Tuesday, 04 March 2014 11:01

የደደቢት ክለብ ፕሬዝዳንት መነሳት አወዛግቧል

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(6 votes)

ክለቡን በነፃ ያስረከብኩት በፍቃደኝነት ነው
- ኮ/ል አወል አብዱራህማን
ክለቡን ያስረከብኩት የባለቤትነትና የአሰራር ጥያቄ ስለተነሳ ነው
- አቶ ጥበቡ አየለ
የደደቢት ስፖርት ክለብ መስራችና ፕሬዚዳንት የነበሩት ኮ/ል አወል አብዱራህማን ከኃላፊነት መነሳት እያወዛገበ ሲሆን አዲሱ ፕሬዚዳንት አቶ ጥበቡ አየለ፤ በክለቡ ባለቤትነትና አሰራሮቹ ላይ ጥያቄዎች እንደተነሱ ጠቅሰው በቦርድ ውሳኔ መተላለፉን ገልፀዋል፡፡ ኮ/ል አወል በበኩላቸው፤ ክለቡን የመሰረትኩት ባለቤቱ እኔ ነኝ፤ ነገር ግር የፋይናንስ ችግር ስላለበት በራሴ ፈቃድ አቅም ላለው አካል በነፃ አስተላልፌያለሁ ብለዋል፡፡
ክለቡን በገንዘብ የሚደግፉ ድርጅቶች በየዓመቱ እስከ 20 ሚ.ብር ይሰጡ እንደነበር የተናገሩት አቶ ጥበቡ፣ ገንዘቡ እንዴት ስራ ላይ እንደሚውል ወጪና ገቢውን ለመከታተል ግልፅ አሰራር እንዳልነበር ይገልፃሉ፡፡ በዚህ ምክንያት የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ ድርጅቶችና የክለቡ ቦርድ ለኮ/ል አወል ሁለት  ምርጫዎችን እንዳቀረቡ የሚናገሩት አቶ ጥበቡ፤ “በአንደኛው አማራጭ፤ ኮሎኔል አወል ክለቡ የግሌ ነው የሚሉ ከሆነ  ክለቡን ይዘው ሊቀጥሉ ይችላሉ” ብለዋል፡፡
የክለቡን ወጪ በራሳቸው መንገድ እየሸፈኑ በግላቸው መቀጠል ከፈለጉ ይችላሉ፤ ክለቡ የገንዘብ ድጋፍ እያገኘ እንዲቀጥል ከተፈለገ ደግሞ ሁለተኛው አማራጭ በግልፅ አሰራር ክለቡን የሚመራ ባለቤት ይበጅለት የሚለው ነው ያሉት አቶ ጥበቡ፤ በዚህ ውሳኔ መሰረት ኮሎኔል አወል ለቀዋል ብለዋል፡፡  “ፋይናንሱንም ሆነ ሌላውን ስራ ሁሉ ኮ/ል አወል ነበር የሚያስተዳድሩት፣ በጀቱ ላይ ጉድለት ይኑር አይኑር ገና የሚጣሩ ነገሮች አሉ፡፡ ማን ምን ሰጠ? ምን ተደረገበት? የሚለው ይታያል” ብለዋል-አቶ ጥበቡ፡፡ ከክለቡ የባለቤትነትና የአሰራር ግልፅነት ጥያቄዎች በተጨማሪ፣ የክለቡ አካሄድ ላይ ጥያቄዎች መኖራቸውን የገለፁት አቶ ጥበቡ፤ ክለቡ ታዳጊ ልጆችን ከታች በማሰልጠን ለክለቡም ሆነ ለአገሪቱ እግር ኳስ ብቁ ተጫዋቾችን ያፈራል የሚል ሃሳብ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ከመነሻው ሃሳብ ውጭ እንደማንኛውም ክለብ ተጫዋቾችን እየገዛ ማጫወት ጀመረ፡፡ የውጭ ተጫዋቾችም ተገዝተዋል ብለዋል -አቶ ጥበቡ፡፡ ተጫዋቾችን ገዝቶ ውጤት ማምጣት አንድ ነገር ነው፤ ይሁንና ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ከመነሻው የፈለጉት ነገር በራሳችን ከታች አሳድገን ውጤታማ መሆንና ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሲሰለፉ ማየት ነው ብለዋል፡፡ “ደደቢት ቢዝነስ ፒኤልሲ” በሚል ስያሜ ለክለቡ የገቢ ምንጭ ይሆናል የተባለውን የድንጋይ ወፍጮ በተመለከተ ተጠይቀውም፤ ድርጅቱ የተሸጠው በባንክ እዳ ነው፤ ነገር ግን ባለቤትነቱና አሰራሩ ግልፅ ስላልነበረ ገና ብዙ መረጃ የለንም ብለዋል፡፡
ኮ/ል አወል በበኩላቸው፤ ክለቡ ሲያድግ ከተለያዩ ድርጅቶችና ከተለያዩ ሰዎች እየለመንኩ ከጓደኞቼ እየወሰድኩ ነበር የምሰራው፣ ክለቡም ስኬታማ ሆኖ ግቡን መትቷል ካሉ በኋላ፤ ክለቡ ሲያድግ ፍላጎቱ እየጨመረ ስለመጣና ለኢትዮጵያ ካስገኛቸው ድል አንፃር በተንጠባጠበ እርዳታ ከሚቀጥል መስመር ይዞ የተሟላ ድጋፍ እንዲያገኝ የሚያስችል ፕሮጀክት ነድፌ ለባለሃብት ለማስተላለፍ ጥረት የጀመርኩት ከሦስት ዓመት በፊት ነው ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ድጋፍ ያደርግ ለነበረው “ደራ ትሬዲንግ” በነፃ  አሳልፌ በራሴ ፈቃድ ሰጠሁ እንጂ እኔ ስራዬን የለቀኩት ቦርዱ ወስኖብኝ አይደለም ብለዋል- ኮ/ል አወል፡፡ ክለቡ የተነሳበትን አላማ ከበቂ በላይ ተወጥቷል፤ ነገር ግን ክለቡ ያገኝ የነበረው ድጋፍ በቂ አልነበረም፤ ደህና ድጋፍ የተገኘው ባለፉት ሁለት አመት ውስጥ ነው፤ በአንድ አመት የተገኘው ትልቁ ድጋፍ 20ሚ. ብር ደርሶ አያውቅም፤ 15.5 ሚ.ብር ነው ብለዋል፡፡ የክለቡ የገንዘብ አቅም ከእጅ ወደ አፍ እንጂ ተርፎ የተበላ እና ለመታለል የሚያበቃ ነገር አልነበረውም ይላሉ-ኮ/ል አወል፡፡
የክለቡ መነሻ የነበረው ህፃናቶችን አሳድጎ ለተሻለ ነገር ማብቃት ብቻ ነው ጫዋቾችን መግዛት አይደለም የሚባለውንም ቢሆን፤ ክለቡን ያስረከብኩት በሐምሌ ወር ነው፡፡ ክለቡ ተጫዋቾችን አሁንም እየተጠቀመ ነው ብለዋል፡፡
የድንጋይ ወፍጮውን በተመለከተም ሲገልፁ ትኩረታቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ እግር ኳሱ ስለሆነ ድርጅቱ መክሰሩን ኮ/ል አወል ጠቅሰው፤ ባንክ የነበረብንን እዳ ባለመክፈላችን ሸጦብናል ብለዋል፡፡
ክለቡን ለደራ ትሬዲንግ ለማስተላለፍ በተፈራረምነው ውል፤ የክለቡ ባለቤት መሆኔንና ከሙሉ ክብር ጋር ነፃ ባለቤትነቴን እንዳስተላልፍኩ የሚገልፅ አንቀፅ ሰፍሯል የሚሉት ኮ/ል አወል፤ በአንድ ወር ውስጥ ኦዲት ይደረጋል ተብሎ ነበር፡፡ ግን እስካሁን የጠየቀኝ ሰው ስለሌለ ባይፈልጉት ይሆናል ብዬ ዝም ብያለሁ ብለዋል፡፡  

Read 3053 times