ግንኙነታቸው ከባንኩ ጋር ነበር፡፡ በተደጋጋሚ ብንናገርም የሚሰማን አልነበረም፡፡ እንነጋገርና እንፍታው ብዬ ደጋግሜ ጠይቄያለሁ፡፡ አሁንም ቢሆን መፍትሄ ሊሆን የሚችለው የሶስትዮሽ ውይይት እና ድርድር ነው፡፡ ከመንግስት በኩል ለሃገሪቱ የነበረን አስተዋፅኦ ታምኖበት፣ በቅንነት ችግሩን የመፍታት ፍላጎት ካለ ተነጋግሮ ለመፍታት አሁንም እኛ ዝግጁ ነን፡፡ ውይይቱን ባንኩ እንኳ ባይፈልግ ኩባንያው እና ደንበኞች ቢወያዩ በቀላሉ ችግሩ ይፈታል፡፡ ምክንያቱም ንብረቱ ተሸጦ ለደንበኞች ይከፋፈል ቢባል ደንበኛው ሊያገኝ የሚችለው በፊት ከከፈለው በጣም ያነሰ ነው የሚሆነው፡፡ የሚሻለው ችግሮች በንግግር ተፈተው ደንበኞች መኪኖቻቸውን የሚያገኙበትን ዘዴ መቀየስ ብቻ ነው፡፡ ይሄን ማድረግ ደግሞ በኛ በኩል ቀላል ነው፡፡ እኔ አሁን የማስተላልፈው መልእክት ደንበኞችን ተነጋግረን ችግሩን ለመፍታት እንችላለን የሚል ነው፡፡ ንብረቱን እንሸጣለን ከተባለ የሚገኝ ትርፍ የለም፡፡ ይሸጥ ቢባል እንኳ ባንክ ቀደም ሲል የወሰደውን ገንዘብ መመለስ አለበት፡፡ እኔ ፍላጎቴ ደንበኞች ገንዘባቸውን ሳይጭበረበሩ እንዲያገኙ ነው እንጂ ድርጅቱን የማዳን ጉዳይ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ መናገር የምፈልገው አንዳንድ ሚዲያዎች “ገንዘብ ይዞ ነው ከሃገር የወጣው” የሚባል ነገር ይወራ ነበር፡፡ እኔ ምንም ገንዘብ ይዤ አልወጣሁም፡፡ ለሁለት ዓመታት ሆላንድ ካር ምንም ትርፍ ገንዘብ አልነበረውም፡፡ በባንክ የተቀመጠውን የደንበኞች ብርም እንዴት ብዬ ማውጣት እችላለሁ? እንኳን ብር ይዤ ከሃገር ልወጣ ማንኛውም የኩባንያው የገንዘብ እንቅስቃሴ በባንኩ እና በደንበኞች ብቻ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ለሰራተኞች ደሞዝ እና ለቤት ኪራይ እንኳ አይበቃኝም ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ ሁኔታዎች ቢመቻቹ ወደ ሃገርዎ ተመልሰው ኢንቨስት የማድረግና ስራውን የመቀጠል ፍላጎት አለዎት?
ይሄ ነገር ከተስተካከለ ለምንድን ነው የማልፈልገው፡፡ የተወለድኩባት ሃገሬ እኮ ነች፡፡ በወቅቱ ነገሮች ስላላማሩኝ ዞር ማለቱን መርጫለሁ፡፡ እስካሁን ግን ሂደቱን ሳየው የሚሻለው ነገር ደንበኛው እንዳይጎዳ የሚደረግበትን ዘዴ መፈለግ ብቻ ነው፡፡ ንብረቱ ተሸጦ ይከፋፈላል ከተባለ፣ ከደንበኛው ባሻገር ትልቁን ኪሳራ የሚጋፈጠው ባንኩ ነው፡፡ እኔ በግሌ ያነጋገርኳቸው አንዳንድ ባለስልጣናት አሉ፡፡ በወቅቱ ለመንግሥት ስናቀርበው የነበረው ቅሬታ እና አሁን አቤቱታ የቀረበበት ከታክስ ጋር የተያያዘ ጉዳይ የሆላንድ ካርም ጥያቄ መሆኑን አንስቼላቸው፣ እነሱም ጥያቄው ትክክል ነው ብለዋል፡፡ በዚህ መንገድ የሚፈታ ከሆነም መልካም ነው፡፡ አዳዲስ የጀመርኳቸው ፕሮጀክቶችንም ሃገሬ ላይ መስራት እችላለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ካልቻልኩኝ ግን ወደ ሌላ ሃገር ሄጄ ለመስራት እገደዳለሁ፡፡ በቅን ልቦና ከተነጋገርን ችግሩን ደጋግሜ እንደገለጽኩት መፍታት ይቻላል፡፡
እኔ ምርጥ ታክስ ከፋይ ተብዬ፣ ኩባንያችን ከምርጥ 5 የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ መሃል ተመድቦ ሳለ፣ መንግስት ለምን ነገሩን ችላ እንዳለም አልገባኝም፡፡ እኔ የመንግሥት ድጋፍ ካገኘሁ አሁንም ቢሆን ሃገሬ ላይ ኢንቨስት የማላደርግበት ምክንያት የለም፡፡

Read 4447 times