Tuesday, 04 March 2014 11:13

የቋንቋ ነገር

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(2 votes)

ከ”ግርማዊነትዎ” ወደ “ጓድነትዎ”፤ ከ”ጓድነትዎ” ወደ “ኪራይ ሰብሳቢነትዎ”

አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ ቋንቋን ሲፈቱት “ልሳን፣ የቃል፣ የነገር ስልት” ብለውታል፡፡ ትልቁ ጉዳይ ግን የነገር ስልታችን ሲጠፋ ምን ሊበጀን ይችላል? ነው፡፡ ድሮ የሰው ልጅ ቋንቋ ሁሉ አንድ ነበረ አሉ፡፡ ምን አልባት ያ ቋንቋ እብራይስጥ ወይም አካድያን፤ ወይም ደግሞ ሱመራዊኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ደግሞ ድርጊቱ የተፈፀመበት ቦታ በጥንታዊቷ ባቢሎን ስለሆነ ቋንቋው አካድያን መሆኑ ለመላምት ቅርብ ሊሆን ይችላል፡፡
አካድያን ከክርስቶስ ልደት 2500 ዓመት በፊት በባቢሎን የሚኖሩ ሰዎች ይናገሩት የነበረ ቋንቋ ነው፡፡ ከተጠቀሰው ጊዜ በኋላ ግን ህልውናው አክትሟል፤ ለእማኝነት የተገኘውም በሸክላና ዋሻዎች ውስጥ ተቀርፀው የተገኙ ቃላትን በማጥናት በተደረገ ጥልቅ ምርመራ ነው፡፡
በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ሃይለኞችና ጥበበኞች መሆናቸውን ሃይማኖታዊ መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ ከሃይለኛነታቸው የተነሳ ፈጣሪ ያለበትን ቦታ ለማግኘት ረጅም ህንጻ ለመስራት ተስማሙና ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ይሰሩ ጀመር፡፡ ሠሩ፣ ሠሩና ጦራቸውን ወደ ሰማይ መወርወር ጀመሩ፤ ሰይጣን የጦራቸውን ጫፍ ደም እየቀባ ሲመልስላቸው “አሁን አብን ወጋሁ፤ አሁን ወልድን ወጋሁ፤ አሁን መንፈስ ቅዱስን ወጋሁ” እያሉ በድርጊታቸው ታበዩ፡፡
ይህን ደፋር ድርጊታቸውን የተመለከተው አምላክ ተቆጣና ቋንቋቸውን ቀያየረው፤ በዚህ ምክንያት ግንበኞች ሊግባቡ አልቻሉም፡፡ አንዱ “ውሃ?” ሲል ሌላው ድንጋይ ያቀብላል፤ ሌላው እንጨት ሲል አሁንም ሌላኛው ጭቃ ያቀብላል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጅ ሊግባባ አልቻለም፤ ይሉናል የቤተክርስቲያን አባቶች፡፡
ቋንቋ በተለያዩ ምክንያቶች ሊቀያየር ይችላል፤ በወረራ፣ በጅምላ ስደት፣ እና የሁለት ቋንቋ ተናጋሪዎች አብረው በመኖር የአንዱ ቋንቋ በሌላው ሊዋጥ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በአገራችን ህልውናው በጐረቤት ቋንቋዎች ተፅዕኖ ያከተመውን ጋፋትኛ ማስታወስ በቂ ነው፡፡
የፖለቲካ ሥርዓት መቀያየርም በቋንቋዎች ላይ የራሱን ተፅእኖ ማሳደሩ አይቀርም፤ ለምሳሌ አማርኛን እንውሰድ፡፡ በንጉሡ ዘመን አጼውን ለማናገር ሲፈለግ “ግርማዊነትዎ እንዲህ ያደርግልን ዘንድ ከጫማዎ ሥር ወድቀን እናመለክታለን” ይባል እንደበር ከጽሑፍ ማስረጃዎች መገንዘብ ይቻላል፤ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚያስፈልገው ጉዳዩን ወይም የቀረበውን አቤቱታ ሊያዳምጥና መልስ ሊሰጥ የሚገባው ንጉሡ ሳይሆን “ግርማዊነቱ” ነው፡፡ ግርማዊነቱ ደግሞ ዘውዱ ወይም ፖለቲካዊ ሥልጣኑ መሆኑ ነው፡፡ ከሰውየው በላይ “ግርማዊነቱ” አለ፤ ለዚህም ነው “ግርማዊነትዎ እንዲህ ያርግልኝ” የሚባለው፤ ሰውየውንማ “አንተ ማለት በሞት ባያስቀጣ ከርስት ያስነቅላል፡፡
በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ (ከ1434-1468) እና በጉንዳጉንዶ መነኮሳት መካከል ከፍተኛ ውዝግብ ካስነሱት ጉዳዮች አንዱ “ንጉሡን አንተ ይላሉ” የሚለው መናኛ ምክንያት መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ንጉሡን “አንቱ” ባለማለታቸው ከሌሎች ተልካሻ ምክንያቶች ጋር ተደማምሮ የእንቅስቃሴውን መሪ አባ እስጢፋኖስን ጨምሮ በርካታ መነኮሳት አሰቃቂ ቅጣት ተፈፅሞባቸዋል፡፡
“በኃይለሥላሴ አምላክ?” ብሎ አንድ ሰው ከድርጊቱ እንዲታቀብ ማስፈራራትም ሌላው የንግግር ስልት ነበር፤ ስልቱ ንጉሡ የተለየና የሚፈራ አምላክ የነበራቸው ያስመስላል፤ ግን በአምላክ የተሰየመው የንጉሡ ፈላጭ ቆራጭ ስልጣን ነው፡፡ የንጉሡ አምላክ ልዩ ነው ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው መልስ አስቂኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም መስማት የሚችለውና ተገቢ ፍትህ ሊሰጥ የሚችለው የንጉሡ የኃይለሥላሴ አምላክ እንጂ የድሆች አምላክ አቤቱታ ሊያዳምጥ አይችልም ማለት ነው፡፡ ንጉሡ ብቻ ሳይሆኑ አምላካቸው (የግል አምላክ ከነበራቸው) ከሥልጣን ሲወርዱ አዝማሪዎች “ለካስ፣ ለካስ ጌቶችም እንደኛ ሰው ነበሩ!” ብለው ዘፈኑ፡፡ ከዚያም “ደርግ” የሚባል ሃይል ከሚፈራውና መለኮታዊ ክብር ይሰጠው በነበረው መንበረ ሥልጣን ላይ ቁጭ ሲል ንጉሡም አምላካቸውም ፀጥ ረጭ አሉ፡፡ በነገራችን ላይ “ደርግ” ማለት “ኮሚቴ” የሚለውን ቃል ለመተካት ስለሆነ አጠቃቀሙ ተገቢ ነው፡፡
ደርግ ሲመጣ በአማርኛ ቋንቋ ላይ “አድሃሪ፣ አቆርቋዥ፣ ቀኝ መንገደኛ፣ መሃል ሰፋሪ፣ ነጭ ሽብር፣ ቀይ ሽብር ወዘተ” በማለት ለሽብሩ ሁለ መልክ ተሰጠው፡፡ “ግርማዊነትዎ”ም በ”ጓድነትዎ” ተተካ፡፡ እነ ጓድ መንግሥቱና ባልደረቦቻቸው ሁሉ ጓዶችና ሉዓላዊ የሥልጣን መገለጫቸውም “ጓድነትዎ” ሆነ፡፡
አንድ ወቅት ጓድ ቆምጬ አምባው “ኧረ እባካችሁ ይኸ ጓድ የሚባል ማዕረግ ረከሰ፤ ጓድ የሆነውም ያልሆነውም በጅምላ እየተጠራበት’ኮ ነው…” ካሉ በኋላ መፍትሄውንም “ሞግሼ እንባባል፤ እውነተኛው ጓድ ያኔ አቤት ይላል ሲሉ ሃሳብ አቀረቡ” እየተባለ ሲነገር ነበር፡፡
በቀዩና በነጩ ሽብር ህዝቡን ሲያሸብሩና እንደ ክፍልፋይ ሂሳብ እርስ በርስ በመጠፋፋት ሃገሪቱን ሰው አልባ ካደረጓት በኋላ ኢህአዴግ ደረሰና ሌላ የቃላት ጋጋታ በገፀ በረከት አቀረበልን፡፡ “ዋርድያ፣ ጠርናፊ፣ ባዶ ስምንት፣ አካሄድ፣ እንደ ምሁር፣ እንደ አገር፣ እንደ አቅጣጫ፣ የምለው ያለ፣ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፤ የአመለካከት ችግር፣ የአካሄድ ችግር፣ እንደ አመራር፣ እንደ አሠራር፣ አንጥራት፣ ትንጠር፣ የማስቀምጠው ያለ፣ ዋና የሥራ ሂደት መሪ፣ የሥራ ሂደት ባለቤት” ወዘተ የሚሉ፡፡
ምን ለማለት ታስቦ እንደሆነ ጥቂቱን እንመልከት፤
ዋርድያ    ዘበኛ
ጠርናፊ    ሰብሳቢ (አለቃ) በሌላ አገባቡ
        ጥፍንግ አርጐ የሚያስር
ባዶ ስምንት    ወህኒ ቤት (እስር ቤት)
አካሄድ    “የስብሰባ ሥርዓት ተፋልሷል”
        ለማለት
“እንደ ምሁር፣ እንደ አገር፣ የሚሉት” ሃረጐች በተለይ አስገራሚ ናቸው፡፡ “የምናወራው ምሁር መስለን እንጂ ምሁራን አይደለንም” የሚል ድራማዊ መልእክት ያለው ነው፡፡ “እንደ አገር” ሲባልም “አገር ያለን መስለን እንኑር፣ እንናገር እንጂ አገርስ የለንም” የሚል ይመስላል፡፡ ቀጥታ ለመናገር ቢታሰብ ኖሮ በምሁርነታችን፣ ስለአገራችን፣ ብሎ በእርግጠኝነት መግለፅ ቢቻል አማርኛውን አያወላግደውም ነበር፡፡
“አካሄድ” ከሚለው አጠቃቀም ጋር ተያይዞ አንድ ገጠመኝ አለ፤ ኢህአዴግ መንበረ መንግሥት እንደተረከበ ካድሬዎቹን በየመ/ቤቱ እየላከ ከደርግ የተረፈውን “ንቃት ይሰጥ” ነበር፡፡ አንድ ቀን እኔ ወደነበርሁበት ተቋም አንድ ካድሬ መጥቶ ተመሳሳይ “ንቃት ሲሰጥ” (ንቃትንም እንደ እቃ አንዱ ለሌላው መስጠቱን ልብ ይሏል) ባልደረባችን ሳያስፈቅድ መናገር ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ አንቂው ካድሬ “አካሄድ! አካሄድ!” አለው ደጋግሞ፡፡ ባልደረባችን በዚህ ጊዜ ከመቀመጫው ብድግ አለና “እኔ እገሌ ለአካሄዴ ደግሞ ምን ይወጣልኛል? የድፍን ፒያሳ፣ የአራት ኪሎና የካዛንችስ ልጃገረዶች ይጠየቁ!” ብሎ መንጐራደድ ሲጀምር ተሰብሳቢው ሁሉ በሳቅ አወካ፡፡
“እንደ አቅጣጫ” በሚባልበት ጊዜ መተላለፍ የተፈለገው የኢህአዴግን የትግል መስመር ለማሳየት ይመስላል፤ “መመሪያ ወይም ደንቡ እንደሚለው” ብሎ መተርጐምም ይቻል ይሆናል፡፡ ግን ትክክለኛ ትርጉም ሊሆን የሚችለው “አቅጣጫ ቢጠፋብንም ይህንን ጉዳይ እንደ አቅጣጫ አይተን ተግባራዊ እናድርገው” የሚል ነው፡፡
“አንጥራት! ትንጠር!” የሚሉ ቃላትንም የኢህአዴግ ካድሬዎች በፍቅር ሲጠቀሙባቸው ነበር፡፡ ትርጉማቸው አንድም ለቅቤ አለዚያም ለኳስ የሚያገለግል ነው፡፡ ካድሬዎቹ የሚገለገሉበት ግን “የተናገርኸውን በማስረጃ አስደግፍ! አስረዳ” ለማለት ነው እንጂ እንደ ኳስ ወይም እንደ ቅቤ የሚነጥር ነገር ኖሮ አይደለም፡፡
“እንደ አመራር፣ እንደ አሠራር፣” የሚባሉ ሐረጋትም ግራ የሚያጋቡ ናቸው፡፡ የፖለቲካ መሪዎቻችን የሚያወሩት ስለ አመራር ወይም አሠራር ሳይሆን አመራር ወይም አሰራር ስለሚመስል ነገር ነው፡፡ ወይም እንደ አመራር የመሰለ ጉዳይ፡፡
“ግንባታው፣ ትግሉ ወዘተ የቀጠለበት ሁኔታ ነው ያለው” ሲባልም እንሰማለን፤ “ሁኔታው” ደግሞ ካድሬዎች ብቻ ሳይሆን የመንግሥት ጋዜጠኞች በመደበኛነት ሲጠቀሙበት ማየትና መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህን መሰል ቃል ገና ከመሪዎች አፍ ጠብ ከማለቱ በተለይ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ይቀልቡና እስኪሰለቸን ሊግቱን ይሞክራሉ፡፡
“ውሻ በበላበት ይጮኸል” እንዲሉ በእነሱ ቤት ታማኝነታቸውን ማሳየታቸው ነው፡፡ ግን ደግሞ አብዛኞቹ ጋዜጠኞች አንድም በቋንቋና ሥነፅሁፍ አሊያም በጋዜጠኝነት፣ ወይም በጥበበ ተውኔት (ቲአትሪካል አርት) የተመረቁ ናቸው፡፡ እነዚህ መስኮች ደግሞ አነሰም በዛ ስለመደበኛ ቋንቋና ቀበልኛ ያስተምራሉ፡፡ ጋዜጠኞቻችን ከየት እየመጡ ይሆን እንዲህ ቱልቱላ ነፊዎች የሚሆኑት?
በጣም ከሚያስገርሙኝ ኢህአዴጋዊ (ፖለቲካዊ) ቃላት መሃል “ኪራይ ሰብሳቢነት” ልዩ ትርጉም ትሰጠኛለች፤ ቃሏን የፈጠሯት ነፍሳቸውን ይማርና አቶ መለስ ናቸው፡፡ “ሬንት ሲከር” ለሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ነው ይህ አይነት ትርጉም የሰጡት፡፡ ከዚያ በኋላማ እሳቸው የፈጠሯትን ቃል ምን የቆረጠው ካድሬ ነው የሚቀይራት! “ኪራይ ሰብሳቢ” የክብር ዕቃ ሆነችና ቁጭ አለች፡፡ በንጉሡ ዘመን “ጉቦ” የሚል ቃል ነበር፤ በደርግም ይኸው ቀጥሏል፡፡ በረሃ የወለደውና በበረሃ ስም በሚጠሩ በረኸኞች የተቋቋመው ኢህአዴግ ከተማ ሲገባ ለጉቦም “ኪራይ ሰብሳቢ” የሚል የበረሃ ስም አወጣለት፡፡ ከዚያ በኋላ ሥራውም፣ ስብሰባውም ሁሉ ነገሩ “ኪራይ ሰብሳቢ” ከሚባል በሽታ ጋር ተቆራኘ፡፡
“ጉቦኛ” ወይም “ሙሰኛ” የሚለውን ቃል ቢጠየፈውም ግብሩን ግን ከቀበሌ እስከ ሚኒስትር ያሉ ዋልጌ አባሎቹ እየተዘፈቁበት መቸገሩን በድርጅትም ሆነ በመንግሥታዊ ስብሰባዎች ላይ የሚደግመው የዘወትር ጸሎቱ ሆኗል፡፡ በዚህና በሌሎች ጉዳዮች የተነሳ የአገሪቱ ህዝብ የአንድነቱና የኢትዮጵያዊነቱ ቋንቋ አደጋ ላይ ወድቋል፤ አገራችን አደጋ ላይ ነች፤ የግብፅ ሴራ ያሰጋታል፤ የሻዕቢያ ተንኮል ያሰጋታል፤ የአል-ኢትሃድ ውንብድና ያስፈራታል፤ ከሁሉም በላይ የአንድነት ክር መላላት በእጅጉ ያሰጋታል፤ መፍትሄው ኢህአዴግ አገራዊ ስሜትን፤ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አርጐ ማቀንቀን አለበት፡፡
የመንደር ፖለቲካ ከሰፈር አልፎ የትም አያደርስም፤ በሰበብ አስባቡ ኢትዮጵያውያን እንዲናቆሩ በር መክፈት የለበትም፡፡ በክቡርነትዎ ፋንታ “ኪራይ ሰብሳቢነትዎ” ሊባሉ ጥቂት የቀራቸውን ባለስልጣናቱን በጥብቅ ሊቆጣጠራቸውና መላው ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ “አገሬን አትንኩ!” ማለት የሚያስችል የእኩልነትና የአንድነት ቋንቋ ሊጠቀም ይገባል፡፡ የአድዋ ድል ምስጢሩ መላው ኢትዮጵያዊ እንደ አንድ ሰው መቆሙና የአንድነት ቋንቋ መናገር መቻሉ ነው፡፡Read 3067 times